በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት

ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት

የአምላክ ልጅ ከልጆች ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ ነበረው? እንዲህ ያልተሰማቸው አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። በአንድ ወቅት ሕፃናቶች ወደ ኢየሱስ እንዳይቀርቡ ለመከልከል ሞክረው ነበር። ኢየሱስ ግን “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” በማለት መልስ ሰጥቷል። ከዚያም ብዙ ሕፃናትን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ተቀብሎ ያናግራቸው ጀመር። (ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ እንዲህ በማድረግ ለልጆች ትኩረት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል። ወላጆች በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው? ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍና ተገቢውን ሥልጠና በመስጠት ነው።

እርግጥ ነው፣ ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ ወላጆች ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ኮትኩተው ለማሳደግ ይጥራሉ እንጂ በልጆቻቸው ላይ በደል አያደርሱም። ወላጆች ለልጆቻቸው አክብሮትና አሳቢነት ማሳየታቸው ‘ተፈጥሯዊ’ ነው ሊባል ይችላል። ነገር ግን በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ‘የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው’ እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቅቋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3 NW) ለልጆቻቸው ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳዩ ወላጆችም ቢሆኑ የተሻሉ ወላጆች ለመሆን ሁልጊዜ ሊማሩት የሚገባ ነገር ይኖራል። እንግዲያው ለልጆቻቸው የሚበጀውን ሁሉ ለማድረግ ለሚጥሩ ወላጆች የሚከተሉት ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቀርበውላቸዋል።

ልጆቻችሁን ሳታስቆጡ አሠልጥኗቸው

የታወቁ አስተማሪና የአእምሮ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሮበርት ኮልስ በአንድ ወቅት “በልጅ ውስጥ በማደግ ላይ ያለ የሥነ ምግባር ስሜት አለ። እኔ እንደሚመስለኝ ይህ የሥነ ምግባር ስሜት አምላክ የሰጣቸው ሲሆን ልጆች ደግሞ የሥነ ምግባር መመሪያ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ታዲያ ይህን የሥነ ምግባር መመሪያ የማግኘት ረሃባቸውንና ጥማታቸውን ማርካት ያለበት ማን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በኤፌሶን 6:4 ላይ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። ይህ ጥቅስ በልጆች ልብ ውስጥ ለአምላክ ፍቅርና ለመለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ጥልቅ አድናቆት የመትከል ዋና ኃላፊነት የሰጠው በተለይ ለአባት መሆኑን አስተውለሃል? በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 1 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ልጆች ‘ለወላጆቻቸው መታዘዝ’ እንዳለባቸው ሲናገር ሁለቱንም ማለትም አባትንም እናትንም ጠቅሷል። *

እርግጥ ነው፣ አባት በማይኖርበት ጊዜ እናት ይህንን ኃላፊነት የመቀበል ግዴታ አለባት። ብዙ ነጠላ እናቶች ልጆቻቸውን በይሖዋ አምላክ ምክርና ተግሣጽ በማሳደግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ነገር ግን እናትየዋ ክርስቲያን የሆነ ባል ካገባች ግንባር ቀደም መሆን ያለበት እሱ ነው። በዚህ ጊዜ እናት ልጆቻቸውን በመገሠጹና በማሠልጠኑ ረገድ የአባትየውን አመራር በፈቃደኝነት መከተል ይኖርባታል።

ልጆቻችሁን ‘ሳታስቈጧቸው’ ማሠልጠን ወይም መገሠጽ የምትችሉት እንዴት ነው? እያንዳንዱ ልጅ የተለያየ እንደመሆኑ መጠን ለሁሉም የሚሆን አንድ ደንብ ማውጣት አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ወላጆች ተግሣጽ የሚሰጡበትን መንገድ በጥንቃቄ ማሰብና ሁልጊዜ ለልጆቻቸው ፍቅርና አክብሮት ማሳየት ይኖርባቸዋል። የሚያስገርመው ነገር ልጆችን ያለማስቆጣት ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቆላስይስ 3:21 ላይም በድጋሚ ተገልጿል። እዚያ ላይ “ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው” ሲል አባቶችን ያሳስባቸዋል።

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ይጮኹባቸዋል። ይህ ደግሞ ልጆችን ያበሳጫቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ሲል አጥብቆ ያሳስባል። (ኤፌሶን 4:31 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቃት ያለው፣ ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል” ይላል።—2 ጢሞቴዎስ 2:24

ጊዜያችሁን ስጧቸው

ለልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት ሲባል የራስን ደስታና ምቾት ለልጆች ደኅንነት ብሎ በፈቃደኝነት መሥዋዕት ማድረግንም ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር” ይላል።—ዘዳግም 6:6, 7

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ወላጆች ኑሮን ለማሸነፍ ሲባዝኑ ስለሚውሉ ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ለማግኘት ይቸገራሉ። ሆኖም የዘዳግም መጽሐፍ ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አጥብቆ ያሳስባል። ይህንን ለማድረግ በጥሩ ሁኔታ መደራጀት እንዲሁም መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቃል። የሆነ ሆኖ ልጆች እንደዚህ ያለ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።

ከ12,000 በሚበልጡ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት የተገኘውን ውጤት ተመልከት። ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎች የደረሱበት መደምደሚያ “ከወላጆቻቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ልጆች በተሻለ ሁኔታ ጤናሞች እንደሚሆኑና ከጎጂ ጠባይ እንደሚታቀቡ” የሚያረጋግጥ ነው። አዎን፣ ልጆች የወላጆቻቸውን ትኩረት ይፈልጋሉ። በአንድ ወቅት አንዲት እናት ልጆቿን “የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ ማግኘት እንድትችሉ ዕድል ቢሰጣችሁ ከሁሉ ነገር በላይ ምን ትጠይቁ ነበር?” ስትል ጠየቀቻቸው። አራቱም ልጆች “ከእማማና ከአባባ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ” ብለው መለሱ።

ስለዚህ ኃላፊነት የሚሰማህ ወላጅ ከሆንክ የልጆችህን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ታደርጋለህ። ይህ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማርካትንና ከወላጆቻቸው ጋር የጠበቀ ጓደኝነት የመመሥረት ምኞታቸውን ማሳካትን ያጠቃልላል። ይህ ማለት ልጆች ሲያድጉ ባለሞያ፣ ሰው አክባሪና ታማኞች በመሆን ሌሎችን በደግነት የሚይዙ እንዲሁም ለፈጣሪያቸው ክብር የሚያመጡ እንዲሆኑ መርዳት ማለት ነው። (1 ሳሙኤል 2:26) አዎን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ተግሣጽ እየሰጡ በአምላክ መንገድ የሚያሠለጥኗቸው ከሆነ ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ ነው ለማለት ያስችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 እዚህ ላይ ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ጎነፍሲን የሚል ሲሆን ይህም ጎነስ ከተባለው ቃል የመጣ ነው። ትርጉሙም “ወላጅ” ማለት ነው። በቁጥር 4 ላይ ግን “አባቶች” የሚል ትርጉም ያለውን ፓተረስ የተባለ የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጮኽና ማንባረቅ ልጅን ሊያሳቅቅና ሊያስጨንቅ ይችላል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጆችህ ጋር ጊዜ አሳልፍ