ከልክ በላይ ለመልክ መጨነቅ
ከልክ በላይ ለመልክ መጨነቅ
ማርያ * ኑሮ የተሳካላትና ጥሩ ቤተሰብ ያላት ወጣት ሴት ነች። ቢሆንም ደስታ የራቃት ናት። ለምን? የመልኳ ጉዳይ ቅር ያሰኛታል። ቤተሰቦቿ ሊያግባቧት ቢሞክሩም እሷ ግን ጥሩ መልክ የለኝም ብላ ስለምታስብ ትጨነቃለች።
ሆሴ ከጨዋ ቤተሰብ የተወለደና የተመቻቸ ኑሮ ያለው በመሆኑ ደስተኛ ሊሆን የሚገባው ሰው ነው። ይሁን እንጂ ፈጽሞ ሚስት ሊያገኝ እንደማይችል ሆኖ ይሰማዋል። ለምን? ሆሴ ጥሩ መልክ እንደሌለው፣ እንዲያውም አስቀያሚ እንደሆነ ይሰማዋል። መቼም ቢሆን ደህና ሴት ልትወደኝ አትችልም ብሎ ደምድሟል።
የስምንት ዓመቱ ሉዊስ ከሰው ጋር የሚግባባና ትምህርት ቤት መሄድ የሚወድ ልጅ ነው። ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር መጫወት ያስደስተዋል። ይሁን እንጂ ጓደኞቹ በመልኩ ስለሚያሾፉበት ብዙ ጊዜ ያለቅሳል። ወፍራም ነህ ብለው ይቀልዱበታል።
እነዚህን ለአብነት ያህል ጠቀስን እንጂ የመልካቸው ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው በጣም ብዙ ናቸው። ማርያ፣ ሆሴና ሉዊስ ያለባቸው ችግር በራስ አለመተማመን ብቻ ነው ሊባል አይቻልም። ማንም ቢሆን በመልኩ ወይም በቁመናው ምክንያት መጠላት ወይም መገለል አይፈልግም።
ይሁን እንጂ የምንኖርበት ማኅበረሰብ ለመልክ የሚሰጠው ግምት በጣም የተጋነነ ነው። እንዲያውም ስኬት በመልክ ላይ የተመካ ይመስላል። ለምሳሌ ጥሩ መልክ ያላቸው ሰዎች ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። የላቲን አሜሪካና የካረቢያን ሴቶች የጤና ቅንጅት ዳይሬክተር የሆኑት ፒላር ሙሪያዳስ “ሴቶች የተሳካላቸው እንዲሆኑ ከሚያስፈልጉት ብቃቶች አንዱ ጥሩ መልክ ነው” ብለዋል። ዶክተር ላውራ ማርቲኔዝ እንደሚሉት ደግሞ “ሥራ በማግኘት ረገድ መልክ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው” ሴቶች አሳምረው ያውቃሉ።
እርግጥ፣ ወንዶችም ቢሆኑ ጥሩ የሚባለው መልክና ቁመና እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ጥሩ መልክ ወይም ቁመና እንዲኖራቸው ራሳቸውን በረሐብ እስከ መቅጣት ወይም ከፍተኛ ሕመምና ስቃይ የሚያስከትል ሕክምና እስከ መውሰድ የሚደርሱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በርካታ ናቸው። ታዲያ ለመልክ ይህን ያህል መጨነቅ ተገቢ ይሆናል? ሊያስከትል የሚችለውስ አደጋ ይኖራል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 ስሞቹ ተለውጠዋል
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መልክና ቁመና አንድ ሰው ሊያገኝ የሚችለውን አጋጣሚ ሊነካበት ይችላል