ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ቴክኖሎጂ ሰዎችን እያራራቀ ነው
የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት “በርካታ ብሪታንያውያን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥገኝነታቸው እየጨመረ በመሄዱ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር እያስፈራቸው መጥቷል” ሲል ዘግቧል። ብሪቲሽ ጋዝ የተባለው ድርጅት በ1,000 ሰዎች ላይ ባደረገው ጥናት አንድ ሰው “ጊዜ እንዲቆጥብ ያስችሉታል ተብለው የታሰቡ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም” በአማካይ በቀን አራት ሰዓት ያህል እንደሚያሳልፍ አረጋግጧል። በሪፖርቱ መሠረት “በአማካይ አንድ ብሪታንያዊ በቀን 88 ደቂቃ በመደበኛ ስልክ በማውራት፣ 62 ደቂቃ በተንቀሳቃሽ ስልክ በማውራት፣ 53 ደቂቃ ኢ-ሜይል በመላክና 22 ደቂቃ የጽሑፍ መልእክት በሞባይል ስልክ በማስተላለፍ ያጠፋል።” በዚህ ምክንያት ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመነጋገር ችሎታ እየተዳከመ መሆኑን ጥናቱ ደምድሟል። ጥናቱ ከተደረገባቸው ሰዎች ብዙዎቹ የጽሑፍ መልእክት ለመጠቀም የሚመርጡት “በሰላምታና ጤንነት በመጠያየቅ የሚባክነውን ጊዜ ለማዳን ወይም እስከናካቴው ላለመነጋገር ስለሚፈልጉ” እንደሆነ አምነዋል።
ለከፍተኛ ኪሣራ የሚዳርግ ልማድ
የፊንላንድ የሥራ ላይ ጤንነት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ካሪ ሬዩላ ማጨስ ኪሣራ የሚያስከትለው በአጫሾቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በአሠሪዎችና አጫሽ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል። ሠራተኞች ሥራቸውን አቋርጠው በማጨስ የሚያሳልፉት ጊዜ በራሱ “በብሔራዊ ኢኮኖሚው ላይ በየዓመቱ የ21 ሚሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚያስከትል” የፊንላንድ ብሮድካስቲንግ ኩባንያ ድረ ገጽ ዘግቧል። “በቀን አንድ ፓኮ ሲጋራ የሚያጨሱ ሠራተኞች በዓመት ውስጥ 17 ቀን ከሥራ እንደሚቀሩ” ተገምቷል። የሕመም ፈቃድ ደግሞ ተጨማሪ ኪሣራ ያደርሳል። ሬዩላ አክለው እንዳመለከቱት “የሚያጨሱ ሠራተኞች ለአደጋ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነም ጥናቶች ያሳያሉ።” በተጨማሪም በሪፖርቱ መሠረት “በጭሱ ምክንያት ብዙ አየር ማናፈስ አስፈላጊ ስለሚሆን” ማጨስ በኤሌክትሪክ ፍጆታና በጽዳት ምክንያት ብዙ ኪሣራ እንዲደርስ ምክንያት ይሆናል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ “እስከ 250 የሚደርሱ አጫሽ ያልሆኑ ፊንላንዳውያን በየዓመቱ በመሥሪያ ቤታቸው ወይም በትርፍ ጊዜያቸው ሌሎች ላጨሱት የሲጋራ ጭስ በመጋለጣቸው ሳቢያ በበሽታ ተይዘው ይሞታሉ።”
የአደንዛዥ ዕፆች እንደልብ መገኘት
በፖላንድ ለደስታ ተብለው የሚወሰዱ ዕፆች ማግኘት ቢራ ከማግኘት እንደሚቀል ቭፕሮስት የተባለው መጽሔት ገልጿል። “በየዳንስ ቤቱ፣ በክበቦች፣ በመጠጥ ቤቶችና በሆስቴሎች እንዲሁም በኮሌጆች፣ በሁለተኛ ደረጃና በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማግኘት ይቻላል።” ከዚህም በላይ በትላልቅ ከተሞች “ስልክ ደውሎ ዕፅ ማዘዝ የሚቻል ከመሆኑም ሌላ ለገዢው በፍጥነት እንደሚደርስ” ጋዜጣው ገልጿል። ቭፕሮስት እንደሚለው ርካሽና እንደልብ የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ “ሰው ሠራሽ ዕፆች ጉዳት አያስከትሉም ተብሎ የሚታሰብ” መሆኑ ከፖላንዳውያን ወጣቶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት “ቢያንስ አንድ ጊዜ” አደንዛዥ ዕፆችን እንዲሞክሩ ምክንያት ሆኗል። የወጣቶች ተሐድሶ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ካታርዢና ፑቫስካ-ፖፒየላርሽ እንዳሉት ከእነዚህ ዕፆች መካከል አንዱን ለረዥም ጊዜ በመውሰድ ምክንያት “ራሳቸውን የገደሉ፣ ልብ ድካም የያዛቸው፣ የአእምሮ ሕመምተኛ የሆኑና ሰውነታቸው የቀጨጨ አሉ።”
የጦርነት ክፍለ ዘመን
ቦነስ አይረስ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ “በዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ምክንያት 20ኛው መቶ ዘመን በታሪክ ዘመናት በሙሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የደም መፋሰስ ክፍለ ዘመን ሆኗል” ሲል ዘግቧል። ዘር ማጥፋት አንድን ብሔር፣ ዘር፣ የፖለቲካ ቡድን ወይም ጎሣ በተቀናጀና በተጠና ዘዴ ማጥፋት የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። በ20ኛው መቶ ዘመን ከ41 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች እንደተገደሉ ይገመታል። በ1994 በአብዛኛው “በጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በተነሳሱ ሲቪሎች” 800,000 ሰዎች የተገደሉበት የሩዋንዳ ጭፍጨፋ ለዚህ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው። በ100 ቀናት ውስጥ በአማካይ 8,000 ሰዎች በየቀኑ ይገደሉ እንደነበረ ምሑራን ይናገራሉ። ይህ አኃዝ “በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች ተመሳሳይ በሆነ የጊዜ ርዝማኔ ውስጥ በጋዝ አፍነው ይገድሏቸው ከነበሩት ሰዎች በአምስት እጥፍ ይበልጣል” ሲል ሄራልድ አመልክቷል።
የኢንተርኔት የምልክት ቋንቋ
መስማት የተሳናቸው ሰዎች ለበርካታ ዓመታት ከወዳጆቻቸው ጋር ሐሳብ ለመለዋወጥ ሲጠቀሙ የኖሩት በቴሌታይፕራይተር ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢ-ሜይል መጠቀም ጀምረዋል። የኢንተርኔት ኮምፒውተር ካሜራዎች በተስፋፉበት ባሁኑ ዘመን መስማት የተሳናቸው ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት በምልክት ቋንቋ መነጋገር ችለዋል። ይሁን እንጂ “የእነዚህ ካሜራዎች እይታ ጠባብ በመሆኑ በስልክ ስናወራ የፊትና የቅንድብ እንቅስቃሴዎችን ማየት እንደማይቻል ሁሉ ሰዎች በእነዚህ ካሜራዎች አማካኝነት በምልክት ቋንቋ በሚነጋገሩበት ጊዜም በግልጽ የማይታዩ አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ” ሲል የካናዳው ናሽናል ፖስት ገልጿል። የኢንተርኔት ግንኙነት አዝጋሚ መሆኑና ሌሎች ቴክኒካዊ ችግሮች በኢንተርኔት ካሜራዎች አማካኝነት በምልክት ቋንቋ መነጋገርን አስቸጋሪ አድርገውታል። ታዲያ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እነዚህን እንቅፋቶች የሚወጡት እንዴት ነው? የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎች እንቅስቃሴያቸውን ዝግ በማድረግና በመደጋገም እንዲሁም “እንቅስቃሴያቸውንና ቁመናቸውን ለካሜራ እይታ የተመቸ እንዲሆን በማድረግ
ነው” ሲል ፖስት ገልጿል። በተጨማሪም ምልክት አድራጊዎች እጆቻቸውን ወደ ካሜራው በማስጠጋት ይበልጥ ጉልህ ሆኖ እንዲታይ በማድረግ ለሚናገሩት ነገር ክብደት መስጠት እንደሚችሉም ተገንዝበዋል።ሕይወት ያላቸው የቆሻሻ መጣያዎች
ጥራጊ ቆሻሻ በባሕር እንስሳት ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት የተደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት በሰሜን ባሕር በምትገኘው ፉልማር የተባለች የውቅያኖስ ወፍ ሆድ ውስጥ 30 የፕላስቲክ ቅንጣቶች መገኘታቸውን አሳይቷል። ይህ “በ1980ዎቹ ዓመታት በፉልማሮች ሆድ ውስጥ ከተገኘው በእጥፍ ይበልጣል” ሲል የለንደኑ ዘ ጋርድያን ጋዜጣ ዘግቧል። በፉልማሮች ላይ ጥናት የተደረገው እነዚህ ወፎች “ያገኙትን ሁሉ ስለሚበሉና የዋጡትን መልሰው የማያመነዥኩ በመሆናቸው ነው።” በሞቱ ፉልማሮች ሆድ ውስጥ ከተገኙት የፕላስቲክ ውጤቶች መካከል አሻንጉሊቶች፣ የጥገና መሣሪያዎች፣ ገመዶች፣ የፕላስቲክ ስኒዎች፣ የፍራሽ ስፖንጆች፣ ኮዳዎችና የሲጋራ መለኮሻዎች ይገኛሉ። የስኮትላንድ የምድር ወዳጆች ማኅበር የምርምር ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ዳን ባርሎ “ከዚህ ጥናት በስኮትላንድ የባሕር ጠረፎች የሚገኙ የባሕር እንስሳት ሕይወት ያላቸው የቆሻሻ መጣያዎች እየሆኑ መሄዳቸውን አውቀናል” ብለዋል። “300 ከሚያክሉት የባሕር አእዋፍ ዝርያዎች መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት ሳያውቁት ፕላስቲክ በልተው” እንደተገኙ ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።
አዞዎች የሚያድኑት እንዴት ነው?
በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ለዶክትሬት ዲግሪ የምታጠና አንዲት ተማሪ ሊቃውንቱን ግራ ሲያጋባ የቆየ አንድ ግኝት ላይ ደርሳለች። አዞዎቹ በውኃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ፍጥረታትን እንቅስቃሴ ማወቅ የሚያስችሏቸው በአፍንጫቸው ላይ የሚገኙ የውኃ ግፊት መቆጣጠሪያ ሕዋሳት እንዳሏቸው ደርሳበታለች። በአዞዎችና ከአዞ ጋር የቅርብ ዝምድና ባላቸው ተሳቢ እንስሳት መንጋጋ ዙሪያ የመርፌ ቀዳዳ የሚያህሉ ጥቃቅን እባጮች አሉ። እነዚህ እባጮች አዞዎች በዙሪያቸው ባለው ውኃ የሚደረጉ መጠነኛ ንቅናቄዎችን ማወቅ የሚችሉባቸው መሣሪያዎች እንደሆኑ ባዮሎጂስቷ ዳፍኒ ሶርስ ደርሳበታለች። “አዞዎች የሚያድኑት በማታ ሲሆን ታዳኞቹ እንስሳት ውኃውን እስኪያንቀሳቅሱ ጸጥ ብለው ይጠብቃሉ። ሶርስ “መንጋጋቸውን በአየርና በውኃው ገጽ መካከል አድርገው ያደፍጣሉ። በሚርባቸው ጊዜ የላይኛውን የውኃ ክፍል የሚያንቀሳቅሰውን ማንኛውንም ነገር በፍጥነት ለመያዝ ይነሳሉ” በማለት ታስረዳለች። ግፊት ተቆጣጣሪዎቹ እባጮች አንዲት ጠብታ ውኃ የምትፈጥረውን እንቅስቃሴ ሳይቀር የማወቅ ችሎታ አላቸው።
የላቲን ቅዳሴ ማንሰራራት
በጀርመን “በላቲን ቋንቋ የሚካሄዱ የአብያተ ክርስቲያናት ስብከቶች ተወዳጅነታቸው እየጨመረ መጥቷል” ሲል ፎከስ የተባለው ዜና መጽሔት ዘግቧል። “እንደ ፍራንክፈርት፣ ዱሰልዶርፍና ሚውንስተር ባሉት ከተሞች የሚኖሩ [ቀሳውስት] የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢሄድም በላቲን በሚካሄዱ ቅዳሴዎች ላይ ግን ብዙ ሰዎች እንደሚገኙ” መናገራቸውን መጽሔቱ አመልክቷል። የላቲን ቅዳሴዎች ተወዳጅነት እየጨመረ በመሄዱ በሙኒክ የሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን በላቲን የሚቀርቡ ቅዳሴዎችን በወር ሁለት ጊዜ መሆናቸው ቀርቶ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ በበዓል ቀናት በሙሉ በላቲን እንዲካሄድ አድርጓል።