በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ሻርክ የሚያሸሽ መሣሪያ

ብዙ ሰዎች ውቅያኖስ ውስጥ መዋኘት ይፈልጉና ሻርክ ቢያጋጥመንስ በሚል ፍርሃት ይህን ከማድረግ ይቆጠባሉ። ይሁን እንጂ የደቡብ አፍሪካው የናታል ሻርክ ቦርድ ሻርኮችን የሚያሸሽ መሣሪያ ፈልስፏል። ዊክኤንድ ዊትነስ የተባለው የክዋዙሉ ናታል ጋዜጣ ቦርዱ “መሣሪያው የሚያመነጨው የተለየ ዓይነት የኤሌክትሪክ ሞገድ በሻርኩ አፍንጫ ላይ የሚገኙ ሕዋሶችን ያስቆጣል” በማለት ዘግቧል። ቦርዱ የሠራው መሣሪያ ፕሮቴክቲቭ ኦሽኒክ ዲቫይስ የሚባል ሲሆን ሻርኩ እየቀረበ በሄደ መጠን መሣሪያው በጣም የሚያሳምም ሞገድ ይልክበታል። ሕመሙን መቋቋም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ “ሻርኩ ከአካባቢው ይሸሻል።” አንድ የአውስትራሊያ ኩባንያ ይህንኑ የሚመስል መሣሪያ ለዋናተኞችና ለባሕር ላይ ተንሸራታቾች መገልገያ ይሠራል። ይህ መሣሪያ እግር ላይ የሚታሰር ሲሆን መሣሪያውን ባደረገው ሰው አካባቢ “ከሻርክ ነፃ የሆነ ቀጠና” እንዲፈጠር ያደርጋል። ቢሆንም የመሣሪያው አምራች ኩባንያ “ሁሉንም ሻርኮች በዚህ መንገድ ማባረር ይቻላል ብሎ ዋስትና መስጠት አይቻልም” በማለት ያስጠነቅቃል።

አብዛኛውን ጊዜ በመርዝ የሚጠቁት ትላልቅ ሰዎች ናቸው

የብሪቲሽ ኮሎምቢያ የመድኃኒትና የመርዝ መረጃ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዴብራ ኬንት “ሰዎች ስለ መርዝ ሲያስቡ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጡት ትናንሽ ልጆች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ኬንት “አብዛኛውን ጊዜ በመርዝ ምክንያት የሚሞቱት ጎረምሶችና ትላልቅ ሰዎች ናቸው” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። ዘ ቫንኩቨር ሰን እንደሚለው ከሆነ ትላልቅ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መርዝ የመጠጣት አደጋ የሚያጋጥማቸው “እንደ ውሃ ጠርሙስ ባለ ምልክት ባልተደረገበት ዕቃ ውስጥ የተቀመጠ መርዝ በመጠጣት ነው።” አንድን ነገር ከመውሰዳቸው በፊት መብራት ቢያበሩና በዕቃው ላይ የሠፈረውን ጽሑፍ ቢመለከቱ ከአደጋ ሊድኑ ይችሉ የነበሩ ሰዎችም አሉ። ሰን እንደሚለው ከሆነ “አዋቂዎችን ለሞት ከሚዳርጉ አሥር ዋነኛ ምክንያቶች መካከል በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው መርዝ መውሰድ ነው።”

ቴሌቪዥን ለጨቅላ ሕፃናት አደገኛ ነው

በሜክሲኮ ሲቲ የሚታተመው ዘ ሄራልድ “ቴሌቪዥን የሚመለከቱ ሕፃናት ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ትኩረታቸውን የማሰባሰብ ችግር” እንደሚያጋጥማቸው ዘግቧል። ሪፖርቱ አንድ ዓመትና ሦስት ዓመት በሆናቸው በሁለት የተከፈሉ 1,345 ሕፃናት ላይ የተደረገና ፔድያትሪክስ በተባለ የሕክምና መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት ይጠቅሳል። በጥናቱ መሠረት ሕፃናቱ በየቀኑ ቴሌቪዥን በማየት የሚያሳልፉት አንድ ሰዓት ሰባት ዓመት ሲሆናቸው ትኩረት ለማሰባሰብ ችግር የመጋለጣቸውን ዕድል 10 በመቶ ከፍ ያደርገዋል። ተመራማሪዎቹ “በአብዛኞቹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩት ከወትሮ የተለዩ በጣም ፈጣን እንቅስቃሴዎች የጨቅላ ሕፃናትን የአእምሮ እድገት ያዛባሉ” ብለው ያምናሉ። የጥናቱን ጽሑፍ ያዘጋጁት ዶክተር ዲሚትሪ ክሪስታኪስ “ሕፃናት ቴሌቪዥን ባያዩ ጥሩ የሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ቴሌቪዥን መመልከት አለልክ መወፈርንና ጠበኝነትን የመሳሰሉ ችግሮችን እንደሚያስከትል ሌሎች ጥናቶች አመልክተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሣቅ ጥሩ መድኃኒት ነው

“የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ሐኪሞች ሣቅ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግበትን ተጨማሪ ምክንያት አግኝተዋል” በማለት ዩሲ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር ዘግቧል። “አስቂኝ ሥዕላዊ ታሪኮችን የሚያነቡ ሰዎችን የአእምሮ እንቅስቃሴ ከተከታተሉ በኋላ ቀልድና ሣቅ የደስታ ስሜት አስተላላፊ የሆነውን የአንጎል ክፍል እንደሚቀሰቅሱ ተገንዝበዋል።” አደንዛዥ ዕፆችም የሚቀሰቅሱት ይህን የአንጎል ክፍል ነው። ዌልነስ ሌተር “ሣቅ ውጥረት ይቀንሳል፣ አእምሮን ያድሳል፣ መንፈስንም ያነቃቃል” ይላል። በተጨማሪም ሣቅ ሆርሞን የማመንጨት ኃይላችንንና የልባችንን ምት ከፍ ከማድረጉም በላይ የደማችንን ዝውውርና የጡንቻዎቻችንን ጥንካሬ ከፍ ያደርጋል። “በእርግጥም ከልብ የመነጨ ሣቅ እንደ ጥሩ የአካል እንቅስቃሴ ይቆጠራል” ይላል ዌልነስ ሌተር። “ብዙ በመሣቅ ብዙ ካሎሪ አቃጥሎ ውፍረት መቀነስ አይቻል እንጂ ሌሎች ብዙ ጥቅሞች ማግኘት ይቻላል።”

ፈንጂ ጠቋሚ ዕፅዋት

ኤል ፓይስ የተባለ የስፓኝ ጋዜጣ “አንድ የዴንማርክ ባዮኢንጂነሪንግ ኩባንያ ፈንጂ የተቀበረበት መሬት ላይ ከተተከለ ቅጠሉ ቀይ የሚሆን አንድ ተክል አግኝቷል” ሲል ዘግቧል። ፈንጂ ጠቋሚ የሆነው ይህ ተክል አራቢዳፕሲስ ታልያና በሚባል ሳይንሳዊ ስያሜ የሚታወቅ ሲሆን “ለፈንጂ መስሪያነት ከሚያገለግሉት ዋነኛ ንጥረ ነገሮች አንዱ ከሆነው ከናይትሮጅን ዳይኦክሳይድ” ጋር ሲገናኝ የቅጠሉ ቀለም ይቀየራል። “ይህ ንጥረ ነገር በሥሮቹ አማካኝነት ወደ ተክሉ ሲገባ በሚፈጠረው ኬሚካላዊ ለውጥ አማካኝነት አንቶሳያኒን የተባለ የተፈጥሮ ቀለም ይፈጠራል።” ሳይመን ኦስተርጋር የተባሉት የባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ፕሬዚዳንት “የሚያስፈልገው ዘሩን ፈንጂ የተቀበረበት አካባቢ መዝራት፣ ከዚያም ከአምስት ሳምንት በኋላ ተመልሶ ፈንጂዎቹን ማምከን ነው” ብለዋል። ይህ ፈንጂ ጠቋሚ ተክል በስፋት ሥራ ላይ ቢውል በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ከሞት ማዳን ይቻል ነበር ብለዋል ኦስተርጋር። በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉ ጦርነቶች ምክንያት 100 ሚሊዮን የሚያክሉ ፈንጂዎች በ75 አገሮች ተቀብረዋል።

ስዊፍት የተባሉት ወፎች የበረራ ችሎታ

ስዊፍት የተባሉት ወፎች “በሚያዝያ ወር መጨረሻ አካባቢ ከአፍሪካ ተነስተው ወደ እንግሊዝ በመጓዝ 6,000 ኪሎ ሜትር ይበርራሉ” ይላል የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ። እነዚህ ወፎች “አቅጣጫ ጠቋሚ ሳተላይት፣ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ወይም አብራሪ ሳይኖራቸው” ዘመናዊ አውሮፕላኖች ካሏቸው ዘመናዊ የበረራ መሣሪያዎች ይበልጥ በተራቀቀ የበረራ ችሎታ በመጠቀም በ3,000 ሜትር ከፍታ በማታ ይጓዛሉ። በነፋስ ተገፍተው አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ መንገዳቸውን የሚያስተካክሉት ከዚህ በፊት ይታሰብ እንደነበረው በምድር ላይ በሚያዩዋቸው ምልክቶች ሳይሆን የነፋሱን አቅጣጫ በመከተል ነው። በስዊድን የሉንድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዮሐን ቤክማን የ225 ወፎችን በረራ በራዳር ከተከታተሉ በኋላ “በጣም ዘመናዊ የበረራ መሣሪያ ያላቸው እጅግ የተራቀቁ አውሮፕላኖች እንኳ እንደነርሱ የነፋስ አቅጣጫ መለወጥ አለመለወጡን በቀላሉ ማወቅ ሊቸገሩ ይችላሉ” ብለዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወፎቹ በማታ በረራቸው ጊዜ ግማሹን የአንጎላቸውን ክፍል ይዘጋሉ። ይሁን እንጂ የአእዋፍ ጥበቃ ማኅበር ባልደረባ የሆኑት ግራም ማጅ እንደሚሉት ገና መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ “ይህን ያህል ጊዜ ሲበሩ ምን ይበላሉ?”

የማይጋብዙ መጸዳጃ ቤቶች

ብዙዎቹ የፈረንሳይ ተማሪዎች የሚማሩበት ትምህርት ቤት መጸዳጃ ቤቶች “ወለላቸው እርጥብ፣ ውኃቸው በጣም ቀዝቃዛ፣ ሳሙና የሌላቸውና በራቸው የማይቆለፍ እንዲሁም በጣም አጭር በሆኑ መከፋፈያዎች የተጋረዱ” በመሆናቸው የትምህርት ቤታቸውን መጸዳጃ ቤቶች አይጠቀሙም በማለት ለክስፕረስ የተባለው ሳምንታዊው የፈረንሳይ መጽሔት ዘግቧል። ፌዴራስዮን ዴ ኮንሴይ ደ ፓሮ ዴሌቭ የተባለው ድርጅት ባደረገው ጥናት መሠረት “48 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው መጸዳጃ ቤት አዘውትረው አይጠቀሙም።” ይህም በልጆቹ ጤንነት ላይ ጉዳት ማምጣቱ አልቀረም። ጥናቱ እንዳመለከተው “አንድ አራተኛ የሚሆኑት የአንጀት ወይም የሽንት ቧንቧ ችግር አጋጥሟቸዋል።” የሕፃናት የሽንት ቧንቧ ሐኪም የሆኑት ሚሼል አቬሩ “ሕፃናት በቀን ውስጥ አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መጸዳጃ ቤት መሄድ ይኖርባቸዋል። እንዳስፈላጊነቱ ቶሎ ቶሎ ያልተራገፈ ፊኛ ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል ኢንፌክሽን ሊያጋጥመው ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል።