በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕክምና ሞያ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?

የሕክምና ሞያ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?

የሕክምና ሞያ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?

ስለ ሐኪሞች የወደፊት ዕጣ በሚነሳበት ጊዜ የሚታወሰው በቴክኖሎጂ ረገድ የሚገኘው እድገት ሲሆን ይህ እድገት ሐኪሞችን ተራ ከሆኑ የዕለት ተዕለት ተግባራት ገላግሎ የበለጠ ጊዜ ለታካሚዎቻቸው እንዲሰጡ ያስችላቸው ይሆን የሚል ጥያቄ ይነሳል። የሐኪሞች የወደፊት ዕጣ ከጠቅላላው የሰው ልጅ ዕጣ ተነጥሎ የሚታይ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። በዚህ ረገድ መረጃ የምናገኝባቸው ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስለ ኢየሱስና ስለ ሐዋርያት ይተርካሉ። ሁለቱም መጻሕፍት የተጻፉት በአንድ ሐኪም ነው።

እነዚህን ትረካዎች በተመለከተ በተለይ የሕክምና ባለሞያን አስተያየት ማግኘት ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ከሐኪሞችና ከታካሚዎች የወደፊት ዕጣ ጋርስ ምን የሚያገናኘው ነገር አለ? አንዳንድ ሐኪሞች የእነርሱ ሞያ አስፈላጊ የማይሆንበትን ጊዜ በናፍቆት የሚጠባበቁት ለምንድን ነው?

ብዙ ሐኪሞች ነገሮችን በትኩረት የመከታተል ባሕርይ አላቸው። ‘የተወደደው ሐኪም’ ተብሎ የተጠራው ሉቃስ የሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጸሐፊ ሲሆን ኢየሱስና ሐዋርያት ስለፈወሷቸው አንዳንድ ሕመምተኞች ዝርዝር መግለጫ ሰጥቷል። (ቆላስይስ 4:14) በመሆኑም ሉቃስ እነዚህ ነገሮች በእርግጥ ተፈጽመው ነበር? ተፈጽመውስ ከነበረ ለዘመናችን ሕመምተኞችና ሐኪሞች ምን ትርጉም ይኖራቸዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንድንመረምር ይረዳናል።

የሕክምና መረጃዎች ተመርምረዋል

ሉቃስ የእነዚህን ፈውሶች ተአምራዊ ባሕርይ የዓይን ምሥክሮችን ጠይቆ የማጣራት አጋጣሚ ነበረው። በተጨማሪም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ሆኖ ረዥም ጉዞ አድርጓል። ጳውሎስም ሉቃስ አብሮት እያለ ብዙ ሰዎችን ሳይፈውስ አልቀረም። ይህ ሐኪም በወቅቱ ስለተከናወኑ ሁለት ፈውሶች የሚተርክልንን በምንመለከትበት ጊዜ ሁኔታዎቹን እንዴት ዘርዝሮ እንደገለጸ ልብ በል።

ሉቃስ የሚከተለው ክንውን የተፈጸመበትን ሰዓት፣ ቀንና ቦታ ይገልጻል። በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እኩለ ሌሊት ላይ የተወሰኑ ክርስቲያኖች ጢሮአዳ በምትባለው የሮማ ግዛት በሦስተኛ ፎቅ በሚገኝ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:4-8) የሆነውን ነገር እንዲህ እናነባለን:- “አውጤኪስ የተባለ አንድ ጐበዝም በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አለውና ጭልጥ ብሎ ተኛ፤ ከሦስተኛውም ፎቅ ቊልቊል ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት።” ከዚያም ጳውሎስ በአምላክ ኃይል ፈወሰውና ወደ ሕይወት መለሰው። ምግብ ከበሉ በኋላ “ያን ጐበዝ ሕያው ሆኖ ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ።”—የሐዋርያት ሥራ 20:9-12

በተጨማሪም ሉቃስ ከጳውሎስ ጋር በሚሊጢን ደሴት እንደነበር ዘግቧል። ጳውሎስ ሌላ ተአምር በፈጸመበት በዚህ ወቅት የደሴቲቱ “አለቃ” በነበረው በፑፕልዮስ ቤት ይስተናገዱ ነበር። የተፈወሰው ሰው ዘመናዊ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ባልተገኙበት በዚያ ዘመን ለሞት በሚያደርስ ሕመም ተይዟል። ሉቃስ እንዲህ በማለት ይተርካል:- “የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ፣ በደሴቲቱ የነበሩ ሌሎች ሕመምተኞችም እየመጡ ተፈወሱ።”—የሐዋርያት ሥራ 28:7-9

ሐኪሙን እንዲያምን ያደረገው ነገር ምን ነበር?

ሉቃስ እነዚህን ታሪኮች በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የጻፈው አንባቢዎቹ ያነበቧቸውን ነገሮች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች ጠይቀው ሊያረጋግጡ በሚችሉበት ጊዜ ነው። ሉቃስ በስሙ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ስለጻፋቸው ነገሮች ሲናገር ‘ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ መርምሬ የጻፍኩልህ እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው’ ብሏል። (ሉቃስ 1:3, 4) ይህ ሐኪም የተመለከታቸውና በምርምር የደረሰባቸው ነገሮች የኢየሱስ ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን አሳምነውታል። ተአምራዊዎቹ ፈውሶች የእነዚህ ትምህርቶች አንድ ክፍል ሲሆኑ በሽታ በአምላክ ድል እንደሚነሳ የሚናገረው ትንቢት እርግጠኛ መሆኑን እንድናምን መሠረት ይሆኑናል። (ኢሳይያስ 35:5, 6) ሉቃስ የሕክምና ባለሞያ እንደመሆኑ የብዙ ሰዎችን ሥቃይ ስላየ የእርሱ ሞያ አስፈላጊ የማይሆንበትን ጊዜ አሻግሮ ሲመለከት ልቡ በደስታ ሳይሞላ አልቀረም። አንተስ እንዲህ ያለው ተስፋ ያስደስትሃል?

አምላክን የሚወዱ ሰዎች በሙሉ የትም ይኑሩ የት እንዲህ ያለ የወደፊት ተስፋ ይጠብቃቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት ሥር የሚኖር ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” የማይልበት ዘመን እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 33:24) ብዙ የዘመናችን ሐኪሞችም የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ የምናምንበት በቂ ምክንያት አለ ብለው ለመደምደም ችለዋል።

‘በእጅጉ ልቤን ማረከው’

በሰሜን አሜሪካ የሚኖረውና የቤተሰብ ሐኪም የሆነው ጆን ሺለር “እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ወደ ሕክምና ሞያ የገባሁት በሕመም የሚሰቃዩ ሰዎችን ለመርዳት ስል ነበር” ይላል። “በሽታ የሌለበት ዓለም የመምጣቱ ተስፋ በእጅጉ ልቤን ነካው። የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች መሄድ የጀመርኩት ስለ ምዕራባዊው ሥልጣኔ ታሪክ የሚገልጽ የኮሌጅ ትምህርት ከተከታተልኩ በኋላ ነበር። ከዚህ ትምህርት የብዙ ችግሮች ምንጭ ሃይማኖቶች እንደሆኑ ተረዳሁ። መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን የሚሉት በግብዝነት እንደሆነ ታየኝ። በዚህም ምክንያት ‘መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል የሚለው ምንድን ነው?’ ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።”

“በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ስገኝ መጀመሪያ የሳበኝ ነገር በዚያ ያገኘኋቸው ሰዎች ከዚህ በፊት ከማውቃቸው ሰዎች በተለየ መልኩ ያሳዩኝ የወዳጅነት መንፈስ ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር ቀረበኝና ቤቴ ድረስ እየመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ሊያደርግልኝ ፈቃደኛ እንደሆነ ነገረኝ። በጣም ልቤን የነካው ነገር ምንም ዓይነት ጥያቄ ብጠይቀው መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊያሳየኝ መቻሉ ነበር።”

“ዕድሜዬ እየገፋ በሄደ መጠን የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ይበልጥ እያደነቅሁ መጣሁ። የሕክምና ሞያ እንደጀመርክ አንድ ቁምነገር ያለው ሥራ አከናውናለሁ ብለህ ተስፋ ታደርጋለህ። ይሁን እንጂ በአብዛኛው የተመለከትኩት እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ያለው ሥራ መሥራት ባለመቻላቸው ግራ የተጋቡ ሰዎች ነው። የይሖዋ ምሥክር መሆን የሚያስገኘው ትልቅ ነገር ተስፋና ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ይመስለኛል። ዶክተሮችም ሆን መካኒኮች ወይም ጽዳት ሠራተኞች፣ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ትልቅ ዋጋ እንዳለውና ለይሖዋ አንድ ነገር እያደረግን እንዳለን እናውቃለን። ይህ ደግሞ እርካታ ያስገኝልናል።”

“የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋላችን የቤተሰባችንን ኑሮ አሻሽሎልናል”

ዶክተር ክሪስተር ረንቫል በፊንላንድ የሚኖር ሐኪም ሲሆን ሁልጊዜ ከልጆች ጋር ማውራት ያስደስተዋል። “ከዕለታት አንድ ቀን መዳኛ በሌለው የካንሰር በሽታ ከምትሰቃይ የ12 ዓመት ልጅ ጋር ተነጋገርኩ” ይላል። አክሎም እንዲህ ይላል:- “እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት—ከየት ማግኘት ይቻላል? * (እንግሊዝኛ) የሚል መጽሐፍ ሰጠችኝ። ለሞት በሚያደርስ ሕመም እየተሰቃየች ስለ እምነቷ የተናገረችው ሁሉ ልቤን ቢነካውም መጽሐፉን ለማንበብ ጊዜ አላገኘሁም። እንዲያውም በዚያ ጊዜ እሠራበት በነበረው በሄልሲንኪ በሚገኝ ክሊኒክ ውስጥ በጣም ሥራ ይበዛብኝ ስለነበረ ትዳሬ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቆ ነበር።”

“ከጊዜ በኋላ ግን ባለቤቴ መጽሐፉን ከመደርደሪያ ላይ አንስታ ማንበብ ጀመረች። ወዲያውኑ የምታነበው ሁሉ እውነት እንደሆነ አመነች። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን እየመጣች መጽሐፍ ቅዱስን ታስጠናት ጀመር። መጀመሪያ ላይ ባለቤቴ ልትነግረኝ ፈርታ ነበር። በነገረችኝ ጊዜ ግን ‘ትዳራችንን ሊጠቅም የሚችል ነገር ከሆነ ጥሩ ነው’ አልኳት። እኔም በጥናቱ መካፈል ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋላችን ትዳራችንን ከማሻሻሉም በላይ ለሕይወት አዲስ አመለካከት እንዲኖረን አስቻለን። በሽታ የማይኖርበት ዓለም እንደሚመጣ ማወቄ በጣም አስደሰተኝ። አምላክ ለሰው ልጆች እንዲህ ያለ ዓላማ ያለው መሆኑ ተገቢ ሆኖ ታየኝ። ወዲያው እኔና ባለቤቴ፣ በመጨረሻ ደግሞ ልጆቼ ተጠመቅን። መጀመሪያ ያነጋገረችኝ ያቺ ትንሽ ልጅ ብትሞትም እምነቷ ሕያው ሆኖ ይኖራል።”

በዚህ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘው ዓለም ውስጥ የዶክተሮች ሕይወት ይበልጥ ውጥረት የበዛበት ሆኗል። በመሆኑም ሕሙማንን ለመርዳት ሲሉ የሚከፍሉት መሥዋዕትነት በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ እስከ ዛሬ ገጥሞት የማያውቅ ትልቅ ለውጥ በቅርብ ይመጣል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሐኪሞች አምላክ በሽታ የማይኖርበት ዓለም እንደሚመጣ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በእርግጠኝነት እየጠበቁ ነው። (ራእይ 21:1-4) ይህ በግልህ ልትመረምረው የሚገባ ጉዳይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 10,11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ሕይወት ዓላማ እንዳለው ተገነዘብኩ”

“የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ተማሪዎች እንክብካቤ በማደርግበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ከሌሎቹ የተለዩ እንደሆኑ ተገነዘብኩ። የአካል ጉዳት ላለባቸው ልጆቻቸው እንክብካቤ በማድረግ ረገድ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሚገኙ ሌሎች ወላጆች የተሻሉ ናቸው። በተጨማሪም ያላቸው የእውቀት ደረጃ ከተሰማሩበት ሞያ የማይጠበቅ ነው። ለእምነታቸው አድናቆት አደረብኝ። የእኔ እምነት በዝግመተ ለውጥ አስተማሪዎች ፈጽሞ ጠፍቶብኝ ነበር። ቢሆንም ከሕክምና ትምህርት ያገኘሁት እውቀት በጣም አስደናቂ ስለሆነው የሕይወት ምሥጢር በውስጤ ጥያቄ ፈጥሮብኛል።”

“በዚሁ ጊዜ ልጆቼን እንዴት እንደማሳድግ የማውቀው ነገር እንደሌለ መገንዘብ ጀመርኩ። ምን ነገሮችን ልከልክላቸው? ምን ነገሮችንስ እንዲያደርጉ ላበረታታቸው? የሕይወት ዓላማ ይህ ነው ብዬ ልሰጣቸው የምችለው ነገር ምንድን ነው? የገዛ ራሴም ሕይወት ትርጉም የለሽ ሆኖብኝ ነበር። እርዳታ እንዳገኝ ጸለይኩ።”

“የይሖዋ ምሥክሮች ልጆችን እንዴት ማስተካከልና መገሠጽ እንደሚቻል የሚገልጽ መጽሔት ያመጡልኝ በዚህ ጊዜ ነበር። በመጽሔቱ ውስጥ የተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በእርግጥ ጠቃሚ እንደሆኑ ተገነዘብኩ። በዚህም ምክንያት ያቀረቡልኝን ግብዣ ተቀብዬ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ይሖዋ ሕይወት የፈጠረው ለምን እንደሆነና ኢየሱስ ለምን እንደሞተልን ሳውቅ ሕይወት ዓላማ እንዳለው ተገነዘብኩ። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5:12, 18, 19) ዝግመተ ለውጥ አስተሳሰቤን አጣሞብኝ ነበር። በሽታና ሞት በመጀመሪያው የአምላክ ዓላማ ውስጥ እንደማይገኙ ሳውቅ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። በአሁኑ ጊዜ አምላክ በቅርቡ እንዴት ሁሉንም ዓይነት በሽታዎች እንደሚያስወግድ ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች በማስተማር እውነተኛ እርካታ አገኛለሁ።”

[ሥዕሎች]

ሄሌና ባውሂስ በኔዘርላንድስ የተማሪዎች ሐኪም ነች

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሐዋርያው ጳውሎስ የፑፕልዮስን አባት በፈወሰና አውጤኪስን ከሞት ባስነሳ ጊዜ ሐኪምና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ሉቃስ የጳውሎስ የጉዞ ባልደረባ ነበር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዶክተር ጆን ሺለር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዶክተር ክሪስተር ረንቫል፣ ፊንላንድ