በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሞት ፋብሪካ

የሞት ፋብሪካ

የሞት ፋብሪካ

ጀርመን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሚተልቨርክ ከዓለም ትልቁ የመሬት ውስጥ ፋብሪካ እንደነበር አንዳንዶች ይናገራሉ። ጀርመን ውስጥ ከበርሊን በስተ ደቡብ ምዕራብ 260 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሃርዝ ተራሮች ውስጥ የተቋቋመው ይህ ፋብሪካ በአጠቃላይ 20 ኪሎ ሜትር የሚያህል ርዝመት ያላቸው ሰፋፊ ዋሻዎች አሉት። ከ1943 እስከ 1945 ባሉት ዓመታት ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ የማጎሪያ ካምፕ እስረኞች በእነዚህ ዋሻዎች ውስጥ በባርነት ይሠሩ ነበር። እስረኞቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ሥር ለናዚ መንግሥት የጦር መሣሪያ እንዲያመርቱ ተገደው ነበር።

እስረኞቹ ያመርቱ የነበረው ተራ የጦር መሣሪያ ሳይሆን ቪ-1 እና ቪ-2 የተባሉ ሮኬቶችን ወይም ሚሳይሎችን ነበር። እነዚህ ሚሳይሎች ከሚተልቨርክ በዋነኝነት ፈረንሳይና ኔዘርላንድ ውስጥ ወደሚገኙት መተኮሻ ጣቢያዎች ተጫኑ። ከዚያም ወደ ሰማይ ተወንጭፈው ቤልጅየም፣ ብሪታንያና ፈረንሳይ ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎቻቸው ላይ እንዲፈነዱ ተደረገ። ከዚህም በተጨማሪ ናዚዎች አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ ኒው ዮርክን መምታት የሚችል የበለጠ ኃይል ያለው ቦምብ ተሸካሚ ሮኬት ለመሥራት አልመው ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት እነዚህ የጀርመን ሚሳይሎች በአውሮፓ ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ሆኖም ናዚዎች ጠላቶቻቸውን ለማጥቃት እንጠቀምባቸዋለን ብለው ካመረቷቸው ሚሳይሎች ውስጥ ሥራ ላይ የዋሉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ከተጠቀሙባቸው ሚሳይሎች ውስጥ አንዱም እንኳ ኒው ዮርክ አልደረሰም።

በዓይነቱ ልዩ የሆነ አሳዛኝ ክስተት

ጦርነቱ እንዳለቀ ቪ-1 እና ቪ-2 ሚሳይሎችን ከነደፉት የጀርመን ሳይንቲስቶችና ቴክኒሽያኖች መካከል ብዙዎቹ ጀርመንን ለቅቀው ወጡ። እነዚህ ሳይንቲስቶች ስለ ሮኬት ቴክኖሎጂ የነበራቸውን እውቀት አሁን በሚኖሩባቸው አገሮች ተጠቅመውበታል። ቨርነር ፎን ብራውን የተባለው አንደኛው የሮኬት ሳይንቲስት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሄደ ሲሆን ሰዎችን ወደ ጨረቃ በምትወስደው ሳተርን የተባለች ሮኬት ሥራ ላይ ተካፍሏል።

በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞው ሚተልቨርክ ፋብሪካ አጠገብ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረው ለነበሩ 60,000 ሰዎች መታሰቢያ የሚሆን ሃውልት ቆሟል። አብዛኞቹ እስረኞች በእነዚህ ቀዝቃዛና የታፈጉ ዋሻዎች ውስጥ መሥራት ብቻ ሳይሆን ይኖሩባቸው ነበር። አንዳንዶች እንደሚገምቱት ወደ 20,000 የሚጠጉ እስረኞች መሞታቸው ብዙም አያስደንቅም። ጎብኚዎች የመታሰቢያውን ሙዚየም በሚጎበኙበት ጊዜ ከዛሬ 60 ዓመት በፊት በዋሻዎቹ ውስጥ የተጣሉ የተለያዩ የሮኬት ክፍሎችን ማየት ይችላሉ። አፍተር ዘ ባትል የተባለው መጽሔት በሚተልቨርክ የተመረቱትን ሚሳይሎች በዓይነታቸው ልዩ የሚያደርጋቸው አሳዛኝ ነገር ምን እንደሆነ ሲናገር “ቪ1 እና ቪ2 ሚሳይሎችን እስከዛሬ ከተመረቱት የጦር መሣሪያዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ሥራ ላይ ውለው ካጠፉት ሕይወት ይልቅ ሲመረቱ የሞተው ሰው ብዛት መብለጡ ነው” ብሏል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቪ-1 ሮኬቶች ሲጓጓዙ የሚያሳይ በ1945 የተነሳ ፎቶግራፍ

[ምንጭ]

Quelle: Dokumentationsstelle Mittelbau-Dora

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎብኚዎች የተለያዩ የሮኬት ክፍሎች ተጥለው የሚገኙባቸውን ዋሻዎች ሲጎበኙ