በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በኢንተርኔት ለትዳር ለመጠናናት ብሞክር ምን ችግር አለው?”

“በኢንተርኔት ለትዳር ለመጠናናት ብሞክር ምን ችግር አለው?”

የወጣቶች ጥያቄ . . .

“በኢንተርኔት ለትዳር ለመጠናናት ብሞክር ምን ችግር አለው?”

“በየዕለቱ በኢሜይል መልእክት እንለዋወጥ ነበር። የመኖሪያ ቦታችንንና የምንሠራውን ሥራ በተመለከተ ተነጋግረናል፤ እንዲሁም የጋብቻ ቀለበታችንን እኔ እንዳዘጋጅ ተስማምተናል። ይህ ሁሉ ሲሆን ከተዋወቅን ገና አንድ ወር እንኳ ያልሞላን ከመሆኑም በላይ ፊት ለፊት ተያይተን አናውቅም።”—ሞኒካ፣ ኦስትሪያ *

ምናልባት ወደፊት ልታገቢው የምትችይውን አንድ ሰው መተዋወቅ በጣም ትፈልጊያለሽ። ይሁን እንጂ እስከ አሁን ያደረግሽው ሙከራ ሁሉ አልተሳካም። የሚያስቡልሽ ጓደኞችሽም ሆኑ ቤተሰቦችሽ በዘዴ አንቺን ከአንዱ ጋር ለማስተዋወቅ የሚያደርጓቸው ሙከራዎችም ቢሆኑ ይበልጥ እፍረት እንዲሰማሽና ተስፋ እንድትቆርጪ ከማድረግ በስተቀር ምንም አልፈየዱልሽም። ስለዚህ ዘመኑ ባመጣው ቴክኖሎጂ ብጠቀም የተሻለ ይሆን እያልሽ ልታስቢ ትችያለሽ።

በዚህ የኮምፒውተር ዘመን ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ጥቂት የኮምፒውተር ቁልፎችን መነካካት ብቻ በቂ ሊመስል ይችላል። ማድረግ ያለብሽ ነገር ቢኖር በተለይ ላላገቡ ሰዎች የተዘጋጁትን ድረ ገጾች፣ ቻት ሩሞች ወይም ማስታወቂያዎች መክፈት ብቻ እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ። በአንድ ወር ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 45 ሚሊዮን ሰዎች ለጋብቻ በኢንተርኔት መጠናናትን የሚመለከቱ ድረ ገጾችን እንደቃኙ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በኢንተርኔት የፍቅር ተጓዳኞችን የሚያገናኝ አንድ ድርጅት በ240 አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ደንበኞች እንዳሉት ገልጿል።

በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ የሆነበት ምክንያት

ዓይናፋር በመሆንሽ ምክንያት ከሰዎች ጋር መቀራረብ ይከብድሻል? አልፈልግሽም ቢለኝስ ብለሽ ትፈሪያለሽ? ወይስ በምትኖሪበት አካባቢ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይሰማሻል? በዚህ ጊዜ በኢንተርኔት አማካኝነት ከአንዱ ጋር መተዋወቅና መጠናናት ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ሊሰማሽ ይችላል። እንዲህ እንዲሰማሽ የሚያደርገው አንዱ ምክንያት በኢንተርኔት የፍቅር ተጓዳኞችን የሚያገናኘው ድርጅት ይህ ዘዴ “ለትዳር የምታጠኚውን” ሰው መቆጣጠር እንደሚያስችል አድርጎ ስለሚነግርሽ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ድረ ገጾች ላይ ዕድሜ፣ የመኖሪያ አገር፣ ስለ ግለሰቡ ማንነት የሚገልጽ መረጃ፣ ፎቶና የብዕር ስም ይጻፋል። ተጠቃሚው እንደልብ የመምረጥ ነፃነት እንዲኖረው ስለሚያደርግ በዚህ ዘዴ የትዳር ጓደኛ መፈለግ ውጤታማና ፊት ለፊት እንደ መገናኘት ብዙም የማያስጨንቅ ሊመስል ይችላል።

ይሁን እንጂ እውነታው ምንድን ነው? በኢንተርኔት አማካኝነት መጠናናት በእርግጥ ዘላቂ ደስታ ያስገኛል? እስቲ የሚከተለውን ሐሳብ ተመልከት። አንድ የፍቅር ተጓዳኞች አገናኝ ድርጅት በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 11 ሚሊዮን ደንበኞች ያፈራ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የተጋቡት 1,475ቱ ብቻ ናቸው። ሌላ አገናኝ ድርጅት ከነበሩት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባላት መካከል ደግሞ የተጋቡት 75ቱ ብቻ ናቸው! ችግሩ ምን ይሆን?

እርስ በርስ በትክክል ለመተዋወቅ ያስችላል?

አንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ጽሑፍ “ማንም ሰው ቢሆን ራሱን በኢንተርኔት የሚያቀርበው ማራኪ፣ ሐቀኛና ጥሩ ኑሮ ያለው ሰው እንደሆነ አድርጎ ነው” በማለት ይገልጻል። ይሁን እንጂ ሰዎች ስለ ራሳቸው የሚናገሩት ነገር ምን ያህል እውነት ነው? ሌላ ጽሑፍ “ሁሉም ሰው በጥቂቱም ቢሆን እንደሚዋሽ የተረጋገጠ ነው” ብሏል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙ ልጆች የሚታተም ታዋቂ መጽሔት አዘጋጅ የሆኑ አንዲት ሴት ይህን አባባል ለማረጋገጥ በግላቸው ምርምር አድርገው ነበር። እኚህ ሴት ታዋቂ ለሆኑ ሦስት አገናኞች ስማቸውን ሰጡና ከጥቂት ጊዜ በኋላ በርካታ መልሶች መጡላቸው። በዚህ መልኩ ከበርካታ ወንዶች ጋር መጻጻፍ ጀመሩ። ውጤቱ ምን ነበር? የማይሆን ነገር እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም! ወንዶቹ ስለራሳቸው ዓይን ያወጣ ውሸት ይናገሩ ነበር። እኚህ ሴት “የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች እንደሚዋሹ በራሴ ደርሶ አይቼዋለሁ” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ቁመትን ወይም ክብደትን በተመለከተ ውሸት መናገር ያን ያህል ከባድ ላይመስል ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች ‘አካላዊ ውበትና ቁመና ያን ያህል የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይደለም’ ይሉ ይሆናል። እውነት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ቊንጅና አታላይ ነው፤ ውበትም ይረግፋል” ይላል። (ምሳሌ 31:30) ይሁን እንጂ ትንንሽ በሚመስሉ ነገሮች እየዋሹ ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል? (ሉቃስ 16:10) ይህ ሰው የወደፊት ግብን ስለመሳሰሉ በጣም ከባድ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሚናገራቸውን ነገሮች እንዴት ማመን ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ” ይላል። (ዘካርያስ 8:16) አዎን፣ ሐቀኝነት እየጠነከረ የሚሄድ ወዳጅነት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ነው።

በኢንተርኔት የሚደረግ መጠናናት በአብዛኛው ተጨባጭነት በሌላቸው ቅዠቶች እንድንዋጥ ያደርጋል። በኒውስዊክ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ተጠቃሚዎቹ የሚጽፏቸውን ቃላት በጥንቃቄ ሊመርጡና በጣም ጥሩ መስለው ሊቀርቡ ይችላሉ። . . . ጥሩ መስለው መቅረባቸው ደግሞ ሌላኛው ወገን በበኩሉ ጥሩ መስሎ ምላሽ እንዲሰጥ ያደርገዋል፤ ጥሩ መስለውና አንተን በጣም እንደሚፈልጉህ ሆነው ከቀረቡህ አንተም ጥሩ መስለህና እንደምትፈልጋቸው ሆነህ ትቀርባለህ።” ኒው ዮርክ የሚገኘው ሬንሰሌር የሙያ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑ ሰው በኢንተርኔት ስለሚደረጉት ግንኙነቶች ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች በቀላሉ ጠንካራ የሆነ እርስ በርስ የመፈላለግ ስሜት እንደሚፈጠር አስተውለዋል። ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ እንደታየው ይህ አስደሳች ትዳር ለመመሥረት ጥሩ መሠረት ሊሆን አይችልም። አንድ ሰው በኢንተርኔት መጠናናትን በተመለከተ ምን እንዳጋጠመው ሲናገር “ይህ ወጥመድ ነው። አእምሯችሁ ሁሉን ነገር ልክ እናንተ እንደምትፈልጉት አድርጎ አሳምሮ ይስልላችኋል” ብሏል።

ፊት ለፊት መገናኘት

አንዳንዶች ፊት ለፊት ተገናኝቶ አለመተያየቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ይሰማቸው ይሆናል። በኢንተርኔት የሚደረግ መጠናናት፣ በወደፊቱ የትዳር ጓደኛ ውጫዊ መልክ ሳይደናቀፉ ውስጣዊ ማንነቱን በማወቁ ላይ ትኩረት ለማድረግ እንደሚያስችል ያምናሉ። እውነት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ለውስጣዊ ባሕርያት ትኩረት እንድንሰጥ ያበረታታናል። (1 ጴጥሮስ 3:4) ይሁን እንጂ በኮምፒውተር አማካኝነት በሚደረግ ውይይት የተናጋሪውን አካላዊ መግለጫ፣ ፈገግታ ወይም ፊቱ ላይ የሚነበበውን ስሜት መመልከት አትችሉም። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ሌሎችን እንዴት እንደሚይዝ ማወቅም አትችሉም። እነዚህ ደግሞ አንድን ሰው ልታምኑትና ልትወዱት የምትችሉት ዓይነት ሰው መሆን አለመሆኑን ለመወሰን የሚረዷችሁ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቅር ምን እንደሚል ለመመልከት 1 ቆሮንቶስ 13:4, 5ን አንብቡ። ፍቅር የሚገለጸው በባሕርይ እንጂ በቃላት እንዳልሆነ ልብ በሉ። ስለዚህ ለጋብቻ የምታጠኑት ሰው ንግግሩና ተግባሩ የሚጣጣም መሆኑን ጊዜ ወስዳችሁ አጢኑ።

የሚጠናኑ ሰዎች እንደነዚህ ያሉትን በጣም አስፈላጊ ነገሮች አለማወቃቸው ብዙውን ጊዜ የውስጥ ስሜቶቻቸውንና አሳባቸውን ከተገቢው ጊዜ ቀደም ብለው መገላለጽ እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ የሚጠናኑ ሰዎች ምንም እንኳን እርስ በርሳቸው በቅጡ ባይተዋወቁም ጥንቃቄ ሳያደርጉ በችኮላ ከባድ ቃል ኪዳኖችን ይጋባሉ። “ፍቅር በኢንተርኔት በእርግጥም እውር ነው” የሚል ርዕስ ያለው አንድ ጽሑፍ 12,800 ኪሎ ሜትር ተራርቀው ስለሚኖሩ በኢንተርኔት የተዋወቁ ወንድና ሴት ይዘግባል። ከሦስት ሳምንት በኋላ ፊት ለፊት ተገናኙ። ወንዱ እንዲህ ብሏል:- “ድምቅ ያለ የቅንድብ መገተሪያ ተቀብታ ነበር። እኔ ደግሞ የቅንድብ መገተሪያ ከምትጠቀም ሴት ጋር መጠናናት አልፈልግም።” ወዲያው ግንኙነታቸው ተቋረጠ። ፊት ለፊት የተገናኙ የሌሎች ጥንዶች መጨረሻ ደግሞ በጣም ያሳዝናል፤ ወንድየው ሴቷ እርሱ ወዳለበት እንድትመጣ የአውሮፕላን ትኬት ቢገዛላትም የመመለሻዋን ትኬት ተቀብሎ ሒሳቡን ተመላሽ አደረገ!

ኤደ የተባለች አንዲት ወጣት በኢንተርኔት ስለ መጠናናት ያጋጠማትን ስትገልጽ “ግንኙነታችን በጣም ጥሩና እውነተኛ ይመስል ነበር። ለመጋባትም አቅደን ነበር” ብላለች። ይሁን እንጂ ፊት ለፊት ሲተያዩ ግንኙነታቸው ከባድ አደጋ ተደቀነበት። “እንዳሰብኩት ዓይነት ሰው ሳይሆን ስህተት ለቃቃሚና ነጭናጫ ነበር። ከእሱ ጋር መቀጠል ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነበር” ብላለች። ከአንድ ሳምንት በኋላ ግንኙነታቸው ተቋረጠ፤ በዚህ ምክንያት ኤደ ተስፋዋ ሁሉ ጨለመ።

በኮምፒውተር አማካኝነት የሚመሠረት እንዲህ ያለው ቅርርብ የሚፈጥረው የቅዠት ዓለም ያለጊዜው ኃይለኛ ስሜት በውስጣችሁ እንዲቀሰቀስ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ግንኙነታችሁ ሳይሳካ ቢቀር ስሜታችሁ እንዲጎዳ ምክንያት ይሆናል፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነገር ነው። ምሳሌ 28:26 “በራሱ የሚታመን ተላላ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። አዎን፣ በቅዠትና በስሜት ተገፋፍቶ ከባድ ውሳኔዎችን ማድረግ የጥበብ እርምጃ አይደለም። በመሆኑም የምሳሌ መጽሐፍ በመቀጠል “በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም” ይላል።

መጣደፍ የሚያስከትለው አደጋ

በሚገባ ሳትተዋወቁ ተጣድፋችሁ ግንኙነታችሁ እንዲጠነክር ማድረጋችሁ ፈጽሞ የጥበብ እርምጃ አይደለም። እንግሊዛዊው ደራሲ ሼክስፒር “በችኮላ የተፈጸመ ጋብቻ ብዙም አይሰምርም” በማለት ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ “ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” በማለት ይበልጥ ቀጥተኛ ምክር ይሰጠናል።—ምሳሌ 21:5

የሚያሳዝነው በኢንተርኔት የሚጠናኑ ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሞኒካ ከአንድ ወንድ ጋር ለአንድ ወር ብቻ ከተጻጻፈች በኋላ የትዳር ጓደኛ የማግኘት ሕልሟ እውን የሚሆንበት ጊዜ የደረሰ መስሏት ነበር። ምንም እንኳን ለመጋባት አቅደውና የጋብቻውን ቀለበት እርሷ እንድታዘጋጅ ተነጋግረው የነበረ ቢሆንም ይህን የመሰለው መቻኮል “ከባድ ሐዘን” አስከትሎባታል።

“አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ በማዋል ሐዘን እንዳይደርስባችሁ ማድረግ ትችላላችሁ። (ምሳሌ 22:3) ይሁን እንጂ በኮምፒውተር አማካኝነት የሚደረግ መጠናናት የሚያስከትለው የስሜት መጎዳት ብቻ አይደለም። የሚከሰቱትን ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች ወደፊት በሚወጣ ርዕሰ ትምህርት ላይ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ ሰዎች በኢንተርኔት መልእክት ሲለዋወጡ ስለ ራሳቸው የተጋነነ ወይም ውሸት የሆነ ነገር ይናገራሉ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢሜይል ብዙ የፍቅር መልእክቶችን ሲጻጻፉ የቆዩ ሰዎች ፊት ለፊት ሲገናኙ አብዛኛውን ጊዜ የሚያበሳጭ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል