በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጭፍን ጥላቻ የሚያከትምበት ጊዜ

ጭፍን ጥላቻ የሚያከትምበት ጊዜ

ጭፍን ጥላቻ የሚያከትምበት ጊዜ

በውስጣችን የጭፍን ጥላቻ አዝማሚያ እንዳለ ይሰማናል? ለምሳሌ የአንድን ሰው የቆዳ ቀለም፣ ብሔር፣ ጎሣ ወይም ነገድ ተመልክተን ከዚያ በፊት የማናውቀው ሰው እንኳን ቢሆን እንዲህ ዓይነት ሰው ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን? ወይስ እያንዳንዱን ሰው የምንመዝነው በራሱ የግል ባሕርያት ላይ ተመርኩዘን ነው?

በኢየሱስ ዘመን በይሁዳና በገሊላ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ‘ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበር።’ (ዮሐንስ 4:9) በታልሙድ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው “ሳምራዊ አታሳየኝ” የሚለው አባባል ብዙዎቹ አይሁዶች የነበራቸውን ስሜት የሚያንጸባርቅ እንደሆነ አያጠራጥርም።

የኢየሱስ ሐዋርያት እንኳን በሳምራውያን ላይ መጠነኛ ጥላቻ የነበራቸው ይመስላል። በአንድ ወቅት የአንድ የሳምራውያን መንደር ነዋሪዎች ጥሩ አቀባበል ሳያደርጉላቸው ቀሩ። ያዕቆብና ዮሐንስ እነዚህን ያልተቀበሏቸውን ሰዎች እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲበላቸው ለማድረግ ጠየቁ። ኢየሱስ ተግሣጽ በመስጠት እንዲህ ያለው ዝንባሌ ትክክል እንዳልሆነ አመልክቷል።—ሉቃስ 9:52-56

በኋላም ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲጓዝ ወንበዴዎች አግኝተው ስለደበደቡትና ስለዘረፉት ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ነገራቸው። በዚያ ያልፉ የነበሩ ሁለት አይሁዳውያን ሃይማኖተኛ ሰዎች ሊረዱት አልፈለጉም። አንድ ሳምራዊ ግን ቆሞ የሰውየውን ቁስል አሰረለት። ከዚያም ከጉዳቱ እንዲያገግም የሚያስችለውን ዝግጅት አደረገለት። ይህ ሳምራዊ እውነተኛ ባልንጀራ ሆኖ ተገኝቷል። (ሉቃስ 10:29-37) የኢየሱስ ምሳሌ አድማጮቹ የነበራቸው ጭፍን ጥላቻ የሌሎችን መልካም ባሕርይ እንዳይመለከቱ ያደረጋቸው መሆኑን እንዲያስተውሉ ሳይረዳቸው አልቀረም። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዮሐንስ ወደ ሰማርያ ተመልሶ በብዙ መንደሮች፣ ምናልባትም በአንድ ወቅት ሊያጠፋው ፈልጎ በነበረው መንደር ጭምር ሰብኳል።—የሐዋርያት ሥራ 8:14-17, 25

በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ አንድ መልአክ ሮማዊ መቶ አለቃ ለነበረ ቆርኔሌዎስ የተባለ ሰው ስለ ኢየሱስ እንዲናገር ባዘዘው ጊዜ የነበረውን የአድልዎ ስሜት ማስወገድ ነበረበት። ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር ተቀራርቦ የማያውቅ ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ሮማውያን ወታደሮችን ይጠሉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 10:28) የአምላክን አመራር ከተመለከተ በኋላ ግን “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል” ብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ጭፍን ጥላቻን የምንዋጋበት ምክንያት

ጭፍን ጥላቻ ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” ሲል ያስተማረውን መሠረታዊ ሥርዓት ይጥሳል። (ማቴዎስ 7:12) በትውልድ አካባቢው፣ በቆዳው ቀለም ወይም በቀድሞ ታሪኩ ምክንያት መናቅ የሚፈልግ ማን ይኖራል? በተጨማሪም ጭፍን ጥላቻ የአምላክን ከአድልዎ ነጻ የሆኑ ደንቦች ይቃረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26) ስለዚህ ሁሉም ሰዎች ወንድማማቾች ናቸው።

ከዚህም በላይ አምላክ የሚፈርደው እያንዳንዱ ግለሰብ በተናጠል በሚያሳየው ባሕርይ ነው። ማንንም ሰው ወላጆቹ ወይም የጥንት አባቶቹ ባደረጉት ጥፋት አይኮንንም። (ሕዝቅኤል 18:20፤ ሮሜ 2:6) አንድ ብሔር በሌላው ላይ የሚፈጽመው ጭቆና እንኳን ለተፈጸመው በደል ተጠያቂ ያልሆኑ የዚያ ብሔር አባላት የሆኑ ግለሰቦችን ለመጥላት ምክንያት አይሆንም። ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘ጠላቶቻቸውን እንዲወዱና ለሚያሳድዷቸው እንዲጸልዩ’ አስተምሯል።—ማቴዎስ 5:44, 45

እንደነዚህ ባሉት ትምህርቶች ምክንያት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የነበራቸውን ጭፍን ጥላቻ አሸንፈው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ለመመስረት ችለዋል። እርስ በርሳቸው ወንድምና እህት ተባብለው ከመጠራራታቸውም በላይ ከበርካታ ባሕሎች የተውጣጡ ቢሆኑም በእርግጥ ወንድማማቾች እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። (ቆላስይስ 3:9-11፤ ያዕቆብ 2:5፤ 4:11) እንዲህ ያለውን የአመለካከት ለውጥ ያስገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ዛሬም ተመሳሳይ የሆነ ጥቅም ሊያመጡ ይችላሉ።

በዛሬው ዘመን ጭፍን ጥላቻን መዋጋት

ሁላችንም የየራሳችን ጭፍን አመለካከት ሊኖረን ቢችልም ይህ አመለካከታችን ጭፍን ጥላቻ እንዲያድርብን ምክንያት ሊሆን አይገባም። ዘ ኔቸር ኦቭ ፕረጀዲስ የተባለው መጽሐፍ “ጭፍን አመለካከቶች ወደ ጭፍን ጥላቻ የሚለወጡት በአዲስ እውቀት እንኳን የማይለወጡ ሲሆኑ ነው” ይላል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲተዋወቁ በመካከላቸው የነበረው ጭፍን ጥላቻ ይወገዳል። ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ እንደሚለው “የአመለካከት ለውጥ የሚፈጠረው ሰዎች በጋራ አንድ ነገር እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ዓይነት ግንኙነት ሲኖር ብቻ ነው” ይላል።

ጆን የተባለው ናይጄሪያዊ የኢቦ ጎሣ አባል፣ ለሐውሳዎች የነበረውን ጥላቻ ሊያሸንፍ የቻለው በዚህ መንገድ ነበር። “ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ ከሐውሳ ተማሪዎች ጋር ተገናኘሁና ጓደኛ አደረግኳቸው። በጣም ጥሩ ጠባይ እንዳላቸው ተገነዘብኩ። እኔና አንድ ሐውሳ ተማሪ አንድ የጋራ ፕሮጀክት ሠራን። ከዚህ በፊት አብሮኝ የሠራው የኢቦ ጎሣ አባል የሆነ ባልደረባዬ እየሰነፈ ያስቸገረኝ ሲሆን ከሐውሳው ጓደኛዬ ጋር ግን በጣም ተግባብተን ሠራን” ብሏል።

ጭፍን ጥላቻን ለመዋጋት የሚያስችል መሣሪያ

ዩኔስኮ አጌንስት ሬሲዝም የተባለው ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ “ከአዳዲስ ዓይነት የዘር ጥላቻ፣ ከማዳላትና ከማግለል ጋር በምናደርገው ትግል ትምህርት በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ሊሆን ይችላል።” በዚህ ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የበለጠ ጥሩ መሣሪያ ሊገኝ እንደማይችል የይሖዋ ምሥክሮች ያምናሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ሥራ ላይ ሲያውሉ ጥርጣሬ በመከባበር፣ ጥላቻ ደግሞ በፍቅር ይተካል።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የነበራቸውን ጭፍን ጥላቻ እንዲያሸንፉ እየረዳቸው መሆኑን ተገንዝበዋል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ባሕል ካላቸውና የሌላ ጎሣ አባል ከሆኑ ሰዎች ጋር በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ የሚያስችላቸውን ምክንያትና አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ክርስቲና የይሖዋ ምሥክር ነች። “በመንግሥት አዳራሽ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች በራሴ እንድተማመን ይረዱኛል። በዚያ ያለ ማንም ሰው በጭፍን እንደሚጠላኝ ስለማይሰማኝ ምንም ዓይነት ፍርሃት አይሰማኝም” ትላለች።

የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ጃስሚንም የዘር ጥላቻን ገፈት የቀመሰችው ገና በዘጠኝ ዓመት ዕድሜዋ ነበር። “ከሳምንቱ ቀናት በሙሉ የሐሙስን ያህል የሚቀለኝ ቀን አልነበረም። ምክንያቱም በዚህ ቀን ምሽት ወደ መንግሥት አዳራሽ እሄዳለሁ። እዚያም ሰዎች ፍቅር ያሳዩኛል። የተናቅሁ ሳይሆን ልዩ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጋሉ” ብላለች።

በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዷቸው በፈቃደኛ ሠራተኞች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሰዎችን ያቀራርባሉ። ሳይመን የተወለደው በብሪታንያ ቢሆንም ወላጆቹ ግን የመጡት ከካሪቢያን ደሴቶች ነበር። ለዓለማዊ የግንባታ ኩባንያዎች ግንበኛ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ አንዳንዶች በጭፍን ይጠሉት ነበር። ከእምነት ወንድሞቹ ጋር ሆኖ በዓለም አቀፍ የግንባታ ሥራ በፈቃደኝነት በሰራበት ጊዜ ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ አላጋጠመውም። ሳይመን “ከተለያዩ አገሮች ከመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሠርቻለሁ። እርስ በርሳችን እንዴት ተግባብተን መሥራት እንደምንችል ተምረናል። ከቅርብ ጓደኞቼ አንዳንዶቹ ከሌላ አገር የመጡና ሌላ ዓይነት አስተዳደግ ያላቸው ናቸው” ይላል።

የይሖዋ ምሥክሮች ፍጹማን እንዳልሆኑ የሚካድ ነገር አይደለም። በመሆኑም ወደ ጭፍን ጥላቻ የሚመሩ አዝማሚያዎችን ለመዋጋት ይገደዳሉ። ይሁን እንጂ አምላክ እንደማያዳላ ማወቃቸው ጭፍን ጥላቻን በቁርጠኝነት እንዲዋጉ ይገፋፋቸዋል።—ኤፌሶን 5:1, 2

ጭፍን ጥላቻን መዋጋት ብዙ ጥቅም ያስገኛል። ከሌላ አካባቢ ከመጡ ሰዎች ጋር ስንደባለቅ ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች ይሆናል። ከዚህም በላይ አምላክ በቅርቡ በመንግሥቱ አማካኝነት ጽድቅ የሚሰፍንበት ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ያቋቁማል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያ ጊዜ ጭፍን ጥላቻ ለዘላለም ይወገዳል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጭፍን ጥላቻ በውስጤ ይኖር ይሆን?

ሳታውቀው በውስጥህ የጭፍን ጥላቻ ስሜት ይኖር እንደሆነ ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ራስህን መርምር:-

1. ከአንድ የተወሰነ ዘር፣ አካባቢ ወይም ብሔር የመጡ ሰዎች ምንም ነገር ቢሏቸው እንደማይገባቸውና እንደ ስንፍና ወይም ስስት ያሉ መጥፎ ባሕርያት እንዳሏቸው አድርጌ አስባለሁ? (ብዙ ቀልዶች ሰዎች በውስጣቸው እንዲህ ያለ ጭፍን ጥላቻ ይዘው እንዲኖሩ ያደርጋሉ።)

2. ላሉብኝ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ችግሮች ከሌላ አገር የመጡ ሰዎችን ወይም የሌላ ጎሣ አባላትን ተጠያቂ የማድረግ ዝንባሌ አለኝ?

3. የምኖርበት አገር ከሌላ አገር ጋር ያለው ለረጅም ጊዜ የቆየ ጠላትነት ለዚያ አገር ሰዎች ጥላቻ እንዲያድርብኝ አድርጎኛል?

4. የማገኘውን እያንዳንዱን ሰው ምንም ዓይነት የቆዳ ቀለም ወይም ባሕል ይኑረው ወይም ደግሞ የየትኛውም ጎሣ አባል ይሁን ከራሱ ስብዕና አንጻር የመመልከት ዝንባሌ አለኝ?

5. የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር መተዋወቅ የምችልበት አጋጣሚ ሳገኝ በሚገባ እጠቀምበታለሁ? እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ለማግኘትስ ጥረት አደርጋለሁ?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ጭፍን ጥላቻን እንዴት ማስወገድ እንደምንችል አስተምሯል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ቤት ሳለ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ” ብሏል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተለያየ አካባቢ የመጡና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች አንድ ያደርጋል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች የተማሩትን ሥራ ላይ ያውላሉ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲና--“በመንግሥት አዳራሽ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች በራሴ እንድተማመን ይረዱኛል”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጃስሚን--“ሰዎች ፍቅር ያሳዩኛል። የተናቅሁ ሳይሆን ልዩ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጋሉ”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በግንባታ ሥራ በፈቃደኝነት የሚያገለግለው ሳይመን--“እርስ በርሳችን እንዴት ተግባብተን መሥራት እንደምንችል ተምረናል”