በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውጥረትን መቋቋም ትችላለህ!

ውጥረትን መቋቋም ትችላለህ!

ውጥረትን መቋቋም ትችላለህ!

“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሥራን፣ የቤተሰብ ኑሮንና ሌሎች ግዴታዎችን በሚዛናዊነት ማከናወን ከባድ እየሆነ መጥቷል” በማለት የቤተሰብን ሕይወት በተመለከተ በቅርቡ የታተመ አንድ መጽሐፍ ዘግቧል። አዎን፣ የምንኖረው ውጥረት በሞላበት ዓለም ውስጥ ነው። ይህ ክስተት ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያስደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” እንደሚመጣ አስቀድሞ ተንብዮአል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

የሦስት ልጆች አባት የሆነው ኼሱስ “ውጥረት የተለመደ ክስተት ነው። ስለዚህ እንዴት ልትቆጣጠሩት እንደምትችሉ ማወቅ ይገባችኋል” ብሏል። እርግጥ ነው፣ ውጥረትን መቆጣጠር የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። የሆነ ሆኖ በዚህ ረገድ እርዳታ የሚያደርጉልህ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችና የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አሉ።

ከሥራ ጋር የተያያዙ ውጥረቶችን መቋቋም

በሥራ ቦታህ የሚያጋጥሙህ አንዳንድ ሁኔታዎች ውጥረት አስከትለውብሃል? ጉዳዩን በውስጥህ አምቀህ መያዝህ የባሰ ጭንቀት ውስጥ ሊከትህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 15:22 ላይ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል” ይላል።

በሥራ ቦታ ስለሚከሰት ውጥረት ጥናት የሚያካሂዱ ሰዎች “ከአሠሪህ ጋር ተነጋገር፤ ምክንያቱም ችግር መኖሩን እስካላወቀ ድረስ ምንም ማድረግ አይችልም” የሚል ምክር ይሰጣሉ። እንዲህ ሲባል ግን ሐሳብህን በቁጣ መግለጽና መከራከር አለብህ ማለት አይደለም። መክብብ 10:4 “ትዕግሥት ታላቁን ጥፋት ጸጥ ያደርጋል” ይላል። ከአሠሪህ ጋር ሥርዓት ባለው መንገድ ተወያይ እንጂ ክርክር አትግጠመው። የሥራ ውጥረት መቀነሱ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያስችል አሠሪህን ማሳመን ትችል ይሆናል።

ከሥራ ባልደረቦች ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የመሳሰሉ በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ ሌሎች ችግሮችንም በዚህ መንገድ መፍታት ይቻላል። አስፈላጊ ከሆነ በጽሑፎች ላይ ምርምር በማድረግ እንዲህ ያሉ ችግሮችን በጥሩ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችሉ መንገዶችን ማግኘት ትችል ይሆናል። ይህን በተመለከተ በንቁ! መጽሔት ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዙ በርካታ ርዕሶች ወጥተዋል። * ሁኔታው የሚስተካከል ዓይነት ካልመሰለህ ሥራ ስለ መቀየር ማሰቡ የተሻለ ይሆናል።

የገንዘብ ችግር የሚፈጥረውን ውጥረት መቀነስ

ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ችግር የሚፈጥረውን ጫና እንድትቋቋም የሚረዳ ምክር ይዟል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:25) ይህ እንዴት ይቻላል? ይሖዋ አምላክ መሠረታዊ ፍላጎትህን እንደሚያሟላልህ በመተማመን ነው። (ማቴዎስ 6:33) አምላክ የገባው ቃል ትርጉም የሌለው ተራ ቃል አይደለም። ይህ ቃል በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ትልቅ የመጽናኛ ምንጭ ሆኗቸዋል።

እርግጥ ነው፣ በገንዘብ አጠቃቀምህ በኩል ‘ጥበበኛ’ መሆን ያስፈልግሃል። (ምሳሌ 2:7 የ1980 ትርጉም፤ መክብብ 7:12) መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) ባሉን ጥቂት ነገሮች መርካትን መማር አስተዋይነት ከመሆኑም በላይ ጠቃሚ ነው። በደረሰበት አደጋ ምክንያት በተሽከርካሪ ወንበር ለመንቀሳቀስ የተገደደውን ሌአንድሮን እስቲ በድጋሚ እናንሳ። እርሱና ባለቤቱ ገንዘባቸውን በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን እርምጃ ወሰዱ። ሌአንድሮ እንዲህ ይላል:- “ቆጣቢዎች ለመሆን እየሞከርን ነው። ለምሳሌ ያህል ለኤሌክትሪክ የምናወጣውን ወጪ ለመቀነስ ስንል የማንጠቀምበትን መብራት እናጠፋለን። እንዲሁም ነዳጅ ለመቆጠብ ስንል የምንሄድባቸውን ቦታዎች አስቀድመን እናቅድና አንዴ ወጥተን ሁሉንም ጉዳዮቻችንን ፈጽመን እንመለሳለን።”

ወላጆች ልጆቻቸው ትክክለኛ አመለካከት እንዲይዙ መርዳት ይችላሉ። የሌአንድሮ ልጅ ካርመን እንዲህ ብላለች:- “ድንገት ተነስቼ አንድ ነገር የመግዛት ልማድ ነበረኝ፤ ሆኖም ወላጆቼ የግድ አስፈላጊ የሆነውንና አስፈላጊ ያልሆነውን ነገር እንዳስተውል ረድተውኛል። መጀመሪያ ላይ አመለካከቴን ለማስተካከል ከብዶኝ ነበር። በኋላ ግን በምፈልጋቸውና በእርግጥ በሚያስፈልጉኝ ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት ማወቅ እንደምችል ተማርኩ።”

የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ውጥረትን ያስታግሳል

ቤት ከውጥረት እረፍት የሚገኝበት ቦታ ሊሆን ይገባዋል፤ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ውጥረት ከሚፈጠርባቸው ዋና ዋና ቦታዎች መካከል አንዱ ቤት ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሰርቫይቫል ስትራቴጂስ ፎር ካፕልስ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ “መጠነኛ ውጥረት ያለባቸው . . . ወይም በጥላቻ ዓይን የሚተያዩ የትዳር ጓደኛሞች በመካከላቸው በተደጋጋሚ ለሚነሳው ብጥብጥ ዋነኛው መንስኤ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ” ይላል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትዳር ጓደኛሞች የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል፤ በተጨማሪም ‘በወቅቱ የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው’ በማለት ይናገራል። (መክብብ 3:1, 7፤ ምሳሌ 15:23) ይህን ማወቃችሁ የትዳር ጓደኛችሁ በደከመው ወይም ውጥረት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ሊያስቆጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ከማንሳት እንድትቆጠቡ ሊረዳችሁ ይችላል። እንዲህ ያለውን ጉዳይ የትዳር ጓደኛችሁ ለማዳመጥ ዝግጁ የሆነ የሚመስልበትን ትክክለኛ ጊዜ ጠብቃችሁ ማንሳቱ የተሻለ አይሆንም?

በሥራ ቦታችሁ ላይ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟችሁ ከነበረ ረጋ ማለት ወይም አንዳንድ ነገሮችን በትዕግሥት ማሳለፍ ሊከብዳችሁ እንደሚችል እሙን ነው። ይሁን እንጂ ንዴታችንን ለመወጣት ስንል በትዳር ጓደኛችን ላይ የምንጮህ ከሆነ ምን ሊከሰት ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ቃል . . . ቊጣን ይጭራል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 15:1) በአንጻሩ ግን “ደስ የሚያሰኝ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው።” (ምሳሌ 16:24) ባለ ትዳሮች ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ ‘ከመራርነት፣ ከቊጣና ከንዴት፣ ከጭቅጭቅና ከስድብ’ ለመራቅ ከልባቸው ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። (ኤፌሶን 4:31) ይሁን እንጂ ከሚገኘው ጥቅም አንጻር ጥረቱ አያስቆጭም። ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርጉ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው ሊበረታቱና ሊደጋገፉ ይችላሉ። ምሳሌ 13:10 “ጥበብ . . . ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ትገኛለች” ይላል። *

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ በኩል ያለባቸው ችግር

በተለይ የጊዜ እጥረት ያለባቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ትልቅ ፈተና ይሆንባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ‘በቤታቸው ሲቀመጡ፣ በመንገድ ሲሄዱና’ በሌሎች ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ሁሉ ከልጆቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ ያበረታታል። (ዘዳግም 6:6-8) ሌአንድሮ “ለመነጋገር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለግ ይገባናል፤ ከወንዱ ልጄ ጋር በመኪና አብረን ስንሄድ ጊዜውን እርሱን ለማነጋገር እጠቀምበታለሁ” ብሏል።

አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ እንደሚከብዳቸው የተረጋገጠ ነው። የሦስት ልጆች እናት የሆነችው አሌኻንድራ “እንዴት ማዳመጥ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ባለማድረጌ እናደድና የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር” በማለት ሐቁን ተናግራለች። ወላጆች በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ‘ለመስማት ፈጣን’ በመሆን ጥረታችሁን ጀምሩ። (ያዕቆብ 1:19) ዶክተር ቤቲ የንግስ “በትኩረት ማዳመጥ ውጥረትን ለመቀነስ የሚረዳ በጣም ጥሩ መንገድ ነው” ብለዋል። በትኩረት የማዳመጡን ጉዳይ ልታስቡበት ይገባል። ልጃችሁ ሲያወራችሁ ዓይን ዓይኑን እዩ። የልጆቻችሁን ችግር አቅልላችሁ አትመልከቱ። ልጆቻችሁ ስሜታቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው። አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች አንሱላቸው። ፍቅራችሁንና ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርጉ ያላችሁን እምነት በግልጽ ከመናገር ወደኋላ አትበሉ። (2 ተሰሎንቄ 3:4) ከልጆቻችሁ ጋር አብራችሁ ጸልዩ።

አዘውትሮ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ትግል ይጠይቃል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጉ በቤተሰባችሁ ውስጥ ያለውን ውጥረት ለመቀነስ ሊረዳችሁ ይችላል። የሐሳብ ግንኙነት ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ ውጥረት ይኑርባቸው አይኑርባቸው እንድታውቁ ያስችላችኋል። የልጆቻችሁን ስሜትና ሁኔታ ከተረዳችሁ ደግሞ ይበልጥ ጥሩ መመሪያ ልትሰጧቸው ትችላላችሁ። ለውጥረት የዳረጓቸውን ነገሮች አውጥተው እንዲናገሩ ማበረታቻ የተሰጣቸው ወጣቶች፣ የሚሰማቸውን ውጥረት ለማስታገሥ የተሳሳተ እርምጃ የመውሰድ አጋጣሚያቸው የጠበበ ነው።

ትብብርየቤት ውስጥ ሥራዎችን በሚገባ ለማከናወን የሚያስችል ቁልፍ

ባልም ሚስትም ተቀጥረው የሚሠሩ ከሆነ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የመሥራቱ ጉዳይ ሌላ ውጥረት የሚፈጥር ችግር ሊሆንባቸው ይችላል። ሰብዓዊ ሥራ ያላቸው አንዳንድ እናቶች በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸውን የተለመዱ ተግባሮች ቀለል በማድረግ ችግሩን ለመቋቋም ችለዋል። ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ምግብ ማዘጋጀት የሚከብድና አላስፈላጊ እንደሆነ ይወስኑ ይሆናል። ኢየሱስ ምግብ ለማዘጋጀት ትደክም የነበረችውን ሴት “የሚያስፈልገው . . . አንድ ነገር ብቻ ነው” እንዳላት አስታውስ። (ሉቃስ 10:42) ስለዚህ ሥራዎቻችሁን ቀላል አድርጉ። ዘ ሲንግል ፓረንት ፋሚሊ የተባለ መጽሐፍ “ሥጋና አትክልቶችን አንድ ላይ በማብሰል እንዲሁም በአንድ ድስት ብቻ ሊሠሩ የሚችሉ ሌሎች ምግቦችን በማዘጋጀት የምታጥቧቸውን እቃዎች መጠን መቀነስ ትችላላችሁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። አዎን፤ የዕለት ተዕለት የቤት ውስጥ እንቅስቃሴዎችን ቀላል በማድረግ ውጥረትን መቀነስ ትችላላችሁ።

እንዲህም ሆኖ መሠራት የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች ይኖሩ ይሆናል። ሰብዓዊ ሥራ ያላት አንዲት እናት እንዲህ በማለት እውነታውን ተናግራለች:- “ወጣት ሳለሁ ሁሉንም ነገር መሥራት እችል ነበር። አሁን ግን ዕድሜዬ በመግፋቱ እየከበደኝ መጥቷል። እስከ ዛሬ ያሳለፍኩት ሩጫ የበዛበት ሕይወት ከባድ ጉዳት አስከትሎብኛል። በመሆኑም ሁሉም የቤተሰቤ አባላት ትብብር ማሳየታቸው አሳቢነት ነው፤ እንዲህ ማድረጋቸው ከባድ ውጥረት እንዳይደርስብኝ ይረዳኛል።” አዎን፤ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በፈቃደኝነት ከተባበሩ የቤት ውስጥ ሥራዎች በማንም ላይ ከባድ ሸክም ሳይሆኑ ሊከናወኑ ይችላሉ። ለወላጆች የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ “ልጆችን የቤት ውስጥ ሥራዎች ማሠራት ልጆቹ . . . ማንኛውንም ነገር ለማከናወን የሚያስችል ብቃት እንዳላቸው እንዲሰማቸው ከሚያደርጉ ጥሩ ዘዴዎች መካከል አንዱ ነው። የዕለት ተዕለት የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን ጠቃሚ ልማዶችን ለማዳበርና ለሥራ ጥሩ አመለካከት ለመያዝ ያስችላል” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል። ከዚህም በላይ በጋራ ሆናችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወናችሁ ከልጆቻችሁ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ያስችላችኋል።

ጁልዬታ የተባለች ወጣት “እናቴ ሸክም የሆኑባትን አንዳንድ ሥራዎች ሳግዛት እረፍት እንደሚሰማት ማስተዋል ችያለሁ። ይህም ደስታ እንዳገኝና ኃላፊነት እንዲሰማኝ አድርጎኛል። እንዲሁም ቤቴን እንድወደው ረድቶኛል። የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት መማሬ ለወደፊቱ ጊዜ ጥሩ መሠረት ጥሎልኛል” ብላለች። ሜሪ ካርመን የተባለች ወጣትም “ከልጅነታችን ጀምሮ ወላጆቻችን እንዴት ራሳችንን መንከባከብ እንዳለብን አስተምረውናል። ይህ በጣም ጠቅሞናል” በማለት ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥታለች።

ውጥረትን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ መንገዶች

ውጥረት የዘመናችን አንዱ ገጽታ በመሆኑ ጨርሶ ማስወገድ አይቻልም። ይሁን እንጂ ውጥረትን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ ማወቅ ትችላለህ። (በገጽ 10 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ ማዋል ሊጠቅምህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ጉዳይ ከአቅምህ በላይ እንደሆነብህ ከተሰማህ ‘ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛ እንዳለ’ አስታውስ። (ምሳሌ 18:24) ከጎለመሰ ባልንጀራህ ወይም ከትዳር ጓደኛህ ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋገርበት። ሮናልድ ፒትሰር የተባሉት የማኅበራዊ ኑሮ ተመራማሪ “ስሜታችሁን አፍናችሁ አትያዙ። የሚሰማችሁን ስሜትና ጭንቀታችሁን፣ ችግራችሁን ለሚረዳና ለሚያስብላችሁ ረጋ ያለ አስተዋይ ሰው አካፍሉ” ብለዋል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ራስን ስለ መጥቀም’ ይናገራል። (ምሳሌ 11:17) አዎን፣ በግል የሚያስፈልጉህን ነገሮች ማሟላትህ ምንም ስህተት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:6) ጊዜ በመመደብ ለራስህ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ማድረግህ ውጥረትን ለመቀነስ ትልቅ እገዛ ያደርግልሃል፤ ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን በጠዋት ተነስተህ ሻይ ጠጣ፣ አንብብ፣ ጸልይ ወይም ደግሞ ጸጥታ በሰፈነበት ቦታ ሆነህ አሰላስል።

እንዲሁም ቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን መመገብም ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ለወላጆች የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ ጊዜና ጉልበትን በባንክ ከሚጠራቀም ገንዘብ ጋር በማነጻጸር የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- ‘ውድ ከሆነው ጊዜያችሁና ጉልበታችሁ ውስጥ ጥቂቱን ለራሳችሁ ብታውሉ በሌላ አስፈላጊ ወቅት ልትጠቀሙበት የምትችሉትን ኃይል እያጠራቀማችሁ ነው ለማለት ይቻላል። ኃይል ባወጣችሁ ቁጥር መልሳችሁ መተካት እንደሚኖርባችሁም አትዘንጉ፤ አለበለዚያ ኃይላችሁ ሊዳከም አልፎ ተርፎም ሊሟጠጥ ይችላል።’

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ውጥረትን ለመቋቋም የሚያስፈልጉትን እንደ “ገርነት፣” ትዕግሥትና ደግነት ያሉትን ባሕርያት እንዲያዳብር ይረዳዋል። (ገላትያ 5:22, 23፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:11) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ በሰው ልጆች ላይ ችግር የሚፈጥሩ ነገሮች በሙሉ እንደሚወገዱ የሚገልጽ ይበልጥ አስደሳች የሆነ ተስፋ ይዟል! (ራእይ 21:1-4) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ ማዳበር ተገቢ ነው። እንዲህ ያለውን ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል እርዳታ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ያለምንም ክፍያ በግልህ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

ይህ ሲባል ክርስቲያኖች ከውጥረት ነፃ የሆነ ሕይወት ይመራሉ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘ስለ ኑሮ በመጨነቅ ከመዛል’ መቆጠብ እንደሚቻል ተናግሯል። (ሉቃስ 21:34, 35) እንዲሁም ይሖዋን እንደ ወዳጅህ አድርገህ እያወቅከው ስትሄድ መጠጊያ ይሆንልሃል! (መዝሙር 62:8) ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ውጥረቶች መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 በግንቦት 2004 እትም ላይ የወጣውን “በሥራ ቦታ ጥቃት ቢደርስብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።

^ አን.15 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወጣት ሳለሁ ሁሉንም ነገር መሥራት እችል ነበር። አሁን ግን ዕድሜዬ በመግፋቱ እየከበደኝ መጥቷል። እስከ ዛሬ ያሳለፍኩት ሩጫ የበዛበት ሕይወት ከባድ ጉዳት አስከትሎብኛል”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ውጥረትን እንዴት መቀነስ ይቻላል?

በየዕለቱ በቂ እረፍት አድርግ

ተመጣጣኝ ምግብ ተመገብ። ከልክ በላይ አትብላ

ፈጠን ብሎ እንደ መራመድ ያሉ ጥሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን አዘውትረህ አድርግ

አንድ ያስጨነቀህ ነገር ካለ ጓደኛህን አማክረው

ከቤተሰብህ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ አሳልፍ

የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለሌሎች የቤተሰቡ አባላት አካፍል

ያሉብህን አካላዊና ስሜታዊ የአቅም ገደቦች እወቅ

ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ፤ ፍጽምና አትጠብቅ

የተደራጀህ ሁን፤ ሚዛናዊና ምክንያታዊ ፕሮግራም ይኑርህ

እንደ የዋህነትና ትዕግሥት ያሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አዳብር

ለራስህ የተወሰነ ጊዜ መድብ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአሠሪ ጋር አክብሮት በተሞላበት መንገድ ችግሮችን አንስቶ መወያየት በሥራ ቦታ የሚፈጠረውን ውጥረት ለመቀነስ እገዛ ያደርግ ይሆናል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ገንዘብ መቆጠብ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ከልጆቻቸው ጋር መወያየት ይችላሉ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣት ከሆንክ ውጥረት የፈጠረብህን ነገር አንስተህ ሊረዳህ ከሚችል ሰው ጋር ተወያይ

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁሉም የቤተሰብ አባላት የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ሊተጋገዙ ይችላሉ