በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢንተርኔት ከሚያስከትላቸው አደጋዎች መራቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

ኢንተርኔት ከሚያስከትላቸው አደጋዎች መራቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ኢንተርኔት ከሚያስከትላቸው አደጋዎች መራቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

ሕንድ ውስጥ በሚገኝ ራቅ ያለ መንደር የሚኖር አንድ ገበሬ ምርቱን ለመሸጥ ጥሩ የሚሆንበትን ጊዜ ለመወሰን እንዲረዳው በዩናይትድ ስቴትስ፣ ቺካጎ ውስጥ የአኩሪ አተር ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ በማጣራት ላይ ነው። በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ ጡረታ የወጡ አንዲት አዛውንት ከልጅ ልጃቸው የተላከላቸውን ኢሜይል ፈገግ ብለው በማንበብ ላይ ናቸው፤ አንድ ተጓዥ በሚሄድበት አገር የሚኖረውን የአየር ትንበያ እያነበበ ነው፤ አንዲት እናት ልጅዋ ከትምህርት ቤት የተሰጠውን የቤት ሥራ ለመሥራት የሚረዱትን ጠቃሚ መረጃዎች እያሰባሰበች ነው፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ጉዳያቸውን እየፈጸሙ ያሉት በኢንተርኔት ነው። በዓለም ዙሪያ ወደ 600 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ግንኙነት ያደርጋሉ፤ ይህ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው በኢንተርኔት የመጠቀም ባሕል፣ የዓለምን የግንኙነት ዘዴና የንግድ ልውውጥ ሂደት ቀይሮታል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ በኢንተርኔት በመጠቀም ረገድ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል። በይበልጥ ደግሞ ተማሪዎች ዜና ለማንበብና ምርምር ለማድረግ እንደ ቤተ መጻሕፍት ይጠቀሙበታል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ የኮሌጅ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች ላይ የተደረገውን ጥናት በበላይነት የመሩት ዲያና ቲልኢሽ “በአጭር አነጋገር እነዚህ ተማሪዎች . . . ጥናታቸውን ሁሉ የሚያካሂዱት በኢንተርኔት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አዎን፣ ኢንተርኔት በዘመናችን ላለው ኅብረተሰብ እጅግ ጠቃሚ መሣሪያ ነው።

በጥቅሉ ሲታይ ግን አንድ መሣሪያ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል አደገኛም ሊሆን ይችላል። የኤሌክትሪክ መጋዝ ከእጅ መጋዝ ይልቅ በፍጥነት ሥራን ለማከናወን ይረዳል፤ አጠቃቀሙ ላይ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በተመሳሳይም ኢንተርኔት ብዙ ነገር ማከናወን የሚያስችል ጠቃሚ መሣሪያ ቢሆንም ከባድ አደጋዎችንም ሊያስከትል ስለሚችል በአጠቃቀማችን ረገድ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። ጉዳዩ ያሳሰባቸው 40 የሚያህሉ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል አገራት ኅብረተሰቡን በኢንተርኔት አማካኝነት ከሚፈጸመው ዓመጽ ለመጠበቅ የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ ስምምነት ለማርቀቅ ተገደዋል።

ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? በተለይ ክርስቲያኖችን የሚያሳስቡት ምን ዓይነት አደጋዎች ናቸው? ችግሮቹ ጨርሶ በኢንተርኔት እንዳትጠቀም ሊያደርጉህ ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን መመሪያ ይሰጣል?

ለምን መጠንቀቅ አስፈለገ?

መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ስለ ‘ተንኮለኞች’ እና ‘ክፋትን ስለሚያውጠነጥኑ’ ክፉ ሰዎች አስጠንቅቋል። (ምሳሌ 24:8) ነቢዩ ኤርምያስ “ቤታቸው በማጭበርበር የተሞላ” “ክፉ ሰዎች” እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል። ልክ እንደ ወፍ አጥማጆች “ወጥመድ ዘርግተው ሰው” በመያዝ “ባለጠጎችና ኀያላን ሆነዋል።” (ኤርምያስ 5:26, 27) ሥልጣኔ ለዘመናችን “ክፉ ሰዎች” ለየት ያለ አዲስ ማጥመጃ መሣሪያ አቅርቦላቸዋል። እስቲ ለክርስቲያኖች እጅግ አደገኛ ሊሆኑ የሚችሉ ወጥመዶችን እንመልከት።

ኢንተርኔት ፖርኖግራፊ፣ ማለትም የወሲብ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን አሊያም ፊልሞችን በኢንተርኔት አማካኝነት ማሰራጨት በዓመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚዛቅበት ንግድ ሆኗል። ባለፉት አምስት ዓመታት የፖርኖግራፊ ድረ ገጾች 1,800 በመቶ ገደማ መጨመራቸውን መስማቱ በጣም ያስደነግጣል። በአሁኑ ጊዜ ከ260 ሚሊዮን በላይ የዚህ ዓይነት ድረ ገጾች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ቁጥሩም ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። በኢንተርኔት ሱስ የተለከፉ ሰዎች መርጃ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ኪምበርሊ ኤስ ያንግ እንዲህ ብለዋል:- “ፖርኖግራፊ በኢንተርኔት አማካኝነት በስፋት ስለሚሰራጭ ሳንፈልግም እንኳ ለዚህ የመጋለጥ እድላችን እጅግ የሰፋ ነው። ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት የሚተላለፍ ወሲባዊ ድርጊት የማየት ሱስ እንዲጠናወታቸው አድርጓል።”

መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው” ይላል። (ያዕቆብ 1:14) ፖርኖግራፊ የሚያሰራጩ ሰዎች ማንኛውንም የኮምፒውተር ተጠቃሚ የማጥመድ ዓላማ ስላላቸው ‘የራሳቸውን’ የተጠቃሚዎቹን “ክፉ ምኞት” ማለትም ‘የሥጋ ምኞታቸውንና የዐይን አምሮታቸውን’ ለመቀስቀስ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። (1 ዮሐንስ 2:16) ዓላማቸውም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ሳያውቁት በዘዴ ‘ማባበል’ ነው።—ምሳሌ 1:10

ፖርኖግራፊ የሚያሰራጩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንደነበሩት ክፉዎች ሁሉ ብዙውን ጊዜ የማታለያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ በየቀኑ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ የፖርኖግራፊ ኢሜይል ይሰራጫል። ከዚህ በፊት ከማታውቀው ላኪ ብዙውን ጊዜ ምንም ጉዳት የሌለው የሚመስል ርዕስ ያለው መልእክት ይደርስሃል። ነገር ግን እንዲህ ያሉትን መልእክቶች መክፈትህ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ምስሎች ማቆም በማይቻልበት ሁኔታ እንዲዥጎደጎዱ በር ሊከፍት ይችላል። እንዲህ ያለው መልእክት እንዳይላክልህ ብትጠይቅ ጭራሽ ያለ ፍላጎትህ በጣም ብዙ የፖርኖግራፊ መልእክት ሊጎርፍብህ ይችላል።

ወፍ የሚያጠምድ ሰው ወደ ወጥመዱ በሚወስደው መንገድ ላይ ሆን ብሎ አለፍ አለፍ አድርጎ ጥራጥሬ ይበትናል። ምንም ያልጠረጠረችው ወፍ ደግሞ ወጥመዱ ተስፈንጥሮ እስከሚይዛት ድረስ እያንዳንዱን ጥሬ ተራ በተራ ትለቅማለች። በተመሳሳይም አንዳንዶች የማወቅ ጉጉታቸው የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ምስሎችን አልፎ አልፎ የማየት ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርጓል። ይህን በሚመለከቱበት ጊዜ ማንም አያየንም ብለው ይገምታሉ። በጣም ስሜት የሚቀሰቅስ ሆኖ ስለሚያገኙት አንዳንዶች በተደጋጋሚ መመልከት ይጀምራሉ። መጀመሪያ ላይ ሐፍረትና ፀፀት ቢሰማቸውም ቀስ በቀስ በአንድ ወቅት ይቀፋቸው የነበረውን ነገር እንደ ተራ ጉዳይ ይቆጥሩታል። በኢንተርኔት የሚተላለፈው ፖርኖግራፊ መጥፎ ምኞቶች ወደ ብልግና ድርጊቶች በፍጥነት እንዲያድጉ የሚያደርግ ማዳበሪያ ነው። (ያዕቆብ 1:15) በዚህ ሱስ ተጠምደው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የረዱት ዶክተር ቪክተር ክላይን የተባሉ የሥነ ልቦና ሐኪም እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ የሚያፈሩት “‘ምስጢራዊና አደገኛ የሆነ ባሕርይ’፣ ከሥነ ምግባር ውጪ በሆነ መንገድ ለብቻቸው የሚያረኩት ልቅ ወሲባዊ ፍላጎት ነው” ብለዋል።

ኢንተርኔት ቻት ሩም የሚያስከትለው መዘዝ

ኢንተርኔት ቻት ሩም (በኢንተርኔት መነጋገር) ጊዜ አባካኝ ከመሆኑም በላይ ከቤተሰብ ጋር ያቆራርጣል። አንድ ሰው በኢንተርኔት ግንኙነት ብዙ ጊዜዋን ስለምታጠፋ ባለቤቱ ምሬቱን ሲገልጽ “ከሥራ እንደተመለሰች ኮምፒውተሯን ታበራለች፤ ከዚያ በኋላ ለአምስት ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ሰዓታት አታጠፋውም። በዚህ ምክንያት ትዳራችን ሰላማዊ ሊሆን አልቻለም” በማለት ተናግሯል። አዎን፣ ኢንተርኔት በማየት የምታጠፋው ሰዓት ከትዳር ጓደኛህና ከቤተሰብህ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ ይሻማብሃል።

ከጋብቻ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አንጀላ ሲብሰን፣ ኢንተርኔት “ሌላ ግንኙነት የሚጀመርበት ዋና በር ነው። በዚህ መልኩ የሚፈጠረው ግንኙነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀደም ሲል የነበረው ግንኙነት እንዲበጠስ ያደርጋል” ብለዋል። በኢንተርኔት ውይይት የተጀመረው ቀላል ጓደኝነት በፍጥነት መልኩን ቀይሮ ወደ ሌላ ደረጃ ሊለወጥ ይችላል። ከንጹሕ ሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ግንኙነት የመመሥረት ዓላማ ይዘው ‘ለማሳሳት የታጠቁት’ እነዚህ ሰዎች የወደፊት የጥቃት ዒላማዎቻቸውን የሚያነሆልል “ልዝብ አንደበት” ይጠቀማሉ። (ምሳሌ 6:24፤ 7:10) የዚህ ጥቃት ዒላማ የሆነች በዩናይትድ ኪንግደም የምትኖረው የ26 ዓመቷ ኒኮላ እንዲህ ብላለች:- “ሁልጊዜ እንደሚወደኝ ይነግረኛል። ምን ያህል እንደሚደሰትብኝ በተደጋጋሚ ይገልጽልኝ ስለነበር እውነቱን መሰለኝና ተታለልኩ።” ሴክስ ኤንድ ዚ ኢንተርኔት:- ኤ ጋይድቡክ ፎር ክሊኒሽያንስ የተባለው መጽሐፍ አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር አል ኩፐር “እንደ ዋዛ በኢንተርኔት የተጀመረ ማሽኮርመም ምን ያህል አደገኛ እንደሆነና ብዙውን ጊዜም ትዳርን እንደሚያፈርስ ለሰዎች በመንገር ማስጠንቀቅ” አለብን በማለት ተናግረዋል።

በኢንተርኔት በመተዋወቅና በማባበል በጾታ ለሚያስነውሩ ክፉ ሰዎች በዋነኝነት የተጋለጡት ልጆች ናቸው። ሕፃናትን የሚያስነውሩ ሰዎች ‘ጠማማ አፋቸውን’ እና “ብልሹ ንግግር” የሚናገር ‘ከንፈራቸውን’ ተሞክሮ የሌላቸውን ሕፃናት ለማጥቃት ይጠቀሙበታል። (ምሳሌ 4:24፤ 7:7) በኢንተርኔት ላገኙት ልጅ የተለየ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም ፍቅርና ደግነት በማሳየት ልጁን አስደስተው ለመማረክ ጥረት ያደርጋሉ። የሚወደውን ሙዚቃና ማድረግ የሚያስደስተውን ነገር ጨምሮ ልጁ የሚፈልገውን ሁሉ የሚያውቁ መስለው ለመቅረብ ይሞክራሉ። ልጁ በቤት ውስጥ ያሉትን ጥቃቅን ችግሮች አጋንኖ እንዲመለከት በማድረግ ከወላጆቹ ለማለያየት ይጥራሉ። እንዲያውም ክፉ ምኞታቸውን ለማሳካት ዒላማቸው ላደረጉት ልጅ ትኬት በመላክ አገር አቋርጦ ወደ እነሱ እንዲኮበልል ሊያደርጉ ይችላሉ። መዘዙ አስፈሪ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከአደጋ ይጠብቁሃል

አንዳንድ ሰዎች ኢንተርኔት የሚያስከትለውን አደጋ ከገመገሙ በኋላ ጨርሶ አለመጠቀሙ የተሻለ ነው ብለው ደምድመዋል። ነገር ግን በኢንተርኔት ከሚሰራጩት ነገሮች ውስጥ አደገኛ የሆኑት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውንና ከባድ ችግር የገጠማቸው ብዙ ሰዎች እንዳልሆኑ ማስተዋል ይገባል።

ቅዱሳን ጽሑፎች ከአደጋ ‘እንድንጠበቅ’ የሚረዱንን መመሪያዎች የሚሰጡን መሆኑ ደስ ያሰኛል። መጽሐፍ ቅዱስ እውቀትን፣ ጥበብንና ማስተዋልን እንድናዳብር ያበረታታናል። እነዚህ ባሕርያት ‘ይጋርዱናል’ እንዲሁም ‘ከክፉዎች መንገድ ያድኑናል።’ (ምሳሌ 2:10-12) በጥንት ጊዜ ይኖር የነበረው የአምላክ አገልጋይ ኢዮብ “ታዲያ፣ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች?” ሲል ጠይቆ ነበር። መልሱ ምን ይሆን? “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው።”—ኢዮብ 28:20, 28

“እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት” ማለት ሲሆን አምላካዊ ባሕርያትን ለማፍራት መሠረታዊ የሆነ ነገር ነው። (ምሳሌ 1:7፤ 8:13፤ 9:10) አምላክን መውደድና ማክበር እንዲሁም ለኃይሉና ለሥልጣኑ ተገቢ አክብሮት ማዳበር እርሱ የሚጠላቸውን ነገሮች ከማድረግ እንድንቆጠብና እንድንጠላ ይረዳናል። ጥሩ የማሰብ ችሎታና አምላካዊ እውቀት ተዳምረው አእምሯችንን፣ ልባችንንና መንፈሳዊነታችንን የሚበክሉ አደገኛ ነገሮችን እንድናስተውል ይረዱናል። በተጨማሪም ቤተሰባችንን የሚያፈርስና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ የራስ ወዳድነትና የስስት አስተሳሰብን ወደ መጥላት እንደርሳለን።

ስለዚህ በኢንተርኔት የምትጠቀም ከሆነ አደገኛ ገጽታዎችም እንዳሉት አስታውስ። የአምላክን ትእዛዛት ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ፤ እንዲሁም ችግር ላይ የሚጥልህን ነገር አልፎ አልፎ እንኳ ከማድረግ ተቆጠብ። (1 ዜና መዋዕል 28:7) ኢንተርኔት በምትጠቀምበት ጊዜ መጥፎ ነገር ካጋጠመህ መሸሹ የጥበብ እርምጃ ነው።—1 ቆሮንቶስ 6:18

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከፖርኖግራፊ ፈጽሞ ራቅ!

“ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኵሰት ወይም የስስት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና።”—ኤፌሶን 5:3

“ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም:- ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና . . . መጎምጀት ናቸው።”—ቆላስይስ 3:5

“የእግዚአብሔር ፈቃድ . . . እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤ ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን።”—1 ተሰሎንቄ 4:3-5

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ኢንተርኔት ቻት ሩም ከሚያስከትለው አደጋ ተጠንቀቅ!

በኢንተርኔት የሚፈጸም ወንጀል መርማሪ የሆኑ ሴት ፖሊስ፣ ኢንተርኔት ቻት ሩም (ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት እርስ በርስ ማውራት የሚችሉበት ፕሮግራም ነው) ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለማሳየት አንድ የንቁ! ዘጋቢ ጋበዙ። ከዚያም ቻት ሩም ውስጥ በመግባት የ14 ዓመት ልጃገረድ መስለው በመቅረብ ከሌሎች ሰዎች ጋር መነጋገር ጀመሩ። ከጥቂት ሴኮንዶች በኋላ በርካታ ግለሰቦች መልስ መላክ ጀመሩ። መልእክቱን የሚልኩት ግለሰቦች “የት ነው ያለሽው?”፣ “ለመሆኑ ሴት ነሽ ወይስ ወንድ?” እና “መነጋገር እንችላለን?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ያቀርቡ ነበር። በርካታ መልሶች የመጡት የፆታ ጥቃት ይፈጽማሉ ተብለው ከሚጠረጠሩ ፖሊስ ከሚከታተላቸው ወንጀለኞች ነበር። ይህም፣ ልጅህ በኢንተርኔት አማካኝነት ሕፃናትን ለሚያስነውሩ ወንጀለኞች በቀላሉ ሊጋለጥ እንደሚችል ያሳያል!

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ኢንተርኔት ቻት ሩም ውስጥ ገብተው ከሌሎች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ የሚጻጻፉትን ነገር ሁሉም ሊያየው ስለሚችል ምንም ችግር አይገጥማቸውም ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም አንዴ ቻት ሩም ውስጥ ከገባህ አንድ ለአንድ ብቻ እንድትነጋገር ግብዣ ሊቀርብልህ ይችላል። ልጆችን ከአደጋ ለመጠበቅ የተቋቋመው የዩናይትድ ኪንግደም ኢንተርኔት ቡድን ይህ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ሲያስጠነቅቅ “ይህ ማለት ብዙ ሰዎች ካሉበት የግብዣ ቦታ ወጥቶ ከማያውቁት ሰው ጋር ለብቻ አንድ ክፍል ውስጥ በመሆን ከማውራት ጋር ሊመሳሰል ይችላል” ብሏል።

ወላጆች፣ ሕፃናትን የሚያስነውሩ ሰዎች ከልጆች ጋር በማውራት ብቻ እንደማያበቁ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በኢንተርኔት የሚፈጸም ወንጀልን በተመለከተ በተደረገ ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ “በቻት ሩም የተጀመረው ግንኙነት እንደ ኢሜይልና (ሞባይል) ስልክ በመሳሰሉት ሌሎች መገናኛ ዘዴዎችም ሊቀጥልና ሊያድግ ይችላል” በማለት ዘግቧል። የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የምርመራ ቢሮ ዘገባ ደግሞ እንደሚከተለው ይላል:- “በኢንተርኔት አማካኝነት ተጠቂውን ሕፃን ማናገር የፆታ ወንጀል የሚፈጽመውን ሰው ያስደስተዋል፤ ሆኖም ሁኔታው በጣም ምቹ ላይሆንለት ይችላል። ብዙዎቹ ከልጆቹ ጋር በስልክ ቢነጋገሩ ይመርጣሉ። ወንጀለኞቹ ብዙውን ጊዜ በስልክ ወሲባዊ ግንኙነት ከመሠረቱ በኋላ በቀጥታ የፆታ ብልግና ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ሁኔታ ያመቻቻሉ።”

በኮምፒውተር አማካኝነት በፆታ የሚያስነውሩ ሰዎች ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት ስልክ ቁጥራቸውን ለልጆቹ ይሰጧቸዋል። ልጅህ በተሰጠው ቁጥር ከደወለ ወንጀለኛው ባለው ልዩ መሣሪያ አማካኝነት የተደወለለትን ቁጥር ማየትና መያዝ ይችላል። ሌሎች ወንጀለኞች ደግሞ ልጆቹ ቢደውሉላቸውም የማይከፍሉበት ወይም ደግሞ ልጆቹ ለደወሉት ወንጀለኞቹ ራሳቸው የሚከፍሉበት ስልክ ቁጥር ይሰጧቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ወንጀለኞች ለልጆቹ ተንቀሳቃሽ ስልክ እስከመላክ ደርሰዋል። ምናልባትም ደብዳቤዎች፣ ፎቶግራፎችና ስጦታዎች ሊልኩ ይችላሉ።

ለዚህ አደጋ የተጋለጡት ልጆች ብቻ አይደሉም። በቅርብ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ አንድ ሰው፣ በሚማርክና በሚያሽኮረምም አነጋገር በተመሳሳይ ጊዜ ስድስት ሴቶች እንዲያፈቅሩት አድርጎ ነበር። ከእነዚህም መካከል የምታምረው የ27 ዓመቷ የድህረ ምረቃ ተማሪ ሼረል እንዲህ ብላለች:- “አሁን እንዴት ብዬ እንደምገልጸው አላውቅም። ከእርሱ ጋር የነበረኝ የኢንተርኔት ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ መላ ሕይወቴን ተቆጣጥሮት ነበር።”

“ሴቶች ማንም መልካቸውን አይቶ አስተያየት ስለማይሰጥና በመልካቸው ምክንያት እንዳይሸማቀቁ ስለሚያደርግ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረገው ግንኙነት ያስደስታቸዋል። ነገር ግን ከልክ በላይ ግልጽ በመሆን ራሳቸውን ለችግር ያጋልጣሉ፤ እንዲህ የምንልበት ምክንያት በተለይ ቻት ሩም ውስጥ ገብተን ከሌሎች ጋር በምንነጋገርበት ወቅት ቶሎ ብለን ስለራሳችን የመግለጹ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ስለሆነ ነው” በማለት የሴቶች ኢንተርኔት ግንኙነት መሥራቿ ጄኒ ማድን ተናግረዋል።

በቤያትሪስ አቢላ ማይልሃም ይመራ ከነበረው የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ካዘጋጀው ጥናት ጥያቄ የቀረበለት አንድ ሰው “ማድረግ ያለብኝ ነገር ቢኖር ኮምፒውተሬን ማብራትና በሺዎች ከሚቆጠሩ ሴቶች መሃል መምረጥ ነው” ብሏል። ጥናቱን የመሩት ሴት “ከጥቂት ጊዜ በኋላ በትዳር ላይ ለሚፈጸም ውስልትና ዋናው መንስኤ ኢንተርኔት ይሆናል፤ እስከ አሁንም ካልሆነ ማለቴ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሴክስ ኤንድ ዚ ኢንተርኔት:- ኤ ጋይድቡክ ፎር ክሊኒሽያንስ የተባለውን መጽሐፍ ያዘጋጁት ዶክተር አል ኩፐር “በአገሪቱ ውስጥ ካሉት የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚደርሰን ዘገባ ከሆነ በትዳር ውስጥ ለሚነሱት ችግሮች ዋነኛው መንስኤ በኢንተርኔት የሚፈጸም ማሽኮርመም ነው” በማለት ተናግረዋል።

እነዚህን እውነታዎች በማጤን በኢንተርኔት አጠቃቀማችን ረገድ አስተዋይነት የሞላበት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ከልጆቻችሁ ጋር ተነጋገሩ፤ እንዲሁም ራሳቸውን ከአደጋ ሊጠብቁ የሚችሉበትን መንገድ አስተምሯቸው። ትክክለኛውን እውቀት በመታጠቅ ኢንተርኔት በመጠቀም ከሚመጣው አደጋ ማምለጥ ትችላለህ።—መክብብ 7:12