በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሳቅ ደስ የሚያሰኘው ለምንድን ነው?

ሳቅ የሚያስደስተው ለምንድን ነው? ሳቅ ከመረዳትና ከቋንቋ ችሎታ ጋር ዝምድና ያለውን የአንጎል ክፍል ብቻ ሳይሆን ከደስታና ከፈንጠዝያ ስሜት ጋር ግንኙነት ካለው ኒውክልየስ አኩምበንስ ከሚባለው የአንጎል ክፍል ጋር ጭምር ግንኙነት እንዳለው በጥናት መረጋገጡን ዘ ቫንኩቨር ሰን ዘግቧል። የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አለን ራይስ እንደሚሉት ከሆነ ይህ የአንጎል ክፍል “በጣም ኃይለኛ” ነው። በሳቅና በቀልድ ላይ የሚደረገው ጥናት ሐኪሞች ማኅበራዊ ባሕርያትን ይበልጥ እንዲረዱ እንደሚያስችላቸው ራይስ ያምናሉ። “ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው እንዴት ካለ ሰው ጋር እንደሚወዳጅ ወይም ዘላቂ የሆነ የፍቅር ግንኙነት እንደሚመሰርት የሚወሰነው በቀልደኝነት ባሕርይ ነው” ይላሉ ዶክተር ራይስ። “በተጨማሪም ቀልድና ሳቅ [ሰዎች] የሚያጋጥማቸውን ጭንቀትና ውጥረት የሚቋቋሙበት መሣሪያ ነው።”

‘አዲሱ የ21ኛው መቶ ዘመን በሽታ’

አንዳንድ የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች ለአዲሱ የተንቀሳቃሽ ስልክ “ሱስ” እንዲህ ያለ ስም አውጥተዋል። የማኅበራዊ ሱሶች ሕክምናና መልሶ ማቋቋም ልዩ ማዕከል ባደረገው ጥናት መሠረት በሞባይል ስልክ ሱስ በአብዛኛው የሚያዙት “ከ16 እስከ 25 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዓይናፋር፣ ብስለት የሚጎድላቸውና ብስጩ የሆኑ ያላገቡ ሴቶች ናቸው” ሲል የስፔይኑ ኤል ፓይስ ጋዜጣ ዘግቧል። ብላስ ቦምቢን የተባሉት የሥነ አእምሮ ባለሙያ እንደሚሉት “ይህ ሱስ በተንቀሳቃሽ ስልኮች መልእክት የመለዋወጥና የመነጋገር የማያቋርጥ ግፊት ያሳድራል።” ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን መጠቀም ካልቻሉ “ይጨነቃሉ፣ ይበሳጫሉ።” የተንቀሳቃሽ ስልክ “ሱስ” ሰብዓዊ ግንኙነቶችን ከመጉዳቱም በላይ ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል። ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ስምንት ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚይዙና “ለስልክ በወር እስከ 9,000 ብር የሚከፍሉ” ሱሰኞች እንዳሉ ጠቅሷል።

በመላው ዓለም ትርኪምርኪ ሰፈሮች እየተበራከቱ ነው

አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠለ “በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከዓለም ሕዝቦች ከሦስት እጅ አንዱ ትርኪምርኪ በሆኑ ሰፈሮች እንደሚኖር” የለንደኑ ዘ ጋርድያን ጋዜጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት በመጥቀስ ዘግቧል። “ባሁኑ ጊዜ 940 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች ወይም ከዓለም ሕዝቦች አንድ ስድስተኛ ያህል የሚሆኑት የሚኖሩት በአብዛኛው ውኃ፣ የቆሻሻ ማስወገጃ፣ ምንም ዓይነት ሕዝባዊ አገልግሎትና ሕጋዊ ጥበቃ በማይገኝባቸው አካባቢዎች ነው።” በናይሮቢ፣ ኬንያ በሚገኘው ኪቤራ የሚባል አካባቢ 600,000 የሚያክሉ ሰዎች ትርኪምርኪ በሆኑ ሰፈሮች ይኖራሉ። የሰዎችን አሰፋፈር የሚከታተለው ዩ ኤን ሀቢታት የተባለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አና ቲባዩካ “ሰዎች በማኅበራዊ ኑሮ ላይ እንዲያምጹ የሚያደርጋቸው ሥራ አጥነትና በጣም የተራራቀ የኑሮ ደረጃ ነው። ሁሉም ዓይነት ክፉ ድርጊት አንድ ላይ ተሰባስቦ የሚገኘው ሰላምና መረጋጋት በማይገኝባቸውና ወጣቶች ጥበቃ ሊያገኙ በማይችሉባቸው ትርኪምርኪ መንደሮች ነው” ብለዋል።

በጡንቻዎቻቸውና በጅማቶቻቸው ላይ ችግር የሚያጋጥማቸው ወጣቶች

የካናዳው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል በጡንቻዎቻቸውና በጅማቶቻቸው ላይ ችግር አጋጥሟቸው የሕክምና እርዳታ የሚፈልጉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ዘግቧል። “ዶክተሮችና ፊዚዮቴራፒስቶች በቂ የአካል እንቅስቃሴ የማያደርጉ ልጆች በቤታቸውም ሆነ በትምህርት ቤታቸው ኮምፒውተር ላይ አፍጥጠው የሚቆዩበት ጊዜ እየጨመረ በሄደ መጠን የወጣት ታካሚዎቻቸው ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ይናገራሉ” ይላል ጋዜጣው። ግሎብ እንደሚለው ብዙ ጊዜ ታይፕ ሲመቱ ወይም የቪዲዮ ጨዋታ ሲጫወቱ መቆየት የጡንቻ ሕመምና እብጠት ያስከትላል። ወላጆች የልጆቻቸውን አቀማመጥ ማስተዋል እንዲሁም ልጆቻቸው ክርናቸውን ወይም የእጅ አንጓዎቻቸውን ሲያሻሹ አሊያም ደግሞ እንደ መደንዘዝና መንዘር ያለ የሕመም ስሜት እንደተሰማቸው ሲናገሩ ትኩረት ሰጥተው መከታተል እንደሚገባቸው ይመከራሉ።

አደገኛ የሆነ የሥራ ቦታ?

አንድ በስዊድን የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው “ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ መሥራት ለትዳር አደገኛ” እንደሆነ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። ኢቮን ኤበርግ የተባሉት የጥናቱ ጸሐፊ የመንግሥትን የፍቺና የሥራ መዛግብት ከመረመሩ በኋላ “ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ባልደረቦች ጋር የሚሠሩት ሰዎች የፍቺ መጠን ተመሳሳይ ጾታ ካላቸው የሥራ ባልደረቦች ጋር ከሚሠሩት ሰዎች 70 በመቶ በልጦ እንደተገኘ” ደርሰውበታል። በተጨማሪም የሥራ ባልደረቦች ያገቡ መሆን አለመሆናቸው በፍቺው መጠን ላይ ለውጥ እንዳላመጣ ዶክተር ኤበርግ ተገንዝበዋል። በ1,500 የተለያዩ አካባቢዎች በሚሠሩ 37,000 ሠራተኞች ላይ የተደረገው ይህ ሰባት ዓመት የፈጀ ጥናት መረጃውን ያገኘው ብዙ ጊዜ የተሳሳተ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ ግለሰቦችን በማነጋገር ሳይሆን በቀጥታ ከጽሑፍ መረጃዎች መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። ከትዳር ጓደኛ ጋር በአንድ ቢሮ መሥራት አደጋውን በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ይኸው ጽሑፍ ገልጿል።

እምነት የለሽ ቄስ

“በሰማይ የሚኖር አምላክ የለም፣ የዘላለም ሕይወት የሚባል ነገር የለም፣ ትንሣኤም የለም” በማለታቸው ከቅስና ሥልጣናቸው የተባረሩ አንድ የሉተራን ቄስ በሰባኪነት እንዲቀጥሉ የተፈቀደላቸው መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል። በኮፐንሃገን አጠገብ የሚገኘው የቶቤክ ሰበካ ጉባኤ ቄስ የነበሩት ቶኪል ግሮስበል “ለተናገሩት ቃል ይቅርታ ከጠየቁ” እና ለቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት እንዳለባቸው ካመኑ በኋላ ወደ ሥራቸው እንደተመለሱ የኤልሲኖር ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ሊሰ ሎተ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ግሮስበል ያንኑ ስብከታቸውን ቀጥለዋል። ሰኔ 2004 ላይ ጳጳሱ እንደገለጹት ግሮስበል በገዛ ፈቃዳቸው ቅስናቸውን ለመተው ፈቃደኛ ካልሆኑ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኛል።

ጥንታዊ የሆነ የወንጌል ጽሑፍ

በጳለስጢና የሚገኙ ምሑራን ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተወሰደ ጥቅስ በአንድ የጥንት መቃብር ላይ ተጽፎ እንዳገኙ የጀርመኑ ፍራንክፈርተር አልገማይነ ጻይቱንግ ዘግቧል። የአቤሴሎም መቃብር ተብሎ በተጠራ መቃብር ላይ የተገኘው ይህ የተቀረጸ ጽሑፍ በአጋጣሚ የተገኘ ነው። የሥነ ሰብ ተመራማሪ የሆኑት ጆ ዚያስ መሸትሸት ሲል ደንገዝገዝ ባለ ብርሃን ባነሱት ፎቶግራፍ ላይ እየጠፋ ያለ ጽሑፍ የመሰለ ነገር ተመለከቱ። የጽሑፉ ቅርጽ ረጥቦ የተለወሰ ወረቀት በመደረብ ተነስቶ ሲታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መሆኑ ታወቀ። ከሉቃስ 2:25 የተወሰደ ጥቅስ ሲሆን በአራተኛው መቶ ዘመን ከተጻፈው ኮዴክስ ሲናይቲከስ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በመቃብር ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መጻፍ እየተለመደ የመጣው በ1000 ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ጀምሮ በመሆኑ ይህ ግኝት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሆኗል።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የአመጋገብ ልማድ

“ለሰውነታቸው ቅርጽ በመጨነቅ እንዲሁም የፋሽን አስተዋዋቂዎችንና ታዋቂ ሰዎችን ለመምሰል በመፈለግ፣ ትክክለኛ የአመጋገብ ሥርዓት የማይከተሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጃገረድ ተማሪዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ በመጨመር ላይ ነው” በማለት በለንደን የሚታተመው ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። የብሪታንያ ትምህርት ቤቶች የጤና ትምህርት ክፍል በ300,000 ተማሪዎች የአመጋገብ ልማድ ላይ ባደረገው ጥናት መሠረት በ14 እና በ15 ዓመት ዕድሜ ላይ ካሉት ልጃገረዶች ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት “ቁርሳቸውን ሳይበሉ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ። በ1984 በተደረገ ጥናት ከተጠናቀረው አኃዛዊ መረጃ ጋር ሲወዳደር ቁጥሩ በእጥፍ አካባቢ ጨምሯል።” በተጨማሪም በ1984 ምሳቸውን የማይበሉ ልጃገረዶች ቁጥር 2 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2001 ግን 18 በመቶ ሆኗል። የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን ልጆቹ እንደ ምግብ ፍላጎት ማጣትና ከልክ በላይ መብላት የመሳሰሉ የተዛቡ የአመጋገብ ልማዶች እንዳያዳብሩ በመፍራት በተማሪዎቻቸው ላይ የክብደት ቁጥጥር እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል። ወንዶች ልጆችም ቢሆኑ ምግብ የመቀነስ ፍላጎታቸው እየጨመረ ነው። በ12 እና በ13 ዓመት ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ወንዶች መሃል ክብደት መቀነስ የሚፈልጉት 26 በመቶ ብቻ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን 31 በመቶ ያህል ሆነዋል፤ እንዲሁም 14 እና 15 ዓመት ከሆናቸው ወንዶች ውስጥ 21 በመቶዎቹ ክብደት ለመቀነስ ይፈልጉ የነበረ ሲሆን አሁን ቁጥራቸው ወደ 25 በመቶ ከፍ ብሏል።