በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የላቀ ግምት የሚሰጠው የውበት ዓይነት

የላቀ ግምት የሚሰጠው የውበት ዓይነት

የላቀ ግምት የሚሰጠው የውበት ዓይነት

ሰዎች ጥሩ መልክና ቁመና አላቸው በሚባሉ ሰዎች ይማረካሉ። ይሁን እንጂ አንድን ሰው በእውነት ማራኪ እንዲሆን የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ በተፈጥሮ ያገኘኸውን መልክ መለወጥ የምትችለው በተወሰነ መጠን ብቻ ነው። ደግሞም በዛሬው ጊዜ እርጅናና በሽታ ከሚያስከትለው መጎሳቆል ሊያመልጥ የሚችል ሰው ስለሌለ አካላዊ ቁንጅናና መልክ ረጋፊ ነው። ታዲያ ይበልጥ አስፈላጊና ዘላቂ የሆነ እንዲሁም ሊገኝ የሚችል ውበት አለ?

የውስጣዊ ውበት አስፈላጊነት

ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ለውስጣዊ ውበት ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት።

ይሖዋ ነቢዩ ሳሙኤልን ከእሴይ ልጆች መካከል የእስራኤል ንጉሥ የሚሆነውን እንዲመርጥ በነገረው ጊዜ ዓይኑን የሳበው መልከ ቀና የነበረው ኤልያብ ነበር። ሳሙኤል “በእርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ” አለ። ይሖዋ ግን ለሳሙኤል “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።—1 ሳሙኤል 16:6, 7

ንጉሥ እንዲሆን የተመረጠው የሁሉ ታናሽ የነበረው ዳዊት ሆነ። ዳዊት “ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም” እንደሆነ ቢነገርለትም እንደ ታላላቅ ወንድሞቹ ግርማ ሞገስ ያለው ሆኖ አልታየም። ይሁን እንጂ “ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ።” ፍጹም ያልነበረና ከባድ ኃጢአቶችን የሠራ ሰው ቢሆንም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ሆኖ የኖረና ጥሩ ልብ የነበረው ሰው ሆኗል። (1 ሳሙኤል 16:12, 13) አለጥርጥር በአምላክ ዓይን ውብ ሆኖ የታየው በውስጣዊ ውበቱ ምክንያት ነበር።

ለማነጻጸር ያህል ከዳዊት ወንድ ልጆች አንዱ የነበረውን አቤሴሎምን እንውሰድ። የሚያስቀና መልክ የነበረው ቢሆንም የማይፈለግ ሰው ሆኖ ተገኝቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ሲናገር “መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም።” (2 ሳሙኤል 14:25) ይሁን እንጂ አቤሴሎም የነበረው የሥልጣን ጥም በገዛ አባቱ ላይ እስከ ማመጽና ዙፋኑን እስከ መቀማት አደረሰው። እንዲያውም የአባቱን ቁባቶች እስከ መድፈር ደርሷል። በዚህም የተነሣ አምላክ ስለተቆጣ አቤሴሎም አሰቃቂ ሞት ሊሞት ችሏል።—2 ሳሙኤል 15:10-14፤ 16:13-22፤ 17:14፤ 18:9, 15

አቤሴሎምን ትወደዋለህ? እንደማትወደው የተረጋገጠ ነው። በአጠቃላይ የሚጠላ ሰው ነው። የቁመናውና የመልኩ ማማር ከጥፋት ሊያድነውም ሆነ ዕብሪተኝነቱንና ከሃዲነቱን ሊያካክስለት አልቻለም። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አካላዊ ቁንጅናቸውም ሆነ ስለ ቁመናቸው ምንም ስላልተባለላቸው ጥበበኛ የሆኑና የሚወደዱ ሰዎች ይናገራል። ትልቅ ዋጋ የተሰጠው ለውስጣዊው ውበት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ውስጣዊ ውበት ይማርካል

ውስጣዊ ውበት ሌሎችን ሊማርክ ይችላል? ካገባች አሥር ዓመት ገደማ የሆናት ኪዮርኪና “በእነዚህ ዓመታት በሙሉ ባሌን የምወደው በሚያሳየኝ ሐቀኝነትና እውነተኝነት ምክንያት ነው። በሕይወቱ ውስጥ አምላክን ከማስደሰት የሚያስበልጠው ነገር የለም። ይህም አሳቢና አፍቃሪ እንዲሆን ረድቶታል። በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ስለ እኔ ስሜት ያስባል። በእውነት እንደሚወደኝ አውቃለሁ” ብላለች።

በ1987 ያገባው ዳንኤል “ለእኔ ሚስቴ በጣም ቆንጆ ነች። መልኳንና ቁመናዋን እወደዋለሁ። ይበልጥ የምወዳት ግን በጠባይዋ ምክንያት ነው። ሁልጊዜ ስለ ሌሎች ሰዎች ታስባለች፣ ልታስደስታቸውም ትጥራለች። በጣም ጥሩ ክርስቲያናዊ ባሕርያት አሏት። አብሬያት መኖር የሚያስደስተኝ በዚህ ምክንያት ነው” ብሏል።

በዚህ ውጪያዊ ለሆነ ነገር ብቻ ትኩረት በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ስንኖር ጠለቅ ብለን የውስጡን ማየት ያስፈልገናል። “ተፈላጊ” የሚባለውን መልክና ቁመና ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ነው ባይባልም እንኳን አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ውስን ነው። እውነተኛ ውስጣዊ ውበት የሚያስገኙ ባሕርያትን ማዳበር ግን ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁንጅና አታላይ ነው፤ ውበትም ይረግፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን የተመሰገነች ናት” ይላል። በአንጻሩ ደግሞ “በእርያ አፍንጫ ላይ እንደ ተሰካ የወርቅ ቀለበት፣ ማስተዋል የጎደላት ቆንጆ ሴት እንዲሁ ናት” ሲል ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 11:22፤ 31:30

የአምላክ ቃል ‘ዋጋው እጅግ ለከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ላለበት፣ ምንጊዜም ለማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት’ ትልቅ ዋጋ እንድንሰጥ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 3:4) በእርግጥም ከአካላዊ ውበት በጣም የሚበልጠው ይህ ውስጣዊ ውበት ነው። በተጨማሪም ይህን ውበት ሁሉም ሰው ሊያገኘው ይችላል።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጥሩ ባሕርይ ከማንኛውም መልክ ማሳመሪያ ዘዴ የበለጠ አምረን እንድንታይ ያደርገናል