በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ዕጥፉን መንገድ በመሄዴ’ ተደስቻለሁ

‘ዕጥፉን መንገድ በመሄዴ’ ተደስቻለሁ

‘ዕጥፉን መንገድ በመሄዴ’ ተደስቻለሁ

ክሌር ቨቪ እንደተናገረችው

ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከሞዛምቢክ 400 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ማዳጋስካር ተራራማና ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ያሏት ደሴት ነች። የተወለድኩት በደሴቲቱ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ቤቱኩ 2 በተባለች አነስተኛ መንደር ነው። በአሥራ አምስት ዓመቴ ማለትም በ1987 ለትምህርት በባሕር ዳርቻ ወደምትገኘው ማሃኑሩ የተባለች ከተማ ሄድኩ።

በማሃኑሩ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረው ከታላቅ ወንድሜ ከሴሌስቲን ጋር እኖር ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ እኔም የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በወቅቱ አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር።

ግቤ ላይ ለመድረስ ያደረግሁት ጥረት

ከመጀመሪያ ግቦቼ መካከል አንዱ በቤቱኩ የሚኖሩ ቤተሰቦቼን መርዳት ነበር፤ ስለዚህ ይህን ምኞቴን ከግብ ለማድረስ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ ጸልያለሁ። ይሁን እንጂ ወደ ቤተሰቦቼ መሄድ የምችለው ትምህርት ቤት ሲዘጋ ብቻ ነበር። መንደሩ 100 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ መንገዱ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የመጀመሪያው 40 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ ያለው ሲሆን ቀሪው 60 ኪሎ ሜትር ግን በተራራ ላይ የሚገኝ ጠባብ የእግር መንገድ ነው።

በርካታ ቀጥ ያሉ አቀበቶችን መውጣት ነበረብኝ፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ መንገዱ ከእግሬ መዳፍ የሚበልጥ ስፋት የለውም። በጠዋት ተነስቼ ለዓይን ያዝ እስኪያደርግ ድረስ ብጓዝ ብዙውን ጊዜ መሄድ የምችለው 40 ኪሎ ሜትር ገደማ ነበር። ከ15 ኪሎ ግራም የሚበልጥ ጓዝ እይዝ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ጥቂቱን በጭንቅላቴ ላይ በመሸከም፣ የተወሰነውን በጀርባዬ በማዘልና ቀሪውን ደግሞ በእጄ በማንጠልጠል እጓዝ ነበር። በአብዛኛው የምይዘው ለዘመዶቼና ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የማበረክታቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ነበር። በዚህ ምክንያት “ጓዘ ብዙዋ መንገደኛ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶኝ ነበር።

ለቤተሰቦቼ ስለ አዲሱ እምነቴ ለመንገር በጣም ጓጉቼ የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያ ላይ ሊሰሙኝ ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሐሳባቸውን ለወጡና በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ጀመር፤ አንዳንድ ጊዜ ስንወያይ አምሽተን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እንተኛ ነበር።

የማይረሳ የእረፍት ጊዜ

ታኅሣሥ 24, 1990 ለእረፍት ወደ ቤቱኩ ተጓዝኩ። ቤተሰቦቼ የገናን በዓል አብሬያቸው ላከብር የሄድኩ ስለመሰላቸው ደስ አላቸው። ይሁን እንጂ በዓሉን አብሬያቸው የማላከብርበትን ምክንያት ሲሰሙ ደስታቸው ወደ ቅሬታ ተለወጠ። ቤተሰቦቼ ለመንደሩ ነዋሪዎች በበዓሉ እንደማልካፈል ለመግለጽ በጣም አፈሩ፤ ምክንያቱም ነዋሪዎቹ እርስ በርሳቸው በእጅጉ ይቀራረቡ ነበር። ስለዚህ ስለ አዲሱ እምነቴ ራሴ ለመንደሩ ሰዎች መንገር እንዳለብኝ ተሰማኝ። ግን እንዴት?

ገና ወጣት ስለነበርኩ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። ‘ነገ መንደርተኞቹ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው እያለ ስለ እምነቴ ብገልጽላቸው ምን ችግር አለው?’ ብዬ አሰብኩ። ይሖዋ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንዲመራኝ ረጅም ሰዓት የወሰደ ልባዊ ጸሎት አቀረብኩ። ከዚህ በኋላ የቤተ ክርስቲያን አስተማሪ የሆነውን ታላቅ ወንድሜን ፖልን “ነገ የገና በዓልን የማላከብርበትን ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ለሚመጡ ሰዎች ብገልጽ ምን ችግር ይኖረዋል?” ብዬ ጠየቅኩት። ስለ ጉዳዩ ከሌሎች ጋር ተማከረና በሐሳቡ ተስማሙ።

በቤተ ክርስቲያኑ የሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ካበቃ በኋላ በመልእክተኛ አስጠሩኝ። በድጋሚ ወደ ይሖዋ ጸለይኩና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይዤ ሄድኩ። ራሴን ካስተዋወቅኩ በኋላ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረኝ ስለረዱኝ ሁሉንም አመሰገንኳቸው። ከተማ ከገባሁ በኋላም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን እንደቀጠልኩና ቀደም ሲል ተምረናቸው የማናውቃቸውን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንዳወቅኩ ነገርኳቸው።

በዚህ አጋጣሚ መጽሐፍ ቅዱስ ገነት በሆነች ምድር ላይ ስለምናገኘው የዘላለም ሕይወት የሚናገረውን ተስፋ፣ (መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4) ጥቂት ታማኝ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚወሰዱበትን ምክንያትና (ዮሐንስ 14:2, 3፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3) ሙታን ልክ እንቅልፍ እንደያዘው ሰው ምንም የማያውቁ በመሆናቸው ሥቃይ እንደማይደርስባቸው የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች አካፈልኳቸው። (መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 11:11-14, 38-44) እንዲሁም የጥንት ክርስቲያኖች ገናን እንዳላከበሩና በዓሉ ከአረማውያን የተወረሰ እንደሆነ አስረዳኋቸው።

ንግግሬን ካበቃሁ በኋላ ብዙዎቹ ያልኩት ነገር እውነት እንደሆነ ገለጹልኝ። አንዳንዶቹ እንዲያውም ተጨማሪ ጥያቄዎች አነሱ። ከዚያም የወሰድኳቸውን ጽሑፎች አሳየኋቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዱ ታስበው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ እንደሆኑ ነገርኳቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚፈልግ ሰው ካለ ልረዳው ፈቃደኛ መሆኔን የገለጽኩላቸው ሲሆን አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወሰዱ።

በአስገራሚ ሁኔታ መገናኘት

ከዚያ በፊት የማላውቃት አንዲት ሴት ቀረብ አለችኝና “የአንቺ ዓይነት ሃይማኖት ያላት በሌላ መንደር የምትኖር እህት አለችኝ” ብላ ነገረችኝ። በጣም ተገርሜ “የት ነው ያለችው?” ብዬ ጠየቅኳት።

“አንድራኑማፋና” በማለት መለሰችልኝ። ይህ መንደር ከቤቱኩ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል።

በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርሳቸው ይተዋወቁ ስለነበር እህቷ ምናልባት የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ልትሆን እንደምትችል ለሴትየዋ ነገርኳት። እርሷ ግን እህቷ ልክ እኔ በቤተ ክርስቲያን የተናገርኩትን የሚመስል ትምህርት እንዳስተማረቻት በእርግጠኝነት ገለጸችልኝ። ወደ ተባለው መንደር ወዲያውኑ ለመሄድ ስለጓጓሁ የእህቷን ስምና አድራሻ እንድትሰጠኝ ጠየቅኳት። ይሁን እንጂ ላደርግ ያሰብኩት የእግር ጉዞ በጣም ከባድ ስለነበር እናቴ ጥቂት ቀናት እንድቆይ ጠየቀችኝ። ከሁለት ቀናት በኋላ ከወንድሜ ከቻርልስ ጋር ሆነን ወደ አንድራኑማፋና ተጓዝን።

እዚያ እንደደረስን “እዚህ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ?” ብለን አንዳንድ የመንደሩን ነዋሪዎች ጠየቅናቸው። “በዚህ መንደር ያሉት ካቶሊኮች፣ የጴንጤቆስጤ እምነት ተከታዮችና ኢንዲፔንደንት የሚባል ቤተ ክርስቲያን አባሎች ብቻ ናቸው” ብለው ሲመልሱልን በጣም አዘንኩ።

ከዚያ በኋላ አንዲት ሴት “የምትፈልጊው የይሖዋ ምሥክሮችን ከሆነ ማግኘት የፈለግሽው ምናልባት ማርሰሊንን እና ቤተሰቧን ይሆናል” አለችኝ። የምፈልጋት ሴት ስም ይሄ ነበር!

አንድ ሰው ማርሰሊንን ጠራልኝና ወዲያው መጣች፤ ይሁን እንጂ ፊቷ ላይ ትንሽ ፍርሃት ቢጤ ይነበብባት ነበር። እርሷን ለመመርመር ከሆነ ቦታ የመጣን ባለ ሥልጣናት ስለመሰልናቸው የመንደሩ ነዋሪዎች በሙሉ ከበቡን። እርሷና ቤተሰቧ ‘ተቀባይነት የሌለው ሃይማኖት’ ተከታዮች ናቸው ተብለው ስደት ይደርስባቸው እንደነበር በኋላ ሰማሁ።

ማርሰሊን ከተሰበሰበው ሕዝብ መሃል አወጣችንና መነጋገር ወደምንችልበት ቦታ ይዛን ሄደች። የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ስጠይቃት እንደሆነች ነገረችኝ። በዚህን ጊዜ ተመልሳ ሄደችና ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ይጠቀሙበት የነበረውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት የተባለውን መጽሐፍና የቆዩ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ይዛ መጣች። ጽሑፎቹ በሙሉ ያረጁና የተቀዳደዱ ነበሩ። “ባለፈው እሁድ ያጠናችሁት የትኛውን መጠበቂያ ግንብ ነው?” ብዬ ጠየቅኳት።

“ያሉን መጠበቂያ ግንቦች እነዚሁ ብቻ በመሆናቸው እየደጋገምን የምናጠናው እነዚህን ነው” አለችኝ። በዚህን ጊዜ እኔም የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ስነግራት ማርሰሊን በጣም ደስ አላት! ስብሰባ የሚመራላቸውን ወንድም እንድታስተዋውቀኝ ስጠይቃት ሩቅ ቦታ እንደሚኖር ገለጸችልኝ።

ሌላ አስደሳች ትውውቅ

በሚቀጥለው ቀን እኔና ማርሰሊን ስብሰባ ወደሚመራላቸው ሰው ሄድን። እቤቱ ስንደርስ በጣም ከመገረሙም በላይ ልንጠይቀው ስለሄድን ደስ አለው። ይህ ሰው በስተ ሰሜን ምሥራቅ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ከሚገኘው ቱአማሲና ከሚባል በባሕር ዳርቻ ያለ ከተማ የመጣ የይሖዋ ምሥክር ነው። ወንድም ከበርካታ ዓመታት በፊት በድንገት ከሥራው በመባረሩ ቤተሰቡን ይዞ ወደዚች መንደር ተመለሰ። ወደ መንደሩ ከተመለሰ በኋላ ይሰብክ ጀመር፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችንና ስብሰባዎችን ይመራ ነበር።

ይህ ወንድምና ቤተሰቡ ይዤው ሄጄ የነበረውን በቅርብ የወጣ መጠበቂያ ግንብ በተመለከቱ ጊዜ በደስታ ፈነደቁ። በዚያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት በዋነኝነት እንጠቀምበት የነበረውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ጨምሬ አሳየኋቸው። መጽሐፉን ለመጀመሪያ ጊዜ ማየታቸው ነበር። ቀጥሎ በነበረው እሁድ ወደ አንድራኑማፋና ተመልሼ አብሬያቸው በስብሰባ ላይ ተካፈልኩ። በዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉ መከርኳቸው፤ ምክንያቱም ቢሮው ስለዚህ አነስተኛ ቡድን መኖር ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

ከጥር 1991 ጀምሮ በየወሩ ማለት ይቻላል አዳዲስ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችንና ሌሎች ጽሑፎችን እየያዝኩ ከማሃኑሩ አንድራኑማፋና እሄድ ነበር። ቦታው 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ሲኖረው ከ88 ኪሎ ሜትር በላይ በእግሬ መጓዝ ነበረብኝ፤ ቀጥ ያለውንና ወጣ ገባውን ኮረብታ እየወጣሁና እየወረድኩ፣ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችን እያቋረጥኩ፣ ከዘነበ ደግሞ ቡክት ባለውና በሚያዳልጠው ጭቃ እየተወላከፍኩ እጓዝ ነበር።

ጽሑፎችንና መጽሔቶችን የሚፈልጉ ሰዎች እየተበራከቱ በመጡ ቁጥር ጓዜም እየበዛ ይሄድ ነበር። ይሁን እንጂ የክንዴ መዛል በእያንዳንዱ ጉዞ መጨረሻ ላይ ይሰማኝ በነበረው ጥልቅ እርካታና ደስታ ይካሳል። እያንዳንዱ አዳዲስ እትም ሲደርሳቸው የሚሰማቸውን እርካታና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በሥራ ላይ ሲያውሉ ስመለከት በጣም ደስ ይለኝ ነበር!

ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት

መስከረም 1, 1992 አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንኩ። በአቅኚነት የማገለግለው ማሃኑሩ ቢሆንም ቤቱኩ ከነበሩት ዘመዶቼ ጋር ደብዳቤ እጻጻፍ ነበር። ከጊዜ በኋላ በደብዳቤ አስጠናቸው ጀመር፤ ከዚያም ወደ መንደሩ ተመልሼ እንድረዳቸው ጠየቁኝ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበርኩ፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትና መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ከልባቸው መወሰናቸውን ለማረጋገጥ ፈለግኩ። ስለዚህ ለተወሰነ ጊዜ በማሃኑሩ በአቅኚነት ማገልገሌን ቀጠልኩ።

በ1993 መጨረሻ ገደማ በአንታናናሪቮ ተዘጋጅቶ በነበረው የሁለት ሳምንት የአቅኚዎች ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አገኘሁ። ከዚያ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ፤ ልዩ አቅኚ ከሆንኩ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ልመደብ እችላለሁ። ከጉባኤው አካባቢ ራቅ ብለው በቤቱኩ ይኖሩ የነበሩ ዘመዶቼን ለመርዳት እፈልግ ስለነበር ግብዣውን አልተቀበልኩም። ስለዚህ ወደ ማሃኑሩ ተመልሼ በአቅኚነት ማገልገሌን ቀጠልኩ።

በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች በጎበኘን ጊዜ ወደ መንደሬ ተመልሼ ዘመዶቼን መርዳት እችል እንደሆነ ጠየቅኩት። በዚያን ጊዜ በአንድራኑማፋና ጉባኤ ተመሥርቶ ስለነበር የዚህ ጉባኤ አባል እንድሆንና ወደ ቤቱኩ ክልል እየሄድኩ እንዳገለግል ሐሳብ አቀረበልኝ። ከመስከረም 1, 1994 ጀምሮ በዚህ መልኩ ማገልገል ጀመርኩ። የሃይማኖት መምህር የነበረው ወንድሜ ፖል በዚያው ወር አብሮኝ ወደ አውራጃ ስብሰባ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ በአንድራኑማፋና በስብከቱ ሥራ ላይ የሚካፈሉት አስፋፊዎች ቁጥር 30 የደረሰ ሲሆን በእሁዱ ስብሰባ ላይ ደግሞ በአማካይ 65 ተሰብሳቢዎች ይገኙ ጀመር።

በእግር መጓዜን አላቋረጥኩም

ወደ ቤቱኩ ከተመለስኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አራት የሥጋ ወንድሞቼና እህቶቼ በአገልግሎት ለመካፈል ብቁ የሆኑ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ተጠመቁ። ቤቱኩ ከተመለስኩ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ሁሉ 50 ኪሎ ሜትር ያህል በእግሬ ወደ አኑሲቤ አናላ እየሄድኩ ጽሑፎችና መጽሔቶች አመጣ ነበር። ጉዞው በጣም አድካሚ ቢሆንም በአካባቢው የነበረው አስደሳች መንፈሳዊ እድገት በጣም የሚክስ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ በቤቱኩ ያለው ጉባኤ ጥሩ እድገት እያደረገ ሲሆን በእሁዱ ስብሰባ ላይ በአማካይ 45 ሰዎች ይገኛሉ። እናቴ እንዲሁም ሁሉም ወንድሞቼና እህቶቼ አሁን የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። ታናሽ ወንድሜ ልዩ አቅኚ ነው። እኔም በኅዳር 1, 2001 አንታናምባው ማናምፑትሲ በተባለ መንደር ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ይሁን እንጂ ቤቱኩን ለቅቄ የወጣሁት ልቤ በደስታ ተሞልቶ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመርኩበት በ1987 በማዳጋስካር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ3,000 አይበልጥም ነበር። አሁን ግን ቁጥሩ አድጎ ከ14,000 በላይ ሆኗል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሲያደርጉት እንደነበረው እኔም ጉልበቴን ‘ዕጥፉን መንገድ ለመሄድ’ የመጠቀም መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ። ይሖዋም በዚህ ረገድ ያደረግኩትን ጥረት ስለባረከልኝ አመሰግነዋለሁ።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ስልሳ ኪሎ ሜትር ወደሚርቀው ትውልድ መንደሬ ስሄድ ብዙውን ጊዜ ከ15 ኪሎ ግራም የሚበልጥ ጓዝ እሸከም ነበር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቅ ወንድሜ ፖል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቻርልስ የሚባለው ወንድሜ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጥቂት የቤተሰቤ አባላት ጋር። አሁን እነዚህ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል