በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ በሁሉም ስፍራ ይገኛል?

አምላክ በሁሉም ስፍራ ይገኛል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክ በሁሉም ስፍራ ይገኛል?

አምላክ ሁሉን ቻይና ሁሉን ነገር የሚያውቅ ነው መባሉ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች የአምላክን ታላቅነት ለመግለጽ በሁሉም ስፍራ በተመሳሳይ ጊዜ ይገኛል በማለት ጭምር ይናገራሉ።

ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሁለት መግለጫዎች በግልጽ የሚደግፉ ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ እናገኛለን። (ዘፍጥረት 17:1፤ ዕብራውያን 4:13፤ ራእይ 11:17) አምላክ ሁሉን ቻይ ከመሆኑም በላይ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ በመሆኑ ከእርሱ የሚሰወር ነገር የለም። ነገር ግን አምላክ በሁሉም ቦታ የሚገኝ ነው ወይስ በአንድ የተወሰነ ስፍራ?

አምላክ የሚኖረው የት ነው?

በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች “ሰማይ” የአምላክ “ማደሪያ” እንደሆነ ይናገራሉ። (1 ነገሥት 8:39, 43, 49፤ 2 ዜና መዋዕል 6:33, 39) ይሁን እንጂ ቀጥሎ የተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ አምላክ ምን ያህል ከፍ ያለ መሆኑን ይናገራል:- “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም።”—2 ዜና መዋዕል 6:18

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ይላል። (ዮሐንስ 4:24) ስለዚህ አምላክ ከግዑዙ ጽንፈ ዓለም በተለየ መንፈሳዊ ስፍራ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማይ” የአምላክ መኖሪያ እንደሆነ ሲናገር፣ እርሱ የሚኖርበት ስፍራ እኛ ከምንኖርበት ግዑዙ አካባቢ እጅግ የላቀና ክብር የተላበሰ መሆኑን መግለጹ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መኖሪያ ከግዑዙ ጽንፈ ዓለም ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ የሚናገር ቢሆንም በአንድ የተወሰነ ቦታ እንደሚኖር ጭምር ይገልጻል።—ኢዮብ 2:1, 2

አምላክ ራሱን የቻለ አካል ነው

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ . . . የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው” በማለት ስለ ይሖዋ መኖሪያ ቦታ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:2) ኢየሱስ የሄደው ወዴት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት፣ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ” ይላል። (ዕብራውያን 9:24) ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ሁለት አስፈላጊ ቁም ነገሮችን ያስገነዝበናል። በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ ቃል በቃል የመኖሪያ ቦታ እንዳለው በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በየትኛውም ስፍራ የሚገኝ ይሄ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል ኃይል ሳይሆን አንድ እውን አካል እንደሆነ ያስገነዝበናል።

ኢየሱስ ተከታዮቹ እውን አካል ለሆነውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰማይ ተብሎ በተጠቀሰው መንፈሳዊ ዓለም ለሚኖረው ይሖዋ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 6:9፤ 12:50) ይህ ትምህርት ከዚያ ቀደም ብሎ የአምላክ ሕዝቦች ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት ይጸልዩበት ከነበረው መንገድ ጋር ይመሳሰላል። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ጥንታዊ ጽሑፎች የሚከተለውን ጸሎት ይዘዋል:- “ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ተመልከት፤ ሕዝብህን . . . ባርክ።”—ዘዳግም 26:15

ቦታ የማይገድበው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የተወሰነ መኖሪያ ቦታ እንዳለው ቢናገርም ቅዱስ መንፈሱ ግን በማንኛውም ስፍራ እንደሚገኝ በርካታ ጊዜያት ጠቅሷል። መዝሙራዊው ዳዊት “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል። (መዝሙር 139:7) አንዳንዶች እንዲህ ባሉት አገላለጾች ግራ በመጋባት አምላክ በየትኛውም ስፍራ ይገኛል ብለው ይደመድሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህም ሆነ በሌሎች ጥቅሶች ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስንመለከት ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ወይም የተለያየ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይሉን፣ ካለበት ሥፍራ ሆኖ በግዑዙ ጽንፈ ዓለም ውስጥ ወደ የትኛውም ስፍራ ሊልከው እንደሚችል እንረዳለን።

አንድ አባት ልጆቹን ለመደገፍና ለመርዳት እጁን እንደሚዘረጋላቸው ሁሉ ይሖዋም እጁን ማለትም ቅዱስ መንፈሱን ወደ መንፈሳዊ ዓለምም ሆነ ወደ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም በመላክ ዓላማውን ያከናውናል። መዝሙራዊው “በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው።—መዝሙር 139:9, 10

የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ

ይሖዋ ትሑትና አፍቃሪ በመሆኑ ከእውነተኛ ማንነቱ ጋር በጣም ተቀራራቢ በሆነ መንገድ ስለ ራሱና ስለ መኖሪያ ቦታው የሰው ልጆች በሚገባቸው መልኩ ገልጿል። በዚህና በሌሎች መንገዶች ይሖዋ ‘በሰማይና በምድር ያሉትን ለማየት፣ ራሱን ወደ ታች ዝቅ ያደረገ’ ያህል ነው። (መዝሙር 113:6) ይህም ሆኖ የአምላክ ማንነት ከሰው ልጅ የመረዳት ችሎታ በላይ ነው።

ይሖዋ ዕጹብ ድንቅ፣ እጅግ በጣም ታላቅና በጣም ግሩም አምላክ ስለሆነ በሰብዓዊ አንደበት እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በሰማይ በአንድ የተወሰነ ሥፍራ እንደሚኖር ቢናገርም ሰዎች ይህን መንፈሳዊ የይሖዋ መኖሪያ ሙሉ በሙሉ ሊረዱት አይችሉም።—መዝሙር 139:6

ያም ሆኖ ስለ ይሖዋ እውነተኛ ማንነት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማወቅ መቻላችን ያስደስታል፤ አምላክ ይሄ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል እንዳልሆነና በጽንፈ ዓለም ባሉት ነገሮች ሁሉ ውስጥ የሚገኝ የተወሰነ አካል የሌለው ኃይል እንዳልሆነ ተገንዝበናል። ከዚህ ይልቅ ራሱን የቻለ፣ የተወሰነ መኖሪያ ያለውና በፍቅሩና በርኅራኄው ተለይቶ የሚታወቅ አምላክ ነው። የሰው ልጆች እንዲህ ያለው እውቀት ያላቸው መሆኑ የጽንፈ ዓለሙ ልዑል ከሆነው ሁሉን ቻይ አምላክ ጋር ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ የግል ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።—ያዕቆብ 4:8