ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
አንጎልን ማጨናነቅ
ቶሮንቶ ስታር የተሰኘው የካናዳ ጋዜጣ አንዳንድ ተመራማሪዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ “በአንድ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ለመሥራት መሞከር በአእምሮ ላይ ጫና ይፈጥራል።” በአንድ ጊዜ በርከት ያሉ ሥራዎችን መሥራት ቅልጥፍናን እንደሚቀንስ፣ ለስህተት እንደሚዳርግ ብሎም በሽታ እንደሚያስከትል አንዳንድ ጥናቶች አመልክተዋል። ለምሳሌ ያህል “የማስታወስ ችሎታን ሊያዳክምና የወገብ ሕመም ሊያስከትል የሚችል ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው በጉንፋንና በምግብ አለመፈጨት ችግር በቀላሉ እንዲጠቃ ሊያደርግ አልፎ ተርፎም ጥርስንና ድድን ሊጎዳ” ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጤና ተቋማት ባካሄዱት ጥናት መሠረት ሰዎች አንዳንድ ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ጊዜ በአንጎል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ክፍሎች መሥራት ይጀምራሉ። መኪና እያሽከረከሩ በተንቀሳቃሽ ስልክ እንደመነጋገር ያሉ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ለመሥራት በሚሞክሩበት ጊዜ ግን “አንጎላቸው መቆለፍ ይጀምራል” ሲሉ በኤመሪ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ጆን ስላድኬ ተናግረዋል። “አንጎላቸው ሥራውን ለመሥራት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ለመሥራትም ፈቃደኛ አይሆንም።” ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሰዎች ረጋ ብለው መሥራትና አንጎላቸው የጠየቁትን ነገር ሁሉ ሊሠራላቸው እንደማይችል አምነው መቀበል አለባቸው።
አዳዲስ የዓሣ ዝርያዎች ተገኙ
በቬንዙዌላ የኮውራ ወንዝ ጥናት የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች በቅርቡ “አሥር አዳዲስ የዓሣ ዝርያዎችን እንዳገኙ” አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል “ደማቅ ቀይ ጅራት ያለው” ትንሽ ዓሣ፣ “አናቱ ላይ ጉትዬ የመሰለ አካል ያለው ካትፊሽ የተባለ ዓሣ” እና “ፍራፍሬም ሆነ ሥጋ የሚበላ የፒራና ዓሣ ዝርያ” ይገኙበታል ሲል ኤል ዩኒቨርሳል የተሰኘው የቬንዙዌላ ጋዜጣ ዘግቧል። ያልተነካ የሐሩር ደንና የመርከቦች መተላለፊያ የሆነ የውኃ አካል የሚገኝበት ይህ ክልል በፕላኔታችን ላይ ካሉት በተፈጥሮ ሀብት የበለጸጉና እጅግ በርካታ ዝርያዎች የሚገኙባቸው ቦታዎች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። ሳይንቲስቶች በግብርና፣ በዓሣ ማጥመድ ሥራ፣ በቤቶች ግንባታ፣ በማዕድን ቁፋሮና ሊገነቡ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች አደጋ ያጠላበትን ይህን ክልል መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግለት በመማጸን ላይ ናቸው።
በታካሚዎች ተራ መጠበቂያ ክፍል ውስጥ የሚታይ ውጥረት
“ጀርመናውያን ታካሚዎች ተራ ደርሷቸው ሐኪም ፊት ከመቅረባቸው በፊት በአማካይ ለ48 ደቂቃዎች ያህል ተቀምጠው ለመጠበቅ ይገደዳሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ከዚህ የበለጠ ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል” ሲል ሲኮሎጊ ሆይቴ የተባለው መጽሔት ገልጿል። ቢዝነስ-ማኔጅመንት አናሊስስ፣ ኮንሰልቴሽን ኤንድ ስትራቴጂክ ዴቨለፕመንት የተባለው ተቋም በቅርቡ በ610 ዶክተሮች ሥራ ላይ ያካሄደው ጥናት “ታካሚዎች በሁኔታው በጣም እንደሚበሳጩ” አመልክቷል። ዶክተሮች ችግሩን ለማቃለል ምንም ዓይነት እርምጃ ባልወሰዱባቸው ክሊኒኮች ውስጥ “አዘውትረው ሕክምና ይከታተሉ የነበሩ ሕሙማን ቁጥር በአንድ ዓመት ውስጥ 19 በመቶ እንዳሽቆለቆለ” ዘገባው ገልጿል። ታካሚዎች በሚበዙባቸው ክሊኒኮች ውስጥ በዶክተሮቹም ሆነ በረዳቶቻቸው ላይ የሚታየው ውጥረት በሌሎች ቢሮዎች ከሚታየው ውጥረት በጣም የከፋ ከመሆኑም በላይ የሥራ ቅልጥፍናቸው በአንድ ሦስተኛ ዝቅ ያለ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ረዳቶቻቸው የሚሠሩት ስህተት ሁለት እጥፍ ሆኖ ተገኝቷል።
ትክክልና ስህተት የሆነው ነገር የተማታባቸው ሰዎች
“ከአራት አውስትራሊያውያን መካከል አንዱ ማለት ይቻላል፣ ከሥራ ቦታው የጽሑፍ መሣሪያዎችን እንደሚሰርቅ አምኗል” ሲል የሲድኒው ዘ ሰን-ሄራልድ ዘግቧል። ከ2,000 በሚበልጡ የቢሮ ሠራተኞች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ከሚፈጽሟቸው የተለመዱ ድርጊቶች መካከል የሥራ ባልደረቦቻቸውን የግል መረጃዎች መመልከት፣ በሥራ ሰዓት ለግል ጉዳዮቻቸው በኢንተርኔት አገልግሎት መጠቀም፣ ፈቃድ ያላገኙባቸውን ሶፍትዌሮች የቢሮ ኮምፒውተሮቻቸው ውስጥ ማስገባትና የቢሮ ሶፍትዌሮችን ወደ ቤት ወስዶ መጠቀም ይገኙበታል። ጥናቱን በበላይነት የመሩት ጋሪ ዱሊ “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተው የማያውቁ በርካታ ሰዎች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከቤት እንስሳት ቀብር የሚገኝ ገቢ መቀረጥ አለበት?
በጃፓን የሚገኝ አንድ የቡድሂስት ቤተ መቅደስ ለሞቱ የቤት እንስሳት የቀብር ሥነ ሥርዓት በማከናወን፣ አስከሬናቸውን በማቃጠልና አመዱን በማስቀመጥ የሚያገኘው ገቢ ከቀረጥ ነፃ መሆን አለበት ሲል በቀረጥ ሰብሳቢ ባለ ሥልጣናት ላይ በቅርቡ ክስ መመሥረቱን አሳሂ ሺምቡን የተባለው የጃፓን ጋዜጣ ዘግቧል። ቀረጥ ሰብሳቢ ቢሮው ደግሞ የቤት እንስሳትን አስከሬን ማቃጠልም ሆነ ለእነርሱ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ማካሄድ “ውል በመዋዋል ከሚካሄድ ንግድ” ተለይቶ እንደማይታይና ቤተ መቅደሱ አመዱን የሚያስቀምጥ መሆኑ ደግሞ “የመጋዘን አገልግሎት” እንደሚሰጥ ያሳያል ሲል ተከራክሯል። በአንጻሩ ቤተ መቅደሱ “የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሐዘን የደረሰባቸው የቤት እንስሳት ባለቤቶች ሐዘናቸውን እንዲቋቋሙና የእንስሳቱ ነፍስ እንዲጽናና ለማስቻል የሚደረግ ሃይማኖታዊ ድርጊት” እንጂ ዓላማው ትርፍ ማግኘት እንዳልሆነ ገልጿል።
የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ቀነሰ
በ2003 በዓለም ዙሪያ የደረሰው የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ብዛት ችግሩ ተመዝግቦ መያዝ ከጀመረበት ከ1950ዎቹ ወዲህ ከደረሡት እጅግ ዝቅተኛው መሆኑን ፍላይት ኢንተርናሽናል የተባለው መጽሔት ዘግቧል። በ2003 በአውሮፕላን አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 702 ሲሆን ይህም የአውሮፕላን በረራ 40 በመቶ ከጨመረበት ከ1990 ወዲህ ከተመዘገበው ሁሉ ዝቅተኛው ቁጥር ነው። “በዚህ ረገድ መሻሻል ሊታይ የቻለው የበረራ መሣሪያዎች በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ የተነሳ አውሮፕላኑ ጉብ ካለ ቦታ ጋር ይላተም የነበረበት አጋጣሚ በመቀነሱ ነው። በዚህ ረገድ የመሬቱን ቅርበት የሚጠቁሙ አዳዲስ መሣሪያዎች ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል፤ ይሁንና ቴክኖሎጂው ‘እንከን የለሽ ነው’ ሊባል አይችልም” ሲል የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። አብዛኞቹ የቆዩ አውሮፕላኖች እንዲህ ዓይነት መሣሪያ የላቸውም።