በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምቢ ቢለኝስ?

እምቢ ቢለኝስ?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

እምቢ ቢለኝስ?

መጀመሪያ ላይ እንደ ወንድምሽ ነበር የምታዪው። ሆኖም በመልካም ባሕርይው ወይም ደግሞ ስትነጋገሩ በሚያሳይሽ ጥሩ ፈገግታ ቀስ በቀስ ተማርከሽ አፈቀርሽው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንደሚወድሽ ሳይገልጽልሽ ረጅም ጊዜ አለፈ። ስለዚህ ግንኙነታችሁ ከተራ ጓደኝነት አልፎ ከአንቺ ጋር መጠናናት ይፈልግ እንደሆነ ራስሽ ልትጠይቂው ወሰንሽ። በደግነት ሆኖም በግልጽ ሐሳቡ እንደሌለው ሲነግርሽ መልሱ ፈጽሞ ያልጠበቅሽው ሆነ። *

በነገሩ እንደምትጎጂ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም ከልክ በላይ ከመበሳጨት ይልቅ ለተፈጠረው ነገር ተገቢ አመለካከት ይኑርሽ። እርሱ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖራችሁ እንደማይፈልግ መግለጹ ማንነትሽን እንደማይቀይረውና ሌሎች ለአንቺ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንደማይቀንሰው አስታውሺ። ምናልባትም እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ስለ አንቺ ካለው አመለካከት ተነስቶ ሳይሆን የራሱ ግብና ከማግባቱ በፊት ሊያከናውነው ያቀደው ነገር ስላለው ሊሆን ይችላል።

ክርስቲያን ከሆንሽ “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም” የሚሉትን ቃላት ታስታውሺ ይሆናል። (ዕብራውያን 6:10) ሶንያ * እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “አልረባም የሚል ስሜት ሊያድርባችሁ አይገባም። ነጠላም ብትሆኑ በይሖዋ ዘንድ ተፈላጊ ናችሁ።” ሉዓላዊ የሆነው አምላክና ሌሎች ሰዎች ለአንቺ ከፍ ያለ ግምት ስላላቸው ለምን ራስሽን ዝቅ አድርገሽ ታያለሽ?

ያም ሆኖ ምንም ነገር እንደማይሳካልሽ ወይም ጥሩ የትዳር ጓደኛ ልትሆኚ እንደማትችዪ ይሰማሽ ይሆናል። ነገር ግን ለእርሱ ‘ማራኪ’ ስላልሆንሽ የሌላ ወንድ ‘ልብ መማረክ’ አትችዪም ማለት አይደለም። (መሳፍንት 14:3) ስለዚህ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ያደረግሽው ጥረት መና እንደቀረ ከማሰብ ይልቅ አንድ ጥሩ ትምህርት እንዳገኘሽ ይኸውም ይህ ወጣት ጥሩ ባል ሊሆንልሽ እንደማይችል እንዳስገነዘበሽ አስታውሺ። ለምን እንዲህ እንላለን?

እርሱ አቻሽ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች “ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ” እንደሚገባቸው ይናገራል። (ኤፌሶን 5:28) እንዲሁም ባሎች ሚስቶቻቸውን ‘እንዲያከብሩ’ ያዛል። (1 ጴጥሮስ 3:7) እስቲ ሁኔታውን በጥሞና እንመልከት:- ይህ ወጣት ጓደኝነትሽን በጣም ይወደው ይሆናል። ነገር ግን ከአንቺ ጋር የፍቅር ግንኙነት መመሥረት እንደማይፈልግ ሲነግርሽ በሌላ አባባል እንደ ሚስቱ ቆጥሮ ተገቢውን ፍቅርና አክብሮት ለማሳየት ገና ዝግጁ አለመሆኑን እየገለጸልሽ ነው። ደግሞም እምቢ የማለት መብት አለው። እስቲ አስቢው፣ እንዲህ የሚሰማው ከሆነ በእርግጥ ጥሩ ባል ሊሆንሽ ይችላል? ቅዱሳን ጽሑፎች በሚያዙት መሠረት የማይወድሽንና የማይንከባከብሽን ባል ብታገቢ ምን ያህል ደስታ እንደምታጪ ገምቺ!

በተጨማሪም ይህ ወጣት ያሳይ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለሽ ማሰብሽ ግንኙነታችሁ ከጓደኝነት አልፎ አለመሄዱ ያስከተለብሽን ሐዘን ሊቀንስልሽ ይችል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የወረት ፍቅር ሌሎች በግልጽ የሚያዩት የግለሰቡ መጥፎ ጠባይ ወይም መንፈሳዊ ድክመት እንዳይታየን ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ለእርሱ ያለሽ ስሜት እየተለወጠ መምጣቱን አላወቀም ነበር? ወይስ ግንኙነታችሁ እንዲቀጥል በማድረግ ሆን ብሎ ለእርሱ ያለሽ የፍቅር ስሜት እንዲያድግ አድርጓል? አስቦ ያደረገው ነገር ከሆነ ይህ አሳቢና አዛኝ ክርስቲያን ባል ለመሆን ብቁ እንዳልሆነ አያሳይም? ስለዚህ ምንም ያህል የሚያቆስል ቢሆን እውነቱን ማወቅ መቻልሽ ጠቃሚ ነው።

ማርስያ አንድ ወጣት ለየት ያለ ትኩረት እንዳደረገባት ስታይ ለእርሱ የፍቅር ስሜት አድሮባት ነበር። ሆኖም ዓላማው ምን እንደሆነ ስትጠይቀው ከእርሷ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ እንደሌለው ነገራት። የደረሰባትን ሐዘን እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው? “እንዲሁ በስሜት ከመመራት ይልቅ በማስተዋል ማሰብ መጀመሬ በነገሩ እንዳልጎዳ ረድቶኛል” ትላለች። መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎች ያወጣውን መሥፈርት በማስታወሷ ለትዳር ጓደኝነት እንደማይበቃ ለማስተዋል ቻለች። ይህም ሐዘኗን እንድታሸንፍ ረድቷታል።

አንድሪያም ከአንድ ወጣት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። ከጊዜ በኋላ እርሷ ላይ ያደርግ የነበረው ነገር ብስለት እንደሚጎድለው የሚያሳይ መሆኑን ተገነዘበች። ለጋብቻ ዝግጁ እንዳልነበረ ማስተዋል እንድትችል ይሖዋ ዓይኖቿን ስለከፈተላት በጣም አመስጋኝ ነች። እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋ የስሜት ጉዳት ሊያስከትሉባችሁ ከሚችሉ ሁኔታዎች እንደሚጠብቃችሁ እርግጠኛ ነኝ፤ ይሁንና በእርሱ ልትታመኑ ይገባል።” እርግጥ ነው፣ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚያጋጥመው አንድ ወጣት የሚያስከብር ባሕርይ ሊኖረውና ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረውም በጥሩ ዓላማ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ የደረሰብሽን ሐዘን መቋቋም የምትችዪው እንዴት ነው?

ሐዘንሽን መቋቋም የምትችዪው እንዴት ነው?

እርሱ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖራችሁ አለመፈለጉን አምነሽ ለመቀበል ጊዜ ይወስድብሽ ይሆናል። ለእርሱ ያለሽ ፍቅር እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ቀስ በቀስ እንደሆነ ሁሉ ይህን ስሜትሽንም ለማስወገድ ጊዜ ያስፈልግሻል። ብዙውን ጊዜ የፍቅር ስሜት ልክ እንደ መብራት በቀላሉ ልታጠፊው የምትችዪው ነገር አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ልትሸከሚው ከምትችዪው በላይ የበረታብሽ ይመስልሻል! ቶሎ ብለሽ ተስፋ አትቁረጪ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይህ ስሜት ቀስ በቀስ ይከስማል። ይሁንና ይህ ስሜት በቶሎ እንዲወገድልሽ የምትፈልጊ ከሆነ ስሜቱን የሚቀሰቅሱብሽን ነገሮች ማስወገድ ያስፈልግሻል።

ለምሳሌ ሐሳብሽን ስትገልጭለት የተናገርሻቸውን ቃላትና አኳኋንሽን አንድ በአንድ መልሰሽ በማሰብ ራስሽን ከመኰነን ተቆጠቢ። እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ካላስወገድሽ ‘እምቢ ማለቱ እኮ አይደለም’ ወይም ደግሞ ‘በሌላ መንገድ ልነግረው ብሞክር እሺ ይለኝ ይሆናል’ ብለሽ ማሰብ ትጀምሪያለሽ። ስሜቱን ልትቀይሪ እንደማትችዪ ሃቁን አምነሽ ተቀበዪ። በምንም ዓይነት መንገድ ሐሳብሽን ብትነግሪው ተመሳሳይ መልስ የመስጠቱ አጋጣሚ ሰፊ ነው።

የቀን ቅዠት ደግሞ ሌላው ወጥመድ ነው። አብራችሁ በደስታ ስትኖሩ በዓይነ ሕሊናሽ ይታይሽ ይሆናል። ሐሳቡ የሚያስደስት ቢሆንም በእውን የተፈጸመ ነገር አይደለም። ከሐሳብሽ ስትባንኚ ያጣሽው ነገር እንደገና ትዝ እያለሽ ትሰቃያለሽ። ብርቱ ጥረት አድርገሽ ካላቆምሽው በስተቀር እንዲህ ያለው የቅዠት ደስታን ተከትሎ የሚመጣ ስቃይ ለረጅም ጊዜ መደጋገሙ አይቀርም።

እንዲህ ያለውን የቀን ቅዠት ከአእምሮሽ ለማስወገድ ጥረት አድርጊ። በሐሳብ መዋጥ ስትጀምሪ ወዲያው ተነስተሽ በእግርሽ ተጓዢ። ሌላ ነገር እንድታስቢ የሚያደርግሽ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ አንድ ሥራ ጀምሪ። በሚያንጹሽ ነገሮች ላይ እንጂ ቅስምሽን በሚሰብሩ ነገሮች ላይ ትኩረት አታድርጊ። (ፊልጵስዩስ 4:8) መጀመሪያ ላይ እንዲህ ማድረግ ሊከብድሽ ይችላል፤ በኋላ ግን በትግሉ ልታሸንፊና የአእምሮ ሰላም ልታገኚ ትችያለሽ።

ከቅርብ ወዳጆችሽ የምታገኚው ማበረታቻም ሊረዳሽ ይችላል። (ምሳሌ 17:17) ሆኖም ሶንያ እንደሚከተለው በማለት ታስጠነቅቃለች:- “ጓደኞችሽ በሙሉ ነጠላ፣ እኩዮችሽና የማግባት ጉጉት ያላቸው ከሆኑ ያን ያህል እርዳታ ልታገኚ አትችዪም። ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርሽ ሊረዱሽ የሚችሉ በዕድሜ የበሰሉ ወዳጆችም ያስፈልጉሻል።” በተጨማሪም ችግርሽን መወጣት ትችዪ ዘንድ ከማንም በተሻለ እርዳታ ሊሰጥሽ የሚችል አካል እንዳለ አትዘንጊ።

ይሖዋ ወዳጅና ደጋፊ ነው

በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ሐዘን በገጠመው ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮ ነበር። ውጤቱ ምን ነበር? “አሳብና ጭንቀት በያዘኝ ጊዜ፤ አንተ ታጽናናኛለህ፤ ደስም ታሰኘኛለህ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 94:19 የ1980 ትርጉም) በእምነት ወደ ይሖዋ የምትጸልዪ ከሆነ ለአንቺም ማበረታቻና ማጽናኛ ይሰጥሻል። አንድሪያ ይሖዋ እንዲረዳት ጸልያለች። “ያለፈውን ለመርሳትና በሌሎች ነገሮች ላይ ለማተኮር ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው” ብላለች። ሶንያም ስለ ጸሎት እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ጸሎት ሌሎች ወደዷችሁም አልወደዷችሁ ለራሳችሁ ጥሩ ግምት እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል።”

ስሜትሽን ሙሉ ለሙሉ ሊረዳልሽ የሚችል ሰው የለም፤ ይሖዋ ግን የውስጥሽን ሐሳብ ጠንቅቆ ያውቃል። ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው በትዳር ውስጥ ፍቅር የመስጠትም ሆነ የመቀበል ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያለው የስሜት መሳሳብ ምን ያህል ኃይል እንዳለው እና ይህን ስሜት እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ያውቃል። አንደኛ ዮሐንስ 3:20 “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል” ስለሚል ይሖዋ ከደረሰብሽ የልብ ሐዘን መገላገል እንድትችዪ ይረዳሻል።

ሚዛንሽን ጠብቂ

ጋብቻ ደስታ ሊያስገኝ ቢችልም ብቸኛው የደስታ ምንጭ ግን አይደለም። ደስተኞች የሚሆኑት ይሖዋን የሚያገለግሉ ሁሉ እንጂ ባለትዳሮች ብቻ አይደሉም። በአንዳንድ መስኮች ነጠላነት ባለ ትዳሮች ሊያገኟቸው የማይችሏቸው ጥቅሞች አሉት። ያላገቡ ሰዎች በ1 ቆሮንቶስ 7:28 ላይ የተገለጸው “ብዙ ችግር” አያጋጥማቸውም። እዚህ ላይ የተገለጸው ችግር ባለትዳሮች ሁሉ የሚያጋጥማቸውን ውጥረትና ጭንቀት ያመለክታል። እንዲሁም ያላገቡ ሰዎች ይበልጥ ነጻነት ያላቸው ሲሆን በመረጡት የይሖዋ አገልግሎት ለመካፈል ይበልጥ ይቀላቸዋል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ” በማለት ይመክረናል። (1 ቆሮንቶስ 7:38) ከፍተኛ የማግባት ጉጉት ቢኖርሽም እንኳን በእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰልሽ አሁን ባለሽበት ሁኔታ እንድትደሰቺና ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርሽ ሊረዳሽ ይችላል።

ምናልባት አንዳንድ ጓደኞችሽ በቅንነት “አትጨነቂ፤ አንድ ቀን ጥሩ ሰው ታገኛለሽ” ይሉሽ ይሆናል። ደግሞም ትክክል ናቸው፤ አሁን አንድ ሰው ስላልፈለገሽ ዕድሜ ልክሽን አታገቢም ማለት አይደለም። ካንደስ የተባለች ክርስቲያን እንዲህ ትላለች:- “በይሖዋ ባምንም እኔን ለማስደሰት ብሎ ባል እንዲሰጠኝ አልጠብቅበትም። ሆኖም በዚህ ምክንያት የሚሰማኝን የባዶነት ስሜት ለማሸነፍ የሚረዳኝን ነገር እንደሚሰጠኝ አውቃለሁ።” ይህን የመሰለ ቀና አስተሳሰብ በመያዟ አንድ ወንድ ከእርሷ ጋር ለመጋባት ጥናታዊ ቅርርብ ማድረግ እንደማይፈልግ በነገራት ጊዜ የተሰማትን ሐዘን ለመቋቋም ችላለች።

በዓለማችን ላይ፣ ጥናታዊ ቅርርብ ለመጀመር የሚደረጉ ብዙ ሙከራዎች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ትዳሮችም ሲፈርሱ ይታያል። በይሖዋ ከታመንሽና ምክሮቹን በሥራ ላይ ካዋልሽ ያጋጠመሽ ሐዘን ተወግዶ ደስተኛ እንድትሆኚ ሊረዳሽ ይችላል። ንጉሥ ዳዊት “ጌታ ሆይ፤ ምኞቴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነው፤ ጭንቀቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም። እግዚአብሔር ሆይ፤ በተስፋ እጠብቅሃለሁ፤ ጌታ አምላኬ ሆይ፤ አንተ መልስ ትሰጠኛለህ” ሲል የገለጸው ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥምሽ ይችላል።—መዝሙር 38:9, 15

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የኅዳር 2004 ንቁ! መጽሔት “የወጣቶች ጥያቄ . . . እንደማፈቅረው እንዴት ብዬ ልገልጽለት እችላለሁ?” በሚለው ርዕስ ሥር በአንዳንድ አገሮች አንዲት ሴት አንድን ወንድ እንደምታፈቅረው መንገሯ እንደነውር እንደሚቆጠር ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ ሴት ስሜቷን ቀድማ መግለጽ የለባትም ባይልም ክርስቲያኖች ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆኑ ይመክራል። ስለዚህ በዚህ ረገድ ምን ቢያደርጉ እንደሚሻል የሚያስቡ እህቶች የአምላክን በረከት ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ይገባቸዋል።—ማቴዎስ 18:6፤ ሮሜ 14:13፤ 1 ቆሮንቶስ 8:13

^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አምላክ ከሚሰጠው እርዳታ ተጠቀሚ