በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዳግም እንደማገኘው ተስፋ ተሰጥቷል

ዳግም እንደማገኘው ተስፋ ተሰጥቷል

ዳግም እንደማገኘው ተስፋ ተሰጥቷል

ሮሳሊያ ፊሊፕስ እንደተናገረችው

የመድረኩ መጋረጃ ሊገለጥ ትንሽ ሲቀረው ፒያኖው ጋር ቁጭ ያለው የሙዚቃ መሪያችን “ይሳካልሻል! ለስኬት የተፈጠርሽ ሰው ነሽ!” አለኝ። ሌሎቹም አራት የባንዱ አባላት የእንኳን ደህና መጣሽ ምልክት አሳዩኝ። በዚያን ቀን የለበስኩት በዶቃ ያሸበረቀ ቀይ ቀሚስ ነበር፤ ለባንዱ አዲስ ድምፃዊት እንደመሆኔ መጠን በጣም ፈርቻለሁ። በመዝናኛው መስክ መሥራት የጀመርኩትና ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት የቀረብኩት በሜክሲኮ ሲቲ ታዋቂ በሆነው በዚሁ ቲያትር ቤት ነው! ይህ የሆነው 18 ዓመት ሊሞላኝ አንድ ወር ሲቀረኝ ማለትም መጋቢት 1976 ነው።

አባቴ ይህ ከመሆኑ ሦስት ዓመት ቀደም ብሎ የሞተ ሲሆን ትዝታው ከልቤና ከአእምሮዬ እስከ አሁን ድረስ አልተፋቀም። ሕዝቡም ቢሆን በደንብ ያስታውሰዋል። በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ኮሜዲያን አንዱ በመሆኑ ተወዳጅና አድናቆት ያተረፈ ሰው ነበር። በሜክሲካውያን ሲኒማ ታሪክ ወርቃማው ዘመን ተብሎ በሚጠራው ጊዜ ከ120 በሚበልጡ ፊልሞች ውስጥ ተጫውቷል። በመካከለኛውና በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ስፓንኛ ተናጋሪ በሆኑ የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ አካባቢዎች በሚገኙ የቲያትር ቤቶች የማስታወቂያ ሰሌዳ ሁሉ ላይ የአባቴ ስም ኬርማን ባልዴስ ወይም “ቲን ታን” ይጻፍ ነበር። ከሞተ ከ30 ዓመት በላይ ቢሆነውም እንኳ እርሱ የተወነባቸው ፊልሞች እስከ አሁን ድረስ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ይታያሉ።

ከልጅነቴ ጀምሮ ቤታችን የታዋቂ ሰዎች መሰብሰቢያ ነበር። እናቴና እህቶቿ ለሦስት ሆነው ላስ ሄርማኒታስ ኩልያን የሚባል የሙዚቃ ጓድ አዘጋጅተው ነበር። ወንድሟ ኩልዮ ኩልያን በአውሮፓ ውስጥ የታወቀ የኦፔራ ዘፋኝ የነበረ ሲሆን ኮንቺታ ዶሚንጌስ የተባለችው ስፔይናዊት ሚስቱ ደግሞ ጥሩ ድምፅ ያላት ዘፋኝ ነበረች። ከዚህም በላይ የአባቴ ሁለት ወንድሞች ማለትም “ሎኮ” (እብዱ) የሚባል ቅጽል ስም ያለው ማንዌል ባልዴስ እና ዶን ራሞን በሚለው አጠራር በይበልጥ የሚታወቀው ራሞን ባልዴስ ታዋቂ ኮሜዲያን ነበሩ።

ብዙ ጊዜ አባታችን እኔንና ወንድሜን ሥራ ቦታውም ሆነ ረዥም የሥራ ጉዞ በሚያደርግበት ጊዜ ይዞን ስለሚሄድ ስለ ፊልም ስቱዲዮዎች፣ የተለያየ ዓይነት ትርኢቶች ስለሚታይባቸው ቦታዎችና ስለ ድምፅ መቅረጫ ስቱዲዮዎች በደንብ እናውቃለን፤ አባታችን በዚህ መልኩ ቤተሰባችን አንድነት እንዲኖረው ጥረት ያደርግ ነበር። ለታይታ የሚደረጉ ነገሮች በሞሉበት በመዝናኛው የሥራ መስክና እውነተኛ ስምምነትና ፍቅር ባለበት በእኛ ቤት መካከል ትልቅ ልዩነት ነበር! አባቴ በጣም ሰው የሚወድድ፣ ጠንካራና ለሕይወት አክብሮት ያለው ሰው እንደነበር አስታውሳለሁ። እጅግ በጣም ለጋስ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዴ ደግነቱን ያበዛዋል። ደስታ የሚገኘው ሀብት በማካበት ሳይሆን በመስጠት እንደሆነ አስተምሮኛል።

አስደንጋጭ ለውጥ

በ1971 ማብቂያ ገደማ እናቴ ለእኔና ለወንድሜ አባታችን ሊድን በማይችል በሽታ መያዙን አረዳችን። ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ይወስደው በነበረው ከባድ መድኃኒት ምክንያት ሲሰቃይ እመለከት ነበር።

ቤታችን አምቡላንስ መጥቶ ወደ ሆስፒታል ይዞት የሄደበትን ቀን እስከ አሁን አስታውሳለሁ። በዚያን ጊዜ ወደ ቤት እንደማይመለስ አውቄ ነበር። ምን ያህል እንዳዘንኩ መግለጽ አልችልም። እርሱ እየተሰቃየ ስለነበር እኔም መሰቃየት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ውስጥ እጄን በሲጋራ እየተኮስኩ ምርር ብዬ አለቀስኩ። ሰኔ 29, 1973 አባቴ አረፈ። ‘ጥሩ የሆነና ሊያስደስተን የሚጥር ሰው ለምን ጥሎን ይሄዳል? አሁን አባቴ የት ነው ያለው? ባናግረው ይሰማኝ ይሆን? ያለ እርሱ የምመራው ሕይወት ምን ትርጉም ይኖረዋል?’ እያልኩ ከራሴ ጋር እሟገት ጀመር።

ዓላማ የሌለው ሥራ

ከሐዘኔ ካገገምኩ በኋላ ሕንጻ የማስጌጥ ጥበብ መማር ጀመርኩ። ትንሽ የዓመጸኝነት ባሕርይ ስለነበረብኝ ትምህርት ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ። እኔና እናቴ ይበልጥ ከኅብረተሰቡ ጋር ለመቀራረብ ስለ ወሰንን በመዝናኛው የሥራ መስክ የተሰማሩ ሰዎች በሚያዘጋጅዋቸው ትልልቅ ግብዣዎች ላይ እንገኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ጋባዡ “ሮሳሊያ እባክሽ አሁን አንዱን ዘፈንሽን ዝፈኝልን” በማለት ግብዣውን ይደመድማል። ስዘፍን የሚያዳምጡኝ ሰዎች ድምፄንና ስዘፍን የማሳየውን ስሜት በጣም ይወድዱት የነበረ ሲሆን የወላጆቼን ችሎታ እንደወረስኩ ይናገሩ ነበር።

አርቱሮ ካስትሮ ኤንድ ሂዝ ካስትሮስ 76 የተባለ ባንድ መሪና የሙዚቃ ደራሲ የነበረ አንድ ሰው ከግብዣዎቹ በአንዱ ላይ ስዘፍን ሰምቶ ቡድኑን እንድቀላቀል ጋበዘኝ። መጀመሪያ ላይ በሐሳቡ አልተደሰትኩም ነበር። ምንም እንኳን ከ14 ዓመቴ ጀምሮ ጊታር እጫወት፣ ዘፈን እወድድና ሙዚቃ አቀናብር የነበረ ቢሆንም በዘፋኝነት ሙያ የመሰማራት ፍላጎት አልነበረኝም። ይሁን እንጂ እናቴ እንድሠራ ስላበረታታችኝና ቤተሰባችንን በገንዘብ ለመደገፍ ስል ግብዣውን ተቀበልኩ። በዚህ ሁኔታ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት ቀረብኩ።

ሥራዬን ገና ከመጀመሬ እየተሳካልኝ መጣ። የሙዚቃ ቡድናችን በሜክሲኮ በመዟዟር ዝግጅቱን በአንድ ምሽት ሁለት ጊዜ ያቀርብ ነበር። በጓቲማላ፣ በቬኔዙዌላ፣ በኒው ዮርክና በላስ ቬጋስም ሠርተናል። ከዚህ ቡድን ጋር ለሁለት ዓመት ከቆየሁ በኋላ ፊልም እንድሠራ ተጋበዝኩ። ሌሎች መሪ ተዋናይ በሆኑበት ፊልም ላይ ሁለት ጊዜ ስካፈል፣ ሁለት ታላላቅ ሽልማቶች ባገኘሁበት አንድ ፊልም ላይ ደግሞ ራሴ መሪ ተዋናይ ሆኜ ሠርቻለሁ።

አንድ ቀን በአገሪቱ ከሚገኘው ትልቅ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስልክ ተደወለልኝ። ጣቢያው ከታላላቅ ተዋንያን ጋር ብቻ የሚያደርገውን ውል እንድንዋዋልና በእኔ ስም በተሰየመ አንድ ተከታታይ ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ ሆኜ እንድሠራ ግብዣ አቀረበልኝ። ይህን ውል መዋዋሌ በመዝናኛው የሥራ መስክ ትልቅ ደረጃ ላይ እንድደርስ የሚያስችለኝ ከመሆኑም በላይ በቋሚነት ባልሠራም እንኳን ጥሩ ደመወዝ እንዳገኝ ያስችለኝ ነበር። ይህን ትልቅ መብት ማግኘት አይገባኝም በሚል ስሜትና ነፃነቴን አጣ ይሆናል በሚል ፍራቻ ውል ለመግባት ፈቃደኛ ሳልሆን ቀረሁ። ይሁን እንጂ በዩኒቨርሲቲ እማር የነበረውን የቲያትር ትምህርት ለመቀጠል ስል ብቻ በተከታታዩ ፊልም ላይ እንድሠራ የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ያም ሆኖ ግን ደስተኛ አልነበርኩም። ሌሎች መሪ ተዋናይ ለመሆን በርካታ ዓመታት ሲጥሩ እኔ ግን የቲን ታን ልጅ ስለሆንኩ ብቻ መሪ ተዋናይ መሆኔ በጣም ይሰማኝ ነበር።

ከዚያ በኋላ ደግሞ ዘፈን ማውጣት ጀመርኩ። በመጀመሪያው ሥራዬ ላይ ለተከታታይ ፊልም ማጀቢያነት ራሴ የደረስኩትን ግጥምና ዜማ ጨምሬ አውጥቼ ነበር። ቆየት ብሎም ለንደን በሚገኝ አንድ ታዋቂ ስቱዲዮ ዘፈኖቼን አስቀዳሁ። በቀጣዮቹ ጊዜያትም ተጨማሪ ዘፈኖችን ያወጣሁ ሲሆን በተከታታይ ፊልሞችና በሌሎች ፊልሞች ላይ ሠርቻለሁ። የተለያዩ ጋዜጦች በመዝናኛ አምዶቻቸው የመጀመሪያ ገጾች ላይ እኔን የሚመለከቱ ጽሑፎች ማውጣት ጀመሩ፤ ስለዚህ የስኬትን ጣሪያ እንደነካሁ መገመት አያዳግትም። በዚህም ጊዜ ቢሆን ግን አንድ ቅር የሚለኝ ነገር ነበር። ተዋናዮች ኩራተኞችና የፉክክር መንፈስ የተጠናወታቸው ከመሆኑም በላይ ሥነ ምግባራቸው ያዘቀጠና ግብዞች ነበሩ። በዚህ ምክንያት ሰው ማመን አቃተኝ።

በ1980 የመከር ወቅት በቤተ ዘመድ ስብሰባ ላይ ከአጎቴ ከኩልዮ ጋር ተገናኘን። በዚያን ጊዜ መዝፈኑን ለማቆም ወስኖ የነበረ ሲሆን አምላክ ቃል ስለገባው ገነት ሲናገር ሰማሁ። አጎቴ ኩልዮ የፍትህ መጓደልና ሐዘን ከምድር እንደሚወገዱና ፍቅር እንደሚነግሥ እንዲሁም የእውነተኛው አምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ነገረን። በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች በገነት ውስጥ ትንሣኤ እንደሚያገኙ መስማቴ ደግሞ ይበልጥ ስሜቴን ነካው። አባቴን እንደገና የማየቱ ተስፋ በጣም አስደሰተኝ። አባቴን እናፍቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ድጋፉንና ፍቅሩን ለማግኘት እጓጓ ነበር። እንደገና እርሱን ማግኘት እንዴት ደስ ይላል! ይሁን እንጂ በውስጤ ይህ ሊሆን እንደማይችል ይሰማኝ ነበር። አጎቴ ኩልዮ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝና እኔና እናቴ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይደረግ በነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ጋበዘን። እኛም ምናልባት እንገኝ ይሆናል የሚል መልስ ሰጠነው።

ሕይወቴን ለመለወጥ ወሰንኩ

አንድ ቀን ማታ አልጋ ውስጥ ሆኜ አጎቴ የሰጠኝን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብኩ ሲጋራ አጨሳለሁ። ከመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ብርሃን፣ ማስተዋልና ሕይወት ከአምላክ የተገኘ እንደሆነና ጨለማ፣ ሁከትና ሞት ደግሞ የእርሱ ተቃራኒ ከሆነ ወገን የመነጨ መሆኑን መገንዘብ ቻልኩ። በዚያው ምሽት ዳግም ላላጨስ ወስኜ የመጨረሻዋን ሲጋራ ካጠፋሁ በኋላ እናቴ እስክትመጣ መጠበቅ ጀመርኩ። ስትመጣ አንዳንድ ከባድ ውሳኔዎችን ላደርግ ስለሆነ እንድትደግፈኝ እያለቀስኩ ጠየቅኳት። ከዚያም ኪንግ ሊር በተባለው የሼክስፒር ድርሰት ላይ የተገለጸችውን ኮርዴልያ የተባለች ገጸ ባሕርይ ወክዬ ለመሥራት ወደምለማመድበት ቲያትር ቤት ሄጄ ሥራዬን እንደማቆም ነገርኳቸው፤ እንዲሁም ታዋቂ ተዋናይ ከነበረው የወንድ ጓደኛዬ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋረጥኩ።

ይሁን እንጂ አምላክን ማገልገልን በተመለከተ ምንም ስለማላውቅ የምጽናናበት ነገር አልነበረኝም። በዚህ ጊዜ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያዘኝ። በዘር በወረስኩት ተሰጥኦ ወይም ባገኘሁት ታዋቂነት ሳይሆን በስብእናዬ ብቻ ከአንድ ወገን እንደሆንኩ እንዲሰማኝ እንዲያደርግ አምላክን ለመንኩት። ከጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ከማቋረጤም ሌላ ከመደበኛ እንቅስቃሴዬ ራሴን አገለልኩ።

እውነተኛ ስኬት የሚገኝበት መንገድ

ግራ ተጋብቼ እያለሁ አጎቴ በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ እንደጋበዘን ትዝ አለኝ። ደወልኩለትና ስብሰባው ወደሚደረግበት ስታዲየም ይዞኝ ሄደ። በዚያ ያየሁት ነገር ልቤን በጥልቅ ነካው። መጥፎ ቃል ከአፋቸው የማይወጣ እና የማያጨሱ እንዲሁም የሌላውን ትኩረት ለመሳብ የማይሞክሩ ሥርዓታማ ሰዎችን ተመለከትኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብ የሰማሁት ሐሳብ አባቴ ከሞተ በኋላ እቤታችን ውስጥ ካገኘሁት ኢዝ ዘ ባይብል ሪሊ ዘ ወርድ ኦቭ ጎድ? * የሚል ርዕስ ካለው ትንሽ መጽሐፍ ላይ ያነበብኩትን አስታወሰኝ።

በዚሁ ጊዜ አካባቢ በአንድ ተከታታይ ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ ሆኜ እንድሠራ ተጋበዝኩ። የምወክለው ገጸ ባሕርይ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተማርኳቸው አምላካዊ ባሕርያት ጋር የማይጋጭ ስለነበር ደስ አለኝ። ከዚህ በመነሳት ሥራውን ለመሥራት ተስማማሁ። በሌላ በኩል ደግሞ “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ . .  [ብርሃን] ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በአእምሮዬ ውስጥ ይመላለስ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 6:14

አምላክን የማስደሰት ፍላጎት በውስጤ እያቆጠቆጠ ሄደ። እንዲሁም ከአጎቴና ከባለቤቱ ጋር በመንግሥት አዳራሽ ወደሚደረገው ስብሰባ የመሄድ ፍላጎት አደረብኝ። የእነርሱ ጉባኤ ከእኔ ቤት አንድ ሰዓት የሚያስኬድ ቢሆንም በቀጣዮቹ ሦስት እሁዶች በዚያው ተገኘሁ። በኋላም አጎቴ በአካባቢዬ ወደሚገኝ ጉባኤ ሊወስደኝ አሰበ። የመንግሥት አዳራሽ ስንደርስ ስብሰባው አልቆ ነበር፤ ከዚያም እዚያው ጉባኤ ካለች ኢሳቤል ከተባለች በእኔ ዕድሜ ከምትገኝ ወጣት ጋር ተዋወቅኩ። ትሑትና ደግ ወጣት ነበረች። አጎቴ፣ ሮሳሊያ ባልዴስ መሆኔን ገልጾ ሲያስተዋውቃት ቅንጣት ታክል እንኳን በስሜ ላይ አላተኮረችም። ይህም በጣም አስደሰተኝ። እኔ ቤት መጥታ መጽሐፍ ቅዱስን ልታስጠናኝ ግብዣ አቀረበችልኝ።

ከዚያም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት * የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ጀመርን። ኢሳቤል እኔ በሚመቸኝ ሰዓት ልታስጠናኝ ፈቃደኛ ነበረች። አንዳንድ ጊዜ ተከታታይ ፊልም ስሠራ እቆይ ስለነበር በጣም መሽቶም እንኳ ትጠብቀኝ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማጥናት በመፈለጌ ብቻ ለእኔ ትኩረት የሚሰጥ ሰው በማግኘቴ የአመስጋኝነት መንፈስ ይሰማኝ ነበር! ኢሳቤል ልበ ቀና፣ ታማኝ እና ጨዋ ሴት ነበረች፤ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር የሚቻለው ፍልስፍናና ሥነ ጥበብ በመማር ብቻ ነው ብዬ አስብ ነበር። ረጅም ሰዓት ለማጥናት ፕሮግራም አውጥተን የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በሳምንቱ ውስጥ ለበርካታ ቀናት እናጠናለን።

መጀመሪያ ላይ የነበሩኝን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ማስወገድ ከብዶኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ አመለካከቴ ቀስ በቀስ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይተካ ጀመር። “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” የሚለው አምላክ የገባው ቃል ምን ያህል ያበረታታኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። (መዝሙር 37:10, 11) እንዲሁም አባቴን በገነት ውስጥ እንደገና የማየቱ ተስፋ እውን እየሆነልኝ መጣ። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ . . . ይወጣሉ” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስል ነበር።—ዮሐንስ 5:28, 29

እሳተፍበት የነበረውን ተከታታይ ፊልም እንደጨረስኩ ሌላ ፊልም እንድሠራ ግብዣ ቀረበልኝ። የምካፈልባቸው ፊልሞች ይበልጥ ታዋቂ እንድሆን የሚያስችሉኝ ቢሆኑም የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ጣዖት አምልኮንና ሌሎች የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን የምደግፍ ያስመስሉብኝ ነበር። ሰይጣን ሕያው መሆኑንና ይሖዋን እንድናገለግል እንደማይፈልግ ተምሬ ስለነበር የቀረቡልኝን ግብዣዎች አልቀበልም ብዬ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። እናቴና ወንድሜ በርካታ አጋጣሚዎቼንና ብዙ ገንዘብ የማግኘት ዕድሌን ለምን እንደምተው ሊገባቸው አልቻለም። ይሁን እንጂ የባሕርይ ለውጥ እያደረግኩ መሆኔን ማስተዋል ችለው ነበር። ደስታ ያልነበረኝና በራስ መተማመን የማላውቅ ሴት ብርታት እያገኘሁና ደስተኛ እየሆንኩ መጣሁ። በመጨረሻ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ጀመርኩ!

የተማርኩትን ነገር ለሌሎች የማካፈል ጉጉት ስላደረብኝ ብዙም ሳልቆይ የአምላክን መንግሥት አስደሳች መልእክት ማስፋፋት ጀመርኩ። ብዙዎች የሚያውቁኝ በተዋናይነቴ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ ስሰብክ የቤቱ ባለቤቶች በምናገረው መልእክት ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ እቸገር ነበር። ተካፍዬበት የነበረው ተከታታይ ፊልም በቲቪ ሲታይ እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ሰዎች ቤት የደረስንባቸው ወቅቶች ነበሩ። የቤቱ ባለቤቶች በራቸው ላይ የቆምኩት እኔ መሆኔን ማመን ይቸግራቸው ነበር!

መስከረም 11, 1982 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ተጠመቅኩ። በዚያን ጊዜ እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት የጀመርኩ ሲሆን የተለያዩ ሥራዎች ከፊቴ ይጠብቁኝ ነበር። ኢሳቤል ለአገልግሎት የነበራት ቅንዓት የእኔንም ስሜት የሚያነሳሳ ነበር። በዚያን ጊዜ የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆና ይሖዋን ታገለግል ነበር። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች ስታስጠና አብሬያት መገኘት ጀመርኩ። ከኢሳቤል ጋር የቅርብ ጓደኛሞች ሆንን።

የተዋናይነት ሥራዬን ወደ መተዉ አመዝኜ ስለነበር እኔና እናቴ ዝቅተኛ ኑሮ መኖር ነበረብን። በዚያው ጊዜ አዲሱን አመለካከቴንና እምነቴን የሚገልጹ አንዳንድ ዘፈኖችን ጨምሮ የያዘውን አራተኛ አልበሜን አቀናበርኩ። ከእነዚህም መሃል አባቴን የማግኘት እርግጠኛ ተስፋ እንዳለኝ የሚገልጽ ዘፈን ይገኝበት ነበር። ለዚህ ዘፈን “ዳግም እንደማገኘው ተስፋ ተሰጥቷል” የሚል ርዕስ ሰጠሁት። ይህን ዘፈን መጀመሪያ ላይ ለእናቴ ስዘፍንላት ስሜቷ በጥልቅ ከመነካቱም በላይ ከልብ የመነጨ እምነት እንዳለኝ ተረዳች። ቀጥላም መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ፍላጎት እንዳላት ስትነግረኝ በጣም ተደሰትኩ። ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ሆነች። እስከ አሁን ድረስ በአገልግሎት ላይ በንቃት ትካፈላለች።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የሚቀርቡልኝን የሥራ ግብዣዎች አልቀበልም ለማለት እየቀለለኝ መጣ። ፈተና ሲያጋጥመኝ ወይም ተገቢ ያልሆኑ አንዳንድ ነገሮችን የማድረግ ጉጉት ሲያድርብኝ ውብ በሆነች ገነት ውስጥ ከአባቴ ጋር አብረን ሆነን ይታየኝና እምነቴና ይሖዋን ለማገልገል ያደረግኩት ቁርጥ ውሳኔ እንደገና ይጠናከራል።

አንድ ጊዜ ሲሳም ስትሪት በተባለ በስፓንኛ ቋንቋ በሚቀርብ የልጆች ፕሮግራም ላይ እንድሠራ ተጠየቅኩ። መሥራት እንደማልችል ስለተሰማኝ ለአዘጋጁ የምመራበት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ስለማይፈቅድልኝ እንደ በዓላትና የልደት ቀናት ያሉ ሥነ ሥርዓቶችን የተመለከተ ዝግጅት እንደማላስተላልፍ ነገርኩት። አዘጋጁም ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኛ ልሁን እንጂ እምነቴን እንደሚያከብርልኝና አቋሜን በዝርዝር የሚገልጽ ውል እንደምንፈራረም ገለጸልኝ። በዚህ ተስማምቼ 200 ክፍል ያለው ፊልም ሠራሁ። ለመጨረሻ ጊዜ ተዋናይ ሆኜ የሠራሁት በዚህ ፊልም ላይ ነው።

ከአንድ ሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት ጋር ያደረግኩትና ገና ያልጨረስኩት ስምምነት ነበር፤ ስለዚህ ስለ አባቴና ስለ ትንሣኤ ያቀናበርኩትን ዘፈን ጨምሮ አሥር ሥራዎቼን አስቀዳሁ። ይህን ዘፈን በቴሌቪዥንና በሰዎች ፊት ቀርቤ የመዝፈን አጋጣሚዎች አግኝቻለሁ እንዲሁም በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ስለ እምነቴ ገልጫለሁ። ይሁን እንጂ ይህ ድርጅት የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ነገር እንዳቀርብ ይጫነኝ ጀመር። ስለዚህ የሥራ መልቀቂያ አቀረብኩ።

አምላክን በማገልገል ያገኘሁት በረከት

በታኅሣሥ ወር 1983 ከኢሳቤል ጋር ሆነን በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች መሥሪያ ቤት ጎበኘን። እዚያም በኋላ የትዳር ጓደኛዬ ከሆነው ከረስል ፊሊፕስ ጋር ተዋወቅኩ። ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ደብዳቤ ተጻጻፍን። ረስል የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል በጀመርኩበት ዕለት ከኒው ዮርክ ድረስ ጽጌረዳ አበባ እንደላከልኝ ፈጽሞ አልረሳም!

ለአንድ ዓመት ከኢሳቤል ጋር አቅኚ ሆኜ ካገለገልኩ በኋላ እርሷ ሜክሲኮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንድታገለግል ተጋበዘች። ስለ አዲሱ ሥራዋ የምትነግረኝ ነገር በውስጤ ይበልጥ የማገልገልና ይሖዋ ከፈቀደም ቤቴል የመግባት ምኞት ቀሰቀሰብኝ።

ረስልም እንዲሁ ሌላ በረከት ሆኖልኛል። ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለው ፍቅር ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት አክብሮት እንዲኖረኝ አስችሎኛል። ቤቴልን በጣም ይወድ የነበረ ሲሆን በብሩክሊን ቤቴል ለሦስት ዓመት አገልግሏል። ከተጋባን በኋላ በኮሎራዶ፣ ዩ ኤስ ኤ በዘወትር አቅኚነት አብረን አገልግለናል። በኋላም በሌሎች አገሮች በሚካሄደው የአዳዲስ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ግንባታ ላይ ለመካፈል ዓለም አቀፍ የግንባታ ሠራተኞች እንድንሆን ተጋበዝን። በሜክሲኮ እንድናገለግል መመደባችንን ስንሰማ በጣም ተደሰትን! በሚያዝያ ወር 1990 በሜክሲኮ የሚገኘው ቤቴል ቤተሰብ አባላት የመሆን አስደሳች መብት አገኘን። የረስል ምሳሌነት በጣም አበረታቶኛል። የመንግሥቱን ፍላጎት ለማስቀደም ሲል መኖሪያ አገሩንና ቤተሰቡን ትቶ ሜክሲኮ እንዲመጣ ያነሳሳው የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያስደንቀኝ ነበር።

እኔም ሆንኩ ረስል በሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ የማገልገል መብት በማግኘታችን በጣም ተደስተን ነበር። ሆኖም ባረገዝኩ ጊዜ ነገሮች በድንገት ተለወጡ። ፈጽሞ እንደዚያ ይሆናል ብለን አላሰብንም ነበር። የሆነ ሆኖ ልጆቻቸውን በእውነት መንገድ የሚያሳድጉ ወላጆችን እናደንቅ ነበር፤ እኛም ይህንን አዲስ ሥራ በደስታ ተቀበልን። በጥቅምት ወር 1993 ኤቫን ተወለደ፤ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ደግሞ ጊያና ተወለደች። ልጆችን ማሳደግ ያለማሰለስ ብርቱ ጥረት ማድረግን ቢጠይቅም የ11 ዓመቱ ወንድ ልጃችንና የ8 ዓመቷ ሴት ልጃችን በአገልግሎት ተሰማርተው እምነታቸውን ሲገልጹ ስንመለከት እንደተካስን ይሰማናል።

በአሁኑ ጊዜ ረስል በአካባቢው የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ኮሚቴ ውስጥ እያገለገለ ሲሆን እኔም እንደገና የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀምሬያለሁ። ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ 12 የቤተሰባችን አባላትና ሌሎች 8 ሰዎች እውነትን አውቀው ይሖዋን እንዲያገለግሉ መርዳት ችያለሁ።

ልጆቼ “እማማ ሙያሽን ለመተው ከብዶሽ ነበር?” ብለው ሲጠይቁኝ “ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቆጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን አጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቆጥራለሁ” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት እጠቅስላቸዋለሁ። (ፊልጵስዩስ 3:8) ይሖዋ ከንቱና ዓላማ ቢስ ሕይወት ከመምራት ስላዳነኝና ግሩም ከሆኑት ሕዝቦቹ ጋር እንድቀላቀል ስለፈቀደልኝ በጣም አመሰግነዋለሁ! በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሰጠን ስፍር ቁጥር የሌለው በረከት እርሱን ከማመስገን ቦዝኜ አላውቅም። ብዙ ጊዜ ስለ አባቴ የጻፍኩትን ዘፈን በደስታ እዘፍናለሁ። ዳግም እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.21 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

^ አን.24 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንድ ዓመት ልጅ ሳለሁ ከወላጆቼና ከወንድሜ ጋር

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርቱሮ ካስትሮ ኤንድ ሂዝ ካስትሮስ 76 የተባለው ባንድ አጅቦኝ ስዘፍን

[ምንጭ]

Angel Otero

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቤ ጋር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Activa, 1979