በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የአውሮፓ ወንዶች ለመቆነጃጀት የሚያውሉት ጊዜ ጨምሯል

ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ የተባለው የለንደን ጋዜጣ “ባለፉት አምስት ዓመታት ወንዶች ለመቆነጃጀት የሚያውሉት ጊዜ በሳምንት በአማካይ 3.1 ሰዓት ሲደርስ የሴቶቹ ግን 2.5 ሰዓት ሆኗል” ሲል ዘግቧል። የወንዶቹ አምሮ የመታየት ፍላጎት በመጨመሩ ምክንያት ለወንዶች ታስበው የሚዘጋጁ የመዋቢያ ቅባቶችና ሽቶዎች ገበያ አድጓል። የእነዚህ ሸቀጦች ገበያ ባለፈው ዓመት 25 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን እስከ 2008 ድረስ 29 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል። የአንድ የወንዶች የውበት ሳሎን ሥራ አስኪያጅ “ገበያው እየተጧጧፈ መጥቷል። ፊታቸውን እንዲሁም የእግርና የእጅ ጥፍራቸውን ለማሳመር በየጊዜው እስከ 360 ዶላር የሚከፍሉ በርካታ ደንበኞች አሉ” ብለዋል። በተጨማሪም “በአሁኑ ጊዜ ከወንድ ሽቶዎች 60 በመቶ የሚሆነው የሚሸጠው ለሴት ጓደኞቻቸው ወይም ለሚስቶቻቸው ሳይሆን በቀጥታ ለወንዶቹ” እንደሆነ ጋዜጣው ገልጿል።

የባለሞያዎች ቁጥር በዝቷል

የሜክሲኮ ሲቲው ኤል ኡኒቨርሳል ጋዜጣ “በዛሬው ጊዜ ባለ ዲግሪ መሆን ሥራ ለማግኘት ዋስትና ሊሆን አልቻለም” ይላል። በሜክሲኮ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት “ከ1991 እስከ 2000 ባሉት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከወጡ ባለሞያዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ከተከታተሉት ትምህርት ጋር ዝምድና የሌለው ሥራ ለመያዝ ተገድደዋል” ሲል ገልጿል። ይህ ማለት 750,000 የሚያክሉ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን “እንደ ስልክ ኦፕሬተርነት፣ ሾፌርነት፣ ኮሜዲያን፣ አስማተኝነትና የመጠጥ ቤት አስተናጋጅነት” ያሉትን ዲግሪ የማይጠይቁ ሥራዎች ይሠራሉ ማለት ነው። በዘገባው ግምት መሠረት በ2006 በሜክሲኮ 131,000 አስተዳዳሪዎች፣ 100,000 የሂሣብ ሠራተኞች፣ 92,000 የኮምፒውተር መሐንዲሶች፣ 92,000 የአንደኛ ደረጃ መምህራን እንዲሁም 87,000 የሕግ ባለሞያዎች በሠለጠኑበት ሞያ ሥራ ሊያገኙ አይችሉም።

በቻይና የመኪናዎችና የብስክሌቶች ብዛት ሲነጻጸር

የቻይና ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ መጠን ብስክሌት ከመጋለብ ይልቅ መኪና መንዳት የሚመርጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ለምሳሌ ባሁኑ ጊዜ በዋነኝነት በብስክሌት የሚጓጓዙ የቤጂንግ ነዋሪዎች 25 በመቶ ሲሆኑ ከአሥር ዓመት በፊት ግን 60 በመቶ ይደርሱ ነበር። የካናዳው ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ “በቤጂንግ ብቻ በየዓመቱ ጎዳና ላይ የሚርመሰመሱ መኪናዎች ብዛት በ400,000 ይጨምራል” ሲል ዘግቧል። በመሆኑም ባሁኑ ጊዜ በዚህች ከተማ “አውራ ጎዳና ላይ በሰዓት ከ12 ኪሎ ሜትር በበለጠ ፍጥነት ማሽከርከር አይቻልም።” በ2003 በቻይና “አዳዲስ ከበርቴ ባለሞያዎች ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ መኪናዎች ተሻምተው የገዙ ሲሆን ይህ አኃዝ በ2002 ከነበረው በ70 በመቶ ይበልጣል” ሲል ናሽናል ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። በማከልም መንገደኞች የሚንቀሳቀሱት በጉልበት በሚነዳ ብስክሌት ሳይሆን በነዳጅ በሚንቀሳቀስ ሞተር በመሆኑ “ባሁኑ ጊዜ ቻይና በነዳጅ ፍጆታዋ ከዓለም የሁለተኛነቱን ቦታ በመያዝ ጃፓንን ሳትበልጥ አልቀረችም” ብሏል። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን በቻይና 470 ሚሊዮን ብስክሌቶች እንደሚኖሩ ይገመታል።

ለጨቅላ ሕፃናት ማንበብ ጠቃሚ ነው

ዘ ቶሮንቶ ስታር እንደሚለው “ለጨቅላ ሕፃናት ማንበብ በቀሪው ሕይወታቸው ላይ በጣም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ባሁኑ ጊዜ የመስኩ ባለሞያዎች ወላጆች ልጆቻቸው በተወለዱ ከሰዓታት ጊዜ ጀምሮ ቢያነቡላቸው ጥሩ እንደሚሆን ይናገራሉ።” በካናዳ አዲስ ለተወለዱ ልጆች የማንበብን አስፈላጊነት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በማራመድ ላይ የሚገኙት ዶክተር ሪቻርድ ጎልድብሉም “ከተማርናቸውና ካስተዋልናቸው ነገሮች አንዱ ጨቅላ ሕፃናት ሲነበብላቸው በትኩረት የሚያዳምጡ መሆናቸውን ነው። በእርግጥም ያዳምጣሉ” ብለዋል። ለልጆች ከጨቅላነታቸው ጀምሮ መጻሕፍት መስጠት የቃላትና የንባብ ችሎታቸውን እንደሚያሻሽልላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ። ጋዜጣው እንደሚለው “ነጥቡ ሕፃናቱ ማንበብ እንዲማሩ ማስገደድ ሳይሆን የቃላት፣ የሆሄያትና የድምፅ መለየት ችሎታ እንዲያዳብሩና ውሎ አድሮም የማንበብ ችሎታ ማግኘት እንዲችሉ ከቋንቋ ባሕርያት ጋር ማስተዋወቅ ነው።”

ጥበቃ ያላገኙ ዝርያዎች በመጥፋት ላይ ናቸው

ኤል ኮመርሲዮ የተባለው የፔሩ ጋዜጣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአካባቢ ጠባቂዎች 10 በመቶ የሚሆነውን የምድር ገጽ ከጥፋት ማዳን እንደቻሉ ገልጿል። ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ የሚያስመሰግን ውጤት ሊገኝ ቢችልም “ቢያንስ 300 የሚያክሉ ጨርሶ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው የአእዋፍ፣ የአጥቢ እንስሳትና የባሕር አራዊት ዝርያዎች” አሁን ባለው የተፈጥሮ ጥበቃ ሥርዓት ምንም ዓይነት ጥበቃ አይደረግላቸውም። ኮንሰርቬሽን ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት የጥበቃ ሳይንስና ፕሮግራሞች ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ጉስታቮ ፎንሴካ ችግሩ ባሁኑ ጊዜ የሚሠራባቸው የጥበቃ ግቦች “በፖለቲካ ረገድ አምረው ቢታዩም” በቂ አለመሆናቸው መሆኑን ገልጸዋል። “ጥበቃችንን ጥፋት ያንዣበበባቸው ዝርያዎች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አለብን” ብለዋል። ጋዜጣው ሊጠፉ የተቃረቡ ዝርያዎችን አደጋ ላይ የጣለውን ሌላ ምክንያት ሲጠቁም ዕፅና የጦር መሣሪያ ከማዘዋወር ቀጥሎ በጣም የተስፋፋ ሕገ ወጥ ንግድ የሆነውን ሊጠፉ የተቃረቡ ዝርያዎችን ሽያጭ ይጠቅሳል። በዓለም አቀፉ ሕገ ወጥ ገበያ ከሚሸጡት የእንስሳት ዝርያዎች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት ከደቡብ አሜሪካ ደኖች የሚመጡ ናቸው።

ከተቀመሙ መጠጦች ተጠንቀቅ

ዘ አውስትራሊያን የተባለው ጋዜጣ በአውስትራሊያ “በቀን እስከ አምስት የሚደርሱ ሰዎች በመጠጥ ቤቶች፣ በክለቦችና በግለሰብ ግብዣዎች ላይ የተቀመሙ መጠጦችን ከጠጡ በኋላ ወሲባዊ ነውር ተፈጽሞባቸዋል” በማለት አስጠንቅቋል። መጠጦቹ ጠጪው ሳያውቅ አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ ይጨመርባቸዋል። ከሚጨመሩት አደንዛዥ ዕፆች መካከል አንዳንዶቹ ቀለም፣ ጣዕም ወይም ሽታ የላቸውም። ይህን ዕፅ የተጨመረበትን መጠጥ የጠጡ ሰዎች ያሉበት ሊጠፋቸው፣ መንቀሳቀስ ሊያቅታቸውና ራሳቸውን ሊስቱ ይችላሉ። አንዳንዶቹም እስከ መሞት ደርሰዋል። የአውስትራሊያ የወንጀል ጥናት ተቋም ባደረገው አገር አቀፍ ጥናት “በየዓመቱ 4500 የሚያክሉ ሰዎች ሳያውቁ የተቀመመ መጠጥ እንደሚጠጡና ከእነዚህ መካከል ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑት ወሲባዊ ነውር እንደሚፈጸምባቸው” መታወቁን ጋዜጣው ዘግቧል። የጠጡት መጠጥ ኃይል ሲያልፍ ግለሰቦቹ ምን እንደተደረገባቸው እንኳን ላያስታውሱ ይችላሉ።

የምድር ኦዞን ሽፋን ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ይታይበታል?

በአውስትራሊያ የኮመንዌልዝ ሳይንሳዊና ኢንዱስትሪያዊ ምርምር ድርጅት የሚታተመው ኢኮስ የተባለ መጽሔት “በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የክሎሮፍሎሮካርበን (ሲ ኤፍ ሲ) መጠን መቀነስ ጀምሯል” ሲል ዘግቧል። በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘው ሲ ኤፍ ሲ ምድርን ከጎጂ ጨረር የሚከላከለውን የኦዞን ንጣፍ ይሸረሽራል። ባለፉት 50 ዓመታት በላይኛው የከባቢ አየር ክፍል የሚገኘው የሲ ኤፍ ሲ መጠን እስከ 2000 ድረስ ሲጨምር ቆይቶ ነበር። ከ2000 ወዲህ ግን የሲ ኤፍ ሲ መጠን በየዓመቱ በአንድ በመቶ ሲቀንስ እንደቆየ ኢኮስ ይገልጻል። በዚህ መጠን እየቀነሰ ከሄደ፣ ይላል ሪፖርቱ “የኦዞን ሽንቁር በዚህ ምዕተ ዓመት አጋማሽ ላይ ጨርሶ እስከ መደፈን ይደርሳል።” ይሁን እንጂ እነዚህ ኬሚካሎች አሁንም ጉዳት ማድረሳቸው አልቀረም። ሪፖርቱ “የመቀነስ አዝማሚያ ቢኖርም በዚህ ዓመት በአንታርክቲካ አናት ላይ የሚገኘው የኦዞን ንጣፍ ሽንቁር . . . 29 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ወይም የአውስትራሊያን የቆዳ ስፋት በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ነው” ይላል።