በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገር መሆን የደካማነት ምልክት ነው?

ገር መሆን የደካማነት ምልክት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ገር መሆን የደካማነት ምልክት ነው?

“የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር . . . መሆን ይገባዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:24

ከስሜት ሕዋሳታችን አንዱ የሆነውን የመዳበስ ስሜት የምናዳብረው ገና በእናታችን ማህፀን ሳለን ነው። ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ እናታችን ስትደባብሰን በጣም ደስ ይለናል። በልጅነት ዕድሜያችን ፈገግ የማለትና ስሜታዊ እድገት የማድረግ ችሎታችን አልፎ ተርፎም የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ያለን ፍላጎት ከወላጆቻችን በምናገኘው ፍቅር ላይ የተመካ ነው።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን ሰዎች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ ትንቢት ተናግሯል። ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዲሁም “ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ” ስለሆኑ እንደ ደግነትና ርኅራኄ ያሉት የገርነት መገለጫ የሆኑ ባሕርያት እምብዛም አይታዩም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ኃይለኛና አንጀተ ደንዳና መሆን እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ገር መሆን የደካማነት ምልክት ነው ይላሉ። ታዲያ ገር መሆን በእርግጥ የደካማነት ምልክት ነው?

ገር ሆኖም ኃይለኛ

ይሖዋ አምላክ ደፋር “ተዋጊ” እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፀአት 15:3) የመጨረሻው የኃይል ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። (መዝሙር 62:11፤ ሮሜ 1:20) ሆኖም ይሖዋ ኃይለኛ መሆኑ ለታማኙ ኢዮብ ወሮታውን ሲከፍለው ከፍተኛ ‘ርኅራኄና ምሕረት’ ከማሳየት አላገደውም። (ያዕቆብ 5:11) ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያደረገላቸውን ነገር አንዲት የምታጠባ እናት ‘ለወለደችው ልጅ’ ካላት የመሳሳት ስሜት ጋር በማመሳሰል እነሱን በከፍተኛ ርኅራኄ እንደያዛቸው ገልጿል።—ኢሳይያስ 49:15

ኢየሱስም በተመሳሳይ ውስጣዊ ጥንካሬም ሆነ ገርነት የተላበሰ ነበር። በዘመኑ የነበሩትን ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች በኃይል አውግዟቸዋል። (ማቴዎስ 23:1-33) በተጨማሪም ስግብግብ ገንዘብ ለዋጮችን ከቤተ መቅደሱ ያባረራቸው በኃይል ነበር። (ማቴዎስ 21:12, 13) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምግባረ ብልሹነትና ለስግብግብነት የነበረው ጥላቻ አንጀተ ደንዳና አድርጎት ነበር? በጭራሽ! ኢየሱስ የሚታወቀው ለሰዎች በሚያሳየው የገርነት ባሕርይ ነው። እንዲያውም ስለ ራሱ የተናገረው “ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ” ዶሮ አድርጎ ነው።—ሉቃስ 13:34

የጥንካሬ መለኪያው ኃይለኝነት ነው ወይስ ገርነት?

እውነተኛ ክርስቲያኖች “እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” በመልበስ ክርስቶስን እንዲመስሉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ኤፌሶን 4:20-24 የ1954 ትርጉም) ሸርጣን የሚባለው የዓሣ ዝርያ እድገቱን ለመቀጠል የሰውነቱን ቅርፊት ገልፍፎ እንደሚጥል ሁሉ እኛም ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቀን እንድንጥል’ ተመክረናል። (ቆላስይስ 3:9) ይሁን እንጂ አሮጌውን ቅርፊት ገልፍፎ ከጣለ በኋላ ሰውነቱ መልሶ ከሚቆረፍደው ሸርጣን በተቃራኒ “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ . . . ትዕግሥትን” ለዘለቄታው እንድንለብስ ታዘናል። (ቆላስይስ 3:12) እንግዲያው ገርነት ከምንታወቅባቸው ባሕርያት መካከል አንዱ መሆን ይኖርበታል።

በባሕርያችን ለስላሳ መሆናችን የደካማነት ምልክት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ እንዲህ ዓይነት ስብዕና መላበስ ‘[በይሖዋ] መንፈስ በኩል በውስጥ ሰውነታችን ጠንካራ’ መሆንን ይጠይቃል። (ኤፌሶን 3:16) ለምሳሌ ያህል ሊ የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል:- “ከጥቂት ጊዜ በፊት ጨካኝና ክፉ ሰው ነበርኩ። ገላዬን ተበስቼ ጌጣጌጥ አድርጌበት ስለነበር ገና ሲያዩኝ አስፈራ ነበር። ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ቆርጬ ተነስቼ ነበር፤ እንዲሁም የምፈልገው ነገር እንዲደረግልኝ አስጸያፊ ቃላት ከመሰንዘርና ጉልበት ከመጠቀም ወደኋላ የማልል፣ ርኅራኄ የሚባል ነገር የማላውቅ ሰው ነበርኩ።” ይሁን እንጂ ሊ ከአንድ የሥራ ባልደረባው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረና ይሖዋን ከማወቅ አልፎ መውደድም ቻለ። አሮጌ ባሕርይውን ገፎ በመጣል ራስን መግዛት ተማረ። አሁን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ጊዜውን በመሠዋት ለእነሱ ያለውን ፍቅር ያሳያል።

በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስም ዓላማውን ለማሳካት የኃይል እርምጃ የሚወስድ “ዐመፀኛ” ሰው ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:13፤ የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2) ሆኖም ጳውሎስ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳዩትን ምሕረት እንዲሁም ፍቅር ሲገነዘብ እነዚህን ባሕርያት ለማንጸባረቅ ጥረት በማድረግ አመስጋኝነቱን ገለጸ። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ምንም እንኳን ጳውሎስ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥብቅ ይከተል የነበረ ቢሆንም ሌሎችን በገርነት መያዝ እንዳለበት ተማረ። በእርግጥም ጳውሎስ ለወንድሞቹ የነበረውን ልባዊ ፍቅር ከመግለጽ ወደኋላ አይልም ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 20:31, 36-38፤ ፊልሞና 12

ገር ለመሆን የሚያስችለውን ጥንካሬ ማግኘት

የሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ የሊ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ገርነት ለማሳየት በባሕርይው ደካማ መሆን አለበት ማለት አይደለም። እንዲያውም ሐቁ የዚህ ተቃራኒ ነው። ገርነትን ለማዳበር የአስተሳሰብና የተግባር ለውጥ ማድረግ እንዲሁም ‘ክፉን በክፉ የመመለስን’ ሥጋዊ ዝንባሌ መዋጋት ስለሚያስፈልግ ውስጣዊ ጥንካሬ ይጠይቃል።—ሮሜ 12:2, 17

እኛም የአምላክን ቃል አዘውትረን በማንበብና ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳዩን ፍቅርና ምሕረት ላይ በማሰላሰል ከአንጀት የመራራትን ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። እንዲህ በማድረግ የአምላክ ቃል ያለው ኃይል ልባችንን እንዲያለሰልስልን እንፈቅዳለን። (2 ዜና መዋዕል 34:26, 27፤ ዕብራውያን 4:12) እንግዲያው አስተዳደጋችን ወይም በሕይወታችን ውስጥ ያሳለፍነው ነገር ምንም ያህል መጥፎ ቢሆንም “ለሰው ሁሉ ገር” መሆንን ማዳበር እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 2:24

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ጥሩ አባት ለልጆቹ የገርነት ባሕርይ ያሳያል