በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው?

ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው?

በአንድ የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት ላይ ሁለት ወንዶች እጅ ለእጅ ተያይዘው ታዋቂ በሆኑ የኤጲስቆጶስ ጳጳስ ፊት ቆመዋል። ከዚያም ሁለቱ ሰዎች “በአምላክ እና በቤተ ክርስቲያኗ ፊት . . . ቃል ኪዳን” አደረጉ። በነጭ ልብሳቸው ላይ ወርቅማ ቀለም ያለው ካባ የደረቡት ጳጳስ በሕዝብ ፊት ጋብቻቸውን ባረኩት። ቀጥሎም ተጋቢዎቹ ተቃቅፈው ሲሳሳሙ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘው ሕዝብ ከመቀመጫው በመነሳት ሞቅ ያለ ጭብጨባ አደረገላቸው። ጳጳሱ ይህ ዓይነት ግብረ ሰዶማዊ ጋብቻ “ቅዱስ ከመሆኑም በላይ ሊባረክ፣ . . . እንዲያውም ቅዱስ ተብሎ ሊጠራ ይገባዋል” ብለዋል።

ሆኖም ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረገውን ጋብቻ በጣም አውግዘውታል። “[የጳጳሱ] ውሳኔ በጣም አስቆጥቶናል” ስትል ሲንቲያ ብራስት የተባለች የአሜሪካ የአንግሊካን ምክር ቤት በመባል የሚታወቀው የወግ አጥባቂ ኤጲስቆጶሳውያን ቡድን ቃል አቀባይ ተናግራለች። ሲንቲያ “ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረገውን ጋብቻ መባረክ ጋብቻንና የጾታ ግንኙነትን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከሰፈረው ትምህርት ጋር ይጋጫል” ብላለች። እንዲሁም “የጾታ ግንኙነት . . . በቅዱስ ጋብቻ በተቆራኙ ወንድና ሴት መካከል ብቻ መወሰን ይገባዋል” በማለት ጨምራ ተናግራለች።

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተነሳው የጦፈ ክርክር በሃይማኖት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ይህ ጉዳይ ከጡረታ አበል፣ በትዳር ጓደኛ አማካኝነት ከሚገኝ የሕክምና ዝግጅትና ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የሚያስከትለው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መዘዝ ቀላል ባለመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለጋለ ፖለቲካዊ ውዝግብ መንስኤ ሆኗል።

ሰብዓዊ መብትንና ሕጋዊ እውቅናን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ብዙውን ጊዜ በጣም ውስብስብ ከመሆናቸውም በላይ ሕዝቡ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ያለው አመለካከት የተከፋፈለ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ባለመግባት የገለልተኝነት አቋማቸውን ለመጠበቅ ይጠነቀቃሉ። (ዮሐንስ 17:16) * ይሁን እንጂ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያላቸው አንዳንዶች ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻንና ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ ግራ ተጋብተዋል። አንተስ ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረገውን ጋብቻ እንዴት ትመለከተዋለህ? አምላክ ለትዳር ያወጣው መሥፈርት ምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ ያለህ አመለካከት ከአምላክ ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

የጋብቻን መሥፈርት የሚያወጣው ፈጣሪያችን ነው

መንግሥታት ጋብቻን በተመለከተ ሕግጋት ከማውጣታቸው ከብዙ ጊዜያት በፊት ፈጣሪያችን ጋብቻ ሊመራበት የሚገባውን ሥርዓት ሰጥቷል። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 2:24) በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ቢብሊካል ዎርድስ “ሚስት” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “አንስታይ ጾታ ያላትን ሰብዓዊ ፍጥረት ያመለክታል” ብሏል። ኢየሱስም በጋብቻ የሚጣመሩት “ወንድና ሴት” መሆን እንዳለባቸው ገልጿል።—ማቴዎስ 19:4

እንግዲያው የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ዘላቂ ወዳጅነት እንዲሆን ነበር። ስለዚህ ወንዶችና ሴቶች የተፈጠሩት አንዳቸው የሌላኛውን ስሜታዊ፣ መንፈሳዊና ጾታዊ ፍላጎቶች በማርካት ለትዳር ጓደኞቻቸው ማሟያ እንዲሆኑ ተደርገው ነው።

ስለ ሰዶምና ገሞራ የሚናገረው የታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አምላክ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን አመለካከት እንዳለው ያሳያል። እንዲህ ብሎ ነበር:- “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቶአል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቶአል።” (ዘፍጥረት 18:20) ሁለት እንግዶች ጻድቅ የሆነውን ሎጥን በጎበኙት ወቅት የሰዶም ሰዎች በሥነ ምግባር ምን ያህል ልቅ እንደሆኑ በግልጽ ታይቷል። “የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከያካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት። ሎጥንም ጠርተው፣ ‘በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን’ አሉት።” (ዘፍጥረት 19:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ “የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ” ይላል።—ዘፍጥረት 13:13

መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶም ስለሚፈጽሙ ሰዎች ሲናገር “እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ” ይላል። (ሮሜ 1:27) “ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ።” (ይሁዳ 7) የግብረ ሰዶማውያን መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ጥረት በሚደረግባቸው አገሮች አንዳንዶች ግብረ ሰዶም “ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ” ተብሎ መጠራቱን ይቃወማሉ። ይሁን እንጂ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማውን ወይም ከተፈጥሮ ውጭ የሆነውን ነገር መወሰን ያለበት አምላክ መሆን የለበትም? የጥንት ሕዝቦቹን “ከሴት ጋር እንደሚደረገው ሁሉ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ይህ አስጸያፊ ነው” በማለት አዝዟቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 18:22

በአምላክ ፊት ተጠያቂ ነህ

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ግብረ ሰዶማዊነትን እንደማይቀበለው ወይም በቸልታ እንደማይመለከተው በግልጽ ይናገራል። ‘እንዲህ የሚያደርጉትን የሚያበረታቱ’ ሰዎችንም አጥብቆ ይቃወማቸዋል። (ሮሜ 1:32) “ጋብቻ” ግብረ ሰዶምን የተከበረ ድርጊት አያደርገውም። “ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር” የሚለው የአምላክ መመሪያ በግብረ ሰዶማውያን መካከል የሚደረገውን ጥምረት የማይጨምር ከመሆኑም በላይ አምላክ ይህንን ድርጊት ይጸየፈዋል።—ዕብራውያን 13:4

አሁንም ቢሆን ከአምላክ በሚገኝ እርዳታ ማንም ሰው ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ከማንኛውም ዓይነት ‘ዝሙት መራቅን’ እንዲሁም “የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ[ን]” ሊማር ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 4:3, 4) እርግጥ ይህን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ግብረ ሰዶም ይፈጽም የነበረ ናታን * የተባለ አንድ ሰው “ከዚህ ልማድ መላቀቅ የምችል አይመስለኝም ነበር” ብሏል። ሆኖም ‘ከአምላክ መንፈስ’ ባገኘው እርዳታ ሊለወጥ ችሏል። (1 ቆሮንቶስ 6:11) ናታን፣ ይሖዋ ሊያሸንፈው የማይችለው ችግር እንደሌለና የእርሱን መሥፈርቶች በማሟላት በረከቶቹን ለማግኘት ለሚጥሩ ሰዎች አስፈላጊውን ኃይልና እርዳታ እንደሚሰጣቸው ተገንዝቧል።—መዝሙር 46:1

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 የይሖዋ ምሥክሮች የአገሪቱ ሕግ በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነው ሕሊናቸው ጋር በሚጋጭበት ጊዜም እንኳን ሕጉን ለማስለወጥ በሚደረገው ተቃውሞም ሆነ በማንኛውም የፖለቲካ ትግል አይካፈሉም።

^ አን.14 እውነተኛ ስሙ አይደለም።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photo by Chris Hondros/Getty Images