በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውጥረት—መንስኤዎቹና የሚያስከትላቸው ችግሮች

ውጥረት—መንስኤዎቹና የሚያስከትላቸው ችግሮች

ውጥረት—መንስኤዎቹና የሚያስከትላቸው ችግሮች

ውጥረት ምንድን ነው? አንዲት ዶክተር እንደገለጹት ውጥረት “በማንኛውም አካላዊ፣ ኬሚካላዊ ወይም ስሜታዊ ሁኔታ ምክንያት በሰውነት ወይም በአእምሮ ላይ የሚፈጠር ጭንቀት” የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። እንዲህ ሲባል ውጥረት ሁሉ ጎጂ ነው ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ሜሊሰ ስቶይፕለር የተባሉ ዶክተር “ቀላል የሆነ ውጥረትና ጭንቀት አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አንድ ሥራ ስንፈጽም ቀለል ያለ የውጥረት ስሜት የሚሰማን ከሆነ በአብዛኛው ኃላፊነታችንን በሚገባ መወጣትና በሙሉ ኃይላችን መሥራት እንችላለን” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ታዲያ ውጥረት ጎጂ የሚሆነው መቼ ነው? ስቶይፕለር “ውጥረቱ ከመጠን ሲያልፍ ወይም ደግሞ ተገቢው እርምጃ ሳይወሰድ ሲቀር ጎጂ ጎኖቹ ብቅ ይላሉ” ብለዋል። እስቲ የተለመዱ የውጥረት መንስኤዎችን እንመልከት።

ሥራ የሚያስከትለው ውጥረት

ንጉሥ ሰሎሞን “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም” ብሏል። (መክብብ 2:24) ይሁን እንጂ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ቦታቸው ከውጥረት ጋር የሚፋለሙበት ስፍራ ሆኖባቸዋል።

ዩሮፒያን ኤጀንሲ ፎር ሴፍቲ ኤንድ ሄልዝ አት ወርክ የተባለው ድርጅት ባቀረበው ዘገባ ላይ ሰዎች የሥራ ቦታቸው ውጥረት እንዲፈጥርባቸው ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ጠቅሷል፤ እነዚህም:- በአስተዳደሩና በሠራተኞቹ መካከል በቂ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖሩ፣ አስተዳደሩ ሠራተኞቹን የሚመለከት ውሳኔ ሲያደርግ እነርሱን አለማማከሩ፣ በሥራ ባልደረቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት፣ የሥራው አስተማማኝ አለመሆን እና/ወይም በቂ ክፍያ አለማግኘት ናቸው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ በሥራ ቦታቸው ከሚያጋጥማቸው ውጥረት ጋር የሚታገሉ ሰዎች የቤተሰባቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚያሟሉበት አቅም ያጣሉ። ቤተሰባቸው ደግሞ ብዙ ነገር ይጠብቅባቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ለታመሙ ወይም በዕድሜ ለገፉ የቤተሰባቸው አባላት እንክብካቤ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። የገንዘብ ችግርም እንዲሁ በቤተሰብ ውስጥ ከባድ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሪታ፣ ባሏ ሌአንድሮ በመኪና አደጋ ምክንያት በተሽከርካሪ ወንበር ካልሆነ በስተቀር መንቀሳቀስ በተሳነው ጊዜ ከባድ የገንዘብ ችግር አጋጠማት። ሪታ “የገንዘብ ችግር ውጥረት ይፈጥራል። የቤቱን ወጪ በሙሉ ለመሸፈን የሚያስችል ገንዘብ ከሌላችሁ ደስታችሁን ታጣላችሁ” በማለት የተሰማትን ተናግራለች።

ነጠላ ወላጆች የሚያጋጥማቸው ውጥረት

ነጠላ ወላጆችም በተመሳሳይ የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለማሟላት በሚጣጣሩበት ጊዜ ከባድ ውጥረት ያጋጥማቸዋል። ቁርስ ለማዘጋጀት በጠዋት መነሳት፣ ልጆችን ማልበስና ትምህርት ቤት ማድረስ፣ ሥራ በሰዓቱ ለመገኘት መጣደፍና በሥራ ገበታ ላይ የሚጠበቀውን ያህል ለማከናወን መጣጣር በነጠላ ወላጆች ላይ የአካልና የስሜት መዛል ያስከትልባቸዋል። ነጠላ እናቶች ከሥራ ከወጡ በኋላ ደግሞ ሌላ የውጥረት ጊዜ ይጀምራል። ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ለማምጣት በሩጫ ይሄዳሉ፣ ከዚያ ደግሞ እራት ያዘጋጃሉ፣ ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችንም ያከናውናሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አራት ሴቶች ልጆች ያሏት ማሪያ የተባለች ነጠላ እናት ሁኔታዋን እሳት ከበዛበት በሚፈነዳ፣ በእንፋሎት ከሚያበስል ድስት (ፕሬዠር ኩከር) ጋር በማመሳሰል “አንዳንድ ጊዜ የሚሰማኝ ውጥረት በጣም ከመባባሱ የተነሳ ልፈነዳ የደረስኩ መስሎ ይሰማኛል” ብላለች።

ውጥረት ያለባቸው ልጆች

ሮነልድ ፒትሰር የተባሉ የማኅበራዊ ኑሮ ተመራማሪ “በርካታ ወጣቶች ከባድ ውጥረት ያጋጥማቸዋል” ብለዋል። ወጣቶች ጉርምስና የሚያስከትለውን አካላዊና ስሜታዊ ለውጥ መታገል ይገባቸዋል፤ እንዲሁም የትምህርት ቤት ውጥረት አለባቸው። ቻይልድስትረስ! የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ እንደገለጸው እያንዳንዱ የትምህርት ቀን “ውጥረት በሚፈጥሩ ችግሮችና ጭንቀቶች የተሞላ ነው፤ የቀለምና የስፖርት ትምህርቶች እንዲሁም ከእኩዮችና ከአስተማሪዎች ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የየራሳቸው ራስ ምታት አላቸው።”

በአንዳንድ ቦታዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈጸመው ወንጀል በወጣቶች ላይ ከባድ ስጋት ይፈጥርባቸዋል፤ የሽብርተኞች ጥቃትና ሌሎች አደጋዎች የሚፈጥሩባቸው ፍርሃት ደግሞ ከዚህ በእጅጉ የከፋ ነው። አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ልጃገረድ “ወላጆች፣ ያለንበት ዓለም አስጨናቂ እንደሆነ በየጊዜው ሲናገሩ ስንሰማ ፍርሃት ያድርብናል” በማለት ጽፋለች።

ወላጆች ለልጆቻቸው የብርታት ምንጭ ሊሆኗቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ፒትሰር እንዲህ ብለዋል:- “የሚያሳዝነው ብዙውን ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው የውስጣቸውን ስሜት ለመግለጽ ሲሞክሩ ችግራቸውን ያጣጥሉባቸዋል፣ አይቀበሏቸውም፣ ምክንያት ይደረድሩላቸዋል ወይም ደግሞ ችላ ይሏቸዋል።” አልፎ አልፎ ወላጆች የትዳር ጫና ስለሚኖርባቸው የልጆቻቸውን ፍላጎት ማሟላት ይከብዳቸዋል። በኋላ ላይ ወላጆቹ የተፋቱበት ቲቶ የተባለ ወጣት “የወላጆቼ ጥል ማብቂያ ያለው አይመስልም ነበር” ብሏል። ቻይልድስትረስ! የተባለው መጽሐፍ “የስሜት መቃወስ የሚያስከትለው ድብድብና ንትርክ ብቻ አይደለም። እንደ ማር በሚጣፍጡ ቃላት የሚሰነዘሩ የብስጭት መግለጫዎችም ልጆችን ያሸብራሉ” በማለት ይገልጻል።

ውጥረት የሚያስከትለው መዘዝ

ወጣትም ሆንክ በዕድሜ የገፋህ፣ ውጥረት ያስከተለብህ ሥራም ይሁን ትምህርት፣ ሥር የሰደደ ውጥረት በጤናህ ላይ ከባድ ችግር ሊያመጣብህ ይችላል። ስለ ሕክምና ጉዳዮች የሚጽፉ አንድ ሰው “ውጥረት ያለበት ሰው ሰውነት፣ ለመብረር እያኮበኮበ ካለ አውሮፕላን ጋር ይመሳሰላል” ብለዋል። አዎን፤ ውጥረት በሚሰማህ ጊዜ የልብ ምትህና የደም ግፊትህ በፍጥነት ይጨምራል። እንዲሁም በደምህ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ ይላል። ሆርሞኖችም በደምህ ውስጥ ይሰራጫሉ። ጸሐፊው ጨምረው እንዲህ ብለዋል:- “ውጥረቱ ከቀጠለ . . . ውጥረት የያዛቸው የሰውነታችን ክፍሎች በሙሉ (አንጎል፣ ልብ፣ ሳምባ፣ የደም ሥሮችና ጡንቻዎች) ከመጠኑ ያለፈ ሥራ ያከናውናሉ ወይም ደግሞ ይዳከማሉ። ይህም ከጊዜ በኋላ አካላዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።” የሚገርመው ነገር በውጥረት ምክንያት በጣም ብዙ ሕመሞች ይከሰታሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ የልብ ሕመም፣ የደም መርጋት፣ በሽታ የመከላከል አቅም መዛባት፣ ካንሰር፣ የአጥንት እና የጡንቻ ሕመም እንዲሁም የስኳር በሽታ ጥቂቶቹ ናቸው።

ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበው ጉዳይ ብዙዎች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች ውጥረትን ለመቋቋም ሲሉ የተሳሳተ እርምጃ የሚወስዱ መሆናቸው ነው። ቤቲ የንግስ የተባሉ አንዲት ዶክተር “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከሥቃያቸው ለመገላገል ሲሉ አልኮል መጠጥ ማዘውተራቸው፣ የአደገኛ ዕፆች ተጠቃሚ መሆናቸው፣ ከትምህርት ቤት መቅረታቸው፣ ዱርዬዎች መሆናቸው፣ ልቅ የጾታ ብልግና መፈጸማቸው፣ ጠበኛና ተደባዳቢ መሆናቸው፣ ከቤታቸው መኮብለላቸውና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን መፈጸማቸው በጣም ያሳዝናል። ይህ አካሄዳቸው ደግሞ ሊሸሹት ወደሚፈልጉት ችግር ይበልጥ ጠልቀው እንዲገቡ ያደርጋቸዋል” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ውጥረት የዘመናችን አንዱ ገጽታ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ሊወገድ አይችልም። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ውጥረትን ለመቆጣጠር ማድረግ ስለምንችላቸው ነገሮች ይብራራል!

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አንዳንድ ጊዜ የሚሰማኝ ውጥረት በጣም ከመባባሱ የተነሳ ልፈነዳ የደረስኩ መስሎ ይሰማኛል”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ የነጠላ ወላጆች ሕይወት በውጥረት የተሞላ ነው

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶች ከመጠን በላይ እንዲጨነቁ የሚያደርጋቸው ትምህርት ሊሆን ይችላል