እንስሳት ልጆቻቸውን የሚመግቡበትና የሚያሠለጥኑበት መንገድ
እንስሳት ልጆቻቸውን የሚመግቡበትና የሚያሠለጥኑበት መንገድ
በስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ሰዎች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ብዙውን ጊዜ ሁለት አሥርተ ዓመታት ገደማ ይወስድባቸዋል። በሌላ በኩል ብዙ እንስሳት በጥቂት የበጋ ወራቶች ውስጥ ልጆቻቸውን የሚመግቡበትና የሚያሠለጥኑበት የተሟላ ፕሮግራም አላቸው። የሚቀጥሉት ጥቂት ምሳሌዎች አንዳንድ እንስሳት ልጆቻቸውን ለማሳደግ በየዓመቱ የሚያጋጥሟቸውን አድካሚ ሥራዎች የሚያሳዩ ናቸው።
1. ነጭ ሽመላ በፎቶ ግራፉ ላይ የምትታየው ይህቺ ወፍ በበጋም እንኳ እረፍት የላትም። ጎጆዋን በየጊዜው ለመጠገን ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ የተራቡ ጫጩቶቿን ለመመገብ እንቁራሪት፣ ትንንሽ ዓሣዎች፣ እንሽላሊት ወይም ፌንጣ ለመፈለግ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሐይቅ ብዙ ጊዜ ትመላለሳለች። ሁለቱም ወላጆች በዚህ መንገድ ያለማቋረጥ ሲመላለሱ ይውላሉ። ጫጩቶቹ በጣም ብዙ ምግብ ይመገባሉ። የሚገርመው በተፈለፈሉ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ብቻ እንኳ በየቀኑ የሰውነታቸውን ክብደት ግማሽ ያህል መመገብ ይችላሉ! መብረር ከተማሩ በኋላም ትንንሾቹ ሽመላዎች ለብዙ ሳምንታት ከወላጆቻቸው ጥገኝነት አይላቀቁም።
2. አቦ ሸማኔ ግልገሎችን የመንከባከቡ ኃላፊነት የወደቀው በእናትየዋ ላይ ብቻ በመሆኑ ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል አቦ ሸማኔዎች የሚያድጉት በአንድ ወላጅ ነው። ብዙውን ጊዜ ከሦስት እስከ አምስት ግልገሎችን የምትወልደው አቦ ሸማኔ ራሷን በሚገባ መግባ ልጆቿን ማጥባት እንድትችል በየቀኑ ማደን ይኖርባታል። ለማደን የምታደርገው ጥረት በአብዛኛው ስለማይሳካላት በየዕለቱ ምግብ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሥራ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንበሳ እርሷ ዞር ስትል ግልገሎቿን ለመብላት ስለሚያደባ በየጥቂት ቀናቱ ጉድጓድ ትቀያይራለች። ልጆቹ ሰባት ወር ሲሆናቸው ራሳቸውን ችለው ማደን እንዲችሉ ማሠልጠን ትጀምራለች፤ ይህ ደግሞ ዓመት ወይም ከዚያም የበለጠ ጊዜ ይወስዳል። በመሆኑም ግልገሎቹ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ከእናታቸው ጋር ይቆያሉ።
3. ትንሿ ግሬብ ግሬቦችና ጫጩቶቻቸው ፈጽሞ አይነጣጠሉም ለማለት ይቻላል። ጫጩቶቹ እንደተፈለፈሉ ተንሳፋፊ ጎጇቸውን በመተው ምቹ በሆነው የወላጆቻቸው ጀርባ ላይ ይሰፍራሉ። ጫጩቶቹ በወላጃቸው ጀርባ ላይ ተፍጨርጭረው ከወጡ በኋላ በክንፎችና የጀርባ ላባዎች መካከል በሚገኘው እንደ ከረጢት ያለ ቦታ ላይ ይቀመጣሉ። ስለዚህ እናትየው ወይም አባትየው በአካባቢው በሚዋኙበት ጊዜም እንኳ ጫጩቶቹ ሙቀትና ጥበቃ አይለያቸውም። አንደኛው ወላጅ ምግብ ፍለጋ ወደ ውኃ ውስጥ ሲጠልቅ ሌላው ልጆቹን ያዝላል፤ ይህንንም በየተራ ያከናውናሉ። ጫጩቶቹ ውኃ ውስጥ ጠልቀው የራሳቸውን ምግብ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ በፍጥነት ቢማሩም እንኳ ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸው ቅርርብ ለተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል።
4. ቀጭኔ ቀጭኔዎች ከአንድ ግልገል በላይ የሚወልዱት ከስንት አንዴ ነው፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም። በፎቶ ግራፉ ላይ እንዳለው ዓይነት አዲስ የተወለደ ቀጭኔ እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብደትና 2 ሜትር ቁመት ሊኖረው ይችላል! ከተወለደ ከአንድ ሰዓት በኋላ ግልገሉ በእግሮቹ መቆምና የእናቱን ጡት መጥባት ይጀምራል። ብዙም ሳይቆይ ራሱን ችሎ መመገብ ቢችልም ለዘጠኝ ወራት ያህል የእናቱን ጡት መጥባት ይቀጥላል። ግልገሉ አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመው እናትየው ኃይለኛ እርግጫ በመሰንዘር ከአብዛኞቹ ጠላቶቹ ስለምትጠብቀው ቶሎ ብሎ እግሮቿ መሃል ይገባል።
5. የዓሣ ዓመቴ የዓሣ ዓመቴዎች ለጫጩቶቻቸው የሚመግቧቸውን ዓሦች ለመያዝ ቀልጣፎች ብቻ ሳይሆን መራጮች መሆን ይኖርባቸዋል። የሥነ አዕዋፍ ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ ሁለቱም ወላጆች አዲስ የተፈለፈሉ ጫጩቶቻቸውን እስከ ሁለት ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ ያላቸውን ትንንሽ ዓሦች ይመግቧቸዋል። ወላጆቹ የዓሣውን ጭንቅላት በውጪ
በኩል በማድረግ በመንቆራቸው በጥንቃቄ ይይዙታል። ይህም የተራቡት ጫጩቶች የመጣላቸውን ምግብ በጭንቅላቱ በኩል በቀላሉ ለመዋጥ ያመቻቸዋል። ጫጩቶቹ እያደጉ በሄዱ መጠን ወላጆቻቸው ትንሽ ከፍ ያሉ ዓሣዎችን ያመጡላቸዋል። ጫጩቶቻቸውን የሚመግቡበት ፍጥነትም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱ ጫጩት በ45 ደቂቃ ልዩነት ይመገባል። ሆኖም ጫጩቶቹ 18 ቀን ሲሆናቸው የምግብ ፍላጎታቸው በእጅጉ ስለሚጨምር በየ15 ደቂቃ ልዩነት ይመገባሉ! በፎቶው ላይ የምትታየው ጫጩት ከጎጆዋ ወጥታለች፤ በቅርቡ ራሷን ችላ ዓሣ ማደን ትጀምራለች። በዚህን ወቅት ምናልባት ልጆቻቸው በማደጋቸው ወላጆች እፎይታ ያገኛሉ ብለህ ታስብ ይሆናል። ለዓሣ ዓመቴዎች ግን ሁኔታው ፍጹም የተለየ ነው! ብዙውን ጊዜ በዛው የበጋ ወቅት በድጋሚ ጫጩቶችን በመፈልፈል ተመሳሳዩን ዑደት ይጀምራሉ።እርግጥ ነው፤ የተለያዩ እንስሳት ለልጆቻቸው እንክብካቤ ስለሚያደርጉበት መንገድ በዝርዝር የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች አዳዲስ ነገሮችን በተገነዘቡ ቁጥር በእንስሳት ዓለም በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው ትስስር እጅግ ብርቱ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። አምላክ ለፈጠራቸው እንስሳት ይህን ዓይነት ችሎታ ከሰጣቸው ሰብዓዊ ወላጆችም ልጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን እንክብካቤና ሥልጠና እንዲሰጧቸው እንደሚፈልግ ምንም አያጠራጥርም።