በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በውጥረት ላይ የሚገኙ ሐኪሞች

በውጥረት ላይ የሚገኙ ሐኪሞች

በውጥረት ላይ የሚገኙ ሐኪሞች

“አንድ ወጣት ባልና ሚስት አዲስ የተወለደ ልጃቸውን እንደማድንላቸው ባለሙሉ ተስፋ ሆነው መጡ። ስመረምረው ልቤ ፍስስ አለ። የሕፃኑ ችግር በሕክምና ሊረዳ የሚችል አልነበረም። ለእነዚህ አዲስ ወላጆች ልጃቸው ሊያይ እንደማይችል ስነግራቸው እንዴት እንደተሰማኝ መገመት ትችላላችሁ? ከቢሮዬ ስሸኛቸው በጣም ተረበሽኩ። ይሁን እንጂ ወዲያው ፈገግ ብዬ እንድቀበለው የሚጠብቅ አዲስ ታካሚ ገባ! በጣም ውጥረት የሚሰማኝ በዚህ ምክንያት ነው።”—በደቡብ አሜሪካ የሚኖር የዓይን ሐኪም

ታካሚዎች ወደ ሐኪሞች ቢሮ የሚሄዱት የዶክተሮቻቸውን ችግር ለማየት እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ታካሚው የሚያሳስበው የራሱ ችግር ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች የሐኪሞች ሕይወት ምን ያህል ውጥረት የበዛበት እንደሆነ አይገነዘቡም።

እርግጥ፣ ሁሉም ሰው ውጥረት ያጋጥመዋል። ውጥረት ያለበት ሥራ የሚሠሩትም ሐኪሞች ብቻ አይደሉም። ይሁን እንጂ የሐኪም-ታካሚ ግንኙነት በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ የማይነካው ሰው ስለማይኖር ሐኪሞች እንዴት ያለ ውጥረት እንደሚያጋጥማቸውና ይህም ውጥረት ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው መረዳት ጠቃሚ ነው።

ሐኪሞች ውጥረት የሚደርስባቸው ለሕክምና ትምህርት የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ሲጥሩ ጀምሮ ነው። ይሁን እንጂ ገና ሥልጠናውን ሲጀምሩ በሕይወታቸው ሊረሱት የማይችሉት አስደንጋጭ ነገር ያጋጥማቸዋል። ይህ የሕክምና ተማሪውን ስሜትና መላ ባሕርይ የሚለውጥ ሂደት መጀመሪያ ነው።

የሕክምና ሥልጠና—የሚያስደነግጥ ተሞክሮ

ተማሪው የሕክምና ሥልጠናውን በጀመረባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ከፍተኛ የስሜት ቁስል በሚያስከትለው የአስከሬን መቅደጃ ክፍል እንዲገባ ይደረጋል። ብዙ ተማሪዎች ከዚያ በፊት አስከሬን አይተው እንኳን የማያውቁ ናቸው። የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ለማሳየት ሲባል ተቀድደው የተከፈቱ አስከሬኖችን እርቃናቸውን መመልከት በጣም ይዘገንናል። ተማሪዎቹ ስሜታቸውን ለመቋቋም የሚያስችላቸው ዘዴ መፈለግ ይኖርባቸዋል። ለእያንዳንዱ አስከሬን የቅጽል ስም በመስጠት በቀልድ ለማለፍ የሚሞክሩ አሉ። ይህን ማድረጋቸው ከውጭ ለሚመለከታቸው ጨካኝነትና ለሰብዓዊ አካል አክብሮት ማጣት መስሎ ቢታይም ለተማሪዎቹ ግን በሕይወት ይኖር የነበረውን ሰው ላለማስታወስ የሚፈጥሩት የግድ አስፈላጊ የሆነ ዘዴ ነው።

ከዚያ በኋላ ደግሞ በሆስፒታል ውስጥ የሚሰጣቸው የሥራ ላይ ልምምድ ይከተላል። አብዛኞቹ ሰዎች መካከለኛ ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የሕይወት አጭርነት አይታያቸውም። የሕክምና ተማሪዎች ግን ፈውስ ከሌላቸው በሽታዎችና ከሞት ጋር ፊት ለፊት የሚፋጠጡት ገና በወጣትነታቸው ነው። አንድ ሠልጣኝ በሆስፒታል ስላሳለፈው የመጀመሪያ ተሞክሮ ሲናገር “በጣም የሚያሰቅቅና ዘግናኝ ነበር” ብሏል። በተጨማሪም በድሀም ሆነ በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ተማሪዎች በቂ ገንዘብ ባለመኖሩ የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና ሳያገኙ የሚቀሩ በርካታ ታካሚዎች መኖራቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከቱ ይደነግጣሉ።

አዳዲሶቹ ዶክተሮች ይህን ሁሉ ውጥረት የሚቋቋሙት እንዴት ነው? የሕክምና ሠራተኞች ታካሚዎቻቸውን እንደ አንድ ግለሰብ ላለማሰብ በመሞከር ስሜታቸውን ያደነዝዛሉ። ለምሳሌ እገሌ የሚባል ሰው ከማለት ይልቅ “ዶክተር፣ በቁጥር ሁለት ክፍል ውስጥ አንድ ሰባራ እግር አለ” ሊሉ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ አነጋገር የተነገረበትን ምክንያት ካለወቅክ አስቂኝ ሆኖ ሊታይህ ይችላል።

በሐዘን ምክንያት የሚፈጠር ድካም

ዶክተሮች የሚሰጣቸው ሥልጠና ሳይንሳዊ ይሁን እንጂ ለብዙዎቹ ከሥራ ግዴታዎቻቸው አንዱ ታካሚዎችን ማነጋገር ነው። አንዳንድ ሐኪሞች የሐኪም-ታካሚ ግንኙነት ለሚጠይቀው የስሜት ጥንካሬ ዝግጁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። በመግቢያው ላይ እንደተመለከተው በጣም አስቸጋሪ ከሆኑት የዶክተር ሥራዎች አንዱ መጥፎ ዜና ማርዳት ነው። አንዳንዶቹ በየቀኑ ይህን ለማድረግ ይገደዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ በችግር ላይ የሚገኙ ሰዎች ምሬታቸውንና ሐዘናቸውን ማውጣት ይፈልጋሉ። ሐኪሞች ደግሞ ይህን እንዲያዳምጡ ይጠበቅባቸዋል። ፍርሃትና ሥጋት የተጫናቸውን ሰዎች አይዟችሁ ማለት በጣም አድካሚ ሥራ በመሆኑ አንዳንድ ሐኪሞች በሐዘን ምክንያት በሚፈጠር ድካም ይጎዳሉ።

አንድ በካናዳ የሚኖር የቤተሰብ ሐኪም ስለ ወጣትነት ሕይወቱ ሲናገር “ሥራ እንደጎርፍ ያጥለቀልቀኝ ነበር። ጊዜዬን የሚሻሙ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች፣ ጭንቀታቸውን ለማራገፍ የሚፈልጉ የተጨነቁ ሰዎች፣ እኔ የማደርግላቸውን የሚጠብቁ ሕመምተኞች፣ ወደፈለጉበት ሊገፉኝና ሊጎትቱኝ የሚፈልጉ ተንኮለኛ ሰዎች፣ ሊያነጋግሩኝ የሚፈልጉ ሰዎች፣ እንድመጣላችው የሚጎተጉቱኝ ሰዎች እንዲሁም በስልክ ሽቦ አማካኝነት ቤቴ ድረስ፣ እስከ መኝታ ቤቴ ዘው ብለው የሚገቡ ሰዎች ነበሩ። ሰው፣ ሰው፣ ሰው ብቻ። ጠቃሚ ሆኜ ለመገኘት የምፈልግ ሰው ነበርኩ። ይህ ግን ከልክ ያለፈ በመሆኑ ከእብደት የሚቆጠር ነበር።”—ኤ ዶክተርስ ዳይለማ፣ በጆን ደብልዩ ሆላንድ።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ውጥረቱ እየቀለለ ይሄድ ይሆን? አብዛኛውን ጊዜ ሲንየር መሆን ተጨማሪ ኃላፊነቶች ያስከትላል። የሞትና የሕይወት ውሳኔዎች፣ ምናልባትም በቂ መረጃ ሳይኖር እነዚህን ውሳኔዎች ማድረግ ግድ የሚሆንባቸው ብዙ ጊዜያት ይኖራሉ። አንድ እንግሊዛዊ ዶክተር “ወጣት በነበርኩ ጊዜ ልክ ወጣቶች በአደገኛ ሁኔታ መኪና ማሽከርከራቸው ግድ እንደማይሰጣቸው ሁሉ እኔም ይህ ጉዳይ ብዙ አያስጨንቀኝም ነበር። ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ግን ለሕይወት የምትሰጠው ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል። አሁን የሕክምና ውሳኔዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ያሳስቡኛል” ብለዋል።

ውጥረት በሐኪሞች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? የታካሚዎች ሥቃይ እንዳይሰማቸው ሲሉ ራሳቸውን የማግለልና ከታካሚዎቻቸው የማራቅ ልማዳቸው ውሎ ሲያድር ወደ ቤተሰብ ዝምድናቸው ሊዛመት ይችላል። እንዲህ ያለውን አዝማሚያ ማስወገድ በጣም አዳጋች ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሐኪሞች ታካሚዎቻቸውን በሚያጽናኑበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የርኅራኄና የሐዘኔታ ስሜት ያሳያሉ። ይሁን እንጂ በሐዘኔታ ምክንያት የሚደርሰው ድካም ሳያሸንፋቸው ሊቀጥሉ የሚችሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? ይህ ዶክተሮችን በሙሉ የሚፈታተን ጥያቄ ነው።

አስቸጋሪ ታካሚዎችን በዘዴ መያዝ

ሐኪሞች ስለ ሐኪም-ታካሚ ግንኙነት ሲጠየቁ አብዛኛውን ጊዜ ገለጻቸውን የሚጀምሩት አስቸጋሪ ስለሆኑ ታካሚዎች በመናገር ነው። ምናልባት እንደሚከተሉት ያሉትን ታውቅ ይሆናል።

በመጀመሪያ በቀጥታ ችግሩ ምን እንደሆነ ከመናገር ይልቅ ዳር ዳሩን በመዞር የዶክተሩን ጊዜ የሚያባክን ታካሚ አለ። ቀጥሎ ደግሞ አጣዳፊ የሆነ ችግር ሳያጋጥመው በሌሊት ወይም በእረፍት ቀናት ስልክ እየደወለ ሐኪሙን የሚወተውት ወይም ሐኪሙ ጥሩ ነው ብሎ የማያምንበትን ሕክምና እንዲያዝለት የሚጨቃጨቅ ታካሚ አለ። ተጠራጣሪ የሆነ ታካሚም አለ። ስላጋጠማቸው ችግር እንደ ኢንተርኔት ካሉ ምንጮች መረጃ የሚያሰባስቡ ሰዎች አሉ። ይህም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ጥናት ሊያማክሩ በመጡት ባለሞያ ላይ እንዳይተማመኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። አንድ ዶክተር ያሰባሰቡትን መረጃ ለማስተባበልም ሆነ ለመደገፍ ሙሉ ትንታኔ ለመስጠት ጊዜ ላይኖረው ይችላል። ታካሚው ባደረበት ጥርጣሬ ምክንያት ለሕክምናው ተባባሪ ሳይሆን ሲቀር ዶክተሩ ያዝናል። በመጨረሻ ደግሞ ትዕግሥት የሌለው ታካሚ አለ። ምናልባት የሌሎችን ምክር ይሰማና የተሰጠው ሕክምና ውጤት ከማስገኘቱ በፊት ያቆመዋል።

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ግን ዋነኞቹ የሐኪሞች የውጥረት ምክንያቶች ታካሚዎች ሳይሆኑ ጠበቆች ናቸው።

ክስ እንዳይመጣ እየተጠነቀቁ ማከም

በብዙ አገሮች በዶክተሮች ላይ የሚመሠረት የሞያ ግዴታን በሚገባ ያለመወጣት ክስ እየጨመረ መጥቷል። አንዳንድ ጠበቆች ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲሉ ብቻ ጥቃቅን ምክንያቶችን ይፈልጋሉ። የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት “ጠበቆች የሕክምና ክስ ኢንሹራንስ እንዲያሻቅብ በማድረግ ላይ ናቸው። እነዚህ ክሶች ለሌሎች ችግሮችም ምክንያት እየሆኑ ነው። አግባብ ያልሆነ ክስ በአንድ ሐኪም ላይ ውርደት፣ የጊዜ ብክነት . . . ውጥረትና ሥጋት ስለሚያስከትል በጣም ይጎዳዋል” ሲሉ ተናግረዋል። ራሳቸውን እስከ መግደል የደረሱ ዶክተሮች አሉ።

በዚህ የተነሣ ብዙ ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው የሚሻለውን ሳይሆን ፍርድ ቤት ቢቀርቡ ራሳቸውን መከላከል የሚያስችላቸውን ሕክምና ለመመረጥ እንደሚገደዱ ይሰማቸዋል። ፊዚሽያንስ ኒውስ ዳይጀስት “በአሁኑ ጊዜ መጀመሪያ ራስህን አድን በሚል መርሕ ማከም የተለመደ ነገር ሆኗል” ብሏል።

በዶክተሮች ላይ የሚደርሰው ጫና እየጨመረ በሄደ መጠን ብዙዎቹ መጨረሻችን ምን ይሆን ብለው ያስባሉ። ብዙ ታካሚዎች ደግሞ የሕክምና ሳይንስ እድገት ቢያሳይም በአንዳንድ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎች ብዛት እየጨመረ መሄዱን ሲመለከቱ ስለመጪው ጊዜ ተመሳሳይ ጥያቄ ያነሳሉ። የሚቀጥለው ርዕስ የወደፊቱ ጊዜ ለሐኪሞችም ሆነ ለታካሚዎች ምን ተስፋ እንደያዘ ያብራራል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከሐኪምህ ጋር መተባበር

1. ችግርህን በጣም አንገብጋቢ ከሆነው በመጀመር እንዴት አጠርና ጥሩ አድርገህ እንደምትገልጽ በቅድሚያ ተዘጋጅና ሐኪሙ የሚሰጥህን ጊዜ በአግባቡ ተጠቀምበት

2. አጣዳፊ ሁኔታ ካላጋጠመህ በስተቀር ዶክተርህን ከሥራ ሰዓት ውጭ ደውለህ አታነጋግር

3. ትዕግሥተኛ ሁን። ተገቢ ምርመራ ለማድረግና ሕክምና ለመስጠት ጊዜ ያስፈልጋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘ተራ ሕክምናዎች እንኳን እርካታ ሊያስገኙ ይችላሉ’

“እዚህ በሚሰጠው ሕክምናና ይበልጥ ባለጠጋ በሆኑ አገሮች በሚሰጠው ሕክምና መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሠፊ ነው። እዚህ ከድህነት ለማምለጥ በአንድ ዓይነት ሞያ መሠልጠን አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚታመን ሕክምና ማጥናት በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል። ነገር ግን ሁሉም ዶክተሮች ሥራ ማግኘት አይችሉም። በዚህ ምክንያት ለዶክተሮች የሚከፈለው ደመወዝ በጣም አነስተኛ ነው። በራሳቸው ገንዘብ በግል ሐኪም ሊታከሙ የሚችሉ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። እኔ የምሠራው በጣም መሠረታዊ የሆኑ መሣሪያዎች ብቻ በሚገኙበትና ጣሪያው በሚያፈስ አሮጌ ሆስፒታል ውስጥ ነው። ሠራተኞቻችን ሁለት ዶክተሮችና አምስት ረዳት አስታማሚዎች ብቻ ናቸው። ለ14,000 ሕዝብ አገልግሎት እንሰጣለን።”

“ታካሚዎች በቂ ምርመራ እንደማላደርግላቸው ይሰማቸዋል። ሃያ አምስት ታካሚዎች ቁጭ ብለው እየጠበቁኝ ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ምርመራ ላደርግ አልችልም። ቢሆንም ተራ የሆኑ ቀላል ሕክምናዎች ሳይቀሩ እርካታ ያመጡልኛል። ለምሳሌ እናቶች በተቅማጥ የተጎዱና በቂ ምግብ ያላገኙ ልጆቻቸውን ይዘው ይመጣሉ። ሕፃናቱ የጎረጎደ ዓይንና የተጨነቀ ፊት አላቸው። ለእናቲቱ የምናገረው ወዝ መላሽ ጨው፣ ትላትል የሚገድል መድኃኒትና አንቲባዮቲክ እንድትሰጥ ብቻ ነው። እነዚህ መድኃኒቶች ሥራቸውን እንደጀመሩ ሕፃኑ መብላት ይጀምራል። ከአንድ ሳምንት በኋላ ብሩሕ ዓይን ያለው፣ ፈገግተኛና ተጫዋች ስለሚሆን ሌላ ልጅ ነው የሚመስለው። እንኳን ሐኪም ሆንኩ እንድል የሚያደርጉኝ እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች ናቸው።”

“ከልጅነቴ ጀምሮ የበሽተኞችን ሥቃይ የማስታገስ ሕልም ነበረኝ። ይሁን እንጂ የሕክምና ሥልጠና ባልጠበቅኩት መንገድ ለውጦኛል። ሕይወት አድን የሆነ ቀላል መድኃኒት የሚገዙበት ትንሽ ገንዘብ አጥተው የሚሞቱ ሰዎች አይቻለሁ። በዚህ ምክንያት አዝኜ በራሴ ላይ ጉዳት እንዳላደርስ ስል ራሴን አደነዘዝኩ። የአምላክን ርኅራኄ ለመረዳትና ዳግመኛ የሌሎች ሥቃይ የሚሰማኝ ሰው ለመሆን የቻልኩት የዚህ ሁሉ መከራ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተረዳሁ በኋላ ነው። ማልቀስ እንኳን የቻልኩት ከዚያ በኋላ ነው።”

[ሥዕሎች]

ዶክተር ማርኮ ቪለጋስ በቦሊቪያ በሚገኝ ራቅ ያለ የአማዞን አነስተኛ ከተማ ይሠራል