በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኛ የማግኘት ፍላጎታችንን ማሟላት

ጓደኛ የማግኘት ፍላጎታችንን ማሟላት

ጓደኛ የማግኘት ፍላጎታችንን ማሟላት

ኢን ሰርች ኦቭ ኢንቲመሲ የተባለው መጽሐፍ “የብቸኝነት ስሜት በሽታ አይደለም። . . . ጓደኛ እንደሚያስፈልገን የሚጠቁም የተፈጥሮ ስሜት ነው” በማለት ይገልጻል። ሲርበን ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆነ ምግብ ለመብላት እንደምንገፋፋ ሁሉ ብቸኝነት ሲሰማንም ጥሩ ጓደኛ ለማግኘት መጣር ይኖርብናል።

በፈረንሳይ የምትኖረው ያኤል የተባለች ወጣት “አንዳንዶች ራሳቸውን ፈጽሞ ከሰው ያገላሉ” ስትል ገልጻለች። ሆኖም ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ራሳችንን ከሰው ማግለላችን ከምንጊዜውም ይበልጥ ብቸኝነት እንዲሰማን ከማድረግ ባሻገር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” ይላል። (ምሳሌ 18:1) ስለዚህ በቅድሚያ ጓደኛ እንደሚያስፈልገን መገንዘብና ከዚያም ይህን ፍላጎታችንን ለማሟላት አንድ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።

ጓደኛ ለማፍራት ተግባራዊ እርምጃ ውሰድ

ስለራስህ እያዘንክ ከመቀመጥ ወይም ጓደኛ በማፍራት ረገድ የተሳካላቸው በሚመስሉ ሰዎች ከመቅናት ይልቅ በጣሊያን የምትኖረው ማኑኤላ እንዳደረገችው ሁሉ ለምን አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ አንድ እርምጃ አትወስድም? ማኑኤላ “በተለይ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። ይህን ስሜት ለማሸነፍ ጥሩ ጓደኞች ያሏቸውን ሰዎች ሆነ ብዬ ተከታተልኩ። ከዚያም በሌሎች ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ለመሆን እነዚህ ሰዎች ያሏቸውን ጥሩ ጥሩ ባሕርያት ለማፍራት ጥረት አደረግሁ” በማለት ተናግራለች።

ልትወስደው የሚገባ አንዱ ተግባራዊ እርምጃ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጤንነትህን መጠበቅ ነው። የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቂ ዕረፍት መውሰድና ጥሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናማ እንድትሆን የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል። በንጽሕና ረገድ በሚገባ ራስህን የምትጠብቅ ከሆነ ሌሎች እንዲቀርቡህ የሚጋብዝ ከመሆኑም ባሻገር ለራስህ ያለህ አክብሮት በተወሰነ ደረጃ ይጨምራል። ሆኖም ስለ ውጫዊ መልክህና ቁመናህ ከልክ በላይ የመጨነቅ ዝንባሌ እንዳይጠናወትህ ተጠንቀቅ። በፈረንሳይ የምትኖረው ጌል “እውነተኛ ጓደኞችን ማፍራት የሚያስችለው ፋሽን የሆኑ ልብሶችን መልበስ አይደለም። ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች የሚማረኩት በአንድ ሰው ውስጣዊ ማንነት ነው” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

ደግሞም እኮ ውስጣዊ ስሜታችንና ሐሳባችን በምንናገረው ነገር ሌላው ቀርቶ በመልካችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። ስለ ሕይወት ብሩህ የሆነ አመለካከት አለህ? እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በፊትህ ላይ ደስታ እንዲነበብ ያደርጋል። ከልብ የመነጨ ፈገግታን ያክል የሚማርክ ነገር የለም። ስለ አካላዊ መግለጫ የሚያጠኑ ሮጀር አክስቴል የተባሉ ሰው “[ከልብ የመነጨ ፈገግታ] ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው” ደግሞም “አብዛኛው ሰው በቀላሉ ይረዳዋል” በማለት ይገልጻሉ። * በዚህ ላይ ተጫዋች ከሆንክ ሰዎች አንተን መቅረብ አይከብዳቸውም።

እነዚህ ግሩም ባሕርያት ከውስጥ የሚመነጩ መሆናቸውን ልብ በል። ስለዚህ አእምሮህንና ልብህን አዎንታዊና ገንቢ የሆኑ ነገሮችን መመገብ ይኖርብሃል። አስደሳችና ለሕይወትህ ጠቃሚ ስለሆኑ ነገሮች አንብብ። ለምሳሌ ያህል ወቅታዊ ስለሆኑ ጉዳዮች፣ ስለተለያዩ ባሕሎችና ስለ አንዳንድ አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተቶች ማንበብ ትችላለህ። መንፈስን የሚያድሱ ሙዚቃዎችን አዳምጥ። ሆኖም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመከታተል፣ ፊልሞችን በማየትና ልብ ወለድ ጽሑፎችን በማንበብ አእምሮህንና ልብህን በገሃዱ ዓለም ልትደርስባቸው በማትችላቸው ምኞቶችና ቅዠቶች እንዳትሞላ ተጠንቀቅ። በፊልም ላይ በምታያቸው ገጸ ባሕርያት መካከል ያለው ወዳጅነት የአንድ ሰው የሐሳብ ፈጠራ እንጂ በገሃዱ ዓለም ያለ እውነታ አይደለም።

ግልጽ ሁን

በጣሊያን የምትኖረው ዙሌይካ “ወጣት ሳለሁ ዓይን አፋር ስለነበርኩ ጓደኞች ማፍራት ተቸግሬ ነበር። ሆኖም ጓደኞች ማፍራት ከፈለግን እኛ ቀዳሚ ሆነን ራሳችንን ማስተዋወቅና ሌሎችን ለማወቅ መጣር እንዳለብን አውቅ ነበር” በማለት ተናግራለች። አዎን፣ እውነተኛ ጓደኞችን ለማፍራት ሌሎች እኛን በደንብ እንዲያውቁን ግልጽ መሆን ይኖርብናል። እንዲህ ያለው ቅርርብ እውነተኛ ጓደኞችን በማፍራት ረገድ ከውጫዊ መልክና ቁመና ይበልጥ ትልቅ ድርሻ አለው። ዶክተር አለን ሎይ ማግኒስ የተባሉ አማካሪ “ዓይናፋርም ይሁኑ ተግባቢ፣ ወጣትም ይሁኑ አረጋዊ፣ የሚስቡም ይሁኑ የማይስቡ፣ አዋቂም ይሁኑ አይሁኑ፣ መልከ ቀናም ይሁኑ መልከ ጥፉ ብቻ ግልጽና ቅን የሆኑ ሰዎች ዘላቂ ጓደኝነት መመሥረት ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ግልጽ ስለሆኑ ሌሎች ልባቸው ውስጥ ያለውን በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህ ሲባል ግን ላገኘኸው ሰው ሁሉ ማንነትህን ትገልጻለህ ወይም ብዙም ለማትቀርባቸው ሰዎች ጭምር ገመናህን ዝክዝክ አድርገህ ትናገራለህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለተወሰኑ ሰዎች ቀስ በቀስ እውነተኛ ስሜትህንና ሐሳብህን ታሳውቃቸዋለህ ማለት ነው። በጣሊያን የምትኖረው ሚካኤላ “መጀመሪያ ላይ ትንሽ ድብቅነት ያጠቃኝ ነበር። ሆኖም ጓደኞቼ ስሜቴን እንዲያውቁልኝና ይበልጥ እንዲቀርቡኝ በዚህ ረገድ ለውጥ ማድረግ ነበረብኝ” ስትል ተናግራለች።

በተፈጥሮህ ተግባቢና ተጫዋች ብትሆንም በጓደኝነት ደረጃ እርስ በርስ መቀራረብና መተማመን የሚመጣው በጊዜ ሂደትና አንዳንድ ነገሮችን በጋራ በማድረግ ነው። በተጨማሪም ሌሎች ስለ አንተ ስለሚያስቡት ነገር ከልክ በላይ አትጨነቅ። በጣሊያን የምትኖረው ኤሊዛ “አንዱ ችግሬ፣ የሆነ ነገር ለመናገር በፈለግኩ ቁጥር ብሳሳትስ እያልኩ እፈራ ነበር። በኋላ ግን ‘ሰዎች እውነተኛ ወዳጆቼ ከሆኑ የምለውን በትክክል ይረዳሉ’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። ስለዚህ የተሳሳተ ነገር ብናገር እንኳ በራሴ እስቃለሁ፤ ሌሎችም አብረውኝ ይስቃሉ” ብላለች።

ስለዚህ አትጨነቅ! ራስህን ለመሆን ጥረት አድርግ። የአንተ ያልሆነ ባሕርይ ማሳየትህ ምንም አይጠቅምህም። አሌክሳንደር ሙግዋን የተባሉ አንድ የቤተሰብ አማካሪ “አንድ ሰው ይበልጥ የሚያምርበት ራሱን ሲሆን ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ደስተኛ የሆነ ሰው ያልሆነውን ሆኖ ለመቅረብ ወይም በሌሎች ላይ ያልሆነ ስሜት ለማሳደር አይሞክርም። እውነተኛ ወዳጆችን ማፍራት የምንችለው ራሳችንን ሆነን በመቅረብ ብቻ ነው። በተመሳሳይም ሌሎች ራሳቸውን ሆነው ሲቀርቡን ደስ ሊለን ይገባል። እውነተኛ ጓደኛ የሚፈልጉ ሰዎች ሌሎችን ከነባሕርያቸው ይቀበላሉ እንጂ ተለውጠው እነርሱ የሚፈልጉት ዓይነት ሰው እንዲሆኑ አይጠብቁም። ሌሎች ሰዎች ባሏቸው አንዳንድ ባሕርያት የምትደሰት እንጂ የምታማርር ሰው መሆን የለብህም።

ጓደኛ ለማፍራት አንተ ራስህ ጓደኛ መሆን አለብህ

ጓደኛ ለማፍራት ሌላም ይበልጥ ወሳኝ የሆነ ነገር አለ። የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ኢየሱስ ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ሁሉ ስኬታማ መሆን የሚችሉት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ካላቸው ብቻ መሆኑን አመልክቷል። “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ሲል አስተምሯል። (ሉቃስ 6:31) ይህ ትምህርት ወርቃማው ሕግ በመባል ይታወቃል። እውነተኛ ጓደኞችን ማፍራት የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ራስ ወዳድ ባለመሆን ነው። ይህም ሲባል ከአንተ የሚፈለገውን ለማድረግ ምንጊዜም ዝግጁ መሆን ይኖርብሃል። በሌላ አነጋገር ጓደኛ ለማፍራት አንተ ራስህ ጓደኛ መሆን አለብህ። በጓደኛሞች መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ የሚጠነክረው ለመቀበል ሳይሆን ለመስጠት በመሽቀዳደም ነው። ከራሳችን ፍላጎትና ምርጫ ይልቅ ምንጊዜም የጓደኞቻችንን ፍላጎትና ምርጫ ማስቀደም ይኖርብናል።

ከላይ የተጠቀሰችው ማኑኤላ “ልክ ኢየሱስ እንዳለው እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በመቀበል ሳይሆን በመስጠት ነው። የሚቀበለው ሰው ደስ እንደሚለው የታወቀ ነው፤ ሆኖም ይበልጥ የሚደሰተው ሰጪው ነው። ጓደኞቻችንን በመጠየቅ፣ ያሉባቸውን ችግሮች ለመረዳት ጥረት በማድረግና እነርሱ እስኪጠይቁን ድረስ ሳንጠብቅ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በመርዳት ሰጪ መሆን እንችላለን” ስትል ተናግራለች። አሁን ያሉህን ጓደኞች ጨምሮ ለሌሎች አሳቢነት ለማሳየት ቀዳሚ ሁን። ከእነርሱ ጋር ያለህ ግንኙነት የሚጠናከርበትን መንገድ ፈልግ። ብዙም ዘላቂ ደስታና እርካታ ለማያስገኙ ነገሮች ጊዜህንና ትኩረትህን በመስጠት ከጓደኞችህ መራራቅ የለብህም። ጓደኞቻችን ጊዜና ትኩረት ይሻሉ። በጣሊያን የሚኖረው ሩበን “ጓደኛ ለማፍራትም ሆነ ጓደኝነታችን እየጠነከረ እንዲሄድ ለማድረግ አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ወሳኝ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ጥሩ አዳማጭ ለመሆን ጊዜ ይጠይቃል። ሁላችንም በጥሞና በማዳመጥም ሆነ ሌሎች ለሚናገሩት ነገር ትኩረት በመስጠት ረገድ ማሻሻል እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ሲናገሩ ወሬያቸውን ባለማቋረጥ ነው” ሲል ተናግሯል።

ለሌሎች አክብሮት ይኑርህ

በጓደኛሞች መካከል ያለው ግንኙነት ደስታ የሰፈነበትና ዘላቂ እንዲሆን እርስ በርስ መከባበር ሌላው ወሳኝ ነገር ነው። ይህም ለሌሎች ስሜት መጠንቀቅን ይጨምራል። ጓደኞችህ ከአንተ የተለየ ምርጫ ወይም አመለካከት በሚኖራቸው ጊዜ የአንተን ስሜት እንዲጠብቁልህ ትፈልጋለህ። አይደለም እንዴ? አንተስ እንደዚያ ማድረግ አይኖርብህም?—ሮሜ 12:10

በሌላም በኩል ለጓደኞቻችን አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንፈልግ ከሆነ የማናፈናፍን መሆን የለብንም። እውነተኛ ጓደኛ አይቀናም ወይም ጓደኛውን ለእኔ ብቻ ካልሆነ አይልም። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ፍቅር አይቀናም” ይላል። ጓደኞችህ ከአንተ ሌላ ከማንም ጋር ጓደኝነት መመሥረት እንደሌለባቸው አድርገህ እንዳታስብ ተጠንቀቅ። ምስጢራቸውን ለሌሎች ሰዎች እንዳካፈሉ ብታውቅ ቅር መሰኘትም ሆነ ማኩረፍ የለብህም። ሁላችንም ብንሆን ጓደኝነታችንን ማስፋት እንደምንፈልግ ማወቅ ይኖርብሃል። ጓደኞችህ ከሌሎችም ጋር እንዲቀራረቡ እድል ስጣቸው።

በተጨማሪም ጓደኞችህ ብቻቸውን መሆን የሚፈልጉበት ጊዜ እንዳለ አትዘንጋ። ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ለራሳቸው ነፃ ጊዜ ይፈልጋሉ። ጓደኞችህን በማንኛውም ጊዜ ጎራ ብለህ ልትጠይቃቸው እንደምትችል ቢሰማህም እንዳይሰለቹህ ሚዛናዊና አሳቢ መሆን ያስፈልግሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ፤ ታሰለቸውና ይጠላሃል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 25:17

ፍጽምና አትጠብቅ

ሰዎች ይበልጥ በተቀራረቡ መጠን አንዳቸው የሌላውን ደካማና ጠንካራ ጎን ማየት ይችላሉ። ሆኖም ይህ ጓደኞች በማፍራት ረገድ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም። በፈረንሳይ የሚኖረው ፓኮም “አንዳንዶች ከጓደኞቻቸው ብዙ ይጠብቃሉ። ጥሩ ባሕርይ ብቻ ማየት ይፈልጋሉ፤ ይህ ደግሞ የሚቻል አይደለም” በማለት ተናግሯል። ማናችንም ብንሆን ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ከሌሎች ፍጽምና መጠበቅ አይኖርብንም። ጓደኞቻችን ከነድክመቶቻችን እንዲቀበሉንና ታግሰው እንዲያልፉን እንፈልጋለን። እኛስ የእነርሱን አንዳንድ ድክመቶች አጋነን ባለመመልከት ታግሰን ማለፍ አይኖርብንም? ዴኒስ ፕራገ የተባሉ ደራሲ “ምንም እንከን የማይገኝባቸው (ማለትም በፍጹም የማይነጫነጩ፣ ሁልጊዜ አፍቃሪ፣ መቼም ቢሆን ስሜታቸው የማይለዋወጥ፣ ምንጊዜም ለእኛ ትኩረት የሚሰጡና ፈጽሞ የማያስቀይሙን) ጓደኞች ካሉን እነዚህ፣ ሰዎች ሳይሆኑ ለማዳ እንስሳት ናቸው” በማለት ተናግረዋል። የቅርብ ጓደኞቻችን እንደ ለማዳ እንስሳት እንዲሆኑ የማንፈልግ ከሆነ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናል’ ሲል የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 4:8

ጓደኝነት ደስታን በእጥፍ ይጨምራል ሐዘንን በግማሽ ይቀንሳል ይባላል። ይሁንና ጓደኞቻችን ፍላጎታችንን ሁሉ ያሟሉልናል ወይም ችግሮቻችንን ሁሉ ይቀርፉልናል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ራስ ወዳድነት ነው።

በደስታም ሆነ በመከራ ጊዜ የማይከዱ ጓደኞች

አንድ ጊዜ ጓደኝነት ከመሠረትን ጓደኝነታችን እንዲቀጥል ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ጓደኛሞች ጊዜና ቦታ ቢያራርቃቸውም አንዳቸው ለሌላው ሊያስቡና ሊጸልዩ ይችላሉ። የሚገናኙት ከስንት አንዴ ቢሆንም እንኳ ጓደኝነታቸው ምንጊዜም ያው ነው። በተለይ ደግሞ ጓደኞቻችን ሲቸገሩም ሆነ የእኛ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል። በተለይ፣ በተለይ ጓደኞቻችን ችግር ሲገጥማቸው ልንርቃቸው አይገባም። ደግሞም የእኛ እርዳታ በጣም የሚያስፈልጋቸው በዚህ ጊዜ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) እውነተኛ ጓደኛሞች በመካከላቸው አለመግባባት ቢፈጠር እንኳ ቶሎ ችግሩን ለማስተካከልና ይቅር ለመባባል ጥረት ያደርጋሉ። እውነተኛ ጓደኛሞች አልፎ አልፎ አለመግባባት ስለተፈጠረ ብቻ ጓደኝነታቸውን አያቋርጡም።

ጥቅም ፈላጊ ብቻ ባለመሆንና ሌሎችን በንጹሕ ልብ በመቅረብ ጓደኞችን ማፍራት ትችላለህ። ሆኖም ያሉህ ጓደኞች ምን ዓይነት ናቸው? የሚለውም ጉዳይ ሊታሰብበት የሚገባ ነው። ጥሩ ጓደኞችን መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በተጨማሪም በሐምሌ 2000 ንቁ! ላይ የወጣውን “ፈገግታ ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ወንድና ሴት “እንዲሁ ጓደኛሞች” ሊሆኑ ይችላሉ?

ያልተጋቡ ወንዶችና ሴቶች ጓደኛሞች ሊሆኑ ይችላሉ? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠውን መልስ “ጓደኛ” ስንል ምን ማለታችን ነው የሚለው ጉዳይ ይወስነዋል። ኢየሱስ በቢታንያ ይኖሩ ከነበሩት ከማርያምና ከማርታ ጋር የቅርብ ጓደኛ ነበር። እነዚህ ሴቶች ያላገቡ ነበሩ። (ዮሐንስ 11:1, 5) ሐዋርያው ጳውሎስ ከጵርስቅላና ከባሏ ከአቂላ ጋር ጓደኛ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:2, 3) እነዚህ ሰዎች በጣም ይዋደዱ እንደነበር መገመት አያዳግትም። ይሁንና ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ይህ ጓደኝነታቸው ወደ ሌላ ዓይነት ቅርርብ እንዲያመራ ፈቅደው ነበር ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው።

ይህ ያለንበት ዓለም ከምንጊዜውም ይበልጥ ወንዶችና ሴቶች አንድ ላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ አድርጓል። በመሆኑም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተገቢ የሆነ ቅርርብ መመሥረት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የማወቁ ጉዳይ ከምንጊዜውም ይበልጥ አንገብጋቢ እየሆነ መጥቷል። ባለ ትዳሮችም ቢሆኑ ከሌሎች ባለ ትዳሮችም ሆነ ካላገቡ ጋር ተገቢ የሆነ ጓደኝነት ሊመሠርቱ ይችላሉ።

ሳይኮሎጂ ቱዴይ የተባለው መጽሔት “ይሁን እንጂ ጓደኝነቱ በጾታዊ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው ወይስ ንጹሕ ጓደኝነት የሚለውን መለየቱ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል። “በንጹሕ ጓደኝነት የተጀመረው ግንኙነት ሳይታወቅ ወደ ሌላ ሊያመራ እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል። በቅንነት ተቃቅፎ ሰላም መባባሉ እንኳ ያልታሰበ የጾታ ስሜት ሊጭር ይችላል።”

በተለይ ባለትዳሮች አስተዋይና ምክንያታዊ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ዴኒስ ፕራገ የተባሉ ደራሲ ሃፒነስ ኢዝ ኤ ሲሪየስ ፕሮብለም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ማንኛውም ዓይነት ቅርርብ ትዳርን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በባለትዳሮች መካከል ያለውን ቅርርብ የጠበቀ የሚያደርገው የጾታ ግንኙነት ብቻ አይደለም። ባልም ሆነ ሚስት የትዳር ጓደኛቸው ከሌላ ተቃራኒ ጾታ ጋር የተለየ ቅርርብ መፍጠር የለበትም የማለት መብት አላቸው” በማለት ጽፈዋል። ኢየሱስ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ ከልብ ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክቷል። (ማቴዎስ 5:28) በመሆኑም ከሌሎች ጋር መቀራረብህ ምንም ስህተት የለውም፤ ሆኖም ልብህን መጠበቅና ለተቃራኒ ጾታ የተለየ ስሜት ወይም ሐሳብ እንዲያድርብህ በሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ እንዳትገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ራስህን መጠበቅህና አእምሮህን በጥሩ ነገሮች መሙላትህ በሌሎች ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ያደርግሃል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጓደኛሞች እርስ በርስ የልባቸውን ይጨዋወታሉ