በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትነዳው ቀኝህን ይዘህ ነው ወይስ ግራህን?

የምትነዳው ቀኝህን ይዘህ ነው ወይስ ግራህን?

የምትነዳው ቀኝህን ይዘህ ነው ወይስ ግራህን?

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ከአሜሪካ የመጣ እንግዳዬን በአውሮፕላን ማረፊያ ተገኝቼ ከተቀበልኩ በኋላ መኪናዬን ወዳቆምኩበት ሄድን። ከዚያም “ጋቢና ግባ” ስለው በሹፌሩ በኩል ለመግባት ሞከረና “አይ፣ ረስቼው እኮ ነው” አለ። በመቀጠልም “እዚህ አገር ደግሞ የምትነዱት የተሳሳተ አቅጣጫ ይዛችሁ ነው” አለኝ።

እርግጥ ነው፣ እኔም ዩናይትድ ስቴትስ ሄጄ ቢሆን ኖሮ ተመሳሳይ አስተያየት እሰጥ ይሆናል። ሆኖም ወደ ቤት እየሄድን ሳለ አብዛኛው ዓለም በቀኝ በኩል ሲነዳ አንዳንድ አገሮች በግራ በኩል የሚነዱት ለምን እንደሆነ ማወቅ አለብኝ ብዬ አሰብኩ።

ጥንት የነበረው የአነዳድ ልማድ

እስቲ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ብሪታንያ በሮማውያን ቁጥጥር ሥር ወደነበረችበት ዘመን መለስ እንበል። አርኪኦሎጂስቶች በዚያ ዘመን ስለነበረው የአነዳድ ልማድ አንድ ፍንጭ የሚሰጥ መረጃ በቁፋሮ አግኝተዋል። እነዚህ አጥኚዎች በ1998 እንግሊዝ፣ ስዊንደን ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ የሮማውያን ካባ የሚወስድ መንገድ አግኝተዋል። መንገዱ በአንድ በኩል ጎድጎድ ያለ ሲሆን በሌላ በኩል ግን ደህና ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ሠረገላዎቹ ባዷቸውን ወደ ካባው የሚገቡበት መሥመርና ድንጋይ ተጭነው ሲወጡ የሚመለሱበት መሥመር ስለሚለያይ ይሆናል። ከመንገዱ ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው ሮማውያን ቢያንስ በዚህ መንገድ ላይ የሚነዱት ግራቸውን ይዘው ነበር።

እንዲያውም አንዳንዶች በጥንት ዘመን በፈረስ የሚጓዙ መንገደኞች በአብዛኛው ግራቸውን ይዘው ይሄዱ እንደነበር ይገምታሉ። ይህም አብዛኞቹ ሰዎች ግራኝ ስላልሆኑ በግራ እጃቸው የፈረሱን ልጓም ለመያዝና በቀኝ እጃቸው እንደልብ ሌሎች መንገደኞችን ሰላም ለማለት ወይም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በሰይፍ ራሳቸውን ለመከላከል ያስችላቸዋል።

ወደ ቀኝ ተለወጠ

በ17ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ከግራ በኩል ወደ ቀኝ ለውጥ የተደረገው እንደ ዩናይትድ ስቴትስ በመሳሰሉ አገሮች በበርካታ ጥንድ ፈረሶች የሚጎተቱ ረጃጅም የዕቃ ማጓጓዣ ሠረገላዎች ጥቅም ላይ መዋል ሲጀምሩ ነው። ሠረገላዎቹ የነጂ መቀመጫ አልነበራቸውም፤ ስለሆነም ነጂው በስተ ግራ በኩል ከኋላ የመጨረሻው ፈረስ ላይ ተቀምጦ ጅራፉን በቀኝ እጁ ይይዛል። ነጂው በግራ በኩል መቀመጡን የሚመርጠው ሌሎች ሠረገላዎች በስተ ግራ በኩል በሚያልፉበት ጊዜ ጎማዎቻቸው ከእሱ ሠረገላ ጎማዎች ጋር ምንም ሳይነካኩ እንዲያልፉ ማድረግ ስለሚያስችለው ነው። ይህንንም የሚያደርገው ቀኙን ይዞ በመንዳት ነው።

ሆኖም እንግሊዞች ግራቸውን ይዘው መንዳታቸውን ቀጠሉበት። ሠረገላዎቻቸው አነስ ያሉ ከመሆናቸውም በላይ ነጂው እዚያው ሠረገላው ላይ በስተ ቀኝ በኩል ከፊት ተቀምጦ ይነዳ ነበር። እዚያ ሆኖ ከኋላ የሚጎተተው ሠረገላ ላይ እንዳይጠመጠምበት እየተጠነቀቀ ረጅም ጅራፉን እንደ ልብ በቀኝ እጁ ይጠቀም ነበር። እንዲሁም የራሱን ሠረገላ ወደ ግራ በማድላት ከሌሎች ሠረገላዎች ጋር ሳይነካካ በቀላሉ መተላለፉን መቆጣጠር ይችላል። ድንበር አቋርጦ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚዘልቅ መንገድ ለመሥራት ስትል ከግራ ወደ ቀኝ እንደቀየረችው እንደ ካናዳ ካሉ አንዳንድ አገሮች በስተቀር በብሪታንያ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች በሙሉ ከእንግሊዞች የወረሱትን በግራ በኩል የመንዳት ልማድ እንደያዙ ቀርተዋል።

በፈረንሳይ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በአነዳድ ልማድ ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በ1789 ከፈነዳው አብዮት በፊት መኳንንቱ ጭሰኞቹን በቀኝ በኩል እንዲነዱ በማስገደድ እነሱ ሠረገላዎቻቸውን በግራ በኩል ይነዱ ነበር። አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ግን እነዚህ መኳንንት ራሳቸውን ለመደበቅ ሲሉ በቀኝ በኩል ከጭሰኞቹ ጋር ተቀላቅለው መንዳት ጀመሩ። በ1794 የፈረንሳይ መንግሥት ማንኛውም ሰው በፓሪስ ውስጥ በቀኝ በኩል እንዲነዳ የሚያዝ ሕግ አወጣ። ከጊዜ በኋላ ይህ ሕግ ናፖሊዮን ድል አድርጎ በያዛቸው አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች ተስፋፋ። ናፖሊዮን በቀኝ በኩል የመንዳት ልምድ እንዲቀጥል መምረጡ ምንም አያስደንቅም። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚናገረው ናፖሊዮን ግራኝ ስለነበረ “ሰይፉን ጠላት ሊመጣ በሚችልበት በኩል መያዝ እንዲመቸው ሠራዊቱ ቀኙን ይዞ መሄድ ነበረበት።”

ናፖሊዮን ድል ያላደረጋቸው የአውሮፓ አገሮች በግራ በኩል የመንዳት ልማድ እንዲቀጥል አድርገዋል። ሩሲያና ፖርቱጋል በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የአነዳድ ልማዳቸውን ከግራ ወደ ቀኝ ለወጡ። ኦስትሪያና ቼኮዝሎቫኪያ በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ በናዚ ጀርመን እጅ ሲወድቁ የአነዳድ ልማዳቸውን ወደ ቀኝ የቀየሩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሃንጋሪም የእነሱን ፈለግ ተከትላለች። በዛሬው ጊዜ በግራ የሚነዱት የአውሮፓ አገሮች አራት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ብሪታንያ፣ አየርላንድ፣ ቆጵሮስና ማልታ ናቸው። የሚያስገርመው ጃፓን የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሆና ባታውቅም እንኳ በግራ በኩል የመንዳት ልማድ ትከተላለች።

መርከቦች፣ አውሮፕላኖች፣ ባቡሮችና እግረኞች

ስለ መርከቦችና አውሮፕላኖችስ ምን ለማለት ይቻላል? በአጠቃላይ ሲታይ የባሕር ላይ ሕግ ቀኝን ይዞ መንዳትን ያዛል። አውሮፕላኖችም ቀኛቸውን ይዘው ይተላለፋሉ። ባቡሮችስ? በአንዳንድ አገሮች ሁለት የሐዲድ መሥመር በሚኖርበት ጊዜ ባቡሩ የትኛውን መሥመር መከተል እንዳለበት የሚወስኑት ምልክቶቹ ናቸው። በዘመናዊዎቹ የባቡር መሥመሮች ላይ ያሉት ምልክቶች በአብዛኛው ባቡሩ በፈለገው አቅጣጫ እንዲሄድ የሚፈቅዱ ሲሆኑ የድሮዎቹ ግን ባቡሩ አንዱን አቅጣጫ ብቻ ተከትሎ እንዲሄድ የሚያስገድዱ ናቸው። በአብዛኛው ባቡር የትኛውን አቅጣጫ ተከትሎ መጓዝ እንዳለበት የወሰኑት መሥመሩን የዘረጉት አገሮች ናቸው።

እግረኞችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ራሱን የቻለ የእግረኛ መንገድ ከሌለ መኪኖች ቀኛቸውንም ይያዙ ግራቸውን እግረኞች መኪና ከፊት ለፊት በሚመጣበት አቅጣጫ ቢጓዙ የተሻለ ነው። መኪኖች ቀኛቸውን ይዘው የሚጓዙ ከሆነ እግረኞች መኪና ከፊት ለፊት በሚመጣበት አቅጣጫ ግራቸውን ይዘው ቢሄዱ ይመረጣል። መኪና በግራ በኩል በሚነዳበት በብሪታንያ እግረኞች በተቻለ መጠን ቀኛችንን ይዘን ለመጓዝ እንሞክራለን። ከአሜሪካ የመጣው እንግዳዬስ የሚጓዘው የትኛውን አቅጣጫ ይዞ ነው? እንደለመደው ግራውን ይዞ ነዋ!