በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይሖዋ እንደገና አገኘኸኝ!”

“ይሖዋ እንደገና አገኘኸኝ!”

“ይሖዋ እንደገና አገኘኸኝ!”

ኔሊ ሌንስ እንደተናገረችው

ቤታችን የመጡትን ሁለት ወንዶች “የይሖዋ ምሥክሮች ናችሁ?” ብዬ ጠየቅኳቸው። “አዎን” ብለው ሲመልሱልኝ በጣም ተደስቼ “እኔም ነኝ!” አልኳቸው። በዚያን ጊዜ ገና የ13 ዓመት ልጅ የነበርኩ ከመሆኑም በላይ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ አልገኝም ነበር። ወላጆቼም ቢሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አልነበሩም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ራሴን የይሖዋ ምሥክር ነኝ ብዬ ያስተዋወቅኩት ለምን ይሆን?

የይሖዋ ምሥክሮች በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ባያድኑኝ ኖሮ አልወለድም ነበር። እናቴ ካናዳ ውስጥ በኩቤክ፣ ሞንትሪያል ትኖር በነበረበት ጊዜ እኔ ተጸነስኩ። ያን ጊዜ ገና 17 ዓመቷ ነበር። የእናቴ ቤተሰቦች እንድታስወርድ በጣም ይጨቀጭቋት ስለነበር በጉዳዩ ተስማማች።

ከዚያም እናቴ ጽንሱን ለማስወረድ ከመሥሪያ ቤቷ እረፍት ጠየቀች። የይሖዋ ምሥክር የነበረችው አለቃዋ እናቴ ለምን እረፍት እንደፈለገች ስላወቀች ሕይወት ምን ያህል ውድ ስጦታ እንደሆነ አጠር አድርጋ ገለጸችላት። (መዝሙር 139:13-16) እናቴ ወደ ክሊኒክ እየሄደች አለቃዋ ባለቻት ነገር ላይ ካሰላሰለች በኋላ ላለማስወረድ ወሰነች። ከዚያም በ1964 ተወለድኩና እናቴ ለሕፃናት ማሳደጊያ ሰጠችኝ።

ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሰማሁ

የሁለት ዓመት ገደማ ልጅ እያለሁ እናቴና በቅርቡ ያገባችው ባሏ ከሕፃናት ማሳደጊያው አስወጥተው ወሰዱኝና አብሬያቸው መኖር ጀመርኩ። እናቴና እንጀራ አባቴ በሳንት ማገሪት ዱዌ ላክ ማሶን ከተማ ይኖሩ በነበረ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ወደ ብዋብሪያን ከተማ በመዘዋወራችን ወላጆቼ ጥናታቸውን አቆሙ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ እንደገና ማጥናት ጀመሩ። ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሲያጠኑ ተደብቄ አዳምጥ ነበር። (ሉቃስ 23:43) ከዚያም ይሖዋን መውደድ ጀመርኩ።

ሆኖም አንድ ቀን እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ማቆማቸውንና ወደ መንግሥት አዳራሽ ዳግም እንደማንሄድ ነገረችኝ። በመጀመሪያ ነገሩ አስደስቶኝ ነበር። ምክንያቱም የስምንት ዓመት ልጅ ስለነበርኩ አንዳንድ ጊዜ የስብሰባዎቹ ሰዓት በጣም ይረዝምብኛል። ያን ዕለት ምሽት ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ፈለግሁ፤ ሆኖም ‘አይሰማኝ ይሆን እንዴ?’ ብዬ ተጨነቅኩ።

በቀጣዩ እሁድ ዕለት ከሰዓት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ጎረቤቶቻችን ለስብሰባ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሲሄዱ አየሁ። “የእነርሱ ልጆች ወደ ስብሰባ ሲሄዱ እኔ የማልሄደው ለምንድን ነው?” ብዬ እያለቀስኩ አምላክን ጠየቅኩት። የሆነ ሆኖ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤ ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኩረዋል” የሚሉት የመዝሙር 33:18 ቃላት እውነት መሆናቸውን አረጋግጫለሁ።

እንደገና በስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ

ከሦስት ሳምንታት በኋላ ወደ ጎረቤቶቻችን ቤት ሄጄ ሊሊያን ለምትባለው የልጆቹ እናት በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደምፈልግ ነገርኳት። እርሷም፣ እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ ስለማትፈልግ ወደ ስብሰባ ይዛኝ ልትሄድ እንደማትችል ነገረችኝ። በጣም ስለ ጨቀጨቅኳት ቤታችን መጥታ ከእነርሱ ጋር እንድሄድ ትፈቅድልኝ እንደሆነ እናቴን ጠየቀቻት። የሚገርመው ነገር እናቴ እንድሄድ ፈቀደችልኝ። በስብሰባዎች ላይ መገኘቴ ስለ መልካም ሥነ ምግባር እንድማር እንደሚያደርገኝ ተናገረች። ከዚያ በኋላ ሁልጊዜ እሁድ እሁድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እገኝ ጀመር።

ለሦስት ዓመታት ያህል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቻልኩ። ሆኖም የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ከባሏ ጋር በመፋታቷ እኔን ይዛ ከቤት ወጣች። አሁንም እንደገና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረኝ ግንኙነት ተቋረጠ።

ያልታሰበ አጋጣሚ

አንድ ቀን በቤታችን የፊት በር በኩል ባለው ደረጃ ላይ ተቀምጬ ሳለ ኤዲ ቤሶን እና ዶን ፊሸር የተባሉ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ቤተሰቦቼ እቤት ውስጥ መኖራቸውን ጠየቁኝ። እንደሌሉ ስነግራቸው ተመልሰው ሄዱ። ነገር ግን በሩጫ ተከተልኳቸውና በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ነገር ተነጋገርን።

ራሴን የይሖዋ ምሥክር ነኝ ብዬ ማስተዋወቄ ሁለቱን ሰዎች እንዳስደነቃቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ታሪኬን ከነገርኳቸው በኋላ ማታ ተመልሰው እንዲመጡ ለመንኳቸው። ለእናቴ የይሖዋ ምሥክሮች ሊጠይቁን እንደሚመጡ ስነግራት በጣም ተበሳጭታ ወደ ቤት እንደማታስገባቸው ነገረችኝ። እንዲያውም እነርሱ ከመምጣታቸው በፊት ከቤት ልትወጣ አስባ ነበር። እያለቀስኩ እንዳትሄድ ለመንኳት። ለመውጣት እየተዘገጃጀች ሳለች የቤቱ ደወል ተደወለ፤ ኤዲ ቤሶን ነበር የመጣው። እናቴ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ስትስማማ ምን ያህል እንደተደሰትኩ መገመት ትችላላችሁ!

አሁንም በድጋሚ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቻልኩ! ሆኖም ይህ ከሆነ አንድ ዓመት ሳይሞላ እናቴ እንደገና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን አቆመች። በዚህን ጊዜ እኔም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረኝ የከለከለችኝ ሲሆን ማግኘት የቻለችውን የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሟቸውን ጽሑፎች በሙሉ ጣለች። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመዝሙር መጽሐፍ፣ ሁለት የመጠበቂያ ግንብ ጥራዞች፣ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጻሕፍት እና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ መደበቅ ቻልኩ። * ይሖዋን በጣም እወድ ስለነበር በመጨረሻ ጥናቴ ላይ ለኤዲ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ጠየቅኩት። እርሱም በግል ማጥናቴን እንድቀጥልና አዘውትሬ እንድጸልይ አበረታታኝ። ይሖዋ በጭራሽ እንደማይተወኝ አስረግጦ ነገረኝ። ያን ጊዜ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ።

የራሴን “ስብሰባዎች” ማካሄድ ጀመርኩ

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየሳምንቱ እሁድ ወደ መኝታ ክፍሌ እገባና ልክ ስብሰባ ላይ እንዳለሁ አድርጌ አስባለሁ። የማስታውሰው “ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ይተከል!” የሚለውን መዝሙር ብቻ ስለነበር “ስብሰባዬን” ስጀምርም ሆነ ስጨርስ ይህን መዝሙር እዘምራለሁ። እስከ አሁን ድረስ ይህ መዝሙር ሲዘመር እንባዬን መቆጣጠር አልችልም። ከመዝሙሩ በኋላ፣ ደብቄ ከመጣል ካዳንኳቸው የመጠበቂያ ግንብ ጥራዞች ላይ አንድ ርዕሰ ትምህርት አጠናለሁ። በመጨረሻም “ስብሰባዬን” በጸሎት እደመድማለሁ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለረጅም ጊዜ ሳልገናኝ ብቆይም እንኳ ይሖዋ አብሮኝ እንዳለ ይሰማኝ ነበር።

አሥራ ሰባት ዓመት ሲሞላኝ በሞንትሪያል ከተማ መኖር ጀመርን። ቤታችን ምንም ፍቅር የሌለበት ስለነበር እነዚህ ጊዜያት በጣም አስቸጋሪ ነበሩ።

ይሖዋ አገኘኝ!

አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ለእናቴ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ አበረከቱላት። ወደ ቤት ስገባ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብሎ አገኘሁትና አንስቼ ማንበብ ጀመርኩ። ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በመጽሐፉ ላይ ሳይ እያለቀስኩ በልቤ “ይሖዋ እንደገና አገኘኸኝ!” በማለት ጸለይኩ።

ከክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ለመገናኘት ፈለግኩ። ግን እንዴት ላገኛቸው እችላለሁ? እናቴ አንድ ጎረቤታችን የይሖዋ ምሥክር ሳይሆን እንደማይቀር ነገረችኝ። ስለዚህ ወደ ሥራ እየሄድኩ ሳለ የነገረችኝን ቤት ደወል ተጫንኩት። ከእንቅልፉ በደንብ ያልነቃ አንድ ሰው በሩን ከፈተ። ከዚያም የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩና መጠመቅ እንደምፈልግ ስገልጽለት በጣም ገረመው! ከዚያም ዮሴ ሚሮን ከተባለች እህት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንድጀምር ዝግጅት አደረገ። የሚገርመው እናቴ አሁንም እንደገና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ተቃወመች። ዕድሜዬ 18 ዓመት ሳይሞላ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን መወሰን እንደማልችል ነገረችኝ።

ጥሩ ቤተሰብ ለማግኘት ስል ይሖዋን ማምለክ ልተው?

አሠሪዬ በቤት ውስጥ ያለብኝ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣ ስላስተዋለ ብዙ ጊዜ ቅዳሜና እሁድን ከእርሱና ከሚስቱ ጋር እንዳሳልፍ ይጋብዘኝ ነበር። ፈረስ በጣም ስለምወድ ብዙውን ጊዜ አብረን እንጋልባለን። እነዚህ ባልና ሚስት የራሴ ቤተሰቦች እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር።

አንድ ቀን አሠሪዬ እርሱና ሚስቱ በጣም እንደሚወዱኝና ከእነርሱ ጋር እንድኖር እንደሚፈልጉ ነገረኝ። ሁልጊዜ አፍቃሪ የሆነ ቤተሰብ እንዲኖረኝ እመኝ ስለነበር የጠየቀኝ የልቤን ፍላጎት ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያለኝን ግንኙነት ካቋረጥኩ ብቻ እንደሆነ ገለጸልኝ። በጉዳዩ ላይ ከመወሰኔ በፊት እንዳስብበት የአንድ ሳምንት ጊዜ የሰጡኝ ቢሆንም እኔ ግን አንድም ቀን ማሰብ አላስፈለገኝም። ወዲያውኑ መልስ ሰጠኋቸው። ይሖዋ እንዳልጣለኝ ሁሉ እኔም አልተወውም።

ለአምላክ ያቀረብኩት አገልግሎት

በቤት ውስጥ ያለብኝ ችግር በጣም ስለከበደኝ ከቤት ወጥቼ ከእንጀራ አባቴ ጋር መኖር ጀመርኩ። የእንጀራ አባቴ በጥናቴ እንድገፋበት ያበረታታኝ ነበር፤ ከዚያም በ19 ዓመቴ ታኅሣሥ 17, 1983 ተጠመቅኩ። ኤዲ ቤሶን በተጠመቅኩበት ዕለት አብሮኝ ስለነበር በጣም ተደሰትኩ። መቼም ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን አይጠራጠርም!

ከተጠመቅኩ በኋላ ግን የእንጀራ አባቴ ባሕርይ ተለወጠብኝ። ስጸልይ ከተመለከተ ጮክ ብሎ ይናገራል ወይም የሆነ ዕቃ ይወረውርብኛል! እንዲሁም አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ለመሆን ካለኝ ፍላጎት ጋር የሚጋጭ ትምህርት እንድማር ይጫነኝ ነበር። ቆይቶም ከቤት እንድወጣለት ጠየቀኝ። ከዚያም 100 የካናዳ ዶላር ቼክ ሰጠኝና ቼኩን ስመነዝር ይሖዋ ምንም እንደማያስብልኝ እንደምገነዘብ ነገረኝ።

መስከረም 1, 1986 አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ ያን ቼክ ግን እስከ አሁን ድረስ አልመነዘርኩትም! አንዳንድ ጊዜ በገጠር ውስጥ ያለመኪና አቅኚ ሆኖ ማገልገል የሚከብድ ቢሆንም የጉባኤው አባላት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ይሰጡኝ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ሩበን ሌንስ የተባለ ደግ ክርስቲያን ወንድም ተዋወቅኩና በ1989 ተጋባን። በአሁኑ ጊዜ ሩበን ከ2002 ጀምሮ በምንኖርበት በካናዳ፣ ኦንታሪዮ፣ በሚልተን ከተማ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። ይሖዋ ከሰጠኝ ታላላቅ በረከቶች መካከል አንዱ ትዳር ነው። የመጀመሪያ ልጃችን ኤሪካ እስከተወለደችበት እስከ 1993 ድረስ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነበርኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ ወንድ ልጃችን ሚካ ተወለደ። ከብዙ ዓመታት የብቸኝነት ኑሮ በኋላ ይሖዋ አምላክ እኔ እርሱን የምወደውን ያህል የሚወዱት ቤተሰቦች በመስጠት ባርኮኛል።

በተደጋጋሚ ጊዜያት ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ተጠፋፍቼ የኖርኩ ቢሆንም አምላክን ተስፋ ማድረጌንና በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደማገኝ ያለኝን ተስፋ ፈጽሞ ዘንግቼ አላውቅም። (ዮሐንስ 3:36) ይሖዋ ‘እንደገና ስላገኘኝ’ በጣም አመስጋኝ ነኝ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአሠሪዬን ፈረስ ስጋልብ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኔሊ ሌንስ ከባሏ ከሩበን እንዲሁም ከልጆቿ ከኤሪካና ከሚካ ጋር