በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእስክንድርያው ቤተ መጻሕፍት በድጋሚ ተከፈተ

የእስክንድርያው ቤተ መጻሕፍት በድጋሚ ተከፈተ

የእስክንድርያው ቤተ መጻሕፍት በድጋሚ ተከፈተ

በወቅቱ ከነበሩት ታዋቂ ቤተ መጻሕፍት መካከል አንዱ ሲሆን እስክንድርያ የተባለችውን የግብፅ ከተማ የዓለም ምሁራን መናኸሪያ እንድትሆን አድርጓት ነበር። ይህ ቤተ መጻሕፍት እንዴት እንደጠፋ ማንም በእርግጠኝነት መናገር ባይችልም በውስጡ ይገኙ የነበሩት ዋጋ የማይተመንላቸው ጽሑፎች አብረው ወድመዋል፤ ይህም በቀለም ትምህርት የእድገት ደረጃ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ አሳድሯል። አሁን ግን ይህ ታላቅ ቤተ መጻሕፍት በድጋሚ ነፍስ ዘርቷል ማለት ይቻላል።

በድጋሚ የተገነባው ዝነኛው የእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍት ለየት ያለ ቅርጽ አለው። ቢብሊዮቲካ አሌክሳንድሪና የሚል ስያሜ የተሰጠው የዚህ አዲስ ቤተ መጻሕፍት ዋነኛ ሕንጻ ዘንበል ያለ ትልቅ ታምቡር ይመስላል። ከመስተዋትና ከአልሙኒየም የተሠራው ጣሪያ (1) ሁለት የእግር ኳስ ሜዳ ገዳማ የሚያክል ስፋት አለው፤ መስኮቶቹ በስተ ሰሜን በኩል ጣሪያ ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህም የንባብ ክፍሉ በቂ ብርሃን እንዲያገኝ ያስችለዋል (2)። ጉርድ በርሜል የመሰለ ቅርጽ ያለው ይህ ግዙፍ ሕንጻ የሕዝብ መናኸሪያ ስፍራዎች ያሉት ሲሆን ግማሽ አካሉ ከባሕር ወለል በታች የተሠራ ነው። ለጥ ያለውና የሚያብረቀርቀው የሕንጻው ጣሪያ ሰባት ፎቅ ከሚያክል ርዝመት ተነስቶ በትንሹ ዘንበል እያለ ቁልቁል ይወርድና ጥልቅ ጉድጓድ ይፈጥራል። ከአልሙኒየም የተሠራው የሕንጻው ጣሪያ ላይ ፀሐይ አንጸባርቆበት ከሩቁ ሲታይ ፀሐይ እየወጣች ያለች ይመስላል።

ያዘነበለ ታምቡር የሚመስለው የዚህ ሕንጻ ግድግዳ የተሠራው ቀጥ ካለ ሰፊ ግራጫ ባልጩት ሲሆን በላዩም ጥንታዊና ዘመናዊ ፊደላት በመደዳ ተቀርጸውበታል (3)። እነዚህ በሥርዓት የተደረደሩ ፊደላት ሕንጻው የእውቀት ማዕከል እንደሆነ በትክክል ያመለክታሉ።

ክብ ቅርጽ ያለው የሕንጻው ውስጠኛ ክፍል በአብዛኛው ሰፊና በሥርዓት የተደረደሩ ወንበሮች ባሉት የንባብ ክፍል የተያዘ ነው (4)። ከመሬት በታች ያለው የሕንጻው ክፍል ግድግዳ 8,000,000 ጥራዞች ሊይዝ የሚችል መደርደሪያ አለው። በተጨማሪም ቤተ መጻሕፍቱ የኤግዚቢሽን ማሳያ ቦታዎች፣ ንግግር የሚሰጥባቸው አዳራሾች፣ ማየት ለተሳናቸው ሰዎች የሚሆኑ ልዩ መገልገያዎች (5) እንዲሁም ከውጪ በኩል ዋናውን ሕንጻ መዞሩን ያቆመ የሚመስል አነስተኛ ክብ ቅርጽ ያለው ኘላኒታሪየም ይገኙበታል (6)። ሕንጻው ውስጥ የሚገኙት ዘመናዊ ኮምፒውተሮችና የእሳት አደጋ መከላከያዎች በአሁኑ ወቅት የሰው ልጅ እውቀት ወይም ቴክኖሎጂ ምን ያህል እንደመጠቀ ይጠቁማሉ።

ይህ የዓለማችን ድንቅ ቤተ መጻሕፍት የተቋቋመው እንዴት ነበር?

በጥንት ዘመን እስክንድርያ ከጥንቱ ዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች መካከል አንዱ በሆነው ከ110 ሜትር በላይ ርዝመት እንደነበረው በሚነገርለት የወደብ መብራትና የታላቁ እስክንድር መቃብርን በመሳሰሉ በአሁኑ ጊዜ በሌሉ በጣም አስደናቂ ነገሮች ትታወቅ ነበር። ቶለሚ የሚባለው የግሪክ ሥርወ መንግሥት ከእስክንድር ሞት በኋላ ግብፅን የተረከበ ሲሆን ነገሥታቱም ኦክቴቪየን በ30 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንቶኒንና ክሊዮፓትራን ድል እስካደረገበት ጊዜ ድረስ አገሪቱን አስተዳድረዋል። እስክንድርያ በቶለሚ ሥርወ መንግሥት አስተዳደር ጊዜ አስደናቂ ለውጥ አድርጋ ነበር። አትላስ ኦቭ ዘ ግሪክ ወርልድ እንደዘገበው በእርግጥም እስክንድርያ “ለተወሰነ ጊዜ የዓለም የንግድና የባሕል ማዕከል ሆና ነበር።” ከፍተኛው የእስክንድርያ ነዋሪዎች ቁጥር 600,000 ገደማ ደርሶ ነበር።

የከተማይቱ ዋነኛ መስህብ የነገሥታቱ ቤተ መጻሕፍት ነበር። ይህ ቤተ መጻሕፍት በቶለሚ ቤተሰቦች ልግስና ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን የተቋቋመ ሲሆን ሚዩዝ የተባለው የሴት አማልክት ቤተ መቅደስ አብሮት ይገኝ ነበር፤ ይህ ቦታ ለሄለናውያን ግዛቶች የትምህርትና የፈጠራ ሥራ ማዕከል ሆኖ ነበር።

በቤተ መጻሕፍቱ 700,000 የፓፒረስ ጥቅልሎች ይገኙ እንደነበር ይገመታል። በ14ኛው ክፍለ ዘመን በመጻሕፍቱ ብዛት ተወዳዳሪ እንደሌለው ይነገርለት በነበረው የሶርቦን ቤተ መጻሕፍት እንኳን 1,700 መጻሕፍት ብቻ ይገኙ ነበር። የግብፅ ገዥዎች ብዙ ጽሑፎችን የመሰብሰብ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ከሌላ ቦታ የሚመጡ መርከቦች ጥቅልል ይዘው እንደሆነ የሚፈትሹ ወታደሮች ነበሯቸው። ፈልገው ካገኙ ዋናውን ያስቀሩና ግልባጩን ለባለቤቱ ይመልሳሉ። አንዳንድ ምንጮች እንደሚገልጹት ሣልሳዊ ቶለሚ በጥንቱ ግሪክኛ ቋንቋ የተጻፉ እጅግ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የቲያትር ጽሑፎችን ከአቴንስ ተውሶ ነበር፤ ንጉሡ እነዚህን ቲያትሮች ገልብጦ እንደሚመልስ ቃል በመግባት ገንዘብ አስይዞ የነበረ ቢሆንም ዋናውን ለራሱ አስቀርቶ ያስያዘውን ገንዘብ ትቶላቸው ግልባጩን መለሰ።

በእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዘክር ውስጥ ከሠሩት ሰዎች ዝርዝር መካከል ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ምሁራንና ከፍተኛ የፈጠራ ሰዎች ይገኙበታል። የእስክንድርያ ምሁራን ጂኦሜትሪና ትሪጎኖሜትሪ በተባሉት የሒሳብ ዘርፎች፣ በከዋክብት ጥናት፣ በቋንቋ፣ በሥነ ጽሑፍና በሕክምና ረገድ የሚያስመሰግን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ሰባ ሁለት አይሁዳውያን ምሁራን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ግሪክኛ የተረጎሙት በዚሁ ቦታ እንደሆነ ይነገራል፤ ይህ ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሴፕቱጀንት ወይም ሰብዓ ሊቃናት ይባላል።

ቤተ መጻሕፍቱ ጠፋ

የሚገርመው ነገር ታሪክ ዘጋቢዎች በእስክንድርያ የሚገኙ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማቸው ነበር። በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበረው ታሪክ ጸሐፊ አተንየስ የሰጠው ሐሳብ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆናል። እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “የመጻሕፍቱን ብዛት በተመለከተ፣ ስለ ቤተ መጻሕፍቶቹ መከፈትና በሙሰዝ ቤተ መቅደስ አዳራሽ ውስጥ ስለሚገኘው ስብስብ ሁሉም ሰው ስለሚያውቅ ስለ እነዚህ ነገሮች ለምን እናገራለሁ?” እንዲህ ያሉት አስተያየቶች ስለዚህ አስደናቂ ጥንታዊ ቤተ መጻሕፍት ለማወቅ ለሚጓጉት የዘመናችን ምሁራን ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል።

አረቦች ግብፅን በ640 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በያዙበት ጊዜ የእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍት ጠፍቶ ነበር። ምሁራን ቤተ መጻሕፍቱ እንዴትና መቼ ጠፋ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ እስከ አሁን ድረስ ስምምነት ላይ አልደረሱም። አንዳንዶች ጁሊየስ ቄሳር በ47 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተወሰነውን የእስክንድርያ ከተማ ባቃጠለ ጊዜ ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ጽሑፎች አብረው ተቃጥለው ይሆናል ይላሉ። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የቤተ መጻሕፍቱ መጥፋት በርካታ የእውቀት ምንጮች እንዲወድሙ አድርጓል። ከጥቂት የሄሮዶተስ፣ የቱሳይዳዲስና የዜኖፈን ሥራዎች በስተቀር በመቶዎች የሚቆጠሩ የግሪክ ተውኔት ደራሲያን ሥራዎችና የመጀመሪያዎቹን 500 ዓመታት የግሪክ ታሪክ የሚዘግቡ ጽሑፎች ጠፍተዋል።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሦስተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን መካከል በነበሩት ጊዜያት እስክንድርያ ውስጥ በተደጋጋሚ ብጥብጥ ይነሳ ነበር። አረማውያን፣ አይሁዳውያንና ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ምስጢራዊ በሆኑ ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶቻቸው ምክንያት እርስ በርሳቸውም ሆነ አንዱ ከሌላው ጋር ለበርካታ ጊዜያት ውጊያ ገጥመው ነበር። ቤተ ክርስቲያን ራሷ ረብሸኞች የአረማውያን ቤተ መቅደሶችን እንዲዘርፉ ብዙ ጊዜ ታበረታታ ነበር። በዚህ ምክንያት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥንታዊ ጽሑፎች ወድመዋል።

ቀድሞ የነበረውን ክብር መመለስ

በድጋሚ የተገነባው ቤተ መጻሕፍት የተከፈተው ጥቅምት 2002 ሲሆን 400,000 መጻሕፍት ይዟል። እጅግ ዘመናዊ የሆነው ኮምፒውተር ሌሎች ቤተ መጻሕፍቶችንም ለመቃኘት ያስችላል። በቤተ መጻሕፍቱ ከሚገኙት ስብስቦች ውስጥ አብዛኞቹ በምሥራቃዊ ሜዲትራንያን የሥልጣኔ ሂደት ላይ ያተኩራሉ። ስምንት ሚሊዮን መጻሕፍት መያዝ የሚችለው የእስክንድርያው ቤተ መጻሕፍት ለዚህች ጥንታዊት ከተማ ውበት ጨምሮላታል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በጥንቷ እስክንድርያ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች

አርኪሚዲዝ:- ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ የሒሳብ ሊቅና የፈጠራ ሰው ነው። የበርካታ ግኝቶች ባለቤት ሲሆን የፓይን (π) ዋጋ ለማስላት ሳይንሳዊ ምርምር ያደረገ የመጀመሪያው ሰው ነው።

የሳሞሱ አርስጥሮኮስ:- ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ የከዋክብት ተመራማሪ ነው። ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ እንደሚሽከረከሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ግምታዊ ሐሳብ ሰንዝሯል። ትሪጎኖሜትሪ የሚባለውን የሒሳብ ዘርፍ ተጠቅሞ ፀሐይና ጨረቃ ከምድር ያላቸውን ርቀትና ስፋታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማስላት ሞክሯል።

ከሊመከስ:- ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ ባለቅኔና የቤተ መጻሕፍት ዋና ኃላፊ ነው። በጥንታዊው የግሪክ ቋንቋ ለተዘጋጁት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እንደ ሕግ ሆኖ ያገለገለውን የእስክንድርያን ቤተ መጻሕፍት የመጀመሪያ ማውጫ አዘጋጅቷል።

ክላውድየስ ቶለሚ:- ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረ የከዋክብት ተመራማሪ ነው። ስለ ጂኦግራፊና ስለ ከዋክብት ጥናት የጻፋቸው ጽሑፎች መመሪያ ሆነው አገልግለዋል።

ኤራተስተኒስ:- ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ እውቀት የነበረውና ከመጀመሪያዎቹ የእስክንድርያ ቤተ መጻሕፍት ኃላፊዎች መካከል አንዱ ነው። የምድርን መጠነ ዙሪያ አስልቶ የተናገረ ሲሆን ውጤቱ ከትክክለኛው መጠን ብዙም አይርቅም።

ዩክላይድ:- ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው መቶ ዘመን የኖረ የሒሳብ ሊቅ ነው። የመጀመሪያው የጂኦሜትሪ ሊቅና የብርሃን ጥናት ፈር ቀዳጅ ነው። ኤለመንትስ የተባለው ሥራው እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ የጂኦሜትሪ መመሪያ ሆኖ አገልግሏል።

ጌለን:- ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረ ሐኪም ነው። ስለ ሕክምና ሳይንስ የጻፋቸው 15 መጻሕፍት ከ1,200 ለሚበልጡ ዓመታት መመሪያ ሆነው አገልግለዋል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በሁለቱም ገጾች ላይ ያሉት ፎቶዎች የተወሰዱት:- Courtesy of the Bibliotheca Alexandrina: Mohamed Nafea, Photographer