በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውጥረት እያደረሰ ያለው ጥቃት!

ውጥረት እያደረሰ ያለው ጥቃት!

ውጥረት እያደረሰ ያለው ጥቃት!

“የአሜሪካ ቁጥር አንድ የጤና ችግር” የሚል ርዕስ ያለው አሜሪካን ኢንስቲትዩት ኦቭ ስትረስ የተባለ ድርጅት ያሳተመው አንድ ጽሑፍ፣ የዘመናችን ከባድ የጤና ችግር ካንሰር ወይም ኤድስ እንዳልሆነ ይገልጻል። አክሎም “ቀላል ሕክምናዎችን ወደሚሰጡ ሐኪሞች ከሚሄዱት ታካሚዎች መካከል ከ75-90 በመቶ የሚሆኑት ከውጥረት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለባቸው ይገመታል” በማለት ዘግቧል።

ሰዎች በዛሬው ጊዜ በውጥረት ጥቃት እየተሰነዘረባቸው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው ናሽናል ኮንሲዩመርስ ሊግ የተባለ ማኅበር እንዳለው “በሕይወታቸው ውስጥ የተለያየ ችግርና ጭንቀት ያለባቸውን አዋቂዎች ውጥረት የሚፈጥርባቸው ዋነኛው ምክንያት ሥራ (39%) ሲሆን ሁለተኛው የቤተሰብ ችግር (30%) ነው። ሌሎቹ የውጥረት መንስኤዎች ደግሞ የጤና መታወክ (10%)፣ የኑሮ ጭንቀት (9%)፣ ዓለም አቀፋዊ ግጭቶችና ሽብርተኝነት (4%) ናቸው።”

ይሁን እንጂ ውጥረት ያለባቸው ሰዎች የሚገኙት በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አይደለም። በ2002 በብሪታንያ የተደረገ አንድ ጥናት “በ2001 እና በ2002 ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በብሪታንያ የሚኖሩ ግለሰቦች እስከ መታመም የሚያደርስ ከሥራ ጋር የተያያዘ ውጥረት እንዳጋጠማቸው ይታመናል” የሚል ግምታዊ ሐሳብ ሰጥቶ ነበር። “ብሪታንያ ውስጥ ከሥራ ጋር በተያያዘ በሚከሰት ውጥረት፣ ጭንቀት ወይም ስጋት” ሳቢያ “በአንድ ዓመት ውስጥ በድምሩ አሥራ ሦስት ሚሊዮን ተኩል ገደማ የሚሆኑ የሥራ ቀናት ይባክናሉ።”

በቀሩት የአውሮፓ አገሮችም ሁኔታው ከዚህ የተሻለ አይደለም። ዩሮፒያን ኤጀንሲ ፎር ሴፍቲ ኤንድ ሄልዝ አት ወርክ የተባለው ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ “ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው ውጥረት በሁሉም ዓይነት የሥራ መስክ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አውሮፓውያን ሠራተኞችን እንደሚያጠቃ ተረጋግጧል።” አንድ ጥናት እንዳመለከተው “በየዓመቱ 41 ሚሊዮን የሚሆኑ [በአውሮፓ ኅብረት አገሮች የሚገኙ] ሠራተኞች፣ ከሥራ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ውጥረቶች ይጠቃሉ።”

ስለ እስያስ ምን ማለት ይቻላል? በቶኪዮ የተደረገ አንድ ስብሰባ ያወጣው ሪፖርት “ሥራ የሚያስከትለው ውጥረት በማደግ ላይ ባሉና በኢንዱስትሪ በበለጸጉ በርካታ አገሮች የተለመደ አሳሳቢ ችግር ነው” በማለት ደምድሟል። ሪፖርቱ እንደገለጸው “ቻይናን፣ ኮሪያንና ታይዋንን ጨምሮ በምሥራቅ እስያ የሚገኙ በርካታ አገሮች ፈጣን ኢንዱስትሪያዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አድርገዋል። አሁን እነዚህን አገሮች በጣም እያሳሰባቸው ያለው ጉዳይ በሥራ ምክንያት የሚመጣው ውጥረትና ይህን ተከትሎ በሠራተኞች ጤና ላይ የሚከሰተው ችግር ነው።”

ሆኖም ሰዎች በውጥረት እየተሰቃዩ እንዳሉ ለማረጋገጥ ጥናት ማካሄድ ላያስፈልግህ ይችላል። ምክንያቱም አንተ ራስህ የዚሁ ችግር ሰለባ ትሆን ይሆናል! ውጥረት በአንተና በምትወዳቸው ሰዎች ላይ ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል? ቤተሰቦች ችግሩን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይችላሉ? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጉዳዮች ያብራራሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች ውጥረት የሚያስከትልባቸው ዋነኛው ምክንያት ሥራቸው ነው