በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች ችግራቸውን ቢነግሩኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ሌሎች ችግራቸውን ቢነግሩኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ሌሎች ችግራቸውን ቢነግሩኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

“በምማርበት ትምህርት ቤት አንዲት ልጅ አለች። ወላጆቿ ሊፋቱ በሂደት ላይ ናቸው፤ እርሷ ደግሞ የፈተና ውጤቷ እያሽቆለቆለ ነው። ስለቤተሰቦቿ ችግር ብዙ ጊዜ ትነግረኛለች።”—ጃን፣ የ14 ዓመት ልጅ

“አብራኝ የምትማር አንዲት ልጅ ከአንድ ልጅ ጋር ወሲብ እንደፈጸመች ነገረችኝ። ማርገዟን ስታውቅ ጽንሱን አስወረደች፤ ይህን ሁሉ ደግሞ ወላጆቿ ፈጽሞ አያውቁም።”—ማይራ፣ የ15 ዓመት ልጅ

ከጓደኛህ ወይም አብሮህ ከሚማር ልጅ ጋር እያወራችሁ ነው እንበል። በድንገት ችግሩን “ያራግፍብህ” ጀመር። * ምናልባት ችግሩ ልብስን፣ ገንዘብን፣ መልክን፣ እኩዮችንና የፈተና ውጤትን የሚመለከት የወጣቶች የተለመደ ችግር ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በጣም አሳሳቢና የሚያስጨንቅ ችግር አጋጥሞት ይሆናል።

በዩናይትድ ስቴትስ ያለው ሁኔታ እንደሚያሳየው ወጣቶችን የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በጣም አሳሳቢ ናቸው። ኒውስዊክ መጽሔት በዘገበው መሠረት “ከወጣቶች መካከል 8 በመቶ የሚያህሉትና ከልጆች ደግሞ 2 በመቶ የሚሆኑት (ገና የ4 ዓመት ልጆችን ጨምሮ) የመንፈስ ጭንቀት ምልክት እንዳለባቸው የአእምሮ ጤና ብሔራዊ ተቋም ገምቷል።” ሌላ ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ “ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ከሆኑ 1,000 ሴቶች መካከል 97ቱ (በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አንድ ሚሊዮን አሜሪካውያን) በየዓመቱ ያረግዛሉ። ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ማለትም 78 በመቶ የሚሆኑት ያልታሰቡ ናቸው።” ከዚህ ሌላ ደግሞ በጠብ በሚታመሱ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉ። በሺዎች የሚቆጠሩት የአካላዊ ወይም የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ ከተቃረቡት መካከል ከግማሽ የሚበልጡት የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ሰክረው የሚያውቁ ናቸው። በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ደግሞ ከአመጋገብ መዛባት ችግር ጋር የሚኖሩ ናቸው።

ብዙ ወጣቶች ችግራቸውን የሚያዋዩትና ምስጢራቸውን የሚያካፍሉት ሰው ማግኘት መፈለጋቸው ምንም አያስደንቅም! ብዙውን ጊዜ ደግሞ መጀመሪያ ማናገር የሚቀናቸው እኩያቸውን ነው። ታዲያ አንድ እኩያህ ምሥጢሩን ሊያካፍልህ ቢፈልግ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የመጽሐፍ ቅዱስ ሰው ከሆንክ ምሥጢራቸውን ሊያካፍሉህ መፈለጋቸው ሊያስገርምህ አይገባም። ክርስቲያኖች በጠባያቸው “አርአያ” እንዲሆኑና ምክንያታዊነት እንዲያሳዩ መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል። (1 ጢሞቴዎስ 4:12፤ ፊልጵስዩስ 4:5) ስለዚህ በእምነት የማይዛመዱህን ጨምሮ አንዳንድ ወጣቶች ምሥጢራቸውን ሊያካፍሉህ ይፈልጉ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ደግሞም የተነገረህ ችግር ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ቢሰማህስ?

ጥሩ አድማጭ መሆን

መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:7) አንድ ወጣት ችግር አጋጥሞት ለአንተ ሊነግርህ ሲፈልግ አብዛኛውን ጊዜ የተሻለው አማራጭ ማዳመጥ ይሆናል። ደግሞም “የድኾችን ጩኸት” ላለመስማት ጆሮ መዝጋት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ነገር ነው። (ምሳሌ 21:13) ይህ ልጅ ለአንተ ችግሩን ገልጦ ለመንገር ድፍረት ጠይቆበት ይሆናል። የሚነግርህን ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆንህ ለመናገር እንዲቀልለው ሊያደርግ ይችላል። “ብዙውን ጊዜ ግለሰቡ ሲናገር ዝም ብዬ አዳምጣለሁ” በማለት ሃይረም የተባለ ክርስቲያን ወጣት ተናግሯል። “የሚረብሸውን ነገር ሁሉ እንዲነግረኝ ካደረግሁ በኋላ ላጽናናውና ላበረታታው እሞክራለሁ።” ቪንሰንት የሚባል ወጣትም በተመሳሳይ “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚፈልጉት ተናግረው እንዲወጣላቸው ነው” በማለት ገልጿል።

ስለዚህ ችግሩን የሚነግርህም ልጅ መፍትሔ እንድትሰጠው አይጠብቅ ይሆናል። የሚፈልገው በጥሞና የሚያዳምጠው ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አዳምጠው! ችግሩን በሚነግርህ ጊዜ ትኩረትህ በሌላ ነገር እንዳይሰረቅ ወይም ሳያስፈልግ እንዳታቋርጠው ተጠንቀቅ። አጠገቡ ተቀምጠህ ማዳመጥህ በራሱ ትልቅ እርዳታ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ማድረግህ በእርግጥ አሳቢ መሆንህን ያሳያል።

እንዲህ ሲባል ታዲያ በምላሹ ምንም ነገር መናገር የለብህም ማለት ነው? ይህ በአብዛኛው የሚመካው በችግሩ ዓይነት ላይ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አሳቢነትና ደግነት የታከለበት ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው። (ምሳሌ 25:11) ለምሳሌ ያህል አንድ የምታውቀው ልጅ የሚያሳዝን ነገር ደርሶበት ከሆነ የሐዘኑ ተካፋይ መሆንህን መግለጽ በጣም ጥሩ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 12:15) ምሳሌ 12:25 “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። ምናልባት የሚያስፈልገው ጥቂት የማበረታቻ ቃል ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ የገጠመውን ችግር በተሳካ ሁኔታ ሊወጣው እንደሚችል ያለህን እምነት ግለጽ። “ለምን እንዲህ እንደተሰማህ ይገባኛል” ወይም “ይህ ችግር ስለደረሰብህ አዝናለሁ” ብለህ መናገርህ ከልብ እንደምታስብለትና ልትረዳው እንደምትፈልግ እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችላል።

ይሁን እንጂ ምሳሌ 12:18 “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” በማለት ያስጠነቅቃል። “ይሄማ ቀላል ነው” ወይም “በቃ እርሳው” አሊያም “እንዲህ ሊሰማህ አይገባም” እንደሚሉት ያሉ አስተያየቶችን ከመሰንዘር መቆጠብ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ቀልድ በመናገር ችግሩን ቀላል ለማስመሰል እንዳትሞክር ተጠንቀቅ። እንዲህ ብታደርግ ምሥጢሩን የሚያካፍልህ ልጅ ለስሜቱ እንደማታስብ ሊሰማው ይችላል።—ምሳሌ 25:20

ችግሩን ካዳመጥክ በኋላ ምን እንደምትለው ግራ ቢገባህስ? ሐቀኛ ሁን። ምን ማለት እንዳለብህ ግራ እንደገባህ ንገረው፤ ይሁንና አሁንም ለመርዳት ፈቃደኛ መሆንህን አስረዳው። “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብለህ ጠይቀው። አዎን፣ ሸክሙን ለማቃለል ሊጠቅሙት የሚችሉ ነገሮች ልታደርግ ትችላለህ።—ገላትያ 6:2

ወዳጃዊ ምክር መስጠት

ጓደኛህ ምክር እንደሚያስፈልገው ቢሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እርግጥ ነው፣ አንተም ወጣት ስለሆንክ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ተሞክሮ ይጎድልሃል። (ምሳሌ 1:4) ስለዚህ ለእያንዳንዱ ችግር ምክር ለመስጠት ብቁ ላትሆን ትችላለህ። ይሁን እንጂ መዝሙር 19:7 “የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል” ይላል። አዎን፣ ተሞክሮ የሚጎድልህ ቢሆንም ምክር የሚያስፈልገውን ጓደኛህን የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማካፈል የሚበቃ እውቀት ሊኖርህ ይችላል። (ምሳሌ 27:9) መመሪያ እየሰጠኸው እንዳለ ሆኖ እንዳይሰማው ጥንቃቄ በማድረግ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነጥቦች አካፍለው። ከጉዳዩ ጋር የሚዛመዱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ እንደሆኑ እርግጠኛ ካልሆንክ ጥቂት ምርምር አድርግ። “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የተሰኘው የዚህ መጽሔት ዐምድ ለበርካታ ዓመታት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ ምክሮች ይዞ ወጥቷል። ሌላው ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተሰኘው መጽሐፍ ነው። *

ምናልባት የራስህን ተሞክሮ ብታካፍለው በጣም ሊጠቅመው ይችል ይሆናል። አንዳንድ ተግባራዊ ምክሮች ልትሰጠው ትፈልግ ይሆናል። የግል አመለካከትህን እንዲቀበል ሳታስገድደው አንተን የረዳህ ምን እንደሆነ ልታስረዳው ትችላለህ። (ምሳሌ 27:17) ይሁንና የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ የተለያየ እንደሆነ አስታውስ። አንተን የጠቀመህ ምክር ለሌላው ላይሠራ ይችላል።

ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች

ይሖዋን የማይፈሩ ወይም ክርስቲያናዊ የአቋም ደረጃዎችን የማያከብሩ ወጣቶችን ችግር በማዳመጥ ብዙ ጊዜ አታጥፋ። የሚያጋጥማቸው አብዛኛው ችግር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማይስማማ አኗኗራቸው ሳቢያ የመጣ ሊሆን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር የሚንቁ ሰዎችን ለመርዳት መጣር ለሁለታችሁም ከንቱ ድካም ሊሆንባችሁ ይችላል። (ምሳሌ 9:7) በተጨማሪም ሳያስፈልግ አልባሌና ጸያፍ ለሆኑ ንግግሮች ልትጋለጥ ትችላለህ። (ኤፌሶን 5:3) ስለዚህ የሚነግርህን ነገር መስማት ከከበደህ ምንም ልትረዳው እንደማትችል ወይም እንዲህ ባለ ርዕስ ላይ መነጋገር ደስ እንደማይልህ ለመናገር ድፍረት ይኑርህ።

ምሥጢሩን ሊያካፍልህ የሚፈልገው ተቃራኒ ፆታ ያለው ሰው ከሆነ ተጠንቀቅ። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልብ አታላይ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቃል። (ኤርምያስ 17:9) ከተቃራኒ ፆታ ጋር መቀራረብ የፍቅር ስሜት ሊቀሰቅስና አልፎ ተርፎም ወደ ፆታ ብልግና ሊያመራ ይችላል።

በተጨማሪም ለማንም እንደማትናገር ቃል አትግባ። ችግሩን የሚነግርህ ወጣት አንተ ልትሰጠው ከምትችለው በላይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ለመቀበል ትሕትና ይኑርህ።—ምሳሌ 11:2

የሌሎች እርዳታ በሚያስፈልግበት ጊዜ

አብዛኛውን ጊዜ ጓደኛህን እንዴት መርዳት እንደምትችል ለማወቅ አንተ ራስህ እርዳታ ማግኘትህ በጣም ጥሩ ይሆናል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ማይራ “እውነት ለመናገር የትምህርት ቤት ጓደኛዬን እንዴት ልረዳት እንደምችል የማውቀው ነገር አልነበረም። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ከአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር ተነጋገርኩና እንዴት ልረዳት እንደምችል ግሩም ምክር ሰጠኝ” ብላለች። አዎን፣ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሊረዱህ የሚችሉ ተሞክሮ ያላቸው ወንዶች አሉ። (ኤፌሶን 4:11, 12) ሽማግሌው ማይራ ልጅቷን ለወላጆቿ እንድትናገር እንድታበረታታት ሐሳብ አቀረበላት። ልጅቷም የማይራን ምክር ተቀበለች። ማይራ እንዲህ ትላለች:- “የልጅቷ ሁኔታ ተሻሽሏል። አሁን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለች።”

ምሥጢር የነገረህ አንድ የእምነት አጋርህ ቢሆንስ? በምትችለው ሁሉ ልትረዳው እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። (ገላትያ 6:10) ስለዚህ ይሖዋ ካወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እየራቀ እንደሆነ ከተሰማህ ‘እውነቱን ከመንገር’ ወደኋላ አትበል። (ኤፌሶን 4:25) ሐቁን ተናገር፤ ሆኖም ራስህን አታመጻድቅ። በግልጽ ለመናገር ፈቃደኛ መሆንህ እውነተኛ ወዳጅ መሆንህን ያሳያል።—መዝሙር 141:5፤ ምሳሌ 27:6

ጓደኛህ ከእውነት እየራቀ እንዳለ ሥጋት ካደረብህ ከወላጆቹ፣ ከሽማግሌ ወይም በአክብሮት ከሚያየው ጎልማሳ ክርስቲያን እርዳታ እንዲሻ ማበረታታትህ በጣም አስፈላጊ ነው። የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ለማንም እንዳልተናገረ ከተረዳህ ያለበትን ሁኔታ አንተ ለአንድ ሰው መንገር ይኖርብሃል። (ያዕቆብ 5:13-15) እንዲህ ማድረግ ድፍረት ይጠይቅብህ ይሆናል፤ ይሁንና ለጓደኛህ እንደምታስብለትና መልካም እንደምትመኝለት ያሳያል።

እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የሰውን ሁሉ ችግር እንድትፈታ አይጠብቅብህም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ችግሩን ሲነግርህ ምንም ማድረግ እንደማትችል ሊሰማህ አይገባም። ያገኘኸውን ክርስቲያናዊ ሥልጠና ተጠቀምበት፤ እንዲሁም ‘የምንጊዜም ወዳጅ’ መሆንህን አረጋግጥ።—ምሳሌ 17:17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ነገሩን ላለማወሳሰብ ሲባል ችግር ያለበትን ልጅ በወንድ ፆታ አድርገነዋል። ርዕሱ ግን ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራል።

^ አን.15 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ጊዜ ችግር ላይ የወደቀ ጓደኛህን ሌሎች እንዲረዱት ለማድረግ ትገደድ ይሆናል