ትልቅ ገንዘብ የሚገኝበት አገር
ትልቅ ገንዘብ የሚገኝበት አገር
ጉዋም የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በጣም ሰፊ በሆነው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የያፕ ደሴቶች ይገኛሉ። በጣም የሚያምሩትና ተስማሚ የአየር ጠባይ ያላቸው እነዚህ የደሴቶች ስብስብ ጸጥታ የሰፈነበት አካባቢ ለሚፈልጉ መንገደኞች አስደሳች የእረፍት ቦታ ናቸው። ይሁንና ጎብኚዎቹን በጣም የሚያስገርማቸው ነገር ነዋሪዎቹ ገንዘባቸውን በየጎዳናው ማስቀመጣቸው ነው። ገንዘቡ ደግሞ እንዲህ የዋዛ አይደለም!
በደሴቶቹ ላይ በሕንፃዎች አጠገብና በመንገድ ዳር ጠፍጣፋ ክብ ድንጋይ መመልከት የተለመደ ነገር ነው። ይህ ክብ ድንጋይ የያፕ ነዋሪዎች የሚጠቀሙበት ገንዘብ ሲሆን በቋንቋቸው ራኢ ብለው ይጠሩታል። አንዳንዶች ገንዘቡን ቤታቸው የሚያስቀምጡ ቢሆንም አብዛኞቹ ሰዎች ግን መንደር ውስጥ የሚገኙ “ባንኮችን” ይጠቀማሉ። በእነዚህ ተቋሞች ውስጥ የታጠቁ ጠባቂዎችም ሆኑ ደንበኞችን የሚያስተናግዱ ገንዘብ ከፋዮች የሉም። ሌላው ቀርቶ ቦታው ላይ ቤት እንኳን አታገኙም። እነዚህ “ባንኮች” ገንዘብ የሚያስቀምጡት ካዝና ውስጥ ሳይሆን ሜዳ ላይ ነው። በቦታው የኮኮናት ዛፎች አሊያም ግንብ ተደግፈው የተቀመጡ መሃል ላይ ቀዳዳ ያላቸው ብዙ ክብ ድንጋዮች ይገኛሉ። እነዚህ ድንጋዮች መሃል ለመሃል ርዝመታቸው ወደ አራት ሜትር ገደማ ሲሆን ክብደታቸው ደግሞ ከአምስት ቶን በላይ ሊመዝን ይችላል።
በምትኖርበት አገር ሣንቲሞች በኪስህ ይዘህ መንቀሳቀስ ትችል ይሆናል። በያፕ ግን ከትልቅነታቸው የተነሳ መኪና ውስጥ እንኳ ማስገባት አይቻልም። ከ1931 ወዲህ እነዚህን የድንጋይ ገንዘቦች መሥራት አቁመዋል። ይሁንና አሁንም ድረስ በደሴቲቷ ውስጥ ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ ያገለግላል። ይህ አስገራሚ ገንዘብ ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት ነው?
በብዙ ልፋት የተገኘ ገንዘብ
በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው በጥንት ጊዜ ከያፕ ደሴት የተነሱ ተጓዦች ፓሉ የተባለች ደሴት ላይ ሲደርሱ አንዳንድ የሚያማምሩ ድንጋዮች አገኙ። እነዚህን ድንጋዮች ወደ ያፕ ይዘዋቸው ከመጡ በኋላ ሕዝቡ የመገበያያ ገንዘብ አድርጎ ሊጠቀምባቸው ተስማማ። ከዚያም ድንጋዮቹን ጠርበው የሙሉ ጨረቃ ቅርጽ ያስያዟቸው ሲሆን መሃል ላይ ደግሞ ቀዳዳ አበጁላቸው።
ያፖች ገንዘቡን ለመሥራት የሚጠቀሙበትን ድንጋይ በጥንቃቄ ነበር የሚመርጡት። ዛሬ አራጎኒት እና ካልሳይት ብለን የምንጠራቸውን ማዕድናት ለሥራቸው ይመርጡ ነበር። አራጎኒት በከርሰ ምድር ውስጥ ተከማችቶ ከመገኘቱም በተጨማሪ በዕንቁ ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ሲሆን ካልሳይት ደግሞ የእብነ በረድ ዋነኛ ክፍል ነው። በጥንቃቄ ከተቀረጹ ሁለቱም ድንጋዮች በጣም ያምራሉ፤ ነገር ግን አንዳቸውም በያፕ አይገኙም። ስለዚህ ያፖች ድንጋዮቹን ለማግኘት ወደ ፓሉ መመላለሳቸውን ቀጠሉ። ፓሉ የምትገኘው ከያፕ በስተ ደቡብ ምዕራብ 400 ኪሎ ሜትር ርቃ ነው፤ ጉዞው አምስት ቀን የሚፈጅ ከመሆኑም ሌላ በታንኳ አደገኛ ባሕር ማቋረጥን ይጠይቃል።
ፓሉ ውስጥ ያፖች ከአካባቢው አለቃ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ድንጋይ የመፍለጡን ሥራ ተያያዙት። ኋላቀር የሆኑ የእጅ መሳሪያዎች በመጠቀም ከመሬት ሥር ካሉ ዋሻዎች ውስጥ ጠፍጣፋ ድንጋዮችን ፈልጠው ካወጡ በኋላ በመጥረብ ክብ ቅርጽ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። አንድን የድንጋይ ገንዘብ መዶሻና መሮ በመጠቀም ለመቅረጽ ወራት አንዳንዴም ዓመታት ሊወስድ ይችላል!
ቀዳዳዎች ያስፈለጉበት ምክንያት ድንጋዩ ተጠርቦ ካለቀ በኋላ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለማድረስ ለመሸከሚያነት የሚያገለግል ጠንካራ አጣና በውስጣቸው ለማሳለፍ ነው። ከዚያ በኋላ አዲሱ ገንዘብ ጀልባ ወይም ታንኳ ላይ ይጫናል። ድንጋዩ በጣም ትልቅ ከሆነ ደግሞ ድንጋዩን ውኃው ውስጥ አቁመው ዙሪያውን ትልቅ ታንኳ ይሠሩለታል። በንፋስ እየታገዙና በኃይል እየቀዘፉ በታንኳ ላይ የተጫነውን ገንዘብ ይዘው ወደ ያፕ ያመራሉ።
ይህ ሁሉ ሥራ የሚከናወነው በእጅ ሲሆን ሂደቱም በጣም አደገኛ ነው። ትላልቅ የድንጋይ ስባሪዎችን ለመፍለጥና ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ሲታገሉ የቆሰሉና የሞቱ ብዙዎች ናቸው። ወደ ያፕ የሚደረገው የመልስ ጉዞም ቢሆን የራሱ አደጋ አለው። ያፕና ፓሉ አካባቢ በውቅያኖሱ ወለል ላይ የሚታዩት የድንጋይ ገንዘቦች አንዳንዶቹ ድንጋዮችም ሆኑ በማጓጓዙ ሥራ የተሰማሩት ሰዎች በሰላም ያፕ መድረስ አለመቻላቸውን ያሳያሉ። ይሁን እንጂ ያ ሰጥሞ የቀረ ገንዘብ ከያፕ ነዋሪዎች መካከል የአንዱ ነው። ዋጋውም ቢሆን በደሴቶቹ ላይ ካሉት የድንጋይ ገንዘቦች በምንም አይተናነስም።
ዋጋው ምን ያህል ነው?
የንግድ ስምምነት ከተከናወነ በኋላ ራኢው ሌላ ሰው እጅ ሲገባ አብዛኛውን ጊዜ አዲሱ ባለቤት ድንጋዮቹን እዚያው የነበሩበት ቦታ ትቷቸው ይሄዳል። ብዙዎቹ አሁን በተቀመጡበት ቦታ በርካታ አሥርተ ዓመታት ያስቆጠሩ ሲሆን የሚገኙት ደግሞ ከባለንብረቱ መኖሪያ በጣም ርቀው ነው። ይሰረቅብኝ ይሆን የሚል ስጋት የለም።
አንድ ሰው ድንጋዩን ለመስረቅ ቢያስብ እንኳን ተሸክሞ ለመሄድ የሚያስችል ጉልበት የሚያስፈልገው
ከመሆኑም ሌላ ዓይን አውጣ መሆን አለበት። በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች እያንዳንዱ ክብ ድንጋይ የማን እንደሆነ ከማወቃቸውም በላይ ለባለቤትነት መብት ትልቅ ግምት ስላላቸው ከሸክሙ ይልቅ አለማፈሩ ይከብዳል።
የአንድ የድንጋይ ገንዘብ ዋጋ የሚለካው በምንድን ነው? በቅድሚያ መጠኑን፣ ተፈጥሯዊ ውበቱን እንዲሁም ጥራት ባለው መንገድ የተቀረጸ መሆኑን ታያለህ። ቀጥሎ ደግሞ ታሪኩን ታጤናለህ። ምን ያህል ዓመት ቆይቷል? ድንጋዩን ፈልጦ ማውጣትና ቅርጽ ማስያዝ በጣም አስቸጋሪ ነበር? ወደ ያፕ ሲመጣ በሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ ወይም የሞተ ሰው ነበር? በመጨረሻም ሻጮቹ በማኅበረሰቡ ወስጥ ያላቸው ቦታ ምን ይመስላል? በተራ ሰው እጅ ከሚገኝ የድንጋይ ገንዘብ ይልቅ በአካባቢው አለቃ እጅ የሚገኘው የበለጠ ዋጋ ያወጣል።
በ1960 አንድ የውጭ አገር ባንክ መሃል ለመሃል ርዝመቱ አምስት ጫማ የሆነ አንድ የድንጋይ ገንዘብ በገዛበት ወቅት የዚህ ድንጋይ ታሪክ በሌላውም ዓለም ተሰማ። እንዲያውም ከ1880ዎቹ ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነበር። በአንድ ወቅት ለግንባታ ሠራተኞች ክፍያ ሆኖ አገልግሏል። በሌላ ጊዜ ደግሞ የአንድ መንደር ነዋሪዎች ከአጎራባች መንደር የመጡ ነዋሪዎች ላሳዩት ለየት ያለ ውዝዋዜ በሽልማት መልክ ተሰጥቷል። ከዚያም አንድ ሰው ለቤት ክዳን የሚሆን ቆርቆሮ ለመግዛት ተጠቅሞበታል። እነዚህ ሁሉ ግብይቶች የተፈጸሙት ድንጋዩ መጀመሪያ ከነበረበት ቦታ ሳይንቀሳቀስና ምንም ዓይነት በጽሑፍ የሠፈረ ውል ሳይኖር ነው። የገንዘቡን ባለቤትና ታሪክ መላው የያፕ ነዋሪ ያውቀዋል።
የገንዘቡ ዋጋ ሁልጊዜ በመጠኑ አይወሰንም
በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ራኢ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል በጣም ብርቅና ውድ ከመሆኑ የተነሳ የሚገኘው በአካባቢው አለቆች እጅ ብቻ ነበር። ይሁንና በ1800ዎቹ ማብቂያ ላይ የተለያዩ ከብረት የተሰሩ መሣሪያዎችና የጭነት መርከቦች ትላልቅ የሆኑትን ጨምሮ ብዙ የድንጋይ ገንዘቦች ለመቅረጽና ለማጓጓዝ አስችለዋል። አዲስ የተሰሩት ድንጋዮች ከድሮዎቹ በትልቅነት የሚበልጡ ቢሆንም በዋጋ ግን ያነሱ ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት በጣም አድካሚ በሆነው በባህላዊው መንገድ የተሠሩ ባለመሆናቸው ነው።
በ1929 በተደረገ ቆጠራ 13,281 የድንጋይ ገንዘቦች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን ይህም በደሴቲቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች ቁጥር ይበልጣል! የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መከሰት በቁጥሩ ላይ ለውጥ አስከትሏል። ወታደሮች አብዛኛውን የድንጋይ ገንዘብ በመውረስ የተወሰነውን ሰብረው ለአውሮፕላን መንደርደርያና ለምሽግ መሥሪያ ተጠቀሙበት። የተረፈው ግማሽ ያህሉ ብቻ ነበር። ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ቅርሶችን የሚሰበስቡ ድርጅቶችና በትርፍ ጊዜያቸው ቅርሶችን መሰብሰብ የሚያስደስታቸው ሰዎች ደግሞ ብዙዎቹን ድንጋዮች ወስደዋል። በዛሬው ጊዜ መንግሥት እነዚህን የድንጋይ ገንዘቦች እንደ ቅርስ በማየት ጥበቃ ያደርግላቸዋል።
ያፕ ውስጥ ገንዘብ በቀላሉ አይታፈስም ወይም መንገዶቹ ሁሉ ወርቅ የተነጠፈባቸው አይደሉም። ይሁንና ሰዎች ዛሬም ቢሆን ገንዘባቸውን ማንም ሊያየው በሚችል ቦታ ላይ ያስቀምጡታል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ካርታዎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ጃፓን
የፓስፊክ ውቅያኖስ
ፊሊፒንስ
ሴይፓን
ጉዋም
ያፕ
ፓሉ
[ምንጭ]
ሉል:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የድንጋይ ገንዘብ “ባንክ”
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ በያፕ የሚገኙ የድንጋይ ገንዘቦች ከአምስት ቶን በላይ ይመዝናሉ