በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ጓደኞች—መጥፎ ጓደኞች

ጥሩ ጓደኞች—መጥፎ ጓደኞች

ጥሩ ጓደኞች​—መጥፎ ጓደኞች

ሳራ የምትባል አንዲት ወጣት ጓደኛዬ ብላ የምታምነው አንድ ሰው ነፍሰ ገዳይ ሆኖ በመገኘቱ የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን እንዲህ ስትል በምሬት ተናግራለች:- ‘በጣም አምነው የነበረ ሰው እንዲህ ዓይነት ነገር ከሠራ ማንን ላምን እችላለሁ?’ ይህን እያጫወተችው ያለው ሰው ሳራ ይህ የምትለው ግለሰብ ቀደም ሲል ምን ዓይነት ሥነ ምግባር እንዳለው ታውቅ እንደሆነ ጠየቃት። ሳራም “ምን ማለትህ ነው?” ስትል መልሳ ጠየቀችው። ሳራ ሌላው ቀርቶ “ሥነ ምግባር” ሲል ምን ለማለት እንደፈለገ እንኳ አልገባትም ነበር። አንተስ ጓደኞችህ ምን ዓይነት ሥነ ምግባር እንዳላቸው ታውቃለህ?

ከሳራ ተሞክሮ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳት ያገኘዋል” በማለት ሐቁን አስቀምጦታል። (ምሳሌ 13:20) እንደ ሳራ ሁሉ ብዙ ሰዎች ጓደኛ ሲመርጡ የሚያዩት መግባባታቸውን ብቻ ነው። ከምንግባባቸው ሰዎች ጋር አብረን ስንሆን ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። ሆኖም ስለ እውነተኛ ማንነታቸው ብዙም ትኩረት ሳንሰጥ ስለተግባባን ብቻ ሰዎችን ጓደኛ አድርገን የምንመርጥ ከሆነ ከባድ ችግር ላይ ልንወድቅ እንችላለን። አንድ ሰው ጥሩ ሥነ ምግባር እንዳለውና እንደሌለው እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

የጥሩ ሥነ ምግባር አስፈላጊነት

በቅድሚያ እኛ ራሳችን ጥሩ ሥነ ምግባር ያለን ሰዎች መሆን አለብን። ትክክልና ስህተት የሆነውን፣ ጥሩውንና መጥፎውን ለይተን ማወቅና በማንኛውም ጊዜ ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ጠብቀን መኖር ያስፈልገናል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 27:17) እንደ ብረት የጠነከረ የሥነ ምግባር አቋም ያላቸው ሁለት ሰዎች ጓደኛሞች ከሆኑ መልካም ባሕርያትን በማዳበር ረገድ እርስ በርስ የሚረዳዱ ከመሆኑም በላይ በመካከላቸው ያለው ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል።

በፈረንሳይ የሚኖረው ፓኮም “እኔ እውነተኛ ጓደኛ የምለው በጥሞና የሚያዳምጠኝንና በደግነት የሚያነጋግረኝን እንዲሁም ሳጠፋ የሚገሥጸኝን ሰው ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። አዎ፣ የልብ ጓደኞቻችን ወጣትም ሆኑ አረጋዊ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘን እንድንጓዝ የሚረዱንና ተገቢ ያልሆነ ነገር ልናደርግ ስንል የሚያርሙን መሆን አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የወዳጅ ማቁሰል ይታመናል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 27:6) ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ አቋማችንን ለማጠናከር ለአምላክና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ፍቅር ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆን ይኖርብናል። በፈረንሳይ የምትኖረው ሴሊን “በምማርበት ትምህርት ቤት እንደ እኔ ያለ ክርስቲያናዊ እምነትና ሥነ ምግባራዊ አቋም ያላቸው ተማሪዎች ከሌሉ እውነተኛ ጓደኝነት መመሥረት ያለብኝ በጉባኤ ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር መሆን እንዳለበት ተገንዝቤያለሁ። እነዚህ ጓደኞቼ ሚዛኔን እንድጠብቅ በእጅጉ ረድተውኛል” ስትል ተናግራለች።

ጓደኛ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን መፈለግ

ከአንድ ከተዋወቅከው ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረት ከፈለግህ ‘ጓደኞቹ እነማን ናቸው?’ ብለህ መጠየቅህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የቅርብ ጓደኞቹ እነማን እንደሆኑ ማወቅህ ስለ እሱ ማንነት ጥሩ ግንዛቤ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም በአካባቢው ያሉ የጎለመሱና የተከበሩ ሰዎች ለእርሱ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? እንዲሁም ጓደኛ ልናደርጋቸው ያሰብናቸው ሰዎች ከእኛ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥሩ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ጭምር ማሰብ ይኖርብናል። በተለይ ከጥቅም አንጻር ብዙም ሊያደርጉላቸው ለማይችሉ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ምን ይመስላል? አንድ ሰው በማንኛውም ጊዜ፣ ለሁሉም ሰው እንደ ሐቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ትዕግሥትና አሳቢነት የመሳሰሉ ግሩም ባሕርያትን የማያሳይ ከሆነ ለአንተስ ወደፊት ጥሩ ጓደኛ ሊሆንህ እንደሚችል ምን ዋስትና ይኖርሃል?

አንድ ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚያንጸባርቀውን እውነተኛ ባሕርይ በደንብ ለማወቅ ትዕግሥትና ብልሃት እንዲሁም ጊዜ ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” ይላል። (ምሳሌ 20:5) ጓደኛ ልናደርጋቸው ያሰብናቸውን ሰዎች እውነተኛ ባሕርይ፣ ዝንባሌ እንዲሁም የሥነ ምግባር አቋም መገምገም እንዲያስችለን አንዳንድ ወሳኝ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንሳቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ምን ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ናቸው? ደግ ናቸው ወይስ አይደሉም? እንዲያው በአብዛኛው ሲታዩ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት ያላቸው ናቸው ወይስ አፍራሽ አመለካከት ያላቸውና ተጠራጣሪዎች? ለጋስ ናቸው ወይስ ራስ ወዳድ? እምነት የሚጣልባቸው ናቸው ወይስ የማይታመኑ? አንድ ሰው ሌሎችን ለአንተ የሚያማ ከሆነ አንተንስ ለሌሎች እንዳያማ ምን ይከለክለዋል? ኢየሱስ “በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋል” ሲል ገልጿል። (ማቴዎስ 12:34) ሰዎች የሚናገሩት ነገር ማንነታቸውን ስለሚገልጽ ልብ ብለን ማዳመጥ ይኖርብናል።

በጋራ ሊኖሩን የሚገቡ ወሳኝ ነገሮች

አንዳንዶች ጓደኞቻቸው ልክ እንደ እነሱ ዓይነት ምርጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ አድርገው ያስባሉ። አንድ ትንሽ ልጅ “እኔ የምወደውን ዓይነት ኬክ የማይወድ ሰው በፍጹም ጓደኛዬ እንዲሆን አልፈልግም” ሲል ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ጓደኛሞች እርስ በርስ ይበልጥ ሊግባቡ የሚችሉት በብዙ ነገር የሚመሳሰሉ ከሆነ ነው። በተለይ ደግሞ ተመሳሳይ የሆነ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አቋም ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ሲባል ግን ባሕርያቸውም ሆነ አስተዳደጋቸው አንድ ዓይነት መሆን አለበት ማለት አይደለም። እንዲያውም የተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው መሆኑ ሊጠቅማቸውና ጓደኝነታቸውን ሊያጠነክርላቸው ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው በዮናታንና በዳዊት እንዲሁም በሩትና በኑኃሚን መካከል የነበረው ግንኙነት ጓደኝነትን በተመለከተ ጊዜ የማይሽረው ምሳሌ ይሆነናል። እነዚህ ሰዎች የሚያመልኩት አምላክም ሆነ የሚመሩበት መሠረታዊ ሥርዓት አንድ ነበር። * በዮናታንና በዳዊት እንዲሁም በሩትና በኑኃሚን መካከል በዕድሜም ሆነ በአስተዳደግ ረገድ ትልቅ ልዩነት ነበር። በመሆኑም ጓደኝነትን በተመለከተ ከእነሱ አንድ ቁምነገር እንማራለን። ይኸውም ወጣቶችና በዕድሜ ትልቅ የሆኑ ጓደኝነት ከመሠረቱ አንዳቸው ከሌላው ጥቅም ማግኘታቸው የማይቀር ነው።

በዕድሜ የተለያዩ መሆን ያለው ጥቅም

ከእኛ በዕድሜ ከሚበልጡ ወይም ከሚያንሱ ጋር ጓደኝነት መመሥረታችን ለሁለታችንም ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ጥቅም ያገኙ ወጣቶች የተናገሩትን ተሞክሮ እስቲ እንመልከት።

ማኑኤላ (ጣሊያን):- “በዕድሜ ጠና ያሉ አንድ ባልና ሚስት ጓደኞች ነበሩኝ። እኔ የሚሰማኝን ሁሉ እነግራቸዋለሁ፤ ደስ የሚለው ደግሞ እነሱም የሚሰማቸውን ሁሉ ይነግሩኛል። ልጅ ነች ብለው አይንቁኝም። ይህም ይበልጥ እንድወዳቸው አደረገኝ። ከእነርሱ ጋር ጓደኛ መሆኔ በተለይ ችግር ሲገጥመኝ በእጅጉ ጠቅሞኛል። ችግሬን ለዕድሜ እኩዮቼ ሳጫውታቸው ብዙውን ጊዜ የሚሰጡኝ ምክር ያልታሰበበት እንደሆነ አስተውያለሁ። እነዚህ በዕድሜ ጠና ያሉ ጓደኞቼ ግን እኛ ወጣቶች ገና ያልደረስንበት ተሞክሮ፣ ማስተዋልና ብስለት አላቸው። እነዚህ ጓደኞቼ በሕይወቴ ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎችን እንዳደርግ ረድተውኛል።”

ዙሌይካ (ጣሊያን):- “ተሰባስበን በምንጫወትበት ጊዜ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን በዕድሜ ጠና ያሉትንም እንጨምራለን። ወጣቶችና አዋቂዎች አንድ ላይ ተሰባስበን ስንጫወት ውለን ማታ ስንለያይ ሁላችንም ተበረታተን ወደ ቤታችን እንደምንመለስ አስተውያለሁ። እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ እንድናሳልፍ የሚረዳን ሁላችንም በመጠኑም ቢሆን የተለያየ ዓይነት አመለካከት ያለን መሆኑ ነው።”

እናንተ ትልልቆችም ብትሆኑ ወጣቶችን ልትቀርቧቸው ይገባል። ከላይ የተሰጡት አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ወጣቶች የእናንተን የካበተ ተሞክሮ የሚያደንቁ ከመሆኑም በላይ አብረዋችሁ መሆን ያስደስታቸዋል። ኤሚሊያ የሚባሉ በሰማንያዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አንዲት መበለት “ወጣቶችን ሆነ ብዬ እቀርባቸዋለሁ። የእነሱን ብርታትና ጥንካሬ ሳይ እኔም መንፈሴ ይታደሳል!” በማለት ገልጸዋል። በዚህ መንገድ እርስ በርስ መበረታታት ይህ ነው የማይባል ጥቅም አለው። ብዙ ጎልማሶች በሕይወታቸው ደስተኛና ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት ወጣት በነበሩበት ጊዜ በዕድሜ የሚበልጧቸውና ምሳሌ የሚሆኗቸው ጓደኞቻቸው በሰጧቸው ጥሩ ምክር እንደሆነ ይናገራሉ።

ጓደኝነትን ማጠናከር

ጥሩ ጓደኝነት ለመመሥረት አዲስ ጓደኞችን ማፍራት አለብህ ማለት አይደለም። መልካም ባሕርይ ያላቸው ጓደኞች ካሉህ ጓደኝነታችሁ ይበልጥ የሚጠናከርበትን መንገድ ለምን አትፈልግም? የረጅም ጊዜ ጓደኞች ምንጊዜም ውድ ስለሆኑ በአክብሮት ልንይዛቸው ይገባል። በጓደኝነት ያሳለፋችሁትን ጊዜ አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም።

ከሁሉም በላይ ደግሞ እውነተኛ ደስታም ሆነ እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት የምትችለው ራስህን፣ ጊዜህንና ጥሪትህን በመስጠት መሆኑን አትዘንጋ። የምታገኘው በረከት ከምትከፍለው መሥዋዕትነት በእጅጉ የላቀ ነው። ጓደኛ በምትመርጥበት ጊዜ ሁሌ የራስህን ጥቅም ብቻ የምታስብ ከሆነ መቼም ቢሆን ሊሳካልህ አይችልም። በመሆኑም ጓደኛ ለመምረጥ ስታስብ በምታደንቃቸው ወይም ይጠቅሙኛል ብለህ በምታስባቸው ላይ ብቻ አታተኩር። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ብዙ ትኩረት የማይሰጧቸውን ወይም ጓደኛ በመመሥረት ረገድ ችግር ያለባቸውን መፈለግ ትችላለህ። በፈረንሳይ የምትኖረው ጌል “እርስ በርስ ተገናኝተን ለመጫወት ስናስብ ብቸኝነት የሚሰማቸው ወጣቶች እንዳሉ ስለምናውቅ እነሱንም እንጋብዛቸዋለን። ‘ብቻህን ቤት ቁጭ ከምትል ከእኛ ጋር መጫወት ትችላለህ፤ በዚያውም እርስ በርስ እንተዋወቃለን’ እንላቸዋለን” በማለት ተናግራለች።—ሉቃስ 14:12-14

በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ ሰዎች ጓደኛ ሊያደርጉህ ሲሞክሩ ቶሎ ብለህ ፊት አትንሳቸው። በጣሊያን የምትኖረው ኤሊሳ “ከዚህ ቀደም ሰዎች እንዳገለሉህ ሲሰማህ በውስጥህ ትንሽ ቅሬታ ያድርብሃል። እንዲያውም ‘ጓደኛ ኖረኝ አልኖረኝ ምንም ጥቅም የለውም’ ብለህ ማሰብ ትጀምራለህ። ከዚያም ዝምተኛ ወደመሆን፣ ራስህን ወደማግለልና ስለ ራስህ ብቻ ወደማሰብ ታዘነብላለህ። ጓደኛ ከመፈለግ ይልቅ ሌሎች እንዳይቀርቡህ መንገዱን ሁሉ ትዘጋለህ” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች። አጉል ፍርሃት ወይም ራስ ወዳድነት አዳዲስ ጓደኞች እንዳታፈራ እንቅፋት እንዲሆንብህ ከመፍቀድ ይልቅ ሌሎች እንዲቀርቡህ መንገዱን ክፍት አድርግ። ሌሎች ለአንተ አስበው ጓደኛ ሊያደርጉህ ሲፈልጉ ከልብ ልታደንቃቸው ይገባል።

እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት ትችላለህ

እውነተኛ ጓደኞችን ለማፍራት ምኞት፣ ሌሎች ለጓደኝነት እስኪጋብዙን ድረስ መጠበቅና ጓደኛ ስለማፍራት ምክር የሚሰጡ ይህን የመሳሰሉ ርዕሶችን ማንበብ ብቻ አይበቃም። ጓደኛ ለማፍራት መሞከር ብስክሌት ለመንዳት ከመለማመድ ጋር ይመሳሰላል። እንዲሁ በማንበብ ብቻ ጓደኛ የማፍራትም ሆነ ብስክሌት የመንዳት ችሎታ ማዳበር አይቻልም። በተደጋጋሚ ልንወድቅ ብንችልም የግድ እየነዳን መለማመድ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጋር የጠበቀ ጓደኝነት መመሥረት የምንችለው ከአምላክ ጋር የጸና ወዳጅነት መመሥረት ስንችል እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም አምላክ ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት የማናደርግ ከሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት የምናደርገውን ጥረት አይባርክልንም። በእርግጥ እውነተኛ ጓደኞችን ማፍራት ትፈልጋለህ? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ! አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ሌሎችን ቅረብ እንዲሁም አንተ ራስህ ጓደኛ ሁን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 የእነዚህን ሰዎች ጓደኝነት በተመለከተ ሩት፣ አንደኛ ሳሙኤል እና ሁለተኛ ሳሙኤል የተባሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማንበብ ትችላለህ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ

ሌሎች ብዙ ነገሮችን ከቤት እንደምንማር ሁሉ ስለ ጓደኝነትም መማር የምንጀምረው ከቤት ነው። በመሠረቱ የቤተሰብ ሕይወት ራሱ የአንድን ትንሽ ልጅ የጓደኝነት ፍላጎት በሙሉ ያሟላል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሥር እያለም እንኳ አንድ ልጅ ከቤተሰቡ ውጭ የሚኖረው ግንኙነት በአስተሳሰቡ፣ በስሜቱና በባሕርይው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሌላ አገር ተሰደው የመጡ ሕፃናት ልጆች ከሌሎች ልጆች ጋር ባላቸው ግንኙነት ብቻ አንድን አዲስ ቋንቋ ወዲያው የመናገር ችሎታ እንደሚያዳብሩ አስተውለህ ይሆናል።

ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ልጆችህ ጓደኞችን እንዴት በጥበብ መምረጥ እንዳለባቸው የመርዳት ጥሩ አጋጣሚ አለህ። ትንንሽ ልጆችና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ያለወላጅ እርዳታ ጓደኞቻቸውን በጥበብ ሊመርጡ አይችሉም። ሆኖም በዚህ ረገድ ችግር አለ። አብዛኞቹ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ወይም በዕድሜ ከሚበልጧቸው ጋር ከመወዳጀት ይልቅ ከእኩዮቻቸው ጋር መቀራረብን ይመርጣሉ።

ወጣቶች ምክር ለማግኘት ከወላጆቻቸው ይልቅ ወደ እኩዮቻቸው ዞር የሚሉበት አንዱ ምክንያት ወላጆች የወላጅነት ግዴታቸውን በአግባቡ ስለማይወጡ መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች ተናግረዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው መመሪያ ለመስጠት ጥረት በማድረግና ስለ ልጆቻቸው ከልብ የሚያስቡ በመሆን አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል። (ኤፌሶን 6:1-4) ግን እንዴት? ዶክተር ሮን ታፍል የተባሉ የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻቸው ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችሉ ግራ የገባቸው ብዙ ወላጆች እንደሚያጋጥሟቸው ተናግረዋል። አብዛኞቹ ወላጆች የወላጅነት ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ “በመገናኛ ብዙኃን በስፋት በሚሰራጨው ዘመን አመጣሽ የልጅ አስተዳደግ ይሸነፋሉ” ብለው ጽፈዋል። ወላጆች ግን በዚህ አመለካከት የሚሸነፉት ለምንድን ነው? “ልጆቻቸውን በደንብ ካለማወቃቸው የተነሳ የእነሱን ሐሳብ መረዳትም ሆነ ለጥያቄዎቻቸው መልስ መስጠት ስለማይችሉ ነው።”

ሆኖም ወላጆች ከወጣት ልጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ። ልጆች የሚፈልጉትን ነገር ከወላጅ ካላገኙ ወደ ጓደኞቻቸው ዞር ማለታቸው እንደማይቀር ወላጆች ማወቅ አለባቸው። ታዲያ ልጆች የሚፈልጉት ነገር ምንድን ነው? ታፍል “ማንኛውም ወጣት የሚፈልገውን ሁሉ ይፈልጋሉ፤ ይህም ማለት እንክብካቤ፣ አድናቆት፣ አይዞህ መባል፣ የማያሻማ መመሪያ፣ ከእነሱ ምን እንደሚጠበቅ ግልጽ የሆነ ማብራሪያና በቤተሰቡ ውስጥ ተፈላጊ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ነገር ይፈልጋሉ” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ወጣቶች ወላጆቻቸው ከላይ የተዘረዘሩትን ፍላጎቶቻቸውን ሊያሟሉላቸው አልቻሉም፤ እንዲሁም ቤተሰባቸው ‘የራሳቸው ቤተሰብ እንደሆነ’ አይሰማቸውም” ብለዋል።

ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲያፈሩ እንዴት መርዳት ትችላላችሁ? በመጀመሪያ ደረጃ አንተ ራስህ ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድና የጓደኛ ምርጫህን በተመለከተ በጥሞና አስብ። የአንተም ሆነ የጓደኞችህ አኗኗርና የሕይወት ግብ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነና በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው? መንፈሳዊ ነው ወይስ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ? “ከቃልህ ይልቅ ድርጊትህ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ልጆችህ የአንተንም ሆነ የጓደኞችህን እንዲሁም የጓደኞችህን ልጆች ጠባይና ድርጊት እንደሚያስተውሉ መዘንጋት የለብህም” ሲል ዳግላስ የተባለ የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌ የሆነ አንድ አባት ተናግሯል።

እንስሳት እንኳን በደመ ነፍስ በመመራት ልጆቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ስለ ድብ የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ እንዳሉት “እናት ድቦች ግልገሎቻቸውን ሊያጠቃ ከሚችል ከማንኛውም ነገር በመከላከል ረገድ የታወቁ ናቸው” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ሰብዓዊ ወላጆችስ ከዚህ ያነሰ ነገር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? በጣሊያን የሚኖር ሩበን የተባለ ወጣት “ወላጆቼ ከአጉል ጓደኛ ጋር ስገጥም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እያወጡ በማስረዳት ይመክሩኝ ነበር። በዚህ ጊዜ መጀመሪያ የሚሰማኝ ስሜት ‘ተመልከቱ እንግዲህ! ጭራሽ ጓደኞች መያዝ አልችልም ማለት ነው እኮ’ የሚል ነበር። ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር ግን ወላጆቼ ትክክል መሆናቸውን መገንዘብ ችያለሁ፤ ለትዕግሥታቸው አመሰግናቸዋለሁ፤ ከክፉ እንድጠበቅ ረድተውኛል” በማለት ተናግሯል።

በተጨማሪም ልጆቻችሁን ከሌሎች ማለትም መልካም ምሳሌ ከሚሆኑና ጥሩ ግቦችን ለማውጣት ከሚረዷቸው ጓደኞች ጋር እንዲተዋወቁ አድርጉ። ፍራንሲስ የተባለ ደስተኛና ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ወጣት “እናታችን ወንዶቹ ልጆች ማንኛውንም ነገር የምናደርገው በአብዛኛው እርስ በርሳችን እንደሆነ ስላስተዋለች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ ወጣት ወንድሞችን ቤት ትጋብዝልን ነበር። ይህም ከእነሱ ጋር እንድንተዋወቅና ጓደኝነት እንድንመሠርት ረድቶናል” በማለት እናታቸው ያደረገችላቸውን በማስታወስ ይናገራል። በበኩልህ እንደዚህ የመሰለ ጥረት ካደረግክ ልጆችህ ጥሩ ጓደኝነት ሊመሠርቱ የሚችሉበት አጋጣሚ ልትፈጥርላቸው ትችላለህ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጓደኛ ልታደርግ ያሰብካቸው ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው አስተውል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዕድሜና የአስተዳደግ ልዩነት ቢኖርም ራስ ወዳድነት የሌለበት ጓደኝነት ምንጊዜም ይጸናል