ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ከካፌይን ነፃ የሆነ ቡና
ኤል ፓይስ የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ የብራዚል ሳይንቲስቶች ኮፊ አራቢካ ከተባለው በስፋት ከሚታወቀው የቡና ዝርያ ውስጥ ከካፌይን ነፃ የሆነ አዲስ የቡና ዓይነት ማግኘታቸውን ዘግቧል። ይህ በተፈጥሮው ከካፌይን ነፃ የሆነ የቡና ዓይነት የሚበቅለው በኢትዮጵያ ሲሆን ይህ ግኝት ለቡና ኢንዱስትሪ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል። በመላው ዓለም ከሚኖሩ ቡና ጠጪዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት የሚጠጡት ቡና ካፌይን ባይኖርበት የሚመርጡ ሲሆን ይህ አኃዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። አንድ የቡና ፍሬ በአማካይ 12 ሚሊ ግራም የሚያክል ካፌይን ሲኖረው በዚህ አዲስ በተገኘው የቡና ዓይነት ውስጥ ግን በአንድ ግራም ቡና ውስጥ የሚገኘው ካፌይን ከ0.76 ሚሊ ግራም አይበልጥም። ኤል ፓይስ እንደዘገበው “በኢንዱስትሪያዊ ዘዴ ካፌይን ከቡና እንዲወጣ የሚደረግበት ሂደት ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ለቡና ጥሩ ጣዕም የሚሰጡትን አንዳንድ ቅመሞች ያጠፋል።” ስለዚህ አዲሱ የቡና ተክል ካፌይንን ከቡና አጣርቶ ማውጣት የሚያስከትለውን ይህን ሁለት ችግር ይፈታል።
ሸረሪቶች የስበትን ኃይል የሚቋቋሙት እንዴት ነው?
የለንደኑ ዘ ታይምስ ጋዜጣ “ሸረሪቶች ግድግዳና ጣሪያ ላይ እንዲንጠለጠሉ የሚያስችላቸው ኃይል ምን እንደሆነ ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል” ይላል። ሸረሪት ስምንት እግሮች አሏት። በእያንዳንዱ እግር ጫፍ ላይ ትናንሽ ፀጉራም መቆንጠጫዎች ሲኖሩ እያንዳንዱ ፀጉር ደግሞ ሴትዩልስ በሚባሉ በጣም ጥቃቅን ፀጉሮች የተሸፈነ ነው። 624,000 በሚያክሉት ሴትዩልስ ጫፍ ላይ የሚገኘው የማጣበቅ ኃይል በጣም ከፍተኛ በመሆኑ አንዲት ሸረሪት ግድግዳ ወይም ጣሪያ ላይ ተንጠልጥላ ከራሷ ክብደት 170 እጥፍ የሚበልጥ ክብደት ልትሸከም ትችላለች። በጀርመንና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ተመራማሪዎች የኤሌክትሮን ማጉያ መነጽር በመጠቀም የዘላይ ሸረሪትን እግር አጥንተዋል። የጥናታቸው ግኝት “ተመሳሳይ ዘዴ በመጠቀም በጣም ጠንካራ የሆነና በእርጥበት የማይበገር አዲስ ዓይነት ማጣበቂያ መሥራት እንደሚቻል አረጋግጧል” ሲል ዘ ታይምስ ገልጿል። የጥናቱ ቡድን መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አንቶንያ ከስል በማከል “በተጨማሪም የጠፈር ተጓዦች በመንኮራኩራቸው ግድግዳ ላይ መጣበቅ የሚያስችላቸው የጠፈር ልብስ መጠቀም እንደሚችሉ መገመት ይቻላል” ብለዋል።
የአፈና መብዛት በሜክሲኮ
አንድ የጥበቃ ድርጅት በላቲን አሜሪካ ከኮሎምቢያ ቀጥሎ ብዙ አፈና የሚፈጸምባት አገር ሜክሲኮ እንደሆነች መናገሩን ዘ ማያሚ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ ዓለም አቀፍ እትም ገልጿል። “መንግሥታዊ ያልሆነ ግምት እንደሚያሳየው [በ2003] 3,000 የሚደርስ አፈና ተፈጽሟል።” ይሁን እንጂ የታፋኞቹ ቤተሰቦች ከአፋኞቹ ጋር በምስጢር መደራደር ስለሚፈልጉ አብዛኞቹ አፈናዎች ሪፖርት ሳይደረጉ ይቀራሉ። በተጨማሪም ታፋኞቹ ከአውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች ገንዘብ አውጥተው ከሰጡ በኋላ ወዲያው የሚለቀቁባቸው የአፈና ወንጀሎች በዚህ አኃዝ ውስጥ አልተካተቱም። በሜክሲኮ ሲቲ በየቀኑ 16 የሚያክሉ እንዲህ ዓይነት አፈናዎች እንደሚፈጸሙ ቢገመትም ቁጥሩ እስከ 80 ሊደርስ እንደሚችል ጋዜጣው ገልጿል። የባሰ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ አፋኞቹ ይበልጥ አረመኔ እየሆኑ መሄዳቸውና ታፋኞቹ የተጠየቁትን ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ እንኳን የሚገደሉ መሆናቸው ነው።
የኤድስ ሕሙማን ብዛት አሻቅቧል
በ2003 አምስት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በኤድስ ቫይረስ የተያዙ ሲሆን “ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ ባሉት ሃያ ዓመታት ውስጥ በአንድ ዓመት ይህን ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የመጀመሪያ ጊዜ ነው” ሲል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። “በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ኤች አይ ቪን ለመዋጋት ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ቅስቀሳና ግፊት ቢደረግም በኤድስ ቫይረስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ከመሄዱም በላይ በየዓመቱ በዚሁ በሽታ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው ይቀጠፋል።” በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው ዩኤንኤድስና ሌሎች ድርጅቶች ባወጡት መረጃ መሠረት በየዓመቱ 3 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሲሆን በሽታው ከታወቀበት ከ1981 ወዲህ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ሞተዋል። ባሁኑ ጊዜ በኤች አይ ቪ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ብዛት 38 ሚሊዮን እንደሚደርስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገምቷል። ከሁሉ በላይ የተጠቃው አካባቢ 25 ሚሊዮን የኤድስ ሕሙማን የሚገኙበት ከሰሐራ በስተ ደቡብ የሚገኘው የአፍሪካ አህጉር ሲሆን 6.5 ሚሊዮን ሕመምተኞች የሚገኙበት የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ እስያ አካባቢ በሁለተኝነት ይከተላል። “በመላው ዓለም በየዓመቱ በኤች አይ ቪ ቫይረስ ከሚያዙ አዳዲስ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ” መሆናቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
እንቅልፍ ማጣት ያፈዘዛቸው ወጣቶች
ኤቢሲ የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ “እንቅልፍ መተኛት ጊዜ እንደማባከን መታየት ጀምሯል” ሲል ዘግቧል። “ትናንሽ ልጆች እንኳን ለጥሩ አእምሯዊና አካላዊ እድገት የሚያስፈልጋቸውን ያህል አይተኙም።” በባርሴሎና የሚገኘው የዴክስዮስ ሆስፒታል የእንቅልፍ ክፍል እንደሚለው ሕፃናት በቂ እንቅልፍ
ሳያገኙ ሲቀሩ ነጭናጫ ይሆናሉ፣ የትምህርት ቤት ውጤታቸው ይቀንሳል፣ ቅስማቸው ይሰበራል አልፎ ተርፎም እድገታቸው ይቀጭጫል። ብዙ ወጣቶች እንቅልፍ የሚያጡት ከመተኛታቸው በፊት ሞባይል ስልክና ኮምፒውተር ስለሚጠቀሙ፣ ቴሌቪዥን ስለሚያዩ እንዲሁም የቪዲዮ ጨዋታዎች ስለሚጫወቱ እንደሆነ ሊቃውንቱ ይናገራሉ። እነዚህ መሣሪያዎች እንቅልፍ ማሳጣት ብቻ ሳይሆን ሰዎች እንቅልፍ እንዲወስዳቸው የሚያስፈልጋቸውን ዘና የማለት ስሜትም ያጠፋሉ። “ማጨስ አደገኛ እንደሆነ ሁሉም ልጅ ያውቃል። በቂ እንቅልፍ እንደሚያስፈልጋቸው ግን ማንም ሰው አይነግራቸውም” ይላሉ የሥነ ልቦና ሊቅ የሆኑት ቪክቶሪያ ደ ላ ፉዌንቴ። “ቶሎ ብለን እርምጃ ካልወሰድን በሚያድጉበት ጊዜ እንቅልፍ የማጣት ችግር ይጠብቃቸዋል።”የዛፍ ርዝመት ጣሪያ
“በምድር ላይ ካሉት ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ በቁመቱ የአንደኝነትን ደረጃ የያዘው ሬድዉድ የተባለው ዛፍ ቢሆንም ይህ ዛፍ ምንም ዓይነት አመቺ ሁኔታ ቢፈጠርለትም ሊታለፍ የማይቻል የቁመት ዳርቻ ላይ እየደረሰ ነው” ይላል ላስ ቬጋስ ሪቪው ጆርናል የተባለው ጋዜጣ። ባሁኑ ጊዜ በቁመቱ አንደኛ በሆነው (110 ሜትር ወይም የ30 ፎቅ ቁመት ያለው ነው) ዛፍና ጓደኞቹ በሆኑ አራት ሌሎች ዛፎች ላይ የተደረገ ጥናት የሬድዉድ ቁመት ከ130 ሜትር ሊያልፍ እንደማይችል አረጋግጧል። በቅጠሎቹ በኩል የሚተነውን እርጥበት የሚተካው ውኃ ከሥሮቹ ተስቦና የስበትን ኃይል ተቋቁሞ እስከ ዛፉ ጫፍ መድረስ ይኖርበታል። ይህ እንቅስቃሴ እስከ 24 ቀን ሊፈጅ እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ይገምታሉ። ውኃው ዛይለም በሚባሉት በዛፎቹ ውስጥ በሚገኙ ቱቦዎች ተስቦ በሚወጣበት ጊዜ የውኃው ክብደት እየጨመረ ስለሚሄድ ሊወጣ ከማይችልበት ቁመት ላይ ስለሚደርስ የዛፉ ቁመት በዚያው ተወስኖ ይቀራል። እስከዛሬ በቁመቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ዳግለስ ፈር የተባለው ዛፍ ከፍታው 126 ሜትር ነው።
የሙስሊምን የጸሎት ሰዓት የሚያስታውቅ ስልክ
ለሙስሊሞች የተሠራ አዲስ ዓይነት ሞባይል ስልክ ገበያ ላይ ውሏል። ዲ ሳይት የተባለው የጀርመንኛ ጋዜጣ እንዳለው ስልኩ ሙሉው ቁርዓን የተቀረጸበት ከመሆኑም በላይ ምዕመናኑን በቀን አምስት ጊዜ ለጸሎት ይቀሰቅሳል። እንዲያውም 5,000 ከሚያክሉ የዓለም ከተሞች መካ የምትገኝበትን አቅጣጫ ይጠቁማል። የጎርጎርዮስን አቆጣጠር ወይም እስላማዊውን የሂጅሪ አቆጣጠር የሚያሳይ የቀን መቁጠሪያም አለው። የስልኩ ዋጋ የማይቀመስ ቢሆንም ከዋነኞቹ የእስልምና ትምህርት ማዕከላት የአንዱን ድጋፍ እንዳገኘ ተነግሮለታል።
ምድር እየጨለመች በመሄድ ላይ ነች
“ሳይንቲስቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ምድር ገጽ የሚደርሰው የፀሐይ ብርሃን መጠን እየቀነሰ መምጣቱን እንደደረሱበት” ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት ዘግቧል። “ፀሐይ የምትፈነጥቀው ብርሃን እየቀነሰ ስለመጣ ሳይሆን ደመና፣ የአየር ብክለት፣ ጭስና ጭጋግ አግዶ ስለሚያስቀረው ነው።” ከ1950 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ወደ ምድር የሚደርሰው ብርሃን መጠን 10 በመቶ እንደቀነሰ በበርካታ መሣሪያዎች ተጠቁሟል። ይህ ሁኔታ ተባብሶ የሚገኘው በእስያ፣ በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ ነው። ለምሳሌ በሆንግ ኮንግ የፀሐይ ብርሃን በ37 በመቶ ቀንሷል። የችግሩ ምንነት አሁንም ሙሉ በሙሉ እንዳልታወቀ ሳይንቲስቶች ይስማማሉ።