በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጉልበት ሥራ መሥራት ያለብኝ ለምንድን ነው?

የጉልበት ሥራ መሥራት ያለብኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

የጉልበት ሥራ መሥራት ያለብኝ ለምንድን ነው?

“ብዙ የጉልበት ሥራ እሠራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ደስ ይለኝ የነበረው ኮምፒውተሬ ፊት ቁጭ ብሎ መሥራት ነው።”—ናታን

“አንዳንድ ወጣቶች የጉልበት ሥራ ስንሠራ ሲያዩን ሌላ ምንም ነገር የማናውቅ ይመስል በጣም ይንቁናል።”—ሣራ

ዙዎች የጉልበት ሥራ አሰልቺ፣ የሚያቆሽሽና ጭራሽ የማይፈለግ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑ ሰው ስለ ጉልበት ሥራዎች ሲናገሩ “እንዲህ ዓይነት ሥራዎች በዚህ ክብር ፈላጊ ዓለም ውስጥ ብዙም ክብር አይሰጣቸውም” ብለዋል። በመሆኑም ብዙ ወጣቶች ገና የጉልበት ሥራ ስለ መሥራት ሲነሳ በጣም ቢያስጠላቸው ወይም ቢደብራቸው አያስደንቅም።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉልበት ሥራ ፈጽሞ ከዚህ የተለየ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል። ንጉሥ ሰሎሞን “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም” ብሏል። (መክብብ 2:24) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እስራኤላውያን የሚተዳደሩት በግብርና ነበር። ማረስ፣ ማጨድና መውቃት አድካሚ ሥራዎች ናቸው። ሆኖም ሰሎሞን ጠንክሮ መሥራት ትልቅ ወሮታ እንዳለው ገልጿል።

ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን . . . በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም” በማለት አሳስቧል። (ኤፌሶን 4:28) ጳውሎስ ራሱ የጉልበት ሥራ ይሠራ ነበር። በጣም የተማረ ቢሆንም አንዳንዴ ድንኳን በመስፋት ራሱን ይደግፍ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 18:1-3

አንተስ የጉልበት ሥራ ስለ መሥራት ምን ይሰማሃል? ብታምንም ባታምንም የጉልበት ሥራ መሥራት በብዙ መንገድ ሊጠቅምህ ይችላል።

የጉልበት ሥራ መሥራት ለወደፊት ሕይወትህ ይጠቅምሃል

አጥር ማጠርም ይሁን የግቢህን ሣር ማጨድ ለጤንነትህ ጥሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የጉልበት ሥራዎች ናቸው። የጉልበት ሥራ የሚጠቅመው ጥሩ ጤና ለማግኘት ብቻ አይደለም። የተነፈሰ የመኪና ጎማ ወይም ደግሞ የመኪና ዘይት እንዴት እንደሚቀየር ታውቃለህ? የተሰበረ መስኮት አሊያም የተበላሸ ቧምቧ መጠገን ትችልበታለህ? ምግብ ማብሰልስ ትችላለህ? ግቢ ማጽዳት፣ ቤት መጥረግ ወይም መወልወል ትችላለህ? እነዚህ ችሎታዎች ወጣት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ ናቸው። አንድ ቀን የራስህን ኑሮ መሥርተህ ስትኖር በእጅጉ ሊጠቅሙህ ይችላሉ።

የሚያስገርመው ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የጉልበት ሥራ የሚጠይቅ አንድ ሙያ ነበረው። ኢየሱስ የአናጢነት ሙያ ተምሮ ነበር፤ እንጀራ አባቱ ዮሴፍ አናጢ እንደነበር በመጠቀሱ ይህን ችሎታ የቀሰመው ከእርሱ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3) አንተም የጉልበት ሥራ በመሥራት የተለያዩ ጠቃሚ ችሎታዎችን ማዳበር ትችላለህ።

መልካም ባሕርያትን ማዳበር

የጉልበት ሥራ ለራስህ በሚኖርህ ግምት ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል። ዶክተር ፍሬድ ፕሮቬንዛኖ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኘው ናሽናል ሜንታል ሄልዝ ኤንድ ኤጁኬሽን ሴንተር ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ እንደገለጹት የጉልበት ሥራዎችን መሥራት መማር “በራስ የመተማመን ስሜታችንን” ከፍ የሚያደርግልን ከመሆኑም በተጨማሪ “ሥርዓታማና የተደራጀን እንድንሆን ይረዳናል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በሥራው ዓለም ስኬታማ ለመሆን የሚያስችሉ ጥሩ መሠረቶች ናቸው።” ጆን የሚባል ወጣት “የጉልበት ሥራ ትዕግሥትን እንድትማሩ ይረዳችኋል። ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ትምህርት ታገኛላችሁ” በማለት ተናግሯል።

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሣራ እንዲህ ብላለች:- “የጉልበት ሥራ መሥራቴ ጠንካራና ታታሪ ሠራተኛ እንድሆን ረድቶኛል። በአስተሳሰቤና በአካላዊ ሁኔታዬ ሥርዓታማ መሆን እንዳለብኝ አስተምሮኛል።” ጠንክሮ መሥራት አሰልቺ ነው? ናታን እንዲህ ብሏል:- “የጉልበት ሥራ መሥራት ደስታ እንደሚያስገኝ ተምሬያለሁ። ችሎታዬን እያሻሻልኩና የሥራዬን ጥራት እየጨመርኩ እንዳለሁ ማስተዋል ችያለሁ። ይህም ለራሴ አክብሮት እንዲኖረኝ አድርጎኛል።”

የጉልበት ሥራ የድካምህን ውጤት እያየህ መርካትን እንድትማር ያስችልሃል። ጄምስ የተባለ ወጣት ይህን በተመለከተ ሲገልጽ “የአናጢነት ሙያዬን እወደዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ቢያደክመኝም የሠራኋቸውን ነገሮች ሁልጊዜ ስለምመለከታቸው እረካለሁ። ይህም በጣም ደስ ያሰኛል” ብሏል። ብራየንም በዚህ አስተያየት ይስማማል። “ጋራዥ በመሥራቴ በጣም ደስ ይለኛል። አንድ የተበላሸ ነገር የመጠገንና መልሶ ልክ በአዲስነቱ እንደነበረው የማድረግ ችሎታ እንዳለኝ ማወቄ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖረኝና እርካታ እንዳገኝ አስችሎኛል።”

ቅዱስ አገልግሎት

ክርስቲያን ወጣቶች የጉልበት ሥራ መሥራታቸው ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት ረገድ እርዳታ ሊያበረክትላቸው ይችላል። ንጉሥ ሰሎሞን ለይሖዋ ድንቅ የሆነ ቤተ መቅደስ የመገንባት ኃላፊነት ሲሰጠው ሥራው ብርቱ ጥረትና ችሎታ የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤ የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ።”—1 ነገሥት 7:13, 14

ኪራም ችሎታውን የይሖዋን አምልኮ ለማራመድ ሊጠቀምበት መቻሉ ታላቅ መብት ነው! የኪራም ተሞክሮ “በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል፤ አልባሌ ሰዎችን አያገለግልም” የሚለውን በምሳሌ 22:29 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውነተኝነት ያረጋግጣል።

በዛሬው ጊዜም ስለ ግንባታ ሥራ ብዙም እውቀት ያልነበራቸው ወይም ምንም የማያውቁ ወጣቶች ሳይቀሩ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ የመካፈል መብት አግኝተዋል። አንዳንዶቹ እንዲህ ባሉ ሥራዎች በመካፈላቸው እንደ ኤሌክትሪክ ሥራ፣ የቧምቧ ሥራ፣ የግንበኝነት፣ የአናጢነት ሙያዎችንና የመሳሰሉትን ለመማር ችለዋል። ምናልባት አንተም በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ መካፈል የምትችልበት አጋጣሚ ይኖር እንደሆነ የጉባኤህን ሽማግሌዎች ማነጋገር ትችላለህ።

በበርካታ የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ ላይ የተካፈለው ጄምስ እንዲህ ብሏል:- “አብዛኞቹ የጉባኤ አባላት በሥራው ለመርዳት ጊዜውም ሆነ ችሎታው ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ እርዳታ በምታበረክቱበት ጊዜ መላውን ጉባኤ እየደገፋችሁ ነው።” የአርማታ ሥራ የተማረው ናታን ይህ ችሎታው ለሌላ አምላካዊ አገልግሎት በር እንደከፈተለት ተናግሯል። “ወደ ዚምባብዌ ተጉዤ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ እገዛ የማድረግ መብት አግኝቻለሁ። ለሦስት ወራት ያህል በዚያ ሠርቻለሁ፤ ይህም በሕይወቴ ካገኘኋቸው አስደሳች ተሞክሮዎች አንዱ ነው” ብሏል። ሌሎች ወጣቶችም እንዲሁ የጉልበት ሥራዎችን ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት በአገራቸው በሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉ አነሳስቷቸዋል።

የጉልበት ሥራ የመሥራት ችሎታ ማዳበራችን በተወሰነ ደረጃ ‘ባለን ነገር የምንረካ’ እንድንሆን ይረዳናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:6) ብዙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ያገለግላሉ። አንዳንዶች ሙያ መማራቸው ለሰብዓዊ ትምህርት ብዙ ጊዜና ገንዘብ ሳያጠፉ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ገቢ ለማግኘት አስችሏቸዋል።

የጉልበት ሥራ መሥራት መማር የሚቻለው እንዴት ነው?

በእጅ ሙያ የመተዳደር ፍላጎት ካለህ ወይም ደግሞ ቤት ውስጥ አንዳንድ ነገሮች ማከናወን የምትፈልግ ከሆነ የእጅ ሙያ መማሩ እንደሚጠቅምህ ምንም ጥርጥር የለውም። ከምትማርበት ትምህርት ቤትም ይህን ሙያዊ ሥልጠና ልትቀስም ትችላለህ። እንዲሁም አንዳንድ ሙያዎችን በቤትህ ውስጥ ልትማር ትችላለህ። እንዴት? የቤት ውስጥ ሥራዎች መሥራትን በመማር ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ፕሮቬንዛኖ “በተለይ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት ይገባቸዋል፤ ይህም ልጆቹ ከወላጆቻቸው ተለይተው ራሳቸውን በሚችሉበት ጊዜ የተሳካና የተሟላ ኑሮ ለመኖር እንዲችሉ ይረዳቸዋል” ሲሉ ጽፈዋል። ስለዚህ ቤት ውስጥ መሠራት የሚገባው ነገር እንዳለ ልብ ብለህ ተመልከት። ግቢህ ውስጥ መታጨድ ያለበት ሣር አለ? ወይስ ጥገና የሚያስፈልገው መደርደሪያ ይታይሃል?

የጉልበት ሥራ በበርካታ መንገዶች ስለሚጠቅምህ ልትንቀው ወይም ልታፍርበት አይገባም። የጉልበት ሥራ ከመሥራት አትሽሽ! ከዚህ ይልቅ ጠንክሮ በመሥራት የሚገኘውን “ርካታ” ለመቅመስ ተጣጣር፤ ይህም መክብብ 3:13 እንደሚለው “የእግዚአብሔር ችሮታ” ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በርካታ ወጣቶች አንዳንድ ሙያዎችን መማራቸው ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንዲያሰፉ ረድቷቸዋል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአብዛኛው ወላጆችህ መሠረታዊ የሆኑ ሙያዎችን ሊያስተምሩህ ይችላሉ