በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት የተገነባበት አስደናቂ ሰንሰለት

ሕይወት የተገነባበት አስደናቂ ሰንሰለት

ሕይወት የተገነባበት አስደናቂ ሰንሰለት

ሰውነትህ በአጉሊ መነጽር ብቻ በሚታዩ ሰንሰለቶች የተዋቀረ እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ? እንዲህ አስበህ አታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዘ ዌይ ላይፍ ዎርክስ የተባለው መጽሐፍ “ሕይወት የተገነባባቸው በጣም ጥቃቅን ነገሮች እንደ ሰንሰለት የተሳሰሩ ናቸው” በማለት ገልጿል። በመሆኑም ከእነዚህ ሰንሰለቶች ውስጥ ጥቂቶቹ እንኳ ትንሽ እንከን ቢኖርባቸው በጤናችን ላይ ከባድ ችግር ሊከሰት ይችላል። እነዚህ ሰንሰለቶች ምንድን ናቸው? ተግባራቸውን የሚያከናውኑት እንዴት ነው? ከጤንነታችንና ከደኅንነታችን ጋር የሚያያዙትስ እንዴት ነው?

እነዚህ ሰንሰለት መሰል ሞለኪዩሎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ። በዚህ ርዕስ ላይ ስለ ፕሮቲን ሞለኪዩሎች እንመለከታለን። ሌሎቹ የሞለኪዩል ዓይነቶች የዘርን ጉዳይ የሚመለከቱ መረጃዎችን የሚይዙትና የሚያስተላልፉት ዲ ኤን ኤ እና አር ኤን ኤ ናቸው። በእርግጥ ሁለቱም የሞለኪዩል ዓይነቶች እርስ በርስ ተዛማጅነት አላቸው። እንዲያውም የዲ ኤን ኤ እና የአር ኤን ኤ አንዱ ዋነኛ ተግባር ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ በጣም ብዙ ዓይነት ፕሮቲኖችን ማምረት ነው።

አዋሃጆች፣ ተከላካዮችና ምሰሶዎች

በሰውነታችን ውስጥ ከሚገኙት ትልልቅ ሞለኪዩሎች መካከል ፕሮቲኖች በዓይነት እጅግ የተለያዩ ናቸው። ፕሮቲን ሲባል ፀረ እንግዳ አካላትን፣ ኢንዛይሞችን እንዲሁም ለሰውነት ክፍሎቻችን መልእክት የሚያስተላልፉ፣ እንደ ምሰሶና እንደ መጓጓዣ ሆነው የሚያገለግሉ ፕሮቲኖችን ያጠቃልላል። በጣም በርካታ ፀረ እንግዳ አካላት ወይም ኢሚውኖግሎቡሊንስ ሰውነታችንን እንደ ባክቴሪያና ቫይረሶች ከመሳሰሉ ወራሪ ኃይሎች ጥቃት ይከላከላሉ። ግሎቡሊን የሚባሉ ሌሎች ፕሮቲኖች ደግሞ በአደጋ ምክንያት የተጎዱ ደም ሥሮችን ይጠግናሉ።

አዋሃጅ ሆነው የሚያገለግሉ ኢንዛይሞች ከምግብ መፈጨት ጋር የተያያዙና ሌሎች ተመሳሳይ ኬሚካላዊ ውህደቶች እንዲፋጠኑ ያደርጋሉ። ዘ ትሬድ ኦቭ ላይፍ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ “ኢንዛይሞች ባይኖሩ ኖሮ የበላነው ምግብ ለመፈጨት 50 ዓመት ስለሚፈጅበት እንራብ ነበር” በማለት ገልጿል። የተለያየ ተግባር ያላቸው ፕሮቲኖች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በቅንጅት ነው። ለምሳሌ ማልቴስ የተባለው ኢንዛይም ማልቶስ ተብሎ የሚጠራውን የስኳር ዓይነት ወደ ሁለት የግሉኮስ ሞለኪዩሎች ይቀይራል። ላክቴስ የተባለው ኢንዛይም ላክቶስ የሚባለውን በወተት ውስጥ የሚገኝ ስኳር ያዋህዳል። ሌሎች ኢንዛይሞች ደግሞ አቶሞችንና ሞለኪዩሎችን በማቀላቀል አዲስ ነገር ይፈጥራሉ። ይህንንም የሚያከናውኑት በከፍተኛ ፍጥነት ነው። አንድ ሞለኪዩል ያለው ኢንዛይም በአንድ ሴኮንድ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ኬሚካላዊ ውህደቶችን መፍጠር ይችላል!

አንዳንድ ፕሮቲኖች ከሆርሞኖች የሚመደቡ ሲሆን መልእክት አስተላላፊ ሆነው ያገለግላሉ። እነዚህ ፕሮቲኖች በደም ውስጥ ሲሰራጩ አንዳንድ የሰውነታችን ክፍሎች ሥራቸውን በጣም እንዲያፋጥኑ አሊያም እንዲቀንሱ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ኢንሱሊን፣ ሴሎች የኃይል ምንጭ የሚሆናቸውን ግሉኮስ በፍጥነት እንዲመጥጡ ያነቃቃቸዋል። ለስላሳ አጥንት (ካርትሌጅ)፣ ፀጉር፣ ጥፍርና ቆዳ በዋነኝነት የተሠሩት እንደ ኮላገን እና ኬራቲን ባሉ ምሰሶን የመሰለ ድርሻ ባላቸው ፕሮቲኖች ነው። እነዚህ ፕሮቲኖች ሁሉ “የሴሎች ምሰሶ፣ ማገር፣ ኮምፖንሳቶ፣ ማጣበቂያና ምስማር ናቸው” በማለት ዘ ዌይ ላይፍ ዎርክስ ዘግቧል።

በሴል ሽፋን (ሴል ሜምብሬንስ) ላይ የሚገኙ የማጓጓዝ ሥራ ያላቸው ፕሮቲኖች አንዳንድ ነገሮች ወደ ሴሎች እንዲገቡ ወይም ከሴሎች እንዲወጡ በማድረግ እንደ ፓምፕና ቦይ ሆነው ያገለግላሉ። አሁን ደግሞ ፕሮቲኖች ከምን እንደተሠሩና እንደ ሰንሰለት መቆላለፋቸው ከሚያከናውኑት ተግባር ጋር ያለውን ዝምድና እንመልከት።

በቀላሉ የተሠራ ውስብስብ ነገር

ፊደል ለብዙ ቋንቋዎች መሠረታዊ የሆነ ነገር ነው። ፊደላት ተሰባስበው ቃላት ይመሠረታሉ። ቃላትም በተራቸው ተዳምረው ዓረፍተ ነገር ይሠራሉ። በሞለኪዩል ደረጃም ሕይወት ተመሳሳይ ሥርዓት ይከተላል። ዋነኛውን “ፊደል” የሚያቀርበው ዲ ኤን ኤ ነው። የሚገርመው ነገር “ፊደላቱ” ኤ፣ ሲ፣ ጂ እና ብቻ ናቸው፤ እነዚህ ፊደላት አደኒን፣ ሳይተሲን፣ ጉዋኒን እና ታይሚን የተባሉ መሠረታዊ ኬሚካሎች ምህጻረ ቃላት ናቸው። ፊደላት ተሰባስበው ቃላትን እንደሚፈጥሩ ሁሉ ዲ ኤን ኤ በአር ኤን ኤ አማካኝነት ከእነዚህ አራት መሠረታዊ ኬሚካሎች አሚኖ አሲድ እንዲዘጋጅ ያደርጋል። ይሁን እንጂ አሚኖ አሲዶች ምንጊዜም የሚይዙት ሦስት ፊደላትን ብቻ በመሆኑ ከተለመደው የቃላት ሁኔታ ይለያሉ። “ፕሮቲን መገጣጠሚያ ማሽኖች” የሚባሉት ራይቦዞሞች አሚኖ አሲዶችን አንድ ላይ ይገጣጥማሉ። በውጤቱም ሰንሰለቶቹ ወይም ፕሮቲኖቹ ዓረፍተ ነገር የሠሩ ያህል ይሆናሉ። በጽሑፍ ከሚሰፍር ወይም በቃል ከሚነገር ዓረፍተ ነገር በበለጠ አንድ ፕሮቲን ከ300 እስከ 400 የሚያህሉ አሚኖ አሲዶችን ሊይዝ ይችላል።

አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው በተፈጥሮ ውስጥ በአጠቃላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሚኖ አሲድ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን በአብዛኞቹ ፕሮቲኖች ውስጥ የሚገኙት ግን ከ20 አይበልጡም። እነዚህ አሚኖ አሲዶች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ውሁዶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ለምሳሌ 20 የአሚኖ አሲድ ዓይነቶች እርስ በርስ ተያይዘው የ100 አሚኖ አሲዶች ርዝመት ያለው ሰንሰለት ቢሠሩ ይህ ሰንሰለት 10100 (ከ1 በኋላ 100 ዜሮዎች ተጨምረው) በላይ ብዛት ባላቸው የተለያዩ መንገዶች ሊደራጅ ይችላል!

የፕሮቲኖች ቅርጽና ተግባር

የአንድ ፕሮቲን ቅርጽ የሚወሰነው በሴል ውስጥ በሚጫወተው ሚና ነው። የአሚኖ አሲዶች ሰንሰለት በፕሮቲን ቅርጽ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ላላ ብለው ከተያያዙት የብረት ወይም የፕላስቲክ ሰንሰለቶች በተለየ መንገድ አሚኖ አሲዶች በተለያየ አቅጣጫ እርስ በርስ በመቆላለፍ አንድ ወጥ የሆነ ቅርጽ ይሠራሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የተጠማዘዘ የስልክ ሽቦ ወይም ደግሞ የቀሚስ ሽንሽን ይመስላሉ። እነዚህ ንድፎች “ይጣመሩና” ወይም ይያያዙና ሦስት የተለያየ ገጽ ያለው ውስብስብ መልክ ይፈጥራሉ። ፕሮቲን አንድ ቅርጽ የሚይዘው እንዲያው በአጋጣሚ ነው። በእርግጥ የፕሮቲኑን ቅርጽ የሚወስነው የሚያከናውነው ተግባር ነው፤ ይህ መሆኑ በግልጽ የሚታየው በአሚኖ አሲዱ ላይ እንከን በሚኖርበት ጊዜ ነው።

ሰንሰለቱ እንከን ሲኖርበት

በፕሮቲኖች ውስጥ የሚገኙት የአሚኖ አሲድ ሰንሰለቶች እንከን ሲኖርባቸው ወይም እጥፋታቸው የተሳሳተ በሚሆንበት ጊዜ ሲክል ሴል አኒሚያ የተባለ የደም ማነስና ሲስቲክ ፋይብሮሲስ የተባለውን በሽታ ጨምሮ ለበርካታ ሕመሞች መከሰት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ሲክል ሴል አኒሚያ የተባለው በዘር የሚተላለፍ የደም ማነስ በሽታ የሚከሰተው በቀይ የደም ሴል ውስጥ የሚገኙት ሄሞግሎቢኖች ከወትሮው የተለየ ቅርጽ ሲኖራቸው ነው። ሄሞግሎቢን በአራት ሰንሰለት የተከፈሉ 574 አሚኖ አሲዶችን ይዟል። ከአራቱ ሰንሰለቶች መካከል በሁለቱ ውስጥ የሚገኝ አንድ አሚኖ አሲድ ብቻ እንኳ ቅደም ተከተሉ ቢለወጥ ጤናማ የነበረው ሄሞግሎቢን የማጭድ ቅርጽ ይይዛል። በአብዛኛው ሲስቲክ ፋይብሮሲስ በሽታ የሚከሰተው በአሚኖ አሲዶች ሰንሰለት ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዘው ፌነላለኒን የተባለው አሚኖ አሲድ በፕሮቲን ውስጥ ሳይኖር በሚቀርበት ጊዜ ነው። ይህ ጉድለት፣ አንጀትንና ሳምባን የሚሸፍነው ዝልግልግ ሽፋን ሊኖረው የሚገባውን የጨውና የውኃ መጠን በማዛባት ሽፋኑ ከተለመደው በላይ እንዲወፍርና የሚያጣብቅ እንዲሆን ያደርጋል።

የአንዳንድ ፕሮቲኖች በከፍተኛ ሁኔታ መጓደል ወይም አለመኖር እንደ አልቢኒዝም እና ሄሞፊሊያ ለመሳሰሉ በሽታዎች ያጋልጣል። አልቢኒዝም በሽታ ማለትም ለሰውነት የሚያስፈልጉትን ቀለሞች ያለማምረት ችግር የሚከሰተው ታይሮሲኔዝ የሚባለው ፕሮቲን ሲበላሽ ወይም ሳይኖር ሲቀር ነው። ይህም በአብዛኛው በሰዎች ዓይን፣ ፀጉርና ቆዳ ላይ በሚገኘው ሜላኒን የሚባል ጥቁር ቡናማ ቀለም ምርት ላይ ቀውስ ይፈጥራል። ሄሞፊሊያ የሚከሰተው ደግሞ ለደም መርጋት አስፈላጊ የሆኑ ፕሮቲኖች መጠን ዝቅ ሲል ወይም ጨርሶ ሳይኖሩ ሲቀር ነው። የፕሮቲኖች መበላሸት ከሚያስከትላቸው ሌሎች ችግሮች መካከል ሁለቱ የላክቶስ አለመስማማትና መስኪዩላር ዲስትሮፊ የሚባል በሽታ ናቸው።

በሽታ እንዴት እንደሚከሰት ለማወቅ የሚያስችል ንድፈ ሐሳብ

ሳይንቲስቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንከን ባለው ፕሪዮን የተባለ ፕሮቲን ምክንያት እንደሚከሰት በሚታመን በሽታ ላይ ትኩረት አድርገዋል። የተበላሹ የፕሮቲን ፕሪዮኖች ከጤነኛ ፕሪዮኖች ጋር ሲቆራኙ ፕሮቲኑ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዲታጠፍ ያደርጉታል ተብሎ ይታሰባል። ሳይንቲፊክ አሜሪካ የተባለ መጽሔት በዚህ ምክንያት ስለሚከተለው ችግር ሲዘግብ “ይህ ችግር በሽታው እንዲሰራጭ የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ በጀርም ምክንያት የሚመጡ አዳዲስ በሽታዎች እንዲከሰቱ ያደርጋል” ብሏል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950ዎቹ የሰዎችን ትኩረት የሳበው በፓፑዋ ኒው ጊኒ የተከሰተው በሽታ ፕሪዮን ለሚያስከትለው ሕመም ምሳሌ ይሆነናል። በአንዳንድ ገለልተኛ ክልሎች የሚኖሩ ጎሳዎች በሃይማኖታዊ እምነቶች ምክንያት የሰው ሥጋ ይበላሉ፤ ይህም ክሮይትስፌለት ጃኮፕ ከተባለው ሕመም ጋር ተመሳሳይ ምልክት ላለው ኩሩ ለተባለ በሽታ ዳረጋቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ጎሳዎች ይህን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት መፈጸም በተዉበት ጊዜ ኩሩ በሽታ መከሰቱን በፍጥነት እየቀነሰ መጣ፤ እንዲያውም አሁን ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ለማለት ይቻላል።

አስደናቂ ንድፍ!

ደስ የሚለው ነገር ፕሮቲኖች በአብዛኛው በትክክል የታጠፉ ከመሆናቸውም በላይ በሚያስደንቅ ስምምነትና ቅልጥፍና ተግባራቸውን በትክክል ያከናውናሉ። በሰውነታችን ውስጥ ከ100,000 በላይ የፕሮቲን ዓይነቶች መኖራቸውና ሁሉም በሺዎች በሚቆጠሩ የተለያዩ መንገዶች ተወሳስበው እንደ ሰንሰለት መያያዛቸው ሲታሰብ በጣም ያስደንቃል።

ስለ ፕሮቲኖች ገና ብዙ ያልተደረሰባቸው ነገሮች አሉ። ተመራማሪዎች ፕሮቲኖች ከአሚኖ አሲድነት ደረጃ አንስቶ ምን ዓይነት ቅርጽ እንዳላቸው በይበልጥ ለማወቅ ሲሉ ውስብስብ የሆኑ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን አዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ ስለ ፕሮቲኖች የምናገኘው በጣም ጥቂት እውቀት እነዚህ “ሕይወት የተገነባባቸው ሰንሰለቶች” በከፍተኛ ሁኔታ መደራጀታቸውን ብቻ ሳይሆን እጅግ ታላቅ የማሰብ ችሎታ እንደሚንጸባረቅባቸው ያሳያል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የፕሮቲኖች “ኮድ”

የፖስታ አገልግሎት የሚሰጡ ብዙ ድርጅቶች አገልግሎታቸውን በፍጥነት ለማከናወን እንዲችሉ በደብዳቤ ላይ አድራሻ ብቻ ሳይሆን ኮድም ተጨምሮ እንዲጻፍ ይጠይቃሉ። ፈጣሪም ፕሮቲኖች በሴሎች ውስጥ የሚጓዙበትን ትክክለኛ መንገድ እንዲያገኙ ለማድረግ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ተጠቅሟል። ሴሎች እስከ ቢሊዮን የሚደርሱ ፕሮቲኖችን ስለሚይዙ ይህ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ያም ሆኖ አዳዲስ ፕሮቲኖች ልዩ የሆነ ሞለኪዩላዊ “ኮድ” (በርካታ አሚኖ አሲዶች አንድ የጋራ መለያ) ስላላቸው ወዴት መሄድ እንደሚገባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።

የሴል ተመራማሪ የሆኑት ጉንተር ብሎበል ይህን አስደናቂ ነገር በምርምር ስለደረሱበት በ1999 የኖቤል ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። ብሎበል በምርምር ለደረሱበት ነገር መሸለማቸው የሕያው ሴል ፈጣሪና ውስብስብ የሆነው ሞለኪዩል አደራጅ ይበልጥ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ አያሳይም?—ራእይ 4:11

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፕሮቲኖች የሚሠሩት እንዴት ነው?

ሴል

1 በሴል ኒዩክለስ ውስጥ የሚገኘው ዲ ኤን ኤ ለእያንዳንዱ ፕሮቲን የሚሆን መመሪያ ይዟል

ዲ ኤን ኤ

2 አንድ የዲ ኤን ኤ ክፍል ሲከፈት መልእክት አስተላላፊ አር ኤን ኤ የዘርን ጉዳይ የሚመለከት መረጃ ይቀዳል

መልእክት አስተላላፊ አር ኤን ኤ

3 “መልእክት አንባቢና ፕሮቲን ገጣጣሚ” የሆኑት ራይቦዞሞች ከአር ኤን ኤ ጋር ይያያዛሉ

4 አጓጓዥ አር ኤን ኤዎች አሚኖ አሲዶችን ወደ ራይቦዞም ተሸክመው ያደርሳሉ

ነጠላ አሚኖ አሲዶች

አጓጓዥ አር ኤን ኤዎች

ራይቦዞም

5 ራይቦዞም በአር ኤን ኤ ላይ ያለውን መልእክት “ያነብብና” በመመሪያው መሠረት ነጠላ አሚኖ አሲዶችን አንድ ላይ በማቆራኘት የፕሮቲን ሰንሰለት ይሠራል

ፕሮቲኖች የሚሠሩት ከአሚኖ አሲዶች ነው

6 ሰንሰለት የሚመስለው ፕሮቲን ተግባሩን ለማከናወን በሚያስችለው ትክክለኛ መንገድ መተጣጠፍ አለበት። አንድ ፕሮቲን ከ300 የሚበልጡ “ቁልፍልፎች” ሊኖረው እንደሚችል ታውቃለህ?

ፕሮቲን

በሰውነታችን ውስጥ 100,000 ዓይነት ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ፕሮቲኖች ይገኛሉ

ፀረ እንግዳ አካላት

ኢንዛይሞች

እንደ ምሰሶ ሆነው የሚያገለግሉ ፕሮቲኖች

ሆርሞኖች

አጓጓዦች

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዲ ኤን ኤ የእያንዳንዱን ፕሮቲን “ስም የሚጽፈው” እንዴት ነው?

ዲ ኤን ኤ ጂ ቲ ሲ ቲ ኤ ቲ ኤ ኤ ጂ

ዲ ኤን ኤ ለመጻፍ የሚጠቀመው አራት “ፊደላትን” ብቻ ነው:- ኤ፣ ቲ፣ ሲ፣ ጂ

ኤ ቲ ሲ ጂ

የዲ ኤን ኤ “ስያሜ” ወደ አር ኤን ኤ የአጻጻፍ ስልት ይገለበጣል። አር ኤን ኤ በቲ ፋንታ ዩን (ዩረሲልን) ይጠቀማል

ኤ ዩ ሲ ጂ

ሦስት ፊደላት ያሉት እያንዳንዱ መደዳ አንድ “ቃል” ወይም አሚኖ አሲድ “ይጽፋል።” ለምሳሌ:-

ጂ ዩ ሲ = ቫሊን

ዩ ኤ ዩ = ታይሮሲን

ኤ ኤ ጂ = ላይሲን

የታወቁት 20 አሚኖ አሲዶች በዚህ መንገድ “ስማቸው ይጻፋል።” “ቃላት” አንድ ላይ ተቆራኝተው ሰንሰለት ወይም “ዓረፍተ ነገር” በመፍጠር ፕሮቲን ይሠራሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፕሮቲን “የሚታጠፈው” እንዴት ነው?

ነጠላ አሚኖ አሲዶች አንድ ላይ ተጣምረው . . .

1 ሰንሰለት ይሠራሉ፤ ከዚያ በኋላ . . .

2 እንደ ጠምዛዛ ወይም ሽንሽን ያሉ ቅርጾችን ያበጃሉ፣ ከዚያም . . .

ጥምዝዞቹና

ሽንሽኖቹ

3 እንደገና ተቆላልፈው ሦስት ገጽ ያለው በጣም ውስብስብ መልክ ይፈጥራሉ፣ ይህ ምናልባት . . .

4 ውስብስብ ከሆነው ፕሮቲን አንዱ ክፍል ብቻ ሊሆን ይችላል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ በኮምፒውተር የተሠራ የራይቦዞም ፕሮቲን ክፍል ባለ ቀለም እንዲሆን የተፈለገው ሦስት የተለያዩ ገጾች እንዳሉት ለማሳየት ነው። የቅርጹን ዓይነት ጥምዝምዝና ሽንሽን በማድረግ ለመለየት ተሞክሯል

[ምንጭ]

The Protein Data Bank, ID: 1FFK; Ban, N., Nissen, P., Hansen, J., Moore, P.B., Steitz, T.A.: The Complete Atomic Structure of the Large Ribosomal Subunit at 2.4 A Resolution, Science 289 pp. 905 (2000)

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሥዕሎቹ የተወሰዱት:- THE WAY LIFE WORKS by Mahlon Hoagland and Bert Dodson, copyright ©1995 by Mahlon Hoagland and Bert Dodson. Used by permission of Times Books, a division of Random House, Inc.