በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቲማቲም—ሁለገብ የሆነ “አትክልት”

ቲማቲም—ሁለገብ የሆነ “አትክልት”

ቲማቲም—ሁለገብ የሆነ “አትክልት”

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አንዲት ጣሊያናዊት የቤት እመቤት “ቲማቲም ባይኖር ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር!” በማለት ተናግራለች። በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ምግብ አዘጋጆች ይህን ስሜቷን ይጋራሉ። በእርግጥም ቲማቲም በብዙ አገሮች የምግብ አዘገጃጀት ዘዴዎች ውስጥ አይጠፋም። የጓሮ አትክልት ያላቸው ሰዎች ከማንኛውም ዓይነት አትክልት በላይ የሚያሳድጉት ቲማቲም ነው። ይሁንና ቲማቲም የሚመደበው ከፍራፍሬ ወገን ነው ወይስ ከአትክልት?

በዕጽዋት ጥናት መሠረት ቲማቲም በውስጡ የዘር ፍሬ ስላለው መደቡ ከፍራፍሬ ወገን ነው። ይሁን እንጂ ቲማቲም በአብዛኛው ከዋና ምግብ ጋር የሚቀርብ ስለሆነ ብዙ ሰዎች አትክልት ነው ብለው ያስባሉ። ይህ ጣፋጭ ምግብ አስደናቂ ታሪክ አለው።

አስደናቂ ታሪክ

በሜክሲኮ የሚኖሩት አዝቴክ የሚባሉ ጎሣዎች ቲማቲምን ለምግብነት ያመርቱ ነበር። በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሜክሲኮን ድል ያደረጉ ስፔይናውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ይዘውት የገቡ ሲሆን ቶማትል የተሰኘውን ቃል ከናዋትል ቋንቋ በመውሰድ ቶማቴ ብለው ጠሩት። ብዙም ሳይቆይ በኢጣሊያ፣ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ የስፔይን ማኅበረሰቦች ይህን ጣፋጭ ምግብ ይመገቡ ጀመር።

በዚያው ምዕተ ዓመት ትንሽ ቆየት ብሎ ቲማቲም ወደ ሰሜናዊ አውሮፓ ደረሰ። መጀመሪያ ላይ መርዛማ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ስለነበር የሚተከለው ለውበቱ ብቻ ነበር። ቲማቲም ሶላናኬ ከሚባሉ ዕጽዋት መካከል የሚመደብ የሚያውድ ሽታ ያላቸው ቅጠሎችና መርዛማ የሆኑ ግንዶች ያሉት ተክል ቢሆንም ፍሬው ግን ሙሉ በሙሉ ጉዳት የሌለው መሆኑ ተረጋግጧል።

ይህ በቅርቡ ወደ አውሮፓ የመጣው የቲማቲም ዓይነት ቀለሙ ቢጫ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም ጣሊያኖች ፖሞዶሮ (ወርቃማ እንኰይ) የሚል ስያሜ ሰጡት። እንግሊዞች ቶሜት ያሉት ሲሆን ቆየት ብሎ ደግሞ ቶሜቶ ብለው ይጠሩት ጀመር፤ ይሁንና “የፍቅር እንኰይ” የተሰኘው ስያሜም የተለመደ ነበር። ቲማቲም ከአውሮፓ በመነሳት አትላንቲክ ውቅያኖስን ተሻግሮ ወደ ሰሜን አሜሪካ የገባ ሲሆን በዚያም የኋላ ኋላ በ19ኛው መቶ ዘመን በጣም የሚዘወተር ምግብ ሆነ።

በዓይነቱና በተወዳጅነቱ አስደናቂ የሆነ ተክል

እስቲ የቲማቲም ቀለም ምን ዓይነት ነው ብለህ ጠይቅ፤ መልሱም “ቀይ ነዋ” እንደሚሆን ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ቢጫ፣ ብርቱካንማ፣ ሮዝ፣ የወይን ጠጅ፣ ቡኒ፣ ነጭ ወይም አረንጓዴ አንዳንዶች ደግሞ መሥመር ያላቸው የቲማቲም ዓይነቶች እንዳሉ ታውቅ ነበር? ደግሞም ሁሉም ድቡልቡል አይደሉም። አንዳንዶች ጠፍጣፋ ወይም ሞላላ ቅርጽ ያላቸው ናቸው። የአተር ፍሬን ያህል ትንሽ የሆኑ አሊያም የሰውን ጭብጥ የሚያህሉ ትልልቆችም አሉ።

ይህ ተወዳጅ ምግብ በሰሜን እስከ አይስላንድ፣ በደቡብ ደግሞ እስከ ኒው ዚላንድ ድረስ ባሉ ቦታዎች ይበቅላል። ዋናዎቹ አምራቾች ዩናይትድ ስቴትስና የደቡብ አውሮፓ አገሮች ናቸው። ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ያላቸው አገሮች ቲማቲም የሚያመርቱት በመስተዋት ቤቶች ውስጥ ሲሆን ደረቅ አካባቢዎች ደግሞ ይህን አትክልት የሚያሳድጉት ሃይድሮፖኒክ በሚባል ዘዴ፣ ይኸውም አፈር ሳይኖረው በአፈር ውስጥ የሚገኙት ለተክሉ እድገት የሚያስፈልጉ አልሚ ምግቦች በውኃ ሟምተው በተዘጋጁበት ፈሳሽ ውስጥ ነው።

ቲማቲም ትርፍ ጊዜውን በአትክልተኛነት በሚያሳልፍ ሰው ዘንድ ተወዳጅ ነው። ለማሳደግ ቀላል ሲሆን አነስተኛ ቁጥር ያለውን ቤተሰብ ለመመገብ ጥቂት የቲማቲም ተክል በቂ ነው። በቂ ቦታ ከሌላችሁ ቨረንዳና የመስኮት ጉበኖች ላይ በዕቃ ሊያድጉ የሚችሉ የቲማቲም ዘሮችን ትከሉ።

አንዳንድ ምክሮችና ጤና ነክ መረጃዎች

ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ጣዕሙን ስለሚያበላሽ ቲማቲም በማቀዝቀዣ ውስጥ አታስቀምጡ። ቲማቲም ቶሎ እንዲበስል ለማድረግ የፀሐይ ብርሃን በሚደርስበት መስኮት ላይ ወይም በቤት የሙቀት መጠን በጎድጓዳ ሣህን ውስጥ ከበሰለ ቲማቲም አሊያም ሙዝ ጋር እንዲሁም ቡናማ ቀለም ባለው ኪስ ወረቀት ውስጥ አድርጋችሁ ለጥቂት ቀናት ማስቀመጥ ይቻላል።

ቲማቲም ለጤንነታችሁ ጥሩ ነው። ቲማቲም ቪታሚን ኤ፣ ሲ እና ኢ እንዲሁም ፖታሲየም፣ ካልሲየምና የማዕድን ጨው አለው። ቲማቲም እንደ ካንሰርና የልብ በሽታ ያሉትን አንዳንድ ሕመሞች ለመከላከል እንደሚረዳ የሚታመነው ሊኮፔን የተባለ ንጥረ ነገር እንዳለው ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ቲማቲም ከ93 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው ይዘቱ ውኃ ስለሆነ ክብደት ላለመጨመር የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ ካሎሪ እንደሌለው ማወቃቸው ያስደስታቸዋል።

ለብዙ ነገር የሚያገለግል ጣዕም

ቲማቲም ስትገዙ የትኛውን ዓይነት ትመርጣላችሁ? ለሰላጣ፣ ለሾርባና ለስጎ የሚስማማው በሠፊው የሚታወቀው ቀዩ ዓይነት ነው። ቀይ፣ ብርቱካንማ፣ ወይም ቢጫ ቀለም ያላቸው ትንንሾቹ የቲማቲም ዓይነቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር ስላላቸው እንዳለ ቢበሉ ይጣፍጣሉ። ፒሳ ወይም ፓስታ የምታዘጋጁ ከሆነ ጠንከር ያለ ሥጋ ያላቸው ሞላላዎቹ የቲማቲም ዓይነቶች ተመራጭ ናቸው። መጠኑ ትልልቅ የሆነው ወፍራም ሥጋ ያለው የቲማቲም ዓይነት በውስጡ ሌላ ምግብ ሞልቶ ለማቅረብ ወይም በመጋገሪያ ውስጥ አብስሎ ለመብላት ተስማሚ ነው። አንዳንድ ጊዜ ለየት ያሉ መስመሮች ያሉት አረንጓዴው ቲማቲም ተከትፈው የሚቀርቡ የምግብ ዓይነቶችን ለማጣፈጥ በጣም ጥሩ ነው። ቲማቲም ከአትክልት፣ ከእንቁላል፣ ከፓስታ፣ ከሥጋና ከዓሣ ለሚዘጋጁ ጣፋጭ ምግቦች ጥሩ ጣዕምና መልክ ይሰጣል። ቲማቲም ማግኘት የማትችሉ ከሆነ በአካባቢያችሁ በሚገኙ መደብሮች ውስጥ ብዙ ዓይነት የታሸጉ የቲማቲም ውጤቶች ማግኘት እንደምትችሉ ምንም ጥርጥር የለውም።

እያንዳንዱ የምግብ አዘጋጅ ቲማቲም የሚጠቀምበት የራሱ መንገድ ቢኖረውም ቀጥሎ የቀረቡትን ጥቂት ሐሳቦች መሞከር ትፈልጉ ይሆናል።

1. የተከተፈ ቲማቲም፣ ቺዝ (ፎርማጆ) እና አቮካዶ በመቀላቀል ሲያዩት የሚያምር ከምግብ በፊት የሚቀርብ ማለትም አፒታይዘር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዘጋጀት ይቻላል። በላዩ ላይ ደግሞ ቁንዶ በርበሬና የወይራ ዘይት ጨምሩበትና መልኩ እንዲያምር የበሶብላ ቅጠል ጣል አድርጉበት።

2. የተከተፈ ቲማቲም፣ የፈረንጅ ዱባ (ኪያር) እንዲሁም ከፍየል ወተት የሚዘጋጅ አይብ ከጥቁር የወይራ ፍሬና በስሱ ከተከተፈ ቀይ ሽንኩርት ጋር በመቀላቀል የግሪክ ሰላጣ አዘጋጁ። ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው ጨውና ቁንዶ በርበሬ ጨምሩበት እንዲሁም ማጣፈጫ እንዲሆን የወይራ ዘይትና የሎሚ ጭማቂ አቅርቡ።

3. ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ቃሪያና የድንብላል ቅጠል በደቃቁ ከትፎ ከሎሚ ጭማቂ ጋር በመቀላቀል የሜክሲኮ ስጐ አዘጋጁ።

4. በቆርቆሮ የታሸገ የተከተፈ ቲማቲም በመጥበሻ ላይ ገልብጣችሁ ስኳር ቆንጥራችሁ በመጨመር ትንሽ የወይራ ዘይት፣ የተከተፈ ነጭ ሽንኩርት፣ እንደ በሶብላ፣ ላውሮ ወይም ጦስኝ ያሉ ቅጠሎችን እንዲሁም እንደ ጨውና ቁንዶ በርበሬ ያሉ ማጣፈጫዎችን በማከል ለፓስታ ማባያ የሚሆን በቀላሉ የሚዘጋጅ ሆኖም የሚጣፍጥ የቲማቲም ስጐ አዘጋጁ። ውሕዱን ጣዱትና ስጐው እስኪወፍር ድረስ ለ20 ደቂቃ ያህል ይብሰል። ከዚያም ተቀቅሎ በጠለለው ፓስታችሁ ላይ ጨምራችሁ አቅርቡት።

ሁለገብ የሆነው ቲማቲም እንድንመገባቸው ከተፈጠሩልን የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው።