በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ናይሮቢ—“የቀዝቃዛ ውኃ ሥፍራ”

ናይሮቢ—“የቀዝቃዛ ውኃ ሥፍራ”

ናይሮቢ—“የቀዝቃዛ ውኃ ሥፍራ”

በኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“የሰው ዘር የማይታይበት ረግረጋማና ውኃ ያቆረ ጠፍ መሬት፤ የተለያዩ ዝርያዎች ያላቸው እልፍ አዕላፋት የዱር እንስሳት የሚፈነጩበት ገላጣ ምድር። አልፎ አልፎ ሰው ወደ አካባቢው እንደሚመጣ የሚያሳየው ምልክት የረግረጋማውን ሜዳ ዳርቻ ተከትሎ የሚሄደው የቆየ የእግር መንገድ ብቻ ነው።”—ዘ ጀነሲስ ኦቭ ኬንያ ኮሎኒ

እነዚህ ቃላት የዛሬ አንድ መቶ ዓመት ገደማ የአንበሶች፣ የአውራሪሶች፣ የሊዮፓርዶች፣ የቀጭኔዎች፣ የመርዘኛ እባቦችና የሌሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው እንስሳት መናኸሪያ ስለነበረችው ስለ ናይሮቢ የተነገሩ ናቸው። ደፋሮቹ የማሳይ ጎሳዎች እንደ ውድ ንብረቶቻቸው የሚያዩአቸውን ከብቶቻቸውን ውኃ ለማጠጣት በአካባቢው ወዳለው ወንዝ የሚመጡ ሲሆን ቦታው ለዘላኑ ኅብረተሰብ በጣም ተወዳጅ ስፍራ ነበር። እንዲያውም ለወንዙ “ቀዝቃዛ ውኃ” የሚል ትርጓሜ ያለውን ኡዋሶ ናይሮቢ የሚል ስም ያወጡለት ማሳዮች ናቸው። አካባቢውንም ኢንካሪ ናይሮቢ ወይም “የቀዝቃዛ ውኃ ሥፍራ” ብለው በመጥራት የኬንያን ታሪክ እስከ ወዲያኛው የሚቀይር ስያሜ ሰጥተውታል።

ለናይሮቢ ከተማ እድገት ቁልፍ ሚና የተጫወተው ቀድሞ ሉናቲክ ኤክስፕረስ እየተባለ ይጠራ የነበረው የኬንያ የባቡር መሥመር መዘርጋቱ ነው። * በ1899 አጋማሽ ላይ ከጠረፍ ከተማዋ ከሞምባሳ አንስቶ እስከ ናይሮቢ የሚደርስ 530 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር ሐዲድ ተዘርግቶ ነበር። የግንባታ ሠራተኞቹ በዚህ አካባቢ ሲደርሱ “የሳቮ ሰው በላዎች” የሚል ስም ያተረፉት ሁለት አንበሶች በርካታ የሥራ ባልደረባዎቻቸውን የገደሉባቸው ሲሆን ከፊታቸው ደግሞ ፈጽሞ የማይደፈር የሚመስለው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ይጠብቃቸው ነበር። የባቡር መሥመሩ ወደ መሃል አገር ዘልቆ ስለሚገባ የግንባታ ቁሳቁሶችን በሞምባሳ ማከማቸቱ ብዙም አመቺ ሆኖ አልተገኘም። እናም ናይሮቢ ለመኖሪያነት ተስማሚ ሥፍራ ባትመስልም ለሠራተኞቹ ማረፊያና ለግንባታ ቁሳቁሶች ማከማቻ አመቺ ቦታ እንደሆነች ታመነበት። ይህ ውሳኔ ከጊዜ በኋላ ከተማዋ የኬንያ መዲና እንድትሆን መንገድ ጠርጓል።

በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ናይሮቢ አዲስ ለተቋቋመው የምሥራቅ አፍሪካ የሞግዚት አስተዳደር (ኬንያ በወቅቱ ትጠራበት የነበረው ስም ነው) ዋና መቀመጫ እንድትሆን ተመረጠች። ከተማዋ ገና በማደግ ላይ እንደመሆኗ በእቅድና በፕላን ብትሠራ የተሻለ ይሆን ነበር። ይሁንና ለዚህ አልታደለችም። እንደ ነገሩ የተሠሩ ትርኪ ምርኪ ቤቶች በባቡር ጣቢያው ዙሪያ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ከእንጨት፣ ከቆርቆሮና በአካባቢው ከተለመዱት የግንባታ ቁሳቁሶች የተሠሩት እነዚህ ቤቶች ከተማዋን የወደፊት ዓለም አቀፋዊ መናኸሪያ ሳይሆን የደሳሳ ጎጆዎች መንደር አስመስለዋት ነበር። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በናይሮቢ የነበሩት በጣት የሚቆጠሩ ሕንጻዎች ከተማዋ ወደፊት ልታድግ ትችላለች በሚል ራእይ የታነጹ አልነበሩም። በአቅራቢያው የሚኖሩት የዱር አራዊት የሚፈጥሩት ስጋትም አልተወገደም ነበር።

ብዙም ሳይቆይ አዲሶቹ ሰፋሪዎች በበሽታ ክፉኛ ተጠቁ። የግዛቱ አስተዳዳሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ብቃታቸው የተፈተነው በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ነበር። መቅሰፍቱን ለመግታት ፈጣን መፍትሔ ያስፈልግ ነበር። እናም በሽታው የተዛመተበት የከተማይቱ ክፍል እንዲቃጠል ተደረገ። በቀጣዩ ግማሽ ምዕተ ዓመት ግን ናይሮቢ ይህን አስቀያሚ ታሪኳን ወደ ኋላ ትታና ሙሉ በሙሉ ተለውጣ በምሥራቅ አፍሪካ የንግድና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ እምብርት የምትሆንበት ደረጃ ላይ ትደርሳለች።

የዘመናዊቷ ከተማ እድገት

ከባሕር ወለል በላይ 1,680 ሜትር ገደማ ከፍታ ላይ በምትገኘው በናይሮቢ ከተማ ሆኖ በዙሪያው ያለውን አካባቢ መቃኘት ይቻላል። ጥርት ባለ ቀን በአፍሪካ ጎላ ብለው የሚታዩ ሁለት ተራራዎችን በቀላሉ መመልከት ይቻላል። በስተ ሰሜን በኩል 5,199 ሜትር በሚደርስ ከፍታው በአገሪቱ የአንደኝነትንና በአፍሪካ የሁለተኝነትን ቦታ የያዘው የኬንያ ተራራ ይታያል። ራቅ ብሎ ደግሞ በስተ ደቡብ ኬንያና ታንዛንያ በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ 5,895 ሜትር ከፍታ ያለው የአፍሪካ ቁጥር አንድ ተራራ ኪሊማንጃሮ ይገኛል። በምድር ወገብ አቅራቢያ በሚገኘው የኪሊማንጃሮ ተራራ አናት ላይ ከዓመት እስከ ዓመት የበረዶ ቁልል አለመጥፋቱ ከ150 ዓመታት በፊት አካባቢውን ለመጎብኘት ከአውሮፓ የመጡትን የመልክዓ ምድር አጥኚዎችና አሳሾች ያስደመመ ክስተት ነበር።

ከተማ ተብላ ከተሰየመች ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ያስቆጠረችው ናይሮቢ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አድርጋለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎቿ ለዚህ ምሥክር ናቸው። ከመስተዋትና ከብረት የታነጹት እነዚህ ረጃጅምና ግርማ ሞገስ የተላበሱ ዘመናዊ ሕንጻዎች ጀንበር ስትጠልቅ በምትፈጥረው አንጸባራቂ ብርሃን ሲታዩ ዓይን የሚያፈዝ ውበት አላቸው። የናይሮቢን የንግድ አካባቢ የሚጎበኝ አንድ ቱሪስት የቆመበት መሬት ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት የዱር አራዊት የሚፈነጩበትና ለሰው መኖሪያነት አደገኛ የሆነ ሥፍራ እንደነበር ቢነግሩት ለማመን ሊከብደው ይችላል።

ይህ ሁሉ ግን በጊዜ ሂደት ተለውጧል። ቦጋንቪልና ጃካራንዳ የሚባሉ የዛፍ ዝርያዎች፣ እንዲሁም በፍጥነት የሚያድገውን ባሕር ዛፍንና ግራርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የዕጽዋት ዝርያዎች ከውጭ አገር መጥተው ተተክለዋል። በፊት አቧራማ የነበሩት ጥርጊያ መንገዶች ቀስ በቀስ በግራና በቀኝ ዛፍ የተተከለባቸው የሚያማምሩ አውራ ጎዳናዎች የሆኑ ሲሆን ዛፎቹ በሞቃታማ ወቅቶች ለእግረኞች ግሩም ጥላ ይሰጣሉ። በከተማዋ መሃል በሚገኝ አንድ የዕጽዋት ምርምር ጣቢያ ውስጥ በትንሹ 270 የሚያህሉ የዛፍ ዝርያዎች ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር አንድ ሌላ ጸሐፊ ናይሮቢ “በተፈጥሮ ደን መሃል የተቆረቆረች ትመስላለች” ያለበትን ምክንያት ለመረዳት አይከብደንም። በየቦታው የሚገኘው ዕጽዋት ከተማይቱ ቀን ላይ ሞቃታማ በምሽት ደግሞ ቀዝቀዝ ያለ ተወዳጅ የአየር ሁኔታ እንዲኖራት በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ጉራማይሌ ባሕል

በናይሮቢ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡና የየራሳቸው ባሕሎች ያሏቸው ሰዎች ይኖራሉ። በአሁኑ ወቅት የከተማይቱ ነዋሪዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ሲሆን የባቡር መሥመሩ መጠናቀቁ በርካታ ሰዎች በአካባቢው እንዲሰፍሩ አድርጓል። በሐዲዱ ግንባታ ሥራ የተካፈሉት ሕንዳውያን ሥራው ካለቀም በኋላ በዚያ ቀርተው የንግድ ሥራ የጀመሩ ሲሆን ያቋቋሟቸው ኩባንያዎችም እያደጉ ሄደው በመላ አገሪቱ ተስፋፍተዋል። ሌሎች ባለ ሀብቶችም የሕንዳውያኑን ፈለግ ተከትለው ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳና ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መጥተዋል።

ናይሮቢ ድብልቅ ባሕሎች የሚታዩባት ከተማ ናት። በከተማይቱ ጎዳናዎች ላይ በአገሯ ባሕላዊ አለባበስ ያጌጠች አንዲት ሕንዳዊት የቤት እመቤት ወደ ገበያ ስታመራ፣ አንድ የፓኪስታን መሃንዲስ ወደ ግንባታ ቦታው ሲጣደፍ፣ በአለባበሷ ይህ ቀረሽ የማይባልላት ከኔዘርላንድ የመጣች የበረራ አስተናጋጅ በአንድ ሆቴል ውስጥ ክፍል ስትይዝ ወይም አንድ የጃፓን ነጋዴ በናይሮቢ የአክሲዮን ገበያ የሚካሄድ ወሳኝ ስብሰባ እንዳያመልጠው ሲቻኮል ማየት የተለመደ ነው። የከተማው ነዋሪዎች ደግሞ በፌርማታ ላይ አውቶብስ ሲጠብቁ ወይም በገበያ አዳራሾች፣ በሱቆችና በጉሊቶች ሲገበያዩ አሊያም በቢሮዎች ወይም በከተማዋ ውስጥ በሚገኙት በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሲሠሩ መመልከት ይቻላል።

የሚያስገርመው በከተማይቱ ውስጥ ከሚኖሩት ኬንያውያን መካከል እውነተኛ “የናይሮቢ ተወላጆች” ሊባሉ የሚችሉት ጥቂቶቹ ናቸው። አብዛኞቹ ነዋሪዎች “የተሻለ ሕይወት” ፍለጋ ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የፈለሱ ናቸው። ይሁንና በአጠቃላይ ሲታዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ወዳጃዊና እንግዳ ተቀባይ ናቸው። ምናልባትም የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ድርጅቶች መቀመጫቸውን በከተማይቱ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ይህ እንግዳ ተቀባይነት ሳይሆን አይቀርም። በናይሮቢ የሚገኘውን የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና መሥሪያ ቤት ለዚህ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

ቱሪስቶችን የሚስበው ምንድን ነው?

ኬንያ የዱር እንስሳት በዓይነትም ሆነ በብዛት ተትረፍርፈው የሚገኙባት አገር ናት። በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ጥቂት የማይባሉ ብሔራዊ ፓርኮቿን ለመጎብኘት የሚመጡ ሲሆን አብዛኞቹ የጉብኝት ጉዞዎች የሚዘጋጁት በናይሮቢ ነው። ሆኖም ናይሮቢን ለመጎብኘት ብለው የሚመጡ ቱሪስቶችም አሉ። በዓለማችን ከዱር አራዊት ጋር በጉርብትና የሚኖርባቸው ከተሞች ብዙም አይደሉም። ከመሃል ከተማው ከ10 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ የሚገኘው የናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክ የጎብኚዎች መናኸሪያ ነው። * በፓርኩ ውስጥ የናይሮቢ ግንባር ቀደም ነዋሪዎች የሆኑትን የዱር እንስሳት መመልከት ይቻላል። እንስሶቹን ከሰዎቹ የሚለያቸው አነስተኛ የሽቦ አጥር ብቻ ሲሆን በቅርቡ በመስከረም 2002 በአካባቢው ካለው ደን ያመለጠ አንድ ትልቅ ሊዮፓርድ በአንድ የናይሮቢ ቤት ሳሎን ውስጥ ተይዟል።

ከከተማዋ ማዕከል ብዙም ሳይርቅ የናይሮቢ ሙዚየም ይገኛል። በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች የኬንያን አስገራሚ ታሪክ ለማወቅ ወደዚህ ይመጣሉ። በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኘው የእባብ ፓርክ በርካታ የገበሎ ዝርያዎችን ይዟል። በፓርኩ ውስጥ ያሉት አዞዎች የጎብኚዎች በዚያ መገኘት ብዙም የሚረብሻቸው አይመስልም። ከእነርሱ ብዙም ሳይርቅ ደግሞ አንድ ኤሊ በዙሪያው ያለው ዓለም በጥድፊያ የተሞላ ቢሆንም እርሱ ግን በራሱ ፍጥነት እየተንቀራፈፈ ሲጓዝ ይታያል። እርግጥ፣ እዚህ ዋነኞቹ የፓርኩ ነዋሪዎች እንደ ኮብራ፣ ዘንዶና እፉኝት ያሉት በደረታቸው የሚሳቡ ገበሎዎች ናቸው። እነዚህ ፍጥረታት በሚርመሰመሱበት አካባቢ የሚዘዋወር ጎብኚ “ከአጥሩ ካለፉ በእባብ ይነደፋሉ” የሚለውን ምልክት ማስተዋሉ ይበጀዋል።

በዓይነቱ ለየት ያለ ውኃ

ለናይሮቢ ከተማ ስሟን ያስገኘላት ወንዝ እንደድሮው ሁሉ ዛሬም መፍሰሱን ባያቋርጥም በማደግ ላይ ባሉ ከተሞች የተለመደ ችግር በሆነው የኢንዱስትሪዎችና የመኖሪያ ቤቶች ፍሳሽ ተበክሏል። ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት የናይሮቢ ነዋሪዎች ከፍ ካለ ምንጭ የሚፈስ “ውሃ” ሲቀርብላቸው ነበር። ይህ ውኃ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምሩት የሕይወት መልእክት ነው።—ዮሐንስ 4:14

በ1931 ማለትም ናይሮቢ የዛሬውን ዝናዋን ከማግኘቷ ከረጅም ጊዜ በፊት ግሬይ እና ፍራንክ ስሚዝ የተባሉ ወንድማማቾች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በኬንያ ለማሰራጨት ከደቡብ አፍሪካ መጥተው ነበር። ከሞምባሳ ተነስተው የባቡር ሐዲዱ የተዘረጋበትን መሥመር በመከተል ናይሮቢ የደረሱ ሲሆን በመንገዳቸው ላይ በርካታ አደጋዎችን ከመጋፈጣቸውም በላይ በዱር እንስሳቱ መሃል ጫካ ውስጥ ለማደር የተገደዱባቸው ሁኔታዎችም ነበሩ። ናይሮቢ ከገቡ በኋላ 600 የሚያህሉ ቡክሌቶችንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አሠራጭተዋል። በአሁኑ ወቅት በናይሮቢ ወደ 5,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮችና 61 ጉባኤዎች ይገኛሉ። የናይሮቢ ነዋሪዎች በከተማይቱ ውስጥ የጉባኤ፣ የልዩና የወረዳ እንዲሁም የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ስለሚመለከቱ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በቂ ግንዛቤ አላቸው። ብዙዎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ተስፋዎች ላይ የተመሠረተውን መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኞች ናቸው።

ብሩህ የወደፊት ተስፋ

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “በኢንዱስትሪ በበለጸጉ ከተሞች ውስጥ የመኖሪያ ቤት እጥረት የዘወትር ችግር ነው። . . . ፋብሪካዎችም አየሩንና የውኃ ምንጮችን ይበክላሉ” ይላል። ናይሮቢም ብትሆን ከዚህ ችግር አላመለጠችም። ከገጠራማ አካባቢዎች በየዕለቱ ሰዎች መፍለሳቸውን እስካላቆሙ ድረስ ሁኔታው እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም። እነዚህን የመሳሰሉት ችግሮች እየተደራረቡ በሄዱ መጠን የናይሮቢ አንጸባራቂ ውበትም በቀላሉ እየደበዘዘ ሊሄድ ይችላል።

የሚያስደስተው ግን ወደፊት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የከተማን ኑሮ ተፈታታኝ ያደረጉት ችግሮች ተወግደው ሁሉም ሰዎች ሕይወትን የሚያጣጥሙበት ጊዜ ይመጣል።—2 ጴጥሮስ 3:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 የባቡር መሥመሩን ሥራ በሚመለከት የተሟላ መረጃ ለማግኘት በመስከረም 22, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ 21-4 ላይ የወጣውን “የምሥራቅ አፍሪካ ‘ሉናቲክ ኤክስፕረስ ’” የሚል ርዕስ ተመልከት።

^ አን.17 የሰኔ 8, 2003 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 24-27 ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ናይሮቢ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኪሊማንጃሮ ተራራ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኬንያ ተራራ

[ምንጭ]

Duncan Willetts, Camerapix

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የገበያ ቦታ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍራንክ እና ግሬይ ስሚዝ፣ በ1931

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Crispin Hughes/Panos Pictures