ለቁንጅና ሲባል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች
ለቁንጅና ሲባል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች
እውነተኛ ቁንጅና መለኪያው ምንድን ነው? “ውበት እንደ ተመልካቹ ነው” የሚል የቆየ አባባል አለ። በእርግጥም ቁንጅና እንደየሰዉ አመለካከት ሊለያይ ይችላል። ከዚህም በላይ የቁንጅና መስፈርት ከባሕል ወደ ባሕል እንዲሁም ከዘመን ወደ ዘመን በጣም ይለያያል።
በዩናይትድ ስቴትስ የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግብ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄፍሪ ሶባል “በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን በሙሉ በሁሉም ማኅበረሰቦች ዘንድ ለማለት ይቻላል፣ ውፍረት አንድ ሰው ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ እንዳለው የሚያሳይ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። የወፈረ ሁሉ ኑሮ የደላው ጤነኛ ሰው ተደርጎ ሲታይ ከሲታ የሆነ ደግሞ የሚበላው ያጣ ድሃ ሰው ተደርጎ ይታይ ነበር” ብለዋል። ይህ አመለካከት በዘመኑ የነበሩ የሥነ ጥበብ ሰዎች በሠሯቸው ሥራዎች ላይ በግልጽ ይታያል። የሠሯቸው ሞዴሎች አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ሲሆኑ ጠብደል ያለ እጅ፣ እግር፣ ጀርባ ወይም ዳሌ ያላቸው ናቸው። እነዚህ የሥነ ጥበብ ሥራዎች በአብዛኛው በጣም ቆንጆዎች ናቸው ተብለው ይታሰቡ የነበሩ እውነተኛ ሰዎች ሥዕሎች ናቸው።
ምንም እንኳ ቁንጅና ወፍራም ወይም ከሲታ በመሆን ላይ ብቻ የተመካ ባይሆንም ይህ አመለካከት ዛሬም ጨርሶ አልጠፋም። በደቡብ ፓስፊክ የሚገኙ አንዳንድ ባሕሎች አሁንም ለውፍረት ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። በአንዳንድ የአፍሪካ አካባቢዎች ሊያገቡ የተዘጋጁ ሴቶች እንዲወፍሩና ይበልጥ አምረው እንዲታዩ አንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ለበርካታ ቀናት ብዙ ቅባት
ያለው ምግብ ይቀለባሉ። በናይጄርያ የሚኖር አንድ የምሽት ክበብ ባለቤት “አፍሪካዊት ሴት አብዛኛውን ጊዜ ወፍራም ነች። . . . ውፍረት መልኳ ነው። በባሕላችን ቁንጅና ማለት ውፍረት ነው” ብሏል። በበርካታ የላቲን አሜሪካ ባሕሎችም ለውፍረት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ሲሆን የብልጽግናና የስኬት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።ይሁን እንጂ በሌሎች በርካታ አካባቢዎች ሁኔታው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ለምን? አንዳንዶች እንደሚሉት ንግድና ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ በሄደና በዚህም ምክንያት የምግብ አቅርቦቱ እየጨመረ እንዲሁም ሥርጭቱ እየሰፋ በሄደ መጠን ድሮ ደህና ኑሮ ያላቸው ሰዎች ብቻ ይመገቧቸው የነበሩትን ምግቦች “ዝቅተኛ ኑሮ” ያላቸው ሰዎችም ለመመገብ በመቻላቸው ነው። በዚህም ምክንያት ጠብደል ላለ ቁመና ይሰጥ የነበረው ግምት ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ውፍረትን ከሆዳምነት ጋር ስለሚያያይዙ ለውፍረት አሉታዊ የሆነ አመለካከት ሊስፋፋ ችሏል። በተጨማሪም ውፍረት በጤና ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የሚጠቁሙ ሳይንሳዊ ግኝቶች ብቅ ማለታቸው በሰዎች አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምክንያቶች ሰዎች ለጥሩ መልክና ቁመና ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ በማስከተላቸው ባሁኑ ጊዜ በብዙ የዓለም አካባቢዎች ቅጥነት በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።
መገናኛ ብዙኃንም ይህን አስተሳሰብ ለማስፋፋት ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል። በንግድ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የሚታዩትና በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች የሚቀርቡት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሸንቀጥ ያለ ቁመና ያላቸው ናቸው። ይህም የእነዚህ ሰዎች ዓይነት መልክና ቁመና ያለው ሰው የተሳካለትና የተሟላለት ሰው ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል። የፊልምና የቴሌቪዥን ኮከቦችም ተመሳሳይ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
ይህ ሁሉ ወጣቶችን ጨምሮ በማንኛውም ሰው ላይ እንዴት ያለ ተጽዕኖ ያሳድራል? በቅርቡ ስለ መልክ የወጣ አንድ ጽሑፍ “አንዲት አሜሪካዊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እስከምታጠናቅቅበት ጊዜ ድረስ 22,000 ሰዓታት ቴሌቪዥን በማየት እንደምታሳልፍ” ያመለክታል። በዚህ ጊዜ ሁሉ ፍጹም ውብ ቁመና አላቸው የሚባሉ ሴቶችን ምስል ደጋግማ ትመለከታለች። ጽሑፉ በመቀጠል “ሴቶች እነዚህን ምስሎች ደጋግመው በማየታቸው ምክንያት ክብርን፣ ደስታን፣ ፍቅርንና ስኬትን እንደዚህ ካለው የአካል ቁመና ጋር ማዛመድ ይጀምራሉ” ይላል። ስለዚህ የሞዴሎችን ፎቶ መጽሔቶች ላይ ከተመለከቱ በኋላ ጥናት ከተደረገባቸው ልጃገረዶች መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት መክሳት እንደሚኖርባቸው የተሰማቸው መሆኑ አያስደንቅም። ጥናት ከተደረገባቸው መካከል ግን ክብደታቸው ከፍ ያለ ነው ተብለው የሚታሰቡት 29 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ።
የፋሽኑ ኢንዱስትሪም ሰዎች ስለ ቁንጅና በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። በሜክሲኮ ሲቲ የምትኖረው ቬኔዙዌላዊቷ ሞዴል ጀኒፈር “ሥራዬ አምሮ መታየት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በዛሬው ጊዜ መቅጠን ነው” ብላለች። ቨኒሳ የተባለች ፈረንሳዊት ሞዴል ደግሞ “ያን ያህል መክሳት አለብሽ ብለው ስለሚያስገድዱ ሳይሆን እኛ ራሳችን መክሳት አለብኝ ብለን ስለምናስብ ነው። መቅጠን በዓለም በሙሉ የተስፋፋ ዝንባሌ
ነው” ብላለች። በወጣት ሴቶች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት 69 በመቶ የሚሆኑት በመጽሔቶች ላይ የሚወጡ ሞዴሎች ለቁንጅና ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደሩባቸው ተናግረዋል።ይሁን እንጂ “ጥሩ መልክና ቁመና” የሚያማልለው ሴቶችን ብቻ አይደለም። ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው የሜክሲኮ ጋዜጣ “ይህን የሚያክሉ ብዙ የወንዶች ውበት መጠበቂያ ምርቶች ገበያ ላይ የወጡበት ጊዜ የለም” ብሏል።
“ተፈላጊውን መልክ” ለማግኘት የሚደረግ ጥረት
ብዙ ሰዎች “ተፈላጊ መልክ” እንዲኖራቸው ወይም ተውበው ለመታየት ሲሉ የመልክ ማስተካከያ ቀዶ ሕክምና እስከማድረግ ይደርሳሉ። እንዲህ ያለውን ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ይጠየቅ የነበረው ገንዘብ እየቀነሰ ከመሄዱም በላይ የዚህ ሕክምና ዓይነት በዝቷል። የመልክ ማስተካከያ ቀዶ ሕክምና ወይም ኮስሞቲክ ሰርጀሪ የተጀመረው እንዴት ነው?
ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው ዘመናዊው የመልክ ማስተካከያ ቀዶ ሕክምና ወይም ፕላስቲክ ሰርጀሪ የተጀመረው በጦርነት ላይ የደረሱ ጠባሳዎችን ለማጥፋት ሙከራ ይደረግ በነበረበት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ይህ ዘዴ በቃጠሎ ወይም በሌላ አደጋ የተበላሸ መልክንና ከውልደት ጀምሮ የሚኖር ጉድለትን በማስተካከል ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቷል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ፕላስቲክ ሰርጀሪ የሚደረገው “መልካቸውን ለማሳመር በሚፈልጉ ጤነኛ ሰዎች ላይ” እንደሆነ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ አምኗል። ለምሳሌ የአፍንጫ ቅርጽ ማስተካከል፣ ከፊትና ከአንገት አካባቢ ትርፍ ቆዳ ማንሳት፣ የጆሮን ትልቅነት መቀነስ፣ ከሆድና ከዳሌ አካባቢ ስብ ማስወገድ፣ የአንዳንድ የሰውነት ክፍሎችን መጠን መጨመር ሌላው ቀርቶ የእምብርትን ቅርጽ ማስተካከል ይቻላል።
ይሁን እንጂ እንዲያው መልካቸውን ለማሳመር ሲሉ ብቻ ራሳቸውን ለአደጋ ስለሚያጋልጡ ጤናማ ሰዎች ምን ለማለት ይቻላል? እንዲህ ዓይነቱ ሕክምናስ ለምን ዓይነት አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል? የሜክሲኮ የፕላስቲክ፣ ኤስቴቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ማኅበር ጸሐፊ የሆኑት አንከል ፓፓዶፑሎስ አንዳንድ ጊዜ ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርጉት ባለሞያዎች በቂ ሥልጠና ያላገኙ በመሆናቸው ብዙ ጉዳት ያደርሳሉ። የታካሚዎችን መልክ ለማስተካከል አደገኛ መድኃኒቶችን የሚሰጡ ክሊኒኮች አሉ። በ2003 መጀመሪያ ላይ በመልክ ማሳመሪያ ማዕከል ውስጥ በተፈጠረ ጤንነት የሚጎዳ ሁኔታ ምክንያት በካናሪ ደሴቶች ቀዶ ሕክምና በተደረገላቸው በመቶዎች በሚቆጠሩ ሴቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አንድ የጋዜጣ ዘገባ ገልጿል። *
መልክና ቁመናቸውን ለማሳመር ሲሉ ሌት ተቀን የሚደክሙ ወንዶችም አሉ። አንዳንዶች ጡንቻቸውን ለማፈርጠምና ጥሩ የሰውነት ቅርጽ ለማዳበር በስፖርት መሥሪያ ቦታዎች በርካታ ሰዓት ያሳልፋሉ። ሚለኒዮ የተባለው መጽሔት እንደሚለው “ውሎ አድሮ የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግ በሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰዓት ምክንያት ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው ዝምድናና ማኅበራዊ ግንኙነት ይበላሽባቸዋል” ብሏል። ብዙዎች ፈርጠም ያለ ቁመና እንዲኖራቸው
በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት ስቴሮይድስ እንደሚባሉት ያሉትን በአካል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መድኃኒቶች እስከ መውሰድ ደርሰዋል።አንዳንድ ወጣት ሴቶች ስለ ቁመናቸውና ስለ መልካቸው ከልክ በላይ በመጨነቃቸው ምክንያት ቡልሚያ እና አኖሮክሲያ ነርቮሳ እንደሚባሉት ላሉ ከምግብ ፍላጎት መዛባት ጋር ለተያያዙ ችግሮች ተዳርገዋል። ሌሎች ደግሞ ተደማጭነት ካላቸው የጤና ተቋማት ምንም ዓይነት ድጋፍ ያላገኙና በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የተለፈፈላቸውን የማክሻ መድኃኒቶች ይወስዳሉ። እንደነዚህ ያሉትን መድኃኒቶች መውሰድ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ስለ መልክና ቁመና ከልክ በላይ መጨነቅ የሚያስከትለው አደጋ በአካላዊ ጉዳት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። በዩ ኤስ ኤ የብራውን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ካተርን ፊሊፕስ ስለ ቁመናቸውና ስለ መልካቸው ከልክ በላይ የሚጨነቁ ሰዎች ቦዲ ዳያስሞርፊክ ዲስኦርደር የሚባል የሥነ ልቦና በሽታ እንደሚይዛቸው ተናግረዋል። ይህ በሽታ ያለባቸው ሰዎች አስቀያሚ ነኝ ብለው ከልክ በላይ ይጨነቃሉ። ይህ በሽታ ከ50 ሰዎች መካከል አንዱን ሊይዝ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች “ስለ አስቀያሚነታቸው በጣም እርግጠኛ ስለሚሆኑ ራሳቸውን ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ያገልላሉ። በጭንቀት ሊዋጡና ራሳቸውን የመግደል ሐሳብ ሊያድርባቸው ይችላል” ብለዋል። ዶክተር ፊሊፕስ ፊቷ ላይ ጥቂት ብጉሮች ስላሉባትና እሷ ግን መላ ፊቷ የቆሳሰለ እንደሆነ የምታምንን አንዲት መልከ ቀና ልጃገረድ በምሳሌነት ጠቅሰዋል። ልጅቱ ሰው ፊት ለመታየት እምቢተኛ በመሆኗ ትምህርቷን ከስምንተኛ ክፍል አቋርጣለች።
አንድ ሰው ጥሩ የሚባለው መልክና ቁመና እንዲኖረው ሲል አእምሯዊም ሆነ አካላዊ ጤንነቱን ጉዳት ላይ መጣሉ አስፈላጊ ነው? ማንም ሰው ሊጣጣርለት የሚገባ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ውበት አለ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 መልክን ለማሳመር ሲባል ቀዶ ሕክምና ማድረግ ለክርስቲያኖች በግል የሚወሰን ጉዳይ ነው። ቢሆንም ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት የመስከረም 2002 ንቁ! ገጽ ከ18-20 ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ስድሳ ዘጠኝ ከመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶች ቆንጆ ቁመና ነው የሚሉትን የሚወስኑላቸው በመጽሔቶች ላይ የሚወጡ ሞዴሎች ናቸው
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማስታወቂያዎች ሰዎች አካላዊ ውበትን በተመለከተ ባላቸው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች ከባድ በሆነ የመልክ ማሻሻያ ቀዶ ሕክምና ምክንያት በራሳቸው ላይ ጉዳት አድርሰዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች ተፈላጊ ቁመናና መልክ እንዲኖራቸው ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ