በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናቶች ያሉባቸው ተፈታታኝ ችግሮች

እናቶች ያሉባቸው ተፈታታኝ ችግሮች

እናቶች ያሉባቸው ተፈታታኝ ችግሮች

“የሰው ልጅ ካሉት ተግባሮች መካከል መሠረታዊው ከቤተሰብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሥራዎች ናቸው። . . . እናት ተግባሯን ባታከናውን ኖሮ ተተኪ ትውልድ አይኖርም ነበር፤ ቢኖርም ካለመኖር አይሻልም።”—ቴዎዶር ሩዝቬልት፣ 26ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የእናት መኖር ለሰው ልጅ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ይሁንና የእናት የሥራ ድርሻ ልጆች ከመውለድ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። አንድ ጸሐፊ በአብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች ያሉ እናቶች ያላቸውን የሥራ ድርሻ በሚመለከት “ለእያንዳንዱ ልጅ ጤንነት፣ ትምህርት፣ የማሰብ ችሎታ፣ ባሕርይ፣ ጠባይና ስሜታዊ መረጋጋት ዋነኛ ተጠሪ እርሷ ነች” ብለዋል።

እናት ከምታከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል አንዱ የልጆቿ አስተማሪ መሆኗ ነው። አንድ ልጅ አፉን ሲፈታ የሚናገራቸው የመጀመሪያ ቃላትና የአነጋገሩ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ከእናቱ የሚማረው ነው። በመሆኑም ብዙውን ጊዜ የአንድ ሰው አፍ መፍቻ ቋንቋ የእናት ቋንቋ በመባል ይታወቃል። በአጠቃላይ ሲታይ በየዕለቱ ከአባትየው ይበልጥ ከልጆቹ ጋር ብዙ ጊዜ የምታሳልፈው እናት ስለሆነች ዋነኛዋ አስተማሪና ተግሣጽ ሰጪ እሷው ነች። በመሆኑም “ትምህርት በጡት ይገኛል” የሚለው የሜክሲኮ ምሳሌያዊ አነጋገር እናቶች ጠቃሚ የሥራ ድርሻ እንደሚያበረክቱ ምሥክርነት ይሰጣል።

ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክም ለእናቶች ክብር ይሰጣል። እንዲያውም “በእግዚአብሔር ጣት” በድንጋይ ጽላት ላይ ከተቀረጹት አሥርቱ ትእዛዛት መካከል “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ለልጆች የተሰጠው ማሳሰቢያ ይገኝበታል። (ዘፀአት 20:12፤ 31:18፤ ዘዳግም 9:10) ከዚህም በላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ‘የእናትህ ትምህርት’ በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 1:8) ልጆች ሦስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ይኸውም ገና በእናታቸው እንክብካቤ ሥር እያሉ የማስተማር ጠቀሜታ በአሁኑ ጊዜ በሠፊው ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል።

አንዳንዶቹ ተፈታታኝ ችግሮች ምንድን ናቸው?

ብዙዎቹ እናቶች ልጆቻቸው በዚህ ወሳኝ በሆነ ዕድሜ ላይ ሳሉ እንዳያስተምሯቸው እንቅፋት የሚሆንባቸው ችግር ቤተሰቡን በገንዘብ ለመደጎም ሲባል ተቀጥረው እንዲሠሩ ተጽዕኖ የሚደረግባቸው መሆኑ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰበሰበው አንድ አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በኢንዱስትሪ በበለጸጉ በርካታ አገሮች ውስጥ ከሦስት ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ ልጆች ካሏቸው እናቶች መካከል ከ50 በመቶ የሚበልጡት ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው።

በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ባሎቻቸው ሥራ ፍለጋ ወደ ሌላ ከተማ ወይም አገር ትተዋቸው ስለሚሄዱ ልጆቻቸውን የማሳደጉ ከባድ ኃላፊነት በእናቶች ጫንቃ ላይ ይወድቃል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የአርሜንያ ክልሎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ወንዶች ሥራ ፍለጋ ወደ ባሕር ማዶ ሄደዋል። ሌሎች እናቶች ደግሞ ባሎቻቸው ስለከዷቸው ወይም ስለሞቱባቸው ልጆቻቸውን ብቻቸውን ለማሳደግ ተገድደዋል።

በአንዳንድ አገሮች ለብዙ እናቶች ተፈታታኝ ችግር የሆነባቸው የትምህርት እጦት ነው። በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ልማት የተሰኘው ክፍል እንደገመተው በዓለም ዙሪያ ካሉት 876 ሚሊዮን ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። እንዲያውም ዩኔስኮ እንደሚለው ከሆነ በአፍሪካ፣ በአረብኛ ተናጋሪ አገሮች እንዲሁም በምሥራቅና ደቡብ እስያ ካሉ ሴቶች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማንበብም ሆነ መጻፍ የማይችሉ ናቸው። በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወንዶች ሴቶችን ማስተማር አስፈላጊ እንዳልሆነ እንዲያውም መማራቸው ልጅ የመውለድ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል ብለው ያምናሉ።

አውትሉክ የተሰኘው መጽሔት እንደሚናገረው ሕንድ ውስጥ በ15 ዓመት ዕድሜ የልጅ እናት መሆን የተለመደ በሆነበት በከራላ ግዛት በሚገኝ አንድ አውራጃ ውስጥ የተማረች ሴት ማግባት የሚፈልግ ወንድ የለም። በአጎራባቿ ፓኪስታን ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው ለወንዶች ልጆች ነው። ወንዶች ልጆች ወላጆቻቸው ሲያረጁ መጦር የሚያስችላቸውን ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራ እንዲያገኙ ሲባል ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው እንዲያድጉ ይደረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዉሜንስ ኤጁኬሽን ኢን ዴቨሎፒንግ ካንትሪስ (የሴቶች ትምህርት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች) የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚናገረው “ወላጆች ሴቶች ልጆቻቸው ለቤተሰባቸው የገንዘብ ድጎማ ማድረግ ይችላሉ ብለው ስለማያምኑ እነሱን ለማስተማር ገንዘብ ማውጣት አይፈልጉም።”

ከዚህም ሌላ የአካባቢው ባሕል የሚፈጥረው ተፈታታኝ ችግር አለ። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች አንዲት እናት ጥሎሽ ለማግኘት ሲባል ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ልጅዋን መዳርንና የሴት ልጅ ግርዛትን የመሳሰሉ ልማዶችን እንድትደግፍ ትገደዳለች። በተጨማሪም እናት ወንድ ልጆቿን ማስተማሯም ሆነ መቅጣቷ እንደ ነውር የሚታይባቸው ባሕሎችም አሉ። ታዲያ አንዲት እናት እንዲህ ዓይነቶቹን ልማዶች በመከተል ወንዶች ልጆቿን የማስተማሩን ኃላፊነት ለሌሎች መተው ይኖርባታል?

በሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች ላይ አንዳንድ እናቶች እንዲህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት እየተወጧቸው እንዳሉ እንመለከታለን። እንዲሁም እናቶችንና እናትነትን በእጅጉ ማድነቅ እንድንችል እንዲሁም እናቶች የልጆቻቸው አስተማሪ በመሆን ስለሚያከናውኑት ጠቃሚ ድርሻ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚያስችሉ አንዳንድ ሐሳቦችን እናያለን።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“የሕፃንን የመማር ችሎታና የማወቅ ጉጉት ከመቀስቀስ እንዲሁም የሕፃኑን/የሕፃኗን የፈጠራ ችሎታ ከማሳደግ ጋር በተያያዘ የእናት ድርሻ ወሳኝ ነው።”—በልጆች መብት ላይ በቡርኪናፋሶ የተደረገ የአካባቢው አገሮች የመሪዎች ጉባኤ፣ 1997

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እናቶች ከእያንዳንዱ ልጅ ጤንነት፣ ትምህርት፣ ባሕርይና ስሜታዊ መረጋጋት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ