በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽብርተኞች ጥቃት የሚያስከትለውን ጉዳትና የሥነ ልቦና ቀውስ መቋቋም

የሽብርተኞች ጥቃት የሚያስከትለውን ጉዳትና የሥነ ልቦና ቀውስ መቋቋም

የሽብርተኞች ጥቃት የሚያስከትለውን ጉዳትና የሥነ ልቦና ቀውስ መቋቋም

ስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

መጋቢት 11, 2004 የስፔይኗ ከተማ ማድሪድ በሦስት የተለያዩ ባቡር ጣቢያዎች በተከሰቱ አሥር የቦምብ ፍንዳታዎች ተናወጠች። ከከተማ ወጣ ብለው የሚኖሩ ሠራተኞችን በሚያጓጉዙ አራት ባቡሮች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት በተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት 190 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ 1,800 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ፍንዳታዎቹ የተከሰቱት መንገደኞች በጣም በሚበዙበት የማለዳው ክፍለ ጊዜ ላይ በመሆኑ ባቡሮቹ በሙሉ ጢም ብለው ሞልተው ነበር፤ በዚህም ሳቢያ የደረሰው ጥፋት በጣም አሰቃቂ ሊሆን ችሏል። አሮአ የተባለች አንዲት የዓይን ምሥክር “ከፍንዳታው ኃይል የተነሳ አንድ ፉርጎ እንዳለ አንድ ሜትር ወደ ላይ ተወርውሮ ሲከሰከስ ተመልክቻለሁ” ስትል ተናግራለች። “እኔ ከነበርኩበት ፉርጎ ስወጣ አካባቢው በሙሉ የጦርነት ቀጣና መስሎ ነበር። በገሐዱ ዓለም እንዲህ ያለ እልቂት መመልከት በጣም አሰቃቂ ነው።” ይኸው ዘግናኝ ድርጊት በአራት የተለያዩ ባቡሮችና በአሥር ፉርጎዎች ላይ ተፈጽሟል። ሽብርተኞች ቦምብ የታጨቀባቸውን ጀርባ ላይ የሚነገቱ ቦርሳዎች ባቡሮቹ ውስጥ ትተው በመውረድ በተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካኝነት እንዲፈነዱ አድርገዋል።

ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ያዩትንና የደረሰባቸውን ነገር ማስታወስ ባለመቻላቸው ዕድለኞች ናቸው። እንደ አሮአ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎች ግን አደጋው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጠባሳ ጥሎባቸው አልፏል። “ፍንዳታው በጆሮዬ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሶብኛል” ትላለች አሮአ፤ “ከዚህ የከፋ ጉዳት ያደረሰብኝ ግን አእምሮዬ ውስጥ እየተመላለሰ የሚረብሸኝ ያየሁት አሰቃቂ ሁኔታ ነው።

“ደግነቱ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ብዙ ማጽናኛና ማበረታቻ አግኝቻለሁ። ከዓለም ዙሪያ የደረሱኝ የስልክ ጥሪዎችና መልእክቶች ዓለም አቀፋዊ የሆነ የወንድማማች ማኅበር አባላት እንደሆንን እንዳስታውስ አድርገውኛል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ አረመኔያዊ ድርጊቶች የሚፈጸሙት ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በመጨረሻው ዘመን’ ሰዎች ጨካኞችና ፍቅር የሌላቸው እንደሚሆኑ አስቀድመው እንደተነበዩ ለአንዳንዶቹ የመሥሪያ ቤት ጓደኞቼ ገልጬላቸዋለሁ። ከዚህ ሌላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሠማራሁ መሆኔ ሥቃዩን መቋቋም እንድችል በእጅጉ ረድቶኛል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3

ፔድሮ ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው በርካታ መንገደኞች አንዱ ነው። እሱ በነበረበት ፉርጎ ውስጥ ከፈነዳው ቦምብ ከአራት ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ቆሞ ነበር። ፍንዳታው ወለሉ ላይ ሲዘርረው በጭንቅላቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በመተንፈሻ አካላቱ ላይም ከባድ ችግር አስከትሎበታል። ለአምስት ቀናት ያህል በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ ክትትል ሲደረግለት ከቆየ በኋላ ማገገም ጀመረ። ሊጠይቁት የመጡት በርካታ የእምነት አጋሮቹ መንፈሱን ያነቃቁለት ሲሆን ነርሶቹ በጠያቂዎቹ ብዛት በጣም ተደንቀው ነበር። አንዲት ነርስ “ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ ይህን ያህል በርካታ ሰዎች የጠየቁትና በርካታ ስጦታዎች የጎረፉለት ታማሚ አጋጥሞኝ አያውቅም!” ስትል በአድናቆት ተናግራለች። በሌላ በኩል ደግሞ ፔድሮ ለሆስፒታሉ ሠራተኞች ያለውን አድናቆት ገልጿል። “በጣም ጥሩዎች ናቸው፤ ከደረሰብኝ ጉዳት እንዳገግም በእጅጉ ረድተውኛል” ሲል ተናግሯል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በቅርቡ ወደ ስፔይን የመጡ ስደተኞች ናቸው። ማኑዌል የተባለ አንድ የኩባ ዜጋ በአቶቻ የባቡር ጣቢያ በደረሰው የመጀመሪያው ፍንዳታ የተጎዳ ሲሆን በሁለተኛው ፍንዳታ ወቅት ደግሞ ራሱን ስቶ ወድቆ ነበር። “ወደ ባቡር በሚገባበትና ከባቡር በሚወጣበት ቦታ ላይ ተዘርሬ ሳለ በድንጋጤ ሲራወጡ የነበሩት ሰዎች ረጋገጡኝ። ራሴን ሳውቅ ሁለት የጎድን አጥንቶቼ ከመሰበራቸውም በላይ እግሬ ተጎድቶ ነበር። በተጨማሪም አንደኛው ጆሮዬ ሙሉ በሙሉ ደነቆረ።

“የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ማለትም ፖሊስ፣ የአምቡላንስና የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በቦታው ደርሰው የሚቻለውን እርዳታ ሁሉ አደረጉልን” ሲል ማኑዌል አክሎ ተናግሯል። “ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ናቸው፤ ቅልጥፍናቸውና በሙያቸው የተካኑ መሆናቸው የተፈጠረውን ድንጋጤና ሽብር ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም ተገቢውን ሕክምና እንዳገኝ በማድረግ አሳቢነትና ርኅራኄ አሳይተውኛል።”

ከከባድ አደጋ በኋላ የሚከሰት የሥነ ልቦና ቀውስ

ልክ እንደ አሮአ ሁሉ ማኑዌልም አደጋው ከባድ የስሜት ጠባሳ ጥሎበት አልፏል። “በቅርቡ ባቡር ስሳፈር ከፍተኛ የሆነ የፍርሃት ስሜት አደረብኝ” ሲል ያጋጠመውን ሁኔታ ገልጿል። “ወዲያውኑ ወርጄ ለመሄድ ተገደድኩ። አሁንም ድረስ በሕዝብ ትራንስፖርት በምጓዝበት ጊዜ ጀርባ ላይ የሚነገት ቦርሳ ወይም ተመሳሳይ ነገር የያዘ ሰው ሳይ በጣም ስጋት ያድርብኛል። ይሁንና ቤተሰቦቼ ስፔይን ውስጥ ባይኖሩም ከማንም የተሻለ እርዳታ አግኝቻለሁ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስልክ የደወሉልኝ ሲሆን አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ደግሞ ብቸኝነት እንዳይሰማኝ ብለው ለተወሰኑ ቀናት ቤታቸው እንድከርም ጋብዘውኛል። ከዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ያገኘሁት እንዲህ ያለው ድጋፍ መረጋጋት እንድችል ረድቶኛል።”

ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት ሳይደርስበት ከአደጋው መትረፍ የቻለው ሴርሂዮ የተባለው ተሳፋሪ በወቅቱ ያየው ነገር አሁንም ድረስ ትውስ እያለው ቀን በቀን አእምሮው ይረበሻል። ከፊት ለፊቱ በነበረ የባቡር ፉርጎ ውስጥ የተጠመደ ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ከበስተጀርባው በነበረ ሌላ ፉርጎ ውስጥ የተጠመደ ቦምብ ደግሞ ፈነዳ። ልክ እንደ ማኑዌል እሱም ቤተሰቦቹና የእምነት ባልንጀሮቹ ላደረጉለት ፍቅራዊ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነው። “ምን ያህል እንደሚወዱኝ እንድገነዘብ ያደረጉኝ ከመሆኑም በላይ ለእያንዳንዱ አባል በሚያስብ አንድነት ባለው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የታቀፍኩ መሆኔን እንዳስታውስ አድርገውኛል” ሲል ተናግሯል። “እንዲህ ያለውን ድጋፍና እርዳታ በየቀኑ አገኝ ነበር። ብዙውን ጊዜ ስሜቴን አውጥቼ ለመግለጽ የምቸገር ብሆንም በየጊዜው ይደርሱኝ የነበሩት በርካታ የስልክ ጥሪዎች ይህን ማድረግ እንድችል ረድተውኛል።”

በባቡሮቹ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት አንዳንዶቹ ሰዎች አደጋው የተለያየ ዓይነት ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። ሳይፈነዱ ከቀሩት አራት ቦምቦች መካከል አንደኛው የተቀመጠው ዲዬጎ አጠገብ የነበረ ቢሆንም ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ከባቡሩ መውጣት ችሏል። “ይሁን እንጂ ለተጎዱት ሰዎች ምንም ዓይነት እርዳታ ሳላደርግ በመቅረቴ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል” ሲል የተሰማውን ገልጿል። “በውዥንብሩ መካከል በድንጋጤ እግሬ አውጪኝ ብለው ከባቡር ጣቢያው ከሸሹት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ነበርኩ።”

ሬሞን የተባለ ከብራዚል የመጣ አንድ ወጣት እሱ በነበረበት ባቡር ውስጥ በደረሰው ፍንዳታ እጅግ ከመደናገጡ የተነሳ መንቀሳቀስ እንኳ ተስኖት ነበር። ሆኖም አደጋው ከደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ የአምላክን መንግሥት መልእክት ለሌሎች ለመስበክ ወጣ። የስብከቱን ሥራ እያከናወነ ሳለ ያጋጠመው አንድ ፖርቱጋላዊ ሰው እውነተኛውን ሃይማኖት በመፈለግ ላይ እንደነበረ ነገረው። ሬሞን ይህን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት የጀመረ ሲሆን ሰውየው ወዲያውኑ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምሯል። ሬሞን “ሌሎችን በመንፈሳዊ በምትረዳበት ጊዜ ትደሰታለህ” ሲል ተናግሯል።

የአደጋው ሰለባዎች በሙሉ ከደረሰባቸው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት ለማገገም ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የሚያሳዝነው የምንኖረው በየትኛውም ቦታ በድንገት ትርጉም የለሽ የሆነ የዓመፅ ድርጊት ሊፈጸም በሚችልበት ዘመን ውስጥ ነው። መንፈሳዊ ሰው መሆን እንዲህ ያለው አደጋ የሚያስከትለውን አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለመቋቋም የሚረዳ ቢሆንም እነዚህን አሳዛኝ ክስተቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች/ሣጥን]

አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳትን ለመቋቋም የሚያስችል መንፈሳዊ ብርታት

ማኑዌል ስዋሬስ

“በድንጋጤ ተውጬ ወደ ሆስፒታል እስኪወስዱኝ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ ‘የእግዚአብሔር ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል’ የሚሉትን የምሳሌ 18:10 ቃላት አስብ ነበር። እነዚህ ቃላት አበረታተውኛል።”

አሮአ ሳን ሁዋን

“እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደሆነና ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ከምንጊዜውም በበለጠ እንድታስተውል ያደርግሃል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማራሁ መሆኔ ከደረሰብኝ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት ቀስ በቀስ እንዳገግም ረድቶኛል።”

ፌርሚን ሄሱስ ሞዛስ

“ጭንቅላቴ ላይ ጉዳት ቢደርስብኝም የተጎዱ ሌሎች ተሳፋሪዎችን መርዳትና ማጽናናት ችያለሁ። እንድረጋጋ ያስቻለኝ አምላክ ቃል የገባው የትንሣኤ ተስፋ ይመስለኛል፤ ይህ ተስፋ እንዲህ ባሉ ወቅቶች ብርታት ይሰጠናል።”

ፔድሮ ካራስኪያ

“ኃይለኛ በሆነ የደረት ሕመም እየተሠቃየሁ በሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ተኝቼ ሳለሁ በ1 ጢሞቴዎስ 6:19 ላይ የሚገኙት ቃላት በተደጋጋሚ ወደ አእምሮዬ ይመጡ ነበር። እነዚህ ቃላት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት እናገኝ ዘንድ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት እንድናከማች ያበረታቱናል። ይህ ጥቅስ አምላክ ለሚወዱት ሰዎች ቃል የገባውን የገነት ተስፋ እንዳስታውስ አድርጎኛል። ጥረት እያደረግን ያለነውም ይህን ተስፋ ለመውረስ ነው።”

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ:- የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአቶቻ ባቡር ጣቢያ ውጪ በሚገኙ ሀዲዶች ላይ ቁስለኞችንና በሞት ጣር ላይ ያሉትን ሲረዱ

[ምንጭ]

ከላይ:- CORDON PRESS

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተቀኝ:- በቦታው ያለውን ነገር በመጠቀም የተሠራ መታሰቢያ