በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውብ እና ጣፋጭ!

ውብ እና ጣፋጭ!

ውብ እና ጣፋጭ!

አበቦች የተተከሉበትን ቦታ ስታይ የስሜት ሕዋሳትህን የሚያስደስት ነገር ታገኛለህ። ቀለማቸውን፣ ቅርፃቸውንና ውስብስብ ንድፋቸውን በመመልከት ትደሰታለህ። ግሩም መዓዛቸውን ታሸትታለህ። የአበባው ቅጠል (ፔታል) ላይ ያለውን የተለያየ ቅርጽ መዳሰስ ትችላለህ። ስለ መቅመስ ሕዋስህስ ምን ለማለት ይቻላል? አበቦችን በመብላት ልትደሰት ትችላለህ? በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ያሉ ሰዎች ለብዙ መቶ ዓመታት ለምግብነት የሚያገለግሉ አበቦችን በመብላት ሲደሰቱ ቆይተዋል። ከዚህ በታች ከተገለጹት አበቦች መካከል አንዱ በጓሮህ የሚገኝ ከሆነ አንተም ቀምሰኸው ልትደሰት ትችላለህ። *

የፍቅር መግለጫ የሆነው ጽጌረዳ አበባ

ጽጌረዳ (ጂነስ ሮዛ) በዓለም ዙሪያ በሰፊው የሚታወቅና በጣም የሚወደድ አበባ ነው ለማለት ይቻላል። ከተፈጥሯዊው ጽጌረዳ አበባ በተጨማሪ በሰው ሠራሽ ዘዴ የተዳቀሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዝርያዎች ይገኛሉ። የአበባው ጣዕም በአፈሩ ዓይነት፣ በአየሩ ሁኔታና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተነሳ ሊለወጥ ስለሚችል ጽጌረዳም ሆነ ሌላ አበባ ለምግብነት ከመጠቀምህ በፊት አበባውን መቅመሱ የተሻለ ነው። ምናልባት የአበባው የሥረኛው ክፍል መረር ይልህ ይሆናል። ከመረረህ ይህንን የአበባውን ክፍል ቆርጠህ አውጣው ወይም ሙሉውን አበባ ለምግብነት ካዘጋጀህ ውጪያዊውን ክፍል ብቻ ተመገብ።

በመሠረቱ ጽጌረዳ አበባ የሚገባባቸው የምግብ ዓይነቶች በርካታ ናቸው። በሰላጣ፣ ጣዕሙ ለስለስ ባለ አይብ ወይም በተፈጨ ኦቾሎኒ ውስጥ ጨምረህ ልትቀምሰው ትችላለህ። እንዲሁም በምትወደው የስጎ ዓይነት ውስጥ የተፈጨ ቀይ ጽጌረዳ በመጨመር ይበልጥ እንዲጣፍጥና መልኩ እንዲያምር ለማድረግ ትችላለህ። ወይም ለምን በጠስ በጠስ አድርገህ ባቀረብከው ፓስታ ላይ ጣል ጣል አታደርገውም? ጽጌረዳ አበባ የአይስ ክሬምንና የምትወደውን የአልኮል መጠጥ ጣዕም ይበልጥ ለማጣፈጥም ሊያገለግል ይችላል።

የዱባ አበባ

የዱባ አበባ (ኩኩርቢታ ፒፖ) ከ16ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በአሜሪካ ለምግብነት ያገለግል እንደነበር ዘገባዎች ያሳያሉ፤ የአሜሪካ ሕንዶች ሴቴዎቹ አበቦች (ከጀርባቸው ትንሽ ዱባ የሚያበቅሉት) እንዲራቡ በሚል ወንዴዎቹን አበቦች (ረዥምና ቀጭን አንጓ ያላቸውን) ብቻ ይመገቡ የነበረ ይመስላል። አበቦቹን ከማብሰልህ በፊት ዙሪያውን የሚገኙትን እሾሃማ ቅጠሎች አስወግድ። ሴቴውን የአበባ ክፍል ካልፈለግህ ልትጥለው ትችላለህ። ለስለስ ያለ ጣዕም ያለው የዱባ አበባ ከወይራ ዘይትና ከበቆሎ እሸት ጋር ተደባልቆ እንዲሁም ዱባ ራሱ ተደርጎበት በዋና ምግቦችና በሾርባ ውስጥ ተጨምሮ ሲሠራ በጣም ይጣፍጣል። የዱባው አበባ ጣዕሙ ትንሽ ጠንከር የሚል ከሆነ ደግሞ ከቀይ ሽንኩርት፣ ከነጭ ሽንኩርት፣ ከቅጠላ ቅጠልና ከምትፈልገው ቅመም ጋር አድርገህ በዘይት ወይም በሌላ ቅባት በትንሹ ጠበስ ጠበስ ልታደርገው ትችላለህ። እንዲሁም አይብ፣ ቀይ ሽንኩርትና ቅጠላ ቅጠል በአበባው ውስጥ ትጠቀጥቅና አፉን ትደፍነዋለህ። ከዚያም ነጩን የእንቁላል ክፍል ለብቻው በደንብ ከመታህ በኋላ አስኳሉን ትቀላቅልና የተጠቀጠቀውን የዱባ አበባ ትነክርበታለህ። በመጨረሻም የተፈጨ ዳቦ ውስጥ ከትተህ ታወጣውና በደንብ ጠብሰህ ተመገበው፤ ጣዕሙ ልዩ ነው!

ውቡ የጓሮ ፓንዚ

በአንዱ አበባ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ዓይነት ቀለም የሚኖረው የጓሮ ፓንዚ (ቪዮላ ዊትሮኪያና) በአብዛኛው በአበባው ላይ በሚገኙትና ለየት ያለ መልክ በሚሰጡት ጠቆር ያሉ ነጠብጣቦች ተለይቶ ይታወቃል። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው የጓሮ ፓንዚ ከጫካው ፓንዚ ወይም ከጆኒ ጃምፕ አፕ (ቪዮላ ትራይከለር)፣ ከወይን ጠጁ፣ ከነጩና ከቢጫው አበባ ጋር አንድ ዓይነት ዝርያ አለው ተብሎ ይታሰባል። ይህ የሜዳ አበባም ቢሆን ለምግብነት ያገለግላል፤ ነገር ግን ኤዲብል ፍላወርስ—ፍሮም ጋርደን ቱ ፓሌት የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ “ብዙ ከተበላ መርዝነት ሊኖረው ይችላል።” ይህ አበባ በቅጠላ ቅጠልና በፍራፍሬ ሰላጣ ውስጥ ጣል ከተደረገ ጣዕምና ውበት ይጨምርላቸዋል። ሁሉም የአበባው ክፍል መበላት ይችላል፤ ሰላጣው ውስጥ አቼቶ ካደረግህ በኋላ ከማቅረብህ በፊት ሙሉውን አበባ መጨመር ትችላለህ። በምትወደው ሾርባ ውስጥም ጨምረህ ማቅረብ ትችላለህ።

ከቪዮላ ዝርያዎች ውስጥ የሚበላው ሦስተኛ አበባ ደግሞ የጓሮ ቫዮሌት ወይም ኢንግሊሽ ቫዮሌት (ቪዮላ ኦዶራታ) ሲሆን በጣፋጭ ምግቦችና መጠጦች ውስጥ ቢጨመር ጣዕሙን ግሩም ያደርገዋል። (“መጠጦች ውስጥ የሚጨመሩ ጣፋጭ አበቦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሌሎቹ የቪዮላ አበባ ዝርያዎች እንደማይበሉ ተረጋግጧል።

አስደሳቹ ዴይሊሊ

ዴይሊሊ (ጂነስ ሄመሮካሊስ) በርዝመቱና በቅጥነቱ እንዲሁም ከታች በሚያወጣቸው እጅብ ባሉት ቅጠሎቹ ተለይቶ ይታወቃል። የዚህ ተክል አበባ አጭር ዕድሜ ያለው በመሆኑ ሌሎች ተመሳሳይ ዝርያ ካላቸው ሊሊያሲያ አበቦች ጋር እንዳይምታታብህ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ከቢጫ እስከ ቀይ ቀለም ያላቸው ዴይሊሊዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ለምግብነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይህን አበባ በመጠኑ ካበሰሉ በኋላ እንደ ማንኛውም አትክልት መመገብ ይቻላል። እንዲሁም አበባውን ከምትፈልገው ቅመም ጋር መጥበስ ትችላለህ። ከዚያም ዙሪያውን በአበባ አስጊጠው።

ሌሎች የሚበሉ አበቦች

በተለይ በበረሐማና በከፊል በረሐማ ቦታዎች ላይ የሚበቅለው የሬት ዛፍ አበባ (ጂነስ ዩካ) በቫይታሚንና በካልሲየም ይዘቱ የበለጸገ ነው። መበላት የሚችለው አበባው ብቻ ሲሆን ምሬቱን ለማስወገድ ትንሽ ገንፈል ማድረግ ይኖርብህ ይሆናል። የሎሚ አበባ (ሲትረስ ሊሞን)፣ የብርቱካን አበባ (ሲትረስ ሲኔንሲስ) እና የሜንታ አበባ (ጂነስ ሜንታ) መጠጥ ውስጥ፣ ሰላጣ ውስጥና ጣፋጭ ምግቦች ውስጥ ቢጨመሩ ይበልጥ ያጣፍጧቸዋል። *

አበቦች ለስሜት ሕዋሳታችን የተፈጠሩ ስጦታዎችና ሕይወትን እንድናጣጥም የሚያስፈልጉ ቅመሞች እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ማወቃችን በእውነትም አፍቃሪ የሆነውን ፈጣሪያችንን ለማመስገን የሚያስችል ተጨማሪ ምክንያት ይሆነናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የአበቦቹን ዓይነት በትክክል ለመለየት እንዲያስችል ሳይንሳዊ ስማቸው ጭምር ተጠቅሷል።

^ አን.14 የሚበሉት አበቦች እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ሆኖም ማንኛውንም አበባ ከመመገብ በፊት፣ የሚበሉ መሆን አለመሆናቸውን በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልጋል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጠጦች ውስጥ የሚጨመሩ ጣፋጭ አበቦች

በረዶ መሥሪያ ዕቃህ ውስጥ መጠኑ አነስተኛ የሆነ አንድ ሙሉ አበባ ወይም ቅጠሏን በጥሰህ አድርግና ውኃ ሙላበት። ከዚያም እንደተለመደው በረዶ እስኪሆን ድረስ አቀዝቅዘው። እነዚህን የበረዶ አንኳሮች በምትወደው መጠጥ ውስጥ ጨምረህ መጠጣት ትችላለህ።

[ምንጭ]

ከኤል ኩልቲቮ ዴ ዬርባስ (ኸርብ ካልቸር) የተወሰደ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአበባ ከረሜላ መሥራት

ነጩን የእንቁላል ክፍል ምታና የደረቀውን ንጹሕ አበባ በደቃቅ ብሩሽ በስሱ ቀባው። የአበባውን ቅጠሎች ሙሉ ለሙሉ መቀባትህን አረጋግጥ። ከዚያም ተጠንቅቀህ ደቃቅ ስኳር በወንፊት ነስንስበት። አበባው ላይ ያለው ስኳር ከበዛ አራግፈውና ሊደርቅ በሚችልበት ቦታ ላይ ለረጅም ሰዓት አቆየው።

[ምንጭ]

ከኩክስ ቲሶረስ የተወሰደ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አስፈላጊ ጥንቃቄዎች ማድረግ

አንዳንድ አበቦች መርዝነት ስላላቸው የሚበሉትን በጥንቃቄ ለይተህ ማወቅ ያስፈልግሃል። ከተጠራጠርክ አትብላቸው።

ፀረ ተባይ መድኃኒት ወይም ማንኛውም ኬሚካል የተረጨባቸውን አበቦች ፈጽሞ አትመገብ። (ብዙውን ጊዜ ከአበባ ሻጮች፣ ከአትክልት ቦታዎችና ከአንዳንድ የችግኝ መሸጫ ሱቆች የሚገዙ አበቦች እነዚህ ኬሚካሎች ይደረጉባቸዋል።) ምንም ኬሚካል ሳይደረግባቸው በተፈጥሮ የበቀሉና ከመንገዶች ራቅ ብለው የሚገኙ አበቦችን ብቻ ተመገብ።

አስምና ከአትክልቶች ጋር የተያያዘ አለርጂ ያለበት ሰው አበባ መመገብ የለበትም።

እንደ ፍራፍሬዎችና ቅጠላ ቅጠሎች ሁሉ በተለይ ጥሬያቸውን የሚበሉ አበቦች በሚገባ መታጠብ አለባቸው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጽጌረዳ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዱባ አበባ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓንዚ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዴይሊሊ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሎሚ አበባ