እየተመናመነ የሚገኘው የምድር የተፈጥሮ ሀብት
እየተመናመነ የሚገኘው የምድር የተፈጥሮ ሀብት
“በተፈጥሮ ውስጥ ሁሉ ነገር እርስ በርሱ የተቆላለፈ ነው። በመሆኑም ባሁኑ ጊዜ በቀደሙት ዘመናት ለሠራናቸው ከባድ ስህተቶች ዋጋ በመክፈል ላይ ነን።”—አፍሪካን ዋይልድላይፍ መጽሔት
አንዳንዶች በሰው ልጅ የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀምና ምድር እነዚህን ሀብቶች ለመተካት ባላት ችሎታ መካከል ያለው ልዩነት የሚለካበትን ዘዴ ሥነ ምሕዳራዊ ዱካ ይሉታል። ይህ የመለኪያ ዘዴ ከ1980ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ሰዎች የተፈጥሮን ሀብት ሊተካ በማይችል ፍጥነት እያሟጠጡት መሆናቸውን እንደሚጠቁም ወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ የተባለው ድርጅት ዘግቧል። * ይሁን እንጂ ይህ በአካባቢያችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ጫና የሚለካበት አንደኛው ዘዴ ብቻ ነው።
ሌላው መለኪያ የምድር ሥነ ምሕዳራዊ ሥርዓት ወይም ኤኮሲስተም ተብሎ የሚጠራው ሁኔታ ነው። “ኤኮሲስተም” የሚለው ቃል በተፈጥሮ ከባቢ ውስጥ የሚገኙ ሕይወት ያላቸውና ሕይወት የሌላቸው ፍጥረቶች አንዳቸው ከሌላው ጋር የሚኖራቸውን የተወሳሰበ መስተጋብር ያመለክታል። የእነዚህ ኤኮሲስተሞች ደኅንነት የሚለካው በደኖችና በንጹሕ ውኃ መጠን እንዲሁም እነዚህ ሊያኖሩ በሚችሏቸው የእንስሳት ዝርያዎች ብዛት ነው። ወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ የምድር ሥነ ምሕዳራዊ ሥርዓት ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሚጠቁመውን አኃዛዊ መረጃ ዘ ሊቪንግ ፕላኔት ኢንዴክስ ወይም የፕላኔታችንን ሕይወት የማኖር አቅም የሚጠቁም አኃዛዊ መረጃ በማለት ይጠራዋል። ይህ አኃዝ ከ1970 እስከ 2000 ባሉት ዓመታት 37 በመቶ አሽቆልቁሏል።
ለሁሉም ሊዳረስ የሚችል በቂ የተፈጥሮ ሀብት አለ?
የገበያ አዳራሾች በተለያዩ ሸቀጦች በተጨናነቁባቸውና ሌትም ሆነ ቀን እንደልብ መሸመት በሚቻልባቸው ምዕራባውያን አገሮች የምትኖር ከሆነ የተፈጥሮ ሀብቶች መመናመን አስጊነት ላይታይህ ይችላል። ይሁን እንጂ ከምድር ነዋሪዎች መካከል የተመቻቸ ኑሮ የሚኖሩት ጥቂቶች ናቸው። አብዛኞቹ ጉሮሯቸውን ዘግተው ለማደር ሲማስኑ የሚኖሩ ናቸው። ለምሳሌ ከሁለት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከሦስት ዶላር ባነስ የቀን ገቢ የሚተዳደሩ እንደሆኑና ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት አቅም የሌላቸው እንደሆኑ ይገመታል።
አንዳንዶች በማደግ ላይ ለሚገኙ አገሮች ድህነት ምክንያቱ ሀብታሞቹ አገሮች የሚያራምዱት የንግድ ሥርዓት እንደሆነ ይናገራሉ። ቫይታል ሳይንስ 2003 የተባለው ጽሑፍ “የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት በተለያዩ መንገዶች የድሆቹን ጥቅም ይጻረራል” ይላል። ከተፈጥሮ ሀብት የተወሰነ ድርሻ ለማግኘት የሚሻሙ ሰዎች ቁጥር እየበዛ በሄደ መጠን በኢኮኖሚ የተጎዱ ሕዝቦች ተሻምተው ድርሻቸውን ማግኘት ያቅታቸዋል። ይህ ደግሞ አቅም ያላቸው ባለጠጎች በተፈጥሮ ሀብቶች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
በመውደም ላይ የሚገኙ ደኖች
ከአፍሪካ ነዋሪዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ምግባቸውን የሚያበስሉት በእንጨት እንደሆነ ይገመታል። በተጨማሪም “አፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ጭማሪና
የከተሞች መስፋፋት የሚታይባት አህጉር” እንደሆነች የደቡብ አፍሪካው ጌትአዌይ መጽሔት ይናገራል። በዚህ ምክንያት ሳሄል ተብሎ በሚጠራው በሰሃራ በረሃ ደቡባዊ ጠርዝ በሚገኝ ከፊል በረሃማ የምድር ክፍል ባሉ በአንዳንድ ሰፋፊ ከተሞች ዙሪያ እስከ 100 ኪሎ ሜትር የሚደርስ መሬት ደን አልባ ሆኗል። እነዚህ ዛፎች እንዲሁ ያለምክንያት የተጨፈጨፉ አይደሉም። ፕሮፌሰር ሳሙኤል ናና-ሲንካም እንደሚሉት ‘አብዛኞቹ የአፍሪካ ሕዝቦች የገዛ ራሳቸውን ከባቢ የሚያወድሙት ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ብቻ ነው።’በደቡብ አሜሪካ ያለው ሁኔታ ደግሞ ከዚህ ጨርሶ የተለየ ነው። ለምሳሌ በብራዚል በዝናባማው የደን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ 7,600 የሚያክሉ የተመዘገቡ ዛፍ ቆራጭ ኩባንያዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በርካታ ገንዘብ ያላቸውና ቅርንጫፎቻቸውን በበርካታ አገሮች የዘረጉ ታላላቅ የንግድ ድርጅቶች ንብረቶች ናቸው። አንድ የእንጨት ንግድ ድርጅት አንድ ማሆጋኒ የተባለ ዛፍ ለመግዛት የሚያስፈልገው ገንዘብ ከ30 ዶላር አይበልጥም። ደላሎች፣ ነጋዴዎችና አምራቾች የትርፍ ድርሻቸውን ከወሰዱ በኋላ ግን የዚሁ ዛፍ ዋጋ ለቤት ዕቃ ሸማቾች ከመቅረቡ በፊት 130,000 ዶላር ይደርሳል። ማሆጋኒ “አረንጓዴው ወርቅ” መባሉ አያስደንቅም።
ስለ ብራዚል ደን መውደም ብዙ ተብሏል። ከ1995 እስከ 2000 በብራዚል በየዓመቱ 20,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ደን ይወድም እንደነበረ ከሳተላይት የተነሱ ፎቶ ግራፎች ያመለክታሉ። “ይህን ያህል አስደንጋጭ ውድመት ነበር ማለት አንድ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክል ስፋት ያለው ደን በየስምንት ሴኮንዱ ይወድም ነበር ማለት ነው” ሲል የብራዚሉ ቬጃ መጽሔት ዘግቧል። በ2000 ከተሸጡት የብራዚል ማሆጋኒ እንጨቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆነውን የገዛችው ዩናይትድ ስቴትስ መሆኗ ያስገርማል።
በሌሎች የዓለም ክፍሎችም የሚካሄደው የደን ጭፍጨፋ ከዚህ የተለየ አይደለም። ለምሳሌ ከሜክሲኮ ደኖችና ጫካዎች መካከል ግማሽ የሚያክለው የወደመው ባለፉት 50 ዓመታት ነው። የፊሊፒንስ ደኖች ውድመት ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው። በዚህች አገር በየዓመቱ 100,000 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ደን ይወድማል። በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ በዚህች አገር ከሚገኘው ደን ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚወድም በ1999 ተገምቶ ነበር።
አንድ ለቤት ቁሳቁስ መሥሪያ የሚያገለግል ዛፍ አድጎ ለመቆረጥ እስኪደርስ ከ60 እስከ 100 ዓመት ሊፈጅበት ይችላል። ሆኖም ዛፍ ቆርጦ ለመጣል የሚያስፈልገው ጊዜ ከደቂቃዎች አይበልጥም። ታዲያ ደኖች ተመናምነው ማለቃቸው ሊያስደንቀን ይገባል?
የአፈር መከላት
ሣር ቅጠሉ ወድሞ ምድሩ ራቁቱን በሚቀርበት ጊዜ አፈሩ ይደርቅና በነፋስ ወይም በውኃ ተጠርጎ ይወሰዳል። ይህ ሂደት የአፈር መሸርሸር ይባላል።
የአፈር መሸርሸር ተፈጥሯዊ ሂደት በመሆኑ በሰው
ልጅ መጥፎ አያያዝ ምክንያት ካልተፋጠነ በስተቀር በጣም አሳሳቢ ችግር አይደለም። ለምሳሌ ቻይና ቱዴይ የተባለው መጽሔት አሸዋማ አውሎ ነፋሶች ከደን መጨፍጨፍና ከግጦሽ መሬት መራቆት ጋር ተዳምረው የበረሃማነትን “መስፋፋት በጣም አፋጥነውታል” ሲል ዘግቧል። በቅርብ ዓመታት በተከሰተው ያልተለመደ ድርቅ ምክንያት የአገሪቱ ሰሜናዊና ሰሜን ምዕራባዊ ክፍሎች በቀዝቃዛው የሳይቤሪያ ነፋስ በእጅጉ ተጠቅተዋል። በሚሊዮን ቶኖች የሚመዘን አሸዋና የአፈር ብናኝ ተጠራርጎ እስከ ጃፓንና ኮሪያ ተወስዷል። በአሁኑ ጊዜ ከቻይና መሬት 25 በመቶ የሚሆነው በረሃ ሆኗል።የአፍሪካ አፈርም ለጉዳት የተዳረገው በዚሁ ምክንያት ነው። አፍሪካ ጂኦግራፊክ “ገበሬዎች ደኖችን መንጥረው እህል በመዝራት ከላይ የሚገኘውን ለም አፈር ተመልሶ ሊጠገን በማይችል ሁኔታ አጥፍተዋል” ይላል። አንድ መሬት ከተመነጠረ በኋላ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለምነቱን እስከ 50 በመቶ ድረስ እንደሚያጣ ተገምቷል። ስለሆነም መጽሔቱ በማከል “በአንዳንድ አካባቢዎች ከእርሻ የሚገኘው ምርት ከዓመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ በሚሄድበት ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮን ሄክታሮች የሚለካ መሬት ለምነቱን ያጣ ሲሆን በሚሊዮን ሄክታሮች የሚለካ ሌላ ተጨማሪ መሬት ደግሞ ወደዚሁ አቅጣጫ እያመራ ነው” ብሏል።
ብራዚል በየዓመቱ 500 ሚሊዮን ቶን የሚያክል አፈር በአፈር መሸርሸር ምክንያት እንደምታጣ ይገመታል። በሜክሲኮ የከባቢና የተፈጥሮ ሀብት መሥሪያ ቤት እንደሚለው ከቁጥቋጧማ መሬት 53 በመቶ፣ ጫካ ካለባቸው መሬቶች 59 በመቶ እንዲሁም ከደን መሬቶች ደግሞ 72 በመቶ የሚሆነው በአፈር መከላት ተጎድቷል። በአጠቃላይ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ያዘጋጀው አንድ ሪፖርት እንደሚለው “ለእርሻ ከዋለው የዓለም መሬት ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው በአፈር መከላት ሳይጎዳ አልቀረም። በዚህም ምክንያት የእርሻ ምርት በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ መጥቷል። የዕለት ጉርስ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ግን ከቀን ወደ ቀን ጨምሯል።”
ውኃ—ነፃ ግን ሊተመን የማይችል ዋጋ ያለው
አንድ ሰው ምግብ ሳያገኝ አንድ ወር ያህል በሕይወት ሊቆይ ሲችል ውኃ ካላገኘ ግን በአንድ ሳምንት ውስጥ ይሞታል። ስለዚህ በመጪዎቹ ዓመታት የውኃ አቅርቦት መቀነስ ለብዙ ግጭቶች መንስኤ እንደሚሆን ሊቃውንት ይገምታሉ። ታይም መጽሔት በ2002 ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በመላው ዓለም ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በቀላሉ አያገኙም።
በተለያዩ ምክንያቶች የውኃ እጥረት ይፈጠራል። በፈረንሳይ ዋነኛው ምክንያት ብክለት ሲሆን ይህም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። “የፈረንሳይ ወንዞች ክፉኛ ተበላሽተዋል” ይላል ለ ፊጋሮ የተባለው ጋዜጣ። ሳይንቲስቶች በምክንያትነት የሚጠቅሱት ለግብርና ሥራ ከዋለው ማዳበሪያ እየሰረገ የሚገባውን ናይትሬት ነው። ይኸው ጋዜጣ “ከፈረንሳይ ወንዞች በ1999 ብቻ 375,000 ቶን የሚመዝን ናይትሬት ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ሰርጎ የገባ ሲሆን ይህ አኃዝ በ1985 ከነበረው በእጥፍ አድጓል” ብሏል።
በጃፓን ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በዚህች አገር ገበሬዎች “ለኅብረተሰቡ የሚያስፈልገውን በቂ ቀለብ ለማምረት በኬሚካል ማዳበሪያዎችና ፀረ ተባዮች ከመተማመን ሌላ ምርጫ የላቸውም” ይላሉ የአንድ አትራፊ ያልሆነ የእርሻ ደኅንነት ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዩታካ ኡኔ። በዚህ ምክንያት የከርሰ ምድሩ ውኃ ተበክሏል። ይህ ደግሞ አሳሂ ሺምቡን የተሰኘው የቶኪዮ ጋዜጣ እንደገለጸው “በመላው ጃፓን ዋነኛ ችግር ሆኗል።”
በሜክሲኮ 35 በመቶ የሚሆኑ በሽታዎች “በከባቢ መበከል ምክንያት የሚደርሱ ናቸው” በማለት ሪፎርማ
ጋዜጣ ዘግቧል። ከዚህም በላይ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ የተደረገ ጥናት “ከ4 ነዋሪዎች አንዱ የፍሳሽ ማስወገጃ እንደሌለው፣ ከ8 ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች ውኃ የሚቀዱት ከጉድጓድ፣ ከወንዝ፣ ከሐይቅ ወይም ከምንጭ እንደሆነና ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡት ደግሞ ውኃ የሚያገኙት በቦቴ ተጭኖ እየመጣላቸው እንደሆነ አረጋግጧል።” በሜክሲኮ ከሚያጋጥሙት የተቅማጥ በሽታዎች 90 በመቶ የሚሆኑት በተበከለ ውኃ ምክንያት የሚመጡ መሆናቸው አያስደንቅም።የብራዚሉ ቬጃ መጽሔት ደግሞ “ከሪዮ የባሕር ዳርቻዎች የሚገኘው የሚሞቅ ፀሐይ፣ ነጭ አሸዋና ሰማያዊ ባሕር ብቻ አይደለም” ይላል። የባሕር ዳርቻዎቹ “በዓይነ ምድር አማካኝነት የሚመጡ ባክቴሪያዎችና የዘይት ፍሳሾች መጠራቀሚያም ሆነዋል” ሲል ዘግቧል። ይህ የሆነው ከብራዚል ፍሳሽ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ምንም ሳይጣራ በቀጥታ ወደ ወንዞች፣ ሐይቆችና ውቅያኖሶች እንዲገባ ስለሚደረግ ነው። በዚህ ምክንያት የንጹሕ ውኃ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በብራዚል በስፋት አንደኛ በሆነችው በሳኦ ፓውሎ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ወንዞች በጣም በመበከላቸው ምክንያት ባሁኑ ጊዜ የመጠጥ ውኃ የሚመጣው 100 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ አካባቢ ነው።
በሌላው የዓለም ክፍል በአውስትራሊያ ደግሞ የውኃ እጥረት እየተፈጠረ የሚገኘው በጨዋማነት መስፋፋት ምክንያት ነው። ለበርካታ ዓመታት ባለ መሬቶች መሬታቸውን መንጥረው እህል እንዲዘሩ ሲበረታቱ ቆይተዋል። የከርሰ ምድሩን ውኃ የሚመጡ ዛፎችና ቁጥቋጦዎች በመመናመናቸው ሳቢያ የውኃው ከፍታ ጨምሯል። በዚህም ምክንያት በበርካታ ቶን የሚመዘን ጨው ወደ ላይ መጥቷል። የአውስትራሊያ ኮመንዌልዝ የሳይንስና የኢንዱስትሪ ምርምር ድርጅት “ባሁኑ ጊዜ 2.5 ሚሊዮን ሄክታር የሚያክል መሬት በጨው ክምችት የተነሳ ተጎድቷል” ይላል። “ከዚህ መሬት አብዛኛው ክፍል በከፍተኛ አምራችነቱ የሚታወቅ ለም የእርሻ መሬት ነው።”
አንዳንዶች እንደሚያምኑት የአውስትራሊያ አስተዳዳሪዎች ከሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ይልቅ የሚያገኙትን ትርፍ ባያስቀድሙ ኖሮ ይህ ችግር አይከሰትም ነበር። በፔርዝ፣ አውስትራሊያ የኤዲት ካዋን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሂውጎ ቤከል “ከ1917 ጀምሮ ስንዴ አብቃይ የሆነው የአውስትራሊያ መሬት ጨዋማ የመሆን አደጋ እንደተጋረጠበት በየወቅቱ ለተነሱት መንግሥታት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል” ይላሉ። በማከልም እንዲህ ብለዋል:- “ደኖችን መመንጠር የወንዞች ጨዋማነት እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ የሚያስከትለው ውጤት ከ1920ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ለሕዝብ ሲገለጥ የቆየ ሲሆን የከርሰ ምድር ውኃ ከፍ እንዲል የሚያደርግ መሆኑ ደግሞ ከ1930ዎቹ ዓመታት ወዲህ በእርሻ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል። በ1950
የአውስትራሊያ ኮመንዌልዝ የሳይንስና የኢንዱስትሪ ምርምር ድርጅት ለአውስትራሊያ መንግሥት ሰፊ ጥናት የተደረገበት ሪፖርት አቅርቦ ነበር። . . . መንግሥታቱ ግን የሳይንቲስቶቹን ሐሳብ በማጣጣል ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለውት ቆይተዋል።”የሰው ልጅ ሕልውና አደጋ ተጋርጦበታል
አብዛኞቹ የሰው ልጅ ድርጊቶች በቅን ልቦና የተደረጉ መሆናቸው አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የምናደርጋቸው ነገሮች በከባቢያችን ላይ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያስከትሉ አስቀድሞ ለማወቅ የሚያስችል እውቀት አይኖረንም። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ተፈጽሟል። የደቡብ አውስትራሊያ ቤተ መዘክር ዳይሬክተር የሆኑት ቲም ፍላነሪ “በዚህች አገር የሕያዋን ፍጥረታትን ሚዛን እጅግ በማናጋታችን መተዳደሪያችን በሆነው መሬት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰናል። በዚህም ምክንያት የገዛ ራሳችንን ሕልውና አደጋ ላይ ጥለናል” ብለዋል።
ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? የሰው ልጅ ከከባቢው ጋር ተስማምቶ የሚኖርበትን ዘዴ የሚማርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እውን ፕላኔቷ ምድራችን ከጥፋት ትድናለች?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ለምሳሌ በ1999 ኪሣራው 20 በመቶ ደርሶ እንደነበረ ተገምቷል። ይህ ማለት የሰው ልጆች በዚያ የ12 ወር ጊዜ ውስጥ የፈጁትን የተፈጥሮ ሀብት ለመተካት ከ14 ወር በላይ ጊዜ አስፈልጓል ማለት ነው።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እያንዳንዷ ጠብታ ትልቅ ዋጋ አላት
የሚከተሉትን ቀላል እርምጃዎች በመውሰድ ብዙ ሊትር ውኃ መቆጠብ ይቻላል።
● የሚያንጠባጥብ ቧንቧ ካለ ጠግን።
● ሻወር ስትወስድ ረጅም ሰዓት ውኃ አታፍስስ።
● ጢምህን ስትላጭ ወይም ጥርስህን ስትቦርሽ ውኃው ያለማቋረጥ እንዲፈስ ከማድረግ ይልቅ እየዘጋህ ተጠቀም።
● የገላ ማድረቂያ ፎጣዎችን ቶሎ ቶሎ ከማጠብ ይልቅ ቢያንስ ሁለት ሦስቴ ተጠቀምባቸው።
● ለጥቂት ልብሶች ብለህ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖችን ከማስነሳት ይልቅ በርከት ያሉ ልብሶች እስኪጠራቀሙ ጠብቅ። (ዕቃ ማጠቢያ ማሽኖችንም በተመለከተ እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ።)
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የቆጠበ ተጠቀመ
● ምንም እንኳ አውስትራሊያ ከዓለም ደረቁ አህጉር ቢሆንም 90 በመቶ የሚሆነው የአህጉሩ የመስኖ ውኃ “ሰብሎችን እንዲያጠጣ የሚደረገው በቦይ አማካኝነት ወደ ማሳው እንዲፈስ አሊያም ለተወሰነ ጊዜ ማሳው ላይ እንዲተኛ በማድረግ” መሆኑን ዘ ካንቤራ ታይምስ ዘግቧል። ይህ “ፈርዖኖች ፒራሚዶችን በገነቡበት ዘመን ይጠቀሙበት የነበረ ዘዴ ነው።”
● በዓለም ዙሪያ እያንዳንዱ ሰው (ለግብርናና ለኢንዱስትሪ የሚውለውን ጨምሮ) በዓመት የሚጠቀመው የውኃ መጠን በአማካይ 550,000 ሊትር ነው። በሰሜን አሜሪካ የሚኖር አንድ ሰው ግን በዓመት የሚጠቀመው 1,600,000 ሊትር ገደማ ነው። በቀድሞዋ የሩሲያ ሪፑብሊክ የሚኖር ሰው የውኃ ፍጆታ ደግሞ ከዚህ በእጅጉ የሚበልጥ ሲሆን በዓመት በአማካይ ከ5.3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነው።
● አፍሪካ ጂኦግራፊክ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው እያንዳንዱ ደቡብ አፍሪካዊ ለዓመት የሚበቃውን ሰብል ለማምረት 4.0 ሄክታር መሬት የሚያስፈልግ ሲሆን አገሪቱ ለእያንዳንዱ ሰው ልታቀርብ የምትችለው የእርሻ መሬት ግን 2.4 ሄክታር ብቻ ነው።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተራቆተው የሳሄል ምድር ገጽታ በቡርኪና ፋሶ። ይህ አካባቢ ከ15 ዓመት በፊት ጥቅጥቅ ያለ ደን ነበር
[ምንጭ]
© Jeremy Hartley/Panos Pictures
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለእርሻ ሲባል ጫካን መመንጠርና ማቃጠል የካሜሩንን ዝናባማ ደኖች በማውደም ላይ ነው
[ምንጭ]
© Fred Hoogervorst/Panos Pictures
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዩናይትድ ስቴትስ የመኪናዎች ጭስ እያስከተለ ያለው ብክለት አሁንም አሳሳቢ ነው
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በብራዚል ከ1995 እስከ 2000 በየዓመቱ 20,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ደን ወድሟል
[ምንጭ]
© Ricardo Funari/SocialPhotos.com
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች የቀን ገቢያቸው ከሦስት ዶላር አይበልጥም
[ምንጭ]
© Giacomo Pirozzi/Panos Pictures
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ የሕንድ መንደር የሚኖሩ ሰዎች የመጠጥ ውኃ የሚቀዱበት ጉድጓድ በአካባቢው ያሉ ዓሣ አርቢዎች ከውቅያኖስ በሚያመጡት ጨዋማ ውኃ ተበክሎባቸዋል
[ምንጭ]
© Caroline Penn/Panos Pictures