የተጎሳቆለችው ምድራችን
የተጎሳቆለችው ምድራችን
በ1805 መሪዌዘር ሉዊስ እና ዊልያም ክላርክ የተባሉ ዝነኛ አሳሾች በዛሬዋ ዋሽንግተን ስቴት ዩ ኤስ ኤ ወደሚገኘው ኮሎምቢያ ወንዝ ደረሱ። * የእነዚህን አሳሾች ቀልብ የሳበው ወንዙ ሳይሆን በውስጡ ይገኝ የነበረው ሳልሞን የተባለ የዓሣ ዝርያ ብዛት ነበር። ስለየቀኑ ውሏቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ ላይ “የዚህ ዓሣ ብዛት ፈጽሞ ሊታመን የሚችል አይደለም” ሲሉ ጽፈው ነበር። “በወንዙ እየተገፉ የሚንሳፈፉት ዓሦች እጅግ በጣም ብዙ በመሆናቸው ከወንዙ ተገፍተው በመውጣት በዳርና ዳር ስለሚረፈረፉ በአካባቢው የሚኖሩት ሕንዶች ከመሬት ላይ እየለቀሙ ሆድ ዕቃቸውን ካወጡ በኋላ በእንጨት ርብራብ ላይ እያደረጉ ያደርቋቸዋል።” እንዲያውም ሳልሞን የተባለው ዓሣ እንደልብ ከመገኘቱ የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎች አድርቀው ለማገዶነት ይጠቀሙባቸው ነበር።
ዛሬ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። አንድ የኒውስዊክ ዘገባ እንደሚለው “ሳይንቲስቶች ዓሦች ራሳቸውን ሊተኩ በማይችሉበት ፍጥነት ከውቅያኖሶች እየታፈሱ መሆናቸውን ካወቁ ከአሥር ዓመት በላይ ሆኗቸዋል።” ለምሳሌ በሰሜን አትላንቲክ 90 በመቶ የሚሆኑት ሳልሞን ዓሦች ጠፍተዋል።
ይሁን እንጂ በመመናመን ላይ የሚገኙት ዓሦች ብቻ አይደሉም። እንደ ነዳጅ ዘይት፣ ማዕድናትና ደኖች የመሳሰሉት የተፈጥሮ ሀብቶች በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየተሟጠጡ ነው። እንዲያውም ወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ የተባለው ድርጅት እንደዘገበው ከምድር የተፈጥሮ ሀብት 30 በመቶ የሚሆነው ያለቀው ከ1970 እስከ 1995 ባሉት ዓመታት ነው። የምድርን የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ላይ ለማዋል እየተሠራበት ያለው ዘዴ የተፈጥሮ ሥነ ምሕዳሮችንም የሚያጠፋ በመሆኑ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍ ሆኗል።
አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ችግሮች የፈጠረው የሰው ልጅ ራሱ በመሆኑ መፍትሄያቸውንም ማግኘት አያቅተውም ብለው ያስባሉ። አንድ ምሳሌ ብንወስድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች በሚገኙ በርካታ ከተሞች የአየር ብክለት በእጅጉ ቀንሷል። ታዲያ እንደነዚህ ያሉት የተስፋ ጭላንጭሎች ሁኔታዎቹ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ ያለመሆናቸውን ያመለክታሉ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 ሉዊስ እና ክላርክ የተላኩት አዲስ የተገዛውን ከሚሲሲፒ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚገኝ ግዛት እንዲያስሱና ካርታ ላይ እንዲያሰፍሩ ነበር።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Kevin Schafer/CORBIS