በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሁሉም ዓይነት የኃይል ምንጮች ፈጣሪ ማን ነው?

የሁሉም ዓይነት የኃይል ምንጮች ፈጣሪ ማን ነው?

የሁሉም ዓይነት የኃይል ምንጮች ፈጣሪ ማን ነው?

ዋነኛዋ የምድራችን የኃይል ምንጭ ፀሐይ ነች። በርካታ ሳይንቲስቶች የድንጋይ ከሰልና ነዳጅ ዘይት ከፀሐይ ኃይል ያገኙ ዛፎችና ዕፅዋት ብስባሽ ውጤቶች እንደሆኑ ያምናሉ። * ለኃይል ማመንጫነት ወደ ግድቦች የሚፈሰው ውኃ ከውቅያኖሶች ተንኖ በዝናብ መልክ ወደ ምድር የወረደው ከፀሐይ በተገኘ ሙቀት ነው። በተጨማሪም በነፋስ የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን የሚያንቀሳቅሰው ነፋስ የሚገኘው አየሩን ከሚያሞቀው የፀሐይ ጨረር ነው። ይሁን እንጂ ፀሐይ ከምታመነጨው ጠቅላላ ኃይል ወደ ምድር የሚደርሰው ግማሽ ቢሊዮንኛው ብቻ እንደሆነ ይገመታል።

ፀሐይ በመባል የምትታወቀው ኮከብ ያላት ኃይል በጣም የሚያስደንቅ ቢሆንም በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙ ተመሳሳይ ኃይል ከሚያመነጩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ግዙፍ ከዋክብት መካከል አንዷ ብቻ ናት። የእነዚህ ሁሉ የኃይል ምንጮች ፈጣሪ ማን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ኢሳይያስ ስለ ከዋክብት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።”—ኢሳይያስ 40:26

የከዋክብት ኃይል ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነና ከዚያ ይበልጥ ደግሞ የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው ለማሰብ ስንሞክር በአድናቆት መዋጣችን አይቀርም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ያበረታታናል። (ያዕቆብ 4:8) አዎ፣ የምድራችንና በጣም ብዙ የሆኑት የምድር የኃይል ምንጮች ፈጣሪ፣ ለእኛም የሕይወት እስትንፋስ የሰጠን አምላክ ለሚፈልጉት ሁሉ ይገኛል።—ዘፍጥረት 2:7፤ መዝሙር 36:9

አንዳንድ ሰዎች ምድርና የምድር ንብረቶች ሲበከሉና አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውሉ ሲመለከቱ አምላክ ለምድርም ሆነ በምድር ላይ ለሚኖሩት ሰዎች ያስባል ብለው ለማመን ይቸገራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ የምድርን አስተዳደርና የዓለም የተፈጥሮ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ በተመለከተ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚመጣ ያረጋግጥልናል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋ አምላክ በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራ አንድ ዓለም አቀፍ መንግሥት በሰማይ በማቋቋም በምድር የሚኖር ሰው ሁሉ ከምድር በርካታ ሀብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል። (ሚክያስ 4:2-4) በተጨማሪም ምድርን በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ የሚያጠፉትን ያጠፋል።—ራእይ 11:18

በዚያ ጊዜ በኢሳይያስ 40:29-31 ላይ የሚገኘው ተስፋ በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኛል:- “ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።” አንተም ጊዜ ወስደህ መጽሐፍ ቅዱስን ብታጠና የኃይል ሁሉ ምንጭ ስለሆነው አምላክና እርሱ ለምድራችን የኃይል አቅርቦት ችግር ስለሚያመጣው መፍትሄ ይበልጥ ለማወቅ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በኅዳር 8, 2003 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ነዳጅ ዘይት እንዴት ተገኘ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።