በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፕላኔቷ ምድራችን ከጥፋት ልትድን ትችላለች!

ፕላኔቷ ምድራችን ከጥፋት ልትድን ትችላለች!

ፕላኔቷ ምድራችን ከጥፋት ልትድን ትችላለች!

የሰው ልጅ የምድርን ሀብት በዚህ ፍጥነት እየበዘበዘ ሊቀጥል እንደማይችል ያለፉት ርዕሶች ግልጽ አድርገዋል። የዓለም መሪዎች የአካባቢ ብክለትን፣ የደን ውድመትንና ከከባቢያችን ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስመሰግን ጥረት እንዳደረጉ አይካድም። ከ163 የሚበልጡ አገራት በ1972 ከተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሰው ልጅ ከባቢያዊ ሁኔታ ኮንፈረንስ ጀምሮ የተለያዩ ኮንፈረንሶችን በተከታታይ አድርገው የድርጊት መርሐ ግብሮችን አጽድቀዋል። ሆኖም ውጤቱ ምን ሆነ? የዓለም አቀፍ ከባቢያዊ ሕግ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ሃንተር “እነዚህ በርካታ ውሎች፣ የድርጊት መርሐ ግብሮችና ሌሎች መሣሪያዎች የዓለም አቀፉን ከባቢያዊ ጉስቁልና ሊቀለብሱ አለመቻላቸው በእጅጉ ያሳዝናል” ብለዋል። እንዲያውም ሃንተር በማከል እንዳሉት “የከባቢ ሁኔታ በ1992 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ከተካሄደበት ጊዜ ይበልጥ ዛሬ በከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።”

ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ለማሻሻል የ30 ዓመት ጥረት ከተደረገ በኋላ እንኳን እዚህ ግባ የሚባል እድገት ያልታየው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እድገት የግድ ማስፈለጉ ነው። የአገራትን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሰው የሸማቾች ፍጆታ ነው። ለሸማቾች የሚያስፈልገውን ሸቀጥ ለማቅረብ የንግድ ድርጅቶች ማምረት ይኖርባቸዋል። ለማምረት ደግሞ ጥሬ ዕቃዎች ያስፈልጋሉ። ይህ የማያቋርጥ ሽክርክሪት ሲሆን ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ የሚደርሰው በከባቢያችን ላይ ነው። ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው?

የተሳሳቱ እርምጃዎች

መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ራሱን ለማስተዳደር ያደረገው ጥረት በአሳዛኝ ሁኔታ ውድቅ የሆነበትን ምክንያት ይገልጻል። ነቢዩ ኤርምያስ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” ብሏል። (ኤርምያስ 10:23) በእርግጥም እነዚህ ቃላት ትክክል መሆናቸው ተረጋግጧል።

ጥሩ የአትክልት ቦታ ወይም መናፈሻ ጎብኝተህ ታውቃለህ? በሥርዓት የተተከሉ ቆንጆ ዛፎችን፣ ቁጥቋጦዎችንና አበባዎችን ስናይ በጣም ደስ ይለናል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያማረና የተስተካከለ የአትክልት ቦታ እንዲሁ በራሱ አይገኝም። ጥሩ ችሎታ ያላቸው አትክልተኞች ዛፎቹን በመከርከም፣ ሣሩን አጭደው በማስተካከልና አበባዎቹን በማሳመር በርካታ ሰዓታት ለፍተው የተገኘ ነው። ለአንድ የአትክልት ሥፍራ ወይም መናፈሻ የተለፋውን ለመላዋ ምድራችን ቢለፋ መኖሪያችን የሆነችው ምድር ምን ልትመስል እንደምትችል ገምት።

በመሠረቱ የፈጣሪያችን ዓላማ ፕላኔታችን እንዲህ ዓይነቱን እንክብካቤ እንድታገኝ ነበር። በመንፈስ በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው የፍጥረት ታሪክ “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው” ይላል። (ዘፍጥረት 2:15) ከዚህም በላይ የሰው ልጅ ኤደንን ብቻ ሳይሆን ይህችን የመጀመሪያ ገነት እያስፋፋ መላዋን ምድር ገነት የማድረግ የሥራ ኃላፊነት ተቀብሏል።—ዘፍጥረት 1:28

የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን ታዛዦች ባለመሆናቸው ፍጽምናቸውን እንዲሁም ገነትን የመንከባከብና የማስፋፋት መብታቸውን አጡ። (ዘፍጥረት 3:1-6, 23) እኛም የእነዚህ የመጀመሪያ ባልና ሚስት ልጆች እንደመሆናችን ኃጢአትና አለፍጽምና ወርሰናል። (ሮሜ 5:12) በምድር የተፈጥሮ ሀብት ላይ የደረሰው ጉስቁልናና ብክነት የሰው ልጅ ራሱን ሲያስተዳድር ከፈጸማቸው ስህተቶች አንዱ ብቻ ነው። የሰው ልጅ ያፈጠጡበትን ችግሮች በራሱ ሊያስወግድ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል። የግድ ከሌላ አካል እርዳታ ማግኘት ያስፈልገዋል።

ወደ ተሐድሶ የሚያደርሰው ጎዳና

ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:10) ምድር በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በምትተዳደርበት ጊዜ ወደ ገነትነት እንደምትመለስ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (መዝሙር 37:10, 11) በዚያ ዘመን ዛፎችና ሌሎች ዕጽዋት ንጹሕ በሆነ አካባቢ ሙሉ ምርታቸውን ይሰጣሉ። (መዝሙር 72:16) ምድር በአምላክ አመራር ሥር ስትሆን ከማንኛውም ብክለት ትጸዳለች። የሰው ልጅም ከከባቢው ጋር እንዴት ተስማምቶ እንደሚኖር ይማራል። እንዲህ እንደሚሆን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ምድር ለዘላለም እንደማትናወጥ’ ይናገራል። (መዝሙር 104:5) አምላክ በቀጠረው ጊዜ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ጥሩ ጤንነትን፣ የተትረፈረፈ ምግብንና ጥሩ ቤትን ጨምሮ ዘላለማዊ በረከቶችን ያገኛሉ። ስለ አምላክ ዓላማ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን አነጋግር። ፕላኔቷ ምድራችን ከጥፋት ልትድን እንደምትችልና በእርግጥም እንደምትድን ከመጽሐፍ ቅዱስ በደስታ ያስረዳሃል!

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአምላክ አመራር ሥር የሰው ልጅ ከከባቢው ጋር ተስማምቶ ይኖራል

[ምንጭ]

ልጃገረድና ገበሬ:- © Jeremy Horner/ Panos Pictures