በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተፈታታኝ ችግሮችን እየተቋቋሙ ያሉ እናቶች

ተፈታታኝ ችግሮችን እየተቋቋሙ ያሉ እናቶች

ተፈታታኝ ችግሮችን እየተቋቋሙ ያሉ እናቶች

ብዙ እናቶች ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ችግሮች መካከል ዋነኛው ቤተሰባቸውን በገንዘብ ለመደጎም ሲባል ተቀጥረው የሚሠሩ መሆናቸው ነው። ከዚህም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አንዳንድ እናቶች ልጆቻቸውን ያለ ትዳር ጓደኛቸው እርዳታ ለማሳደግ ተገደዋል።

ማርጋሪታ ሁለት ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድግ በሜክሲኮ የምትኖር ነጠላ እናት ናት። “በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ እነሱን ማሠልጠን አስቸጋሪ ነበር” በማለት ተናግራለች። “አንድ ቀን ጎረምሳ ልጄ በግብዣ ላይ ተገኝቶ ሞቅ ብሎት መጣ። ሁለተኛ እንዲህ ሆኖ ቤት ቢመጣ እንደማላስገባው አስጠነቀቅሁት። ከዚያ በኋላ እንደገና ሰክሮ ሲመጣ እንደምንም ብዬ ጨክኜ ቤት ሳላስገባው አደርኩ። ደግነቱ ከዚያ በኋላ ሰክሮ መጥቶ አያውቅም” ብላለች።

ማርጋሪታ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን ጥናቱ በልጆቿ ልብ ውስጥ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ለመትከል ረድቷታል። አሁን ሁለቱም ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው።

ባሎች ባሕር ማዶ ሲሄዱ

በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ባሎች ልጆቻቸውን ለሚስቶቻቸው ጥለው ሥራ ፍለጋ ወደበለጸጉ አገሮች ይሄዳሉ። በኔፓል የምትኖር ላክሽሜ የተባለች እናት እንዲህ ትላለች:- “ባሌ ውጭ አገር መኖር ከጀመረ ሰባት ዓመቱ ነው። ልጆቻችን ከእኔ ይልቅ የሚታዘዙት ለአባታቸው ነው። እርሱ እዚህ ሆኖ ቤተሰቡን ቢያስተዳድር ኖሮ ችግሩ ቀላል ይሆን ነበር።”

ላክሽሜ ያሉባትን ተደራራቢ ችግሮች እየተጋፈጠች ነው። የትምህርት ደረጃዋ ውስን በመሆኑ ትልልቅ ልጆቿን በትምህርት የሚረዳቸው አስጠኚ ቀጠረችላቸው። ይሁን እንጂ ልጆቿን በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ለመንፈሳዊ ትምህርታቸው ልዩ ትኩረት ትሰጣለች። በዕለት ጥቅሱ ላይ በየቀኑ ውይይት የምታደርግ ሲሆን አዘውትራም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ትወስዳቸዋለች።

ውስን የትምህርት ደረጃ ያላቸው እናቶች

በአንዳንድ አገሮች ያለው ተፈታታኝ ችግር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ሴቶች ያልተማሩ መሆናቸው ነው። በሜክሲኮ የምትኖር አውሬሊያ የምትባል የስድስት ልጆች እናት ያልተማረች እናት መሆን ያለውን ጉዳት ስትገልጽ እንዲህ ትላለች:- “እናቴ ሴቶች መማር እንደሌለባቸው ሁልጊዜ ትናገር ነበር። ስለዚህ ማንበብ ባለመማሬ ልጆቼ የቤት ሥራቸውን ሲሠሩ ልረዳቸው አልቻልኩም። ይህም በጣም ያበሳጨኝ ነበር። ሆኖም ልጆቼ እንደ እኔ ሳይማሩ ቀርተው እንዲሰቃዩ ስላልፈለግሁ እነርሱን ለማስተማር ጥረት አደረግሁ።”

አንዲት እናት ትንሽ ትምህርት እንኳ ቢኖራት የጎላ ተጽዕኖ ልታሳድር ትችላለች። “ሴቶችን ብታስተምር የወንዶች ልጆችን መምህር አስተማርክ ማለት ነው” የሚለው አባባል ትክክል ነው። በኔፓል የምትኖር ቢሽኑ የምትባል አንዲት የሦስት ወንዶች ልጆች እናት ማንበብና መጻፍ አትችልም ነበር፤ ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተምራ ለልጆቿ ለማስተማር ያላት ፍላጎት ማንበብና መጻፍ ለመማር ከፍተኛ ጥረት እንድታደርግ አነሳሳት። ልጆቿ የቤት ሥራቸውን እንዲሠሩ ትከታተል የነበረ ሲሆን ዘወትር ትምህርት ቤታቸው ድረስ በመሄድ ስለ እንቅስቃሴያቸው ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ትወያይ ነበር።

ሲላሽ የሚባለው የቢሽኑ ልጅ የቀሰሙትን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ትምህርት በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “እናቴ እኛን ለማስተማር ከምታደርገው ጥረት ደስ የሚለኝ ነገር ቢኖር ስህተት በምንሠራበት ጊዜ እኛን ለማረም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን የምታቀርብልን መሆኑ ነው። እንዲህ ያለው የማስተማር ዘዴ ውጤታማ ስለነበር ምክሩን እንድቀበል ረድቶኛል።” ቢሽኑ ወንዶች ልጆቿን በማስተማር ረገድ ውጤታማ በመሆኗ ሦስቱም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች ሆነዋል።

ወንድና ሴት ልጆቿን በማሳደግ ላይ ያለችው በሜክሲኮ የምትኖረው አንቶኒያ እንዲህ ትላለች:- “የተማርኩት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ ነበር። የምንኖረው ወጣ ባለ መንደር ስለነበር ቅርብ የሚባለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንኳ ለእኛ በጣም ሩቅ ነበር። ሆኖም ልጆቼ ከእኔ የበለጠ ትምህርት እንዲያገኙ ስለፈለግሁ እነርሱን ለመርዳት ብዙ ጊዜ መደብኩ። ፊደልና ቁጥር አስተማርኳቸው። ሴቷ ልጄ ትምህርት ቤት ከመግባቷ በፊት ስሟንና ሁሉንም ፊደሎች መጻፍ ችላ ነበር። ወንዱ ልጄ ደግሞ ወደ መዋዕለ ሕፃናት ከመግባቱ በፊት በደንብ ማንበብ ይችል ነበር።”

አንቶኒያ ለልጆቿ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ሥልጠና ለመስጠት ምን እንዳደረገች ተጠይቃ ስትመልስ “የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አስተምሬያቸዋለሁ። ሴቷ ልጄ አፍ ከመፍታቷ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በሰውነት እንቅስቃሴዋ ማሳየት ትችል ነበር። ወንዱ ልጄ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍሉን ያቀረበው በአራት ዓመት ዕድሜው ነበር” ብላለች። ውስን ትምህርት ያላቸው ብዙ እናቶች የአስተማሪነት ሥራቸውን በጥሩ ሁኔታ እየተወጡ ነው።

ጎጂ ባሕሎችን መዋጋት

በሜክሲኮ በጾጺል ጎሣ ባሕል መሠረት ሴት ልጆች ለገንዘብ ሲባል ገና በ12 እና በ13 ዓመት ዕድሜያቸው ይዳራሉ። ብዙውን ጊዜ ልጆቹ የሚዳሩት በዕድሜ በጣም ለሚበልጣቸውና ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ሚስት ለሚፈልግ ሰው ነው። ሰውየው በልጅቷ ካልተደሰተ ወደ ወላጆቿ መልሷት ለጥሎሽ የከፈለውን ገንዘብ መውሰድ ይችላል። ፔትሮና የምትባል አንዲት ሴት ልጅ ሳለች እንዲህ ያለው ሁኔታ ተጋርጦባት ነበር። ለገንዘብ ሲባል ተድራ የነበረችው እናቷ ወንድ ልጅ ከወለደች በኋላ ከባሏ ተፋታች። ይህ ሁሉ የደረሰባት ገና በ13 ዓመቷ ነበር! የበኩር ልጅዋ ስለሞተ የፔትሮና እናት ከዚያ በኋላ እንደገና ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ተድራ ነበር። በጠቅላላው ስምንት ልጆች ወልዳለች።

ፔትሮና እንዲህ ያለው ኑሮ ውስጥ መግባት ስላልፈለገች የወሰደችውን እርምጃ እንደሚከተለው በማለት ገልጻለች:- “የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጨርስ እኔ የምፈልገው ማግባት ሳይሆን ትምህርቴን መቀጠል እንደሆነ ለእናቴ ነገርኳት። እሷም በዚህ ረገድ ልትረዳኝ እንደማትችልና ለአባቴ እንድነግረው ሐሳብ አቀረበችልኝ።”

“አባቴ ‘ባል ፈልጌ ልድርሽ ነው’ ብሎ ነገረኝ። ‘ስፓንኛ ቋንቋ መናገር ችለሻል። ማንበብ ትችያለሽ። ከዚህ በላይ ምን ትፈልጊያለሽ? ትምህርትሽን መቀጠል ከፈለግሽ ወጪሽን ራስሽ መቻል ይኖርብሻል’ አለኝ።”

ፔትሮና “እኔም ያደረግሁት ይህንኑ ነበር፤ ልብስ እየጠለፍኩ ወጪዬን እኔው ራሴ ሸፈንኩ” በማለት ተናግራለች። ለገንዘብ ሲባል ከመዳር ያመለጠችው በዚህ መንገድ ነበር። ፔትሮና ስታድግ እናቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት መጀመሯ የመጽሐፍ ቅዱስን እሴቶች በፔትሮና ታናናሽ እህቶች አእምሮ ውስጥ ለመቅረጽ የሚያስችል ድፍረት ሰጣት። የፔትሮና እናት ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ሴት ልጆችን ገና በለጋ ዕድሜያቸው መዳር የሚያስከትለውን አሳዛኝ መዘዝ ልትነግራቸው ችላለች።

በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ሌላው ልማድ ደግሞ ወንዶች ልጆችን መቅጣት የሚችሉት አባቶች ብቻ ናቸው የሚለው ነው። ፔትሮና እንዲህ ትላለች:- “የጾጺል ሴቶች ከወንዶች ያነሱ እንደሆኑ ይነገራቸዋል። ወንዶቹ በጣም ኃይለኞች ናቸው። ወንዶች ልጆች ገና በሕፃንነታቸው አባቶቻቸውን በመኮረጅ እናቶቻቸውን ‘ምን ማድረግ እንዳለብኝ ልትነግሪኝ አትችይም። አባቴ አድርግ እስካላለኝ ድረስ የምትይውን አላደርግም’ ይሏቸዋል። ስለዚህ እናቶች ወንዶች ልጆቻቸውን ማስተማር አይችሉም። አሁን ግን እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ስላጠናች ወንድሞቼን በማስተማር ረገድ ውጤታማ ሆናለች። ወንድሞቼ ‘ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ . . . አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ኤፌሶን 6:1, 2 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ በቃል አጥንተውታል።”

በናይጄሪያ የምትኖር ሜሪ የምትባል እናትም እንደሚከተለው በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች:- “እኔ ባደግሁበት አካባቢ አንዲት እናት ወንዶች ልጆቿን እንድታስተምር ወይም እንድትቀጣ ባሕሉ አይፈቅድላትም። እኔ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን የጢሞቴዎስ አያትና እናት ማለትም የሎይድንና የኤውንቄን ምሳሌነት ተከትዬ ወንዶች ልጆቼን በማስተማር እንዲህ ባለው የባሕል ተጽዕኖ ላለመሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።”—2 ጢሞቴዎስ 1:5

በአንዳንድ አገሮች የሚዘወተረው ሌላው ልማድ ደግሞ ብዙዎች “የሴት ልጅ ግርዛት” ብለው የሚጠሩትና በአሁኑ ጊዜ የሴቶች የጾታ ብልት መቆረጥ የሚባለው ልማድ ነው። በዚህ ልማድ መሠረት የሴት ልጆች የጾታ ብልት የተወሰነው ወይም አብዛኛው ክፍል እንዲቆረጥ ይደረጋል። ይህ ልማድ ይፋ ወጥቶ ሊታወቅ የቻለው ታዋቂ የፋሽን ሞዴልና የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ልዩ አምባሳደር በሆነችው ዋሪስ ዲሪ አማካኝነት ነበር። በሶማሊያ ባለው ልማድ መሠረት እናቷ በልጅነቷ አስገርዘዋታል። በአንድ ዘገባ መሠረት በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ ከስምንት እስከ አሥር ሚሊዮን የሚደርሱ ሴቶችና ልጃገረዶች የዚህ ጎጂ ልማድ ሰለባ የመሆን አደጋ ተጋርጦባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥም እንኳ በግምት 10,000 የሚሆኑ ልጃገረዶች ግርዛት ሊደርስባቸው ይችላል።

ለዚህ ልማድ መሠረት የሚሆነው እምነት ምንድን ነው? አንዳንዶች የሴት ልጅ ብልት መጥፎ ስለሆነ ልጅቷን ያረክሳትና ቆማ እንድትቀር ያደርጋታል ብለው ያስባሉ። በተጨማሪም ልጅቷ ብልቷን መቆረጧ እስክታገባ ድረስ ክብረ ንጽሕናዋን ጠብቃ እንድትኖር ካገባች በኋላም ለባሏ ታማኝ እንድትሆን ዋስትና እንደሚሆን ተደርጎ ይታመናል። አንዲት እናት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ልማድ መሠረት ልጅዋን ሳታስገርዝ ብትቀር የባሏና የአካባቢው ማኅበረሰብ ቁጣ ይጠብቃታል።

ይሁን እንጂ ብዙ እናቶች ይህን ጎጂ ልማድ የሚደግፍ ሃይማኖታዊም ሆነ ሕክምና ነክ ወይም ከንጽሕና ጋር የተያያዘ ምክንያት እንደሌለ መገንዘብ ጀምረዋል። ናይጄሪያ ውስጥ የተዘጋጀ ሪፒውዲዬቲንግ ሪፐግናንት ካስተምስ (አስከፊ ልማዶችን እርግፍ አድርጎ መተው) የተሰኘ አንድ ጥናታዊ መጽሐፍ ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን ለዚህ ባሕል ላለማስገዛት በድፍረት እምቢ እንዳሉ ይገልጻል።

በእርግጥም በዓለም ዙሪያ ያሉ እናቶች በርካታ ተፈታታኝ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ልጆቻቸውን በተሳካ መንገድ እየጠበቁና እያስተማሯቸው ነው። ታዲያ ጥረታቸው በእርግጥ አድናቆት ተችሮታል?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ጥናቶች እንዳረጋገጡት ሴቶች የማይሳተፉበት ውጤታማ የልማት ስትራተጂ የለም። ሴቶች ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሲደረግ ጠቀሜታው ወዲያውኑ ይታያል፤ ማለትም ቤተሰቦች ከበፊቱ ይበልጥ ጤናማና በቂ ምግብ የሚያገኙ ይሆናሉ፤ ገቢያቸው፣ ተቀማጫቸውና ሀብታቸው እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰብ ውሎ አድሮም በብሔራት ደረጃ እውን ይሆናል።”—የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን፣ መጋቢት 8, 2003

[ምንጭ]

UN/DPI ፎቶ በሚልተን ግራንት

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለእኛ ስትል ብዙ መሥዋዕት ከፍላለች

ዡሊያኖ የሚባል አንድ ብራዚላዊ ወጣት እንደሚከተለው ብሏል:- “የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ተስፋ የሚጣልበት ቋሚ ሥራ ነበራት። ይሁን እንጂ እህቴ ስትወለድ እናታችን እኛን ለመንከባከብ ስትል ሥራዋን ለመልቀቅ ወሰነች። በሥራ ቦታዋ የነበሩ አማካሪዎች ሥራዋን እንዳትለቅ ሊያሳምኗት ሞክረው ነበር። እነዚህ ሰዎች ልጆቿ አግብተው ከቤት ሲወጡ ያደረገችላቸው ነገር ሁሉ መና እንደሚቀርና ልፋቷ ሁሉ ትርፍ ለሌለው ነገር እንደነበረ እንደምትገነዘብ ነገሯት። ነገር ግን እነርሱ ተሳስተው እንደነበር አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፤ በፍቅር ተነሳስታ ያደረገችልንን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም።”

[ሥዕሎች]

የዡሊያኖ እናት ከልጆቿ ጋር፣ በስተግራ:- ዡሊያኖ የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቢሽኑ ማንበብና መጻፍ ከተማረች በኋላ ወንዶች ልጆቿ ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ረድታቸዋለች

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንቶኒያ ትንሹ ልጅዋ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል ያቀርባል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፔትሮና ሜክሲኮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የፈቃደኝነት አገልግሎት እየሰጠች ነው። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናቷ የፔትሮናን ታናናሾች እያስተማረች ነው

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዋሪስ ዲሪ የሴቶችን ግዝረት በመቃወም የምትናገር የታወቀች ሴት ናት

[ምንጭ]

ፎቶ በሲያን ጋሉፕ/ Getty Images