በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኛ የማይፈልግ የለም

ጓደኛ የማይፈልግ የለም

ጓደኛ የማይፈልግ የለም

“ጓደኛ፣ የልብህን አውጥተህ የምታጫውተውና በማንኛውም ሰዓት ደውለህ ልታናግረው የምትችለው ሰው ነው።”—ያኤል፣ ፈረንሳይ

“ጓደኛ ጭንቀትህን የሚረዳልህና አብሮህ የሚጨነቅ ነው።”—ጌል፣ ፈረንሳይ

“ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።” (ምሳሌ 18:24) ይህ አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈረ ወደ 3,000 ዓመት ገደማ ሆኖታል፤ ቢሆንም የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት አልተለወጠም። ሰው ለሰብዓዊ አካሉ እህልና ውኃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለስሜታዊ ፍላጎቱም ጓደኛ ያስፈልገዋል። ይሁንና ይህን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ቀላል አይደለም። ዛሬ ብዙዎች ብቸኝነት ይሰማቸዋል። ካሪን ሩበንስቲን እና ፊሊፕ ሻቨር ኢን ሰርች ኦቭ ኢንቲመሲ (የልብ ጓደኛ ፍለጋ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ለዚህ አንዳንዶቹ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ብዙ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም” ሲሉ ጽፈዋል። ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ “የሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ” ማለትም በተደጋጋሚ የመኖሪያ አካባቢ መቀየር፣ “የሰዎች ደንታ ቢስ መሆን፣ በከተሞች ውስጥ የወንጀል መበራከት” እና “የሰዎች እርስ በርስ የመጠያየቅ ባሕል ቤት ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥንና ቪዲዮ በማየት ልማድ መተካት” ናቸው።

በተጨማሪም ዘመናዊው የአኗኗር ዘይቤ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚያሟጥጥ ነው። ደራሲዋ ሌቲ ፖግረቢን አሞንግ ፍሬንድስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በዛሬው ጊዜ ያለ አንድ የከተማ ነዋሪ በአንድ ሳምንት ውስጥ የሚተዋወቃቸው ሰዎች ብዛት በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ የአንድ መንደር ነዋሪ በዓመት ምናልባትም በሕይወት ዘመኑ ሙሉ ከሚተዋወቃቸው ሰዎች ይበልጣል” ሲሉ ጽፈዋል። ከብዙ ሰዎች ጋር ስለምንተዋወቅና ስለምንገናኝ ከተወሰኑ ግለሰቦች ጋር በደንብ ለመተዋወቅና ጓደኝነት ለመመሥረት ልንቸገር እንችላለን።

ሌላው ቀርቶ ሰዎች ሩጫ ያልበዛበት ሕይወት ይመሩ በነበሩባቸው አካባቢዎች ያለው ማኅበራዊ ሕይወት እንኳ አሁን አሁን በጣም እየተለወጠ ነው። በምሥራቅ አውሮፓ የምትኖረው ኡላ “በፊት ከጓደኞቻችን ጋር የነበረን ቅርርብ በጣም የጠበቀ ነበር። አሁን ግን ብዙዎቹ በሥራቸው አሊያም በግል ጉዳያቸው ተጠምደዋል። ማንም ጊዜ የለውም። የቀድሞ ጓደኝነታችን ቀስ በቀስ እየከሰመ መሆኑን እያስተዋልን ነው” በማለት ትናገራለች። በዚህ ሩጫ በበዛበት ዘመን ጓደኝነት እምብዛም ቦታ ላይሰጠው ይችላል።

ያም ሆነ ይህ ጓደኛ የማግኘት ኃይለኛ ፍላጎት አለን። በተለይ ወጣቶች ጓደኛ ማግኘት በጣም ይፈልጋሉ። ከላይ የተጠቀሰችው ያኤል “በተለይ በወጣትነታችሁ የሚወዳችሁ ወይም የሚያቀርባችሁ ሰው እንዳለ ስታውቁ ደስ ይላችኋል” ስትል ተናግራለች። ወጣትም ሆንን አረጋዊ፣ ሁላችንም በጣም የሚቀርቡን ጥሩ ጓደኞች ማግኘት እንፈልጋለን። ይህ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም እውነተኛ ጓደኞችን ለማፍራትም ሆነ ጓደኝነታችን እንዲቀጥል ብዙ ማድረግ የምንችላቸው ነገሮች አሉ። የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።