በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

“በወላጆቼ ስናደድ ማለት የማልፈልገውን ነገር እናገራለሁ። ንዴቴ እስኪበርድልኝ ድረስ ከእነርሱ እርቃለሁ።”—የ13 ዓመቷ ኬት

“የእኔ ትልቁ ትግል በራስ ያለመተማመን ስሜት ነው። አንዳንድ ጊዜ በውስጤ የሞትኩኝ ያህል ሆኖ ይሰማኛል።”—የ19 ዓመቱ ኢቫን

ስሜት ከፍተኛ ኃይል አለው። በመሆኑም በአስተሳሰብህም ሆነ በድርጊትህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖራል። ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር ሊያነሳሳህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ከቁጥጥርህ ውጪ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። የሃያ ዓመቱ ጃኮብ “ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም ለማለት እችላለሁ። ብዙውን ጊዜ ያሰብኩት ነገር ሳይሳካልኝ ይቀራል። አንዳንድ ጊዜ ንዴቴን ለመወጣት አለቅሳለሁ አሊያም አጠገቤ ባሉት ሰዎች ላይ ቁጣዬን እገልጻለሁ። በአጠቃላይ ስሜቴን መቆጣጠር ይሳነኛል” ሲል ተናግሯል።

የጎለመስክና ኃላፊነት የሚሰማህ ወጣት ለመሆን ስሜትህን መቆጣጠር መማር ይኖርብሃል። ስሜትን የመቆጣጠርና ከሰዎች ጋር ተግባብቶ የመኖር ችሎታ ከጭንቅላት እውቀት በእጅጉ እንደሚበልጥ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር መሆኑን ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ምሳሌ 25:28 “ራሱን የማይቈጣጠር ሰው፣ ቅጥሯ እንደ ፈረሰ ከተማ ነው” ይላል። ስሜትን መቆጣጠርን ይህን ያህል አስቸጋሪ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ለወጣቶች ፈታኝ የሚሆንባቸው ነገር

በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ስሜታቸውን በመቆጣጠር ረገድ ትግል አለባቸው። በተለይ ይህ ትግል አንድ ወጣት ከአፍላ ጉርምስና ወደ አዋቂነት በሚሸጋገርበት ዕድሜ ላይ እያየለ ይመጣል። በሩት ቤል የተዘጋጀው ቼንጂንግ ቦዲስ፣ ቼንጂንግ ላይፍስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች የደስታ አይሉት የፍርሃት ብቻ ለመግለጽ የሚያስቸግር የተዘበራረቀ ስሜት ይሰማቸዋል። ብዙ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ስለ አንድ ዓይነት ነገር የተለያየ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። . . . በአንድ ቅጽበት የሆነ ስሜት ተሰምቶህ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ራስህን በሌላ በተቃራኒ ስሜት ውስጥ ታገኘዋለህ።”

ወጣት እንደመሆንህ መጠን በቂ ተሞክሮ የለህም። (ምሳሌ 1:4) በመሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ አዳዲስ ሁኔታዎችና ተፈታታኝ ነገሮች ሲያጋጥሙህ ስጋት ቢያድርብህ ምናልባትም በጣም ብትረበሽ እንግዳ ነገር አይደለም። የሚያስደስተው ስሜትህን በሚገባ የሚረዳልህ ፈጣሪ መኖሩ ነው። በውስጥህ ‘እረፍት የሚነሱህን ሐሳቦች’ ሳይቀር ያውቃል። (መዝሙር 139:23 NW) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስፍሯል።

ስሜትን ለመቆጣጠር የሚረዱ ቁልፍ ዘዴዎች

ስሜትህን ለመቆጣጠር የሚረዳህ የመጀመሪያው ቁልፍ ዘዴ የምታስበውን ነገር መቆጣጠር የምትችልበትን መንገድ መማር ነው። አሉታዊ አስተሳሰብ ትክክለኛ እርምጃ እንዳትወስድ አቅም ሊያሳጣህ ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ሆኖም አዎንታዊ ስለሆኑ ነገሮች ማሰብ የምትችልበትን መንገድ በመማር ስሜትህን የመቆጣጠር ችሎታ የምታዳብረው እንዴት ነው?

አንዱ መንገድ እንድትተክዝ ወይም ስጋት እንዲያድርብህ የሚያደርጉ አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን ከማብሰልሰል ይልቅ ከአእምሮህ ለማውጣት በመጣር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጭምትነት ያለበትን” እና “ጽድቅ የሆነውን” እንድታስብ የሰጠህን ምክር በመከተል አሉታዊ የሆነውን በአዎንታዊ አስተሳሰብ ልትተካው ትችላለህ። (ፊልጵስዩስ 4:8 የ1954 ትርጉም) ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ቢችልም ጥረት ካደረግህ ግን ሊሳካልህ ይችላል።

ጃስሚን የተባለች ወጣት ምሬቷን እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “የሚገጥሙኝ ነገሮች ሁሉ በጭንቀት እንድዋጥ አድርገውኛል። አዲስ ሥራ፣ አዳዲስ ኃላፊነቶች። በጣም ባክኛለሁ። ለመተንፈስ እንኳ ፋታ የለኝም።” አንድ ወጣት አልፎ አልፎ እንደዚህ ቢሰማውና በዚህም ምክንያት ስለራሱ ፍርሃትና ስጋት ቢያድርበት አያስደንቅም። መጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠውን ኃላፊነት በግሩም ሁኔታ ስለተወጣ ጢሞቴዎስ ስለተባለ አንድ ወጣት ይነግረናል። እንደዛም ሆኖ ግን ብቃት የለህም የሚል ስሜት ይታገለው የነበረ ይመስላል።—1 ጢሞቴዎስ 4:11-16፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:6, 7

አንድ አዲስ ወይም የማታውቀው ሥራ ሲሰጥህ በራስ ያለመተማመን ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ‘ይህንን ሥራ ፈጽሞ ልሠራው አልችልም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለውን አሉታዊ አስተሳሰብ በማስወገድ በራስ ያለመተማመንን ስሜት መቆጣጠር ትችላለህ። ሥራውን እንዴት መልመድና አቀላጥፈህ መሥራት እንደምትችል አስብ። ያልገባህን ነገር ጠይቅ፤ እንዲሁም የሚሰጡህን መመሪያዎች ተከተል።—ምሳሌ 1:5, 7

ሥራውን አቀላጥፈህ መሥራት በቻልክ መጠን በራስ ያለመተማመን ስሜትህ በዛው ልክ እየቀነሰ ይሄዳል። ለመሻሻል ጠንክረህ እንዳትሠራ ስለሚያደርግህ ሁልጊዜ በድክመቶችህ ላይ አታሰላስል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ትችት በተሰነዘረበት ጊዜ “የንግግር ችሎታ ባይኖረኝም እንኳ፣ ዕውቀት ግን አለኝ” ሲል መልሷል። (2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:6) በተመሳሳይ አንተም ጠንካራ ጎኖችህን ለይተህ በማወቅና ድክመቶችህን ደግሞ እንድታሻሽል አምላክ እንዲረዳህ በጸሎት በመጠየቅ በራስ የመተማመን ስሜትህን ልትገነባ ትችላለህ። የጥንት ሕዝቦቹን እንደረዳቸው ሁሉ አምላክ አንተንም ይረዳሃል።—ዘፀአት 4:10

ስሜትህን ለመቆጣጠር የሚረዳህ ሌላኛው መንገድ ያልተጋነነ፣ ሊደረስበት የሚችል ግብ ማውጣትና አቅምህን ማወቅ ነው። በተጨማሪም ራስህን ከሌሎች ጋር አላግባብ ከማነጻጸር ተቆጠብ። መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 6:4 ላይ “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል” በማለት ጥሩ ምክር ይሰጣል።

ንዴትን ማብረድ

ንዴትን መቆጣጠር ሌላ ተፈታታኝ ችግር ሊሆን ይችላል። መግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰችው ኬት ሁሉ ንዴት ብዙ ወጣቶችን የሚጎዳ ነገር እንዲናገሩ ወይም እንዲያደርጉ ይገፋፋል።

እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ልንናደድ እንችላለን። ቢሆንም የመጀመሪያውን ነፍሰ ገዳይ ቃየንን እናስታውስ። ‘ክፉኛ በተናደደ’ ጊዜ አምላክ ይህን የመሰለው ንዴት ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም እንደሚመራው አስጠንቅቆት ነበር። ከዚያም “አንተ ግን [ኃጢአትን] ተቈጣጠራት” አለው። (ዘፍጥረት 4:5-7) ቃየን ይህን መለኮታዊ ምክር ሳይሰማ ቀርቷል፤ አንተ ግን በአምላክ እርዳታ ንዴትህን በመቆጣጠር ኃጢአት ከመሥራት ልትቆጠብ ትችላለህ!

አሁንም ንዴትህን መቆጣጠር ማለት አስተሳሰብህን መቆጣጠር ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 19:11 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል፣ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል” ይላል። አንድ ሰው ሲያናድድህ እንደዚያ ያደረገበትን ምክንያት ለመረዳት ሞክር። ግለሰቡ ሆን ብሎ አንተን ለመጉዳት አስቦ ነው? ድርጊቱን የፈጸመው ድንገት ሳያስበው ወይም ካለማወቅ የተነሳ ይሆን? የሌላውን ስህተት ችሎ ማለፍ የአምላክን ምሕረት ከማንጸባረቁም በተጨማሪ ንዴትህን ሊያበርድልህ ይችላል።

ይሁንና እንድትናደድ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ቢኖርህስ? መጽሐፍ ቅዱስ “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ” ይላል። (ኤፌሶን 4:26) ካስፈለገ ከግለሰቡ ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋገሩበት። (ማቴዎስ 5:23, 24) ወይም ከሁሉ የተሻለ የሚሆነው ነገሩን በመርሳት ንዴትህን መተውና የዘወትር ተግባርህን በሰላም መቀጠል ነው።

የሚገርመው ጓደኞችህ ስለ ንዴት ባለህ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ መቻላቸው ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋር አትወዳጅ፤ አለበለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤ ራስህም ትጠመድበታለህ” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 22:24, 25

ንዴታቸውን ከሚቆጣጠሩ ሰዎች ጋር መዋል ራስን የመግዛት ችሎታ እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ጉባኤ ብዙ የጎለመሱና በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ ካንተ የሚበልጡ ግለሰቦችን ያቀፈ ነው። አንዳንዶችን ለማወቅ ሞክር። ችግር ሲገጥማቸው እንዴት አድርገው እንደሚወጡት አስተውል። ችግር በሚያጋጥምህ ጊዜ “መልካም ምክር” ሊሰጡህ ይችላሉ። (ምሳሌ 24:6) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጃኮብ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የአምላክን ቃል ሊያስታውሰኝ የሚችል የጎለመሰ ጓደኛ እጅግ ውድ ሀብት ነው። ምንም እንኳ በራሴ የማልተማመን ሰው ብሆንም ይሖዋ እንደሚወደኝ ሳስታውስ ስሜቴን ተቆጣጥሬ ለመረጋጋት ችያለሁ።”

ሌሎች ተግባራዊ እርምጃዎች

አንድ የታወቀ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “የምታደርገው አካላዊ እንቅስቃሴ በሰውነትህ ውስጥ በሚካሄዱ ኬሚካላዊ ለውጦች አማካኝነት በባሕርይህና በስሜትህ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጥናቶች አረጋግጠዋል። እንደምታደርገው የእንቅስቃሴ ዓይነት በሰውነትህ ውስጥ ያለው የሆርሞንና የኦክሲጅን መጠን ይለዋወጣል።” የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቃሚ መሆኑ አያጠያይቅም። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት ልምምድ ለጥቂት ነገር ይጠቅማልና” ብሎ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ለምን መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምታደርግበት ፕሮግራም አታወጣም? በስሜትህ ላይ ጥሩ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ማዳበርም በዚህ ረገድ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል።

በተጨማሪም ስለ ሙዚቃና መዝናኛ ምርጫህ አስብ። ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ኸልዝ ሌተር በተባለው ጽሑፍ ላይ የወጣ አንድ ጥናት “ዓመጽን መመልከት . . . ተናዳጅና ቁጡ የመሆንን ባሕርይ ይቀሰቅሳል። . . . ዓመጽ የሞላባቸው ፊልሞችን የሚመለከቱ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ቁጡዎች ከመሆናቸውም በተጨማሪ የደም ግፊታቸው ከፍ ያለ ነው” ሲል ገልጿል። ስለዚህ የምታዳምጠውንም ሆነ የምትመለከተውን ነገር በጥበብ መምረጥ ይኖርብሃል።—መዝሙር 1:1-3፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33

በመጨረሻም ስሜትህን ለመቆጣጠር የሚረዳህ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ከፈጣሪህ ጋር የተቀራረበ ዝምድናን ማዳበር ነው። እያንዳንዳችን በጸሎት አማካኝነት የልባችንን አውጥተን እንድንነግረው ይጋብዘናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ” ካለ በኋላ “ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ፣ ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን ይጠብቃል” በማለት አበረታቶናል። አዎን በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ነገር ለመወጣት ውስጣዊ ጥንካሬን ማዳበር ትችላለህ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13

ወጣቷ ማሊካ “ብዙ ጊዜ እየደጋገምኩ መጸለይን ተምሬያለሁ። ይሖዋ እንደሚያስብልኝ ማወቄ እንድረጋጋና ስሜቴን ይበልጥ እንድቆጣጠር ረድቶኛል” ስትል ተናግራለች። አንተም ብትሆን በአምላክ እርዳታ ስሜትህን መቆጣጠር ትችላለህ።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ስሜትህን ለመቆጣጠር የሚረዳህ የመጀመሪያው ቁልፍ ዘዴ የምታስበውን ነገር መቆጣጠር የምትችልበትን መንገድ መማር ነው።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአዋቂዎች ጋር መቀራረብህ ስሜትህን መቆጣጠር የምትችልበትን መንገድ ያስተምርሃል