በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሥርዓተ ፀሐይን ምስጢር የፈታ ሰው

የሥርዓተ ፀሐይን ምስጢር የፈታ ሰው

የሥርዓተ ፀሐይን ምስጢር የፈታ ሰው

በጀርመን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን የኖሩ አውሮፓውያን ጅራታም ተወርዋሪ ከዋክብትን በታላቅ አድናቆት ይመለከቱ ነበር። በዚህም የተነሣ ታይኮ ብራኸ የተባለው የዴንማርክ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ለዓለም ያስተዋወቃት ተወርዋሪ ኮከብ በታየች ጊዜ ካታሪና ኬፕለር የስድስት ዓመት ልጇን ዮሐንስ ኬፕለርን ከእንቅልፉ ቀስቅሳ አሳየችው። ከሃያ ዓመት በኋላ ብራኸ ሲሞት ዳግማዊ ሩዶልፍ በምትኩ የቤተ መንግሥቱ የሂሣብ ሊቅ አድርጎ የሾመው ማንን ነበር? ዮሐንስ ኬፕለር በ29 ዓመቱ የቅድስቲቱ ሮማ ንጉሠ ነገሥት ቤተ መንግሥት ዋነኛ የሂሣብ ሊቅ ሆኖ የተሾመ ሲሆን ዕድሜውን በሙሉ በዚህ ሥልጣን ላይ ቆይቷል።

ኬፕለር ከፍተኛ ዝና ያገኘው በሂሣብ ሊቅነቱ ብቻ አልነበረም። በሥነ ብርሃንና በሥነ ፈለክ የሳይንስ መስክም ከፍተኛ እውቅና አትርፏል። አጭር የነበረው ኬፕለር በጣም አስደናቂ የማሰብ ችሎታና የዓላማ ጽናት ነበረው። ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢደረግበትም እንኳ ወደ ሮማ ካቶሊክ እምነት ለመለወጥ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ መድልዎ ይፈጸምበት ነበር።

የሂሣብ ሊቅ

ዮሐንስ ኬፕለር በ1571 በጀርመን ጥቁር ደን ዳርቻ በምትገኝ ቫይል ደር ሽታት የምትባል አነስተኛ ከተማ ተወለደ። ቤተሰቦቹ ድሆች ቢሆኑም የአካባቢው ባላባቶች በሰጡት የነጻ ትምህርት ዕድል በመጠቀም ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ቻለ። የሉተራን እምነት ቄስ የመሆን እቅድ ስለነበረው በቱበንገን ዩኒቨርሲቲ የሥነ መለኮት ትምህርት ተከታትሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይበልጥ ጎልቶ የወጣው የላቀ የሂሣብ ችሎታው ነበር። በኦስትሪያ፣ ግራትስ በሚገኝ የሉተራን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረ አንድ የሂሣብ መምህር በ1594 ሲሞት ኬፕለር በእግሩ እንዲተካ ተደረገ። እዚያ እያለ ከዋነኛ ሥራዎቹ የመጀመሪያ የሆነውን ኮስሞግራፊክ ሚስትሪ የተባለ መጽሐፍ አሳተመ።

የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የነበረው ብራኸ ለበርካታ ዓመታት የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይመዘግብ ነበር። ኮስሞግራፊክ ሚስትሪ የተባለውን መጽሐፍ ባነበበ ጊዜ በኬፕለር የሂሣብና የሥነ ፈለክ እውቀት በጣም ስለተደነቀ በአሁኑ ጊዜ በቼክ ሪፑብሊክ በሚገኘው በቤናትኪ ከተማ አብሮት እንዲሠራ ጋበዘው። ኬፕለር ይደርስበት በነበረው ሃይማኖታዊ ጥላቻ ምክንያት ግራትስን ለቅቆ ለመውጣት በተገደደበት ወቅት ግብዣውን ተቀበለ። ከዚያም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ብራኸ ሲሞት ኬፕለር በቦታው ተተካ። የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ጥንቁቅና አስተዋይ በሆነው አጥኚ ምትክ የሂሣብ ሊቅ አገኘ።

በሥነ ብርሃን ረገድ የተገኘ ከፍተኛ እድገት

ኬፕለር፣ ብራኸ የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ በሚመለከት የደረሰባቸውን ግኝቶች በተሟላ ሁኔታ ለመጠቀም ስለ ብርሃን ጨረር ባሕርይ በሚገባ መረዳት እንደሚያስፈልገው ተገነዘበ። ከአንድ ፕላኔት የተንጸባረቀ የብርሃን ጨረር ወደ ምድር ከባቢ አየር ሲገባ የሚታጠፈው እንዴት ነው? የኬፕለር ማብራሪያ ቪታሎ የተባለውን የመካከለኛው ዘመን ሳይንቲስት ሥራ በሚተነትነው ሳፕሊመንት ቱ ቪታሎ፣ ኤክስፓውንዲንግ ዚ ኦፕቲካል ፓርት ኦቭ አስትሮኖሚ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ተካቷል። የኬፕለር መጽሐፍ በሥነ ብርሃን ሳይንስ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር። ስለ ዓይን አሠራር ለመግለጽ የመጀመሪያው ሰው ሆነ።

ይሁን እንጂ የኬፕለር ዋነኛ ትኩረት ሥነ ብርሃን ሳይሆን ሥነ ፈለክ ነበር። ቀደምት የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ጠፈር ልክ እንደ ቱቦ እንደሆነና ከዋክብትም በውስጠኛው ክፍል ላይ እንደ አብረቅራቂ የአልማዝ ፈርጦች ተሰክተው እንደሚገኙ ያምኑ ነበር። ቶለሚ ምድር የጽንፈ ዓለሙ እምብርት ናት የሚል አመለካከት የነበረው ሲሆን ኮፐርኒከስ ደግሞ ፕላኔቶች በሙሉ በማትንቀሳቀስ ፀሐይ ዙሪያ እንደሚሽከረከሩ ያምን ነበር። ብራኸ ሌሎች ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ ሲዞሩ ፀሐይ ራሷ ደግሞ በምድር ዙሪያ እንደምትዞር ተናግሮ ነበር። ሌሎቹ ፕላኔቶች በሙሉ ከምድር አንጻር ሲታዩ የሰማይ አካላት በመሆናቸው ፍጹማን ተደርገው ይታዩ ነበር። የእነዚህ የሰማይ አካላት ምሕዋር ፍጹም ክብ እንደሆነና የእያንዳንዳቸውም ፍጥነት የማይለዋወጥ እንደሆነ ተደርጎም ይታመን ነበር። ኬፕለር የቤተ መንግሥት የሂሣብ ሊቅነት ሥራውን የተረከበው እንዲህ ያለ አስተሳሰብ በሰፈነበት ዘመን ነበር።

የዘመናዊው ሥነ ፈለክ አጀማመር

ኬፕለር ብራኸ ያቆየለትን የፕላኔቶች እንቅስቃሴ ሠንጠረዥ በመጠቀም የጠፈር አካላትን እንቅስቃሴ ያጠና ሲሆን በመጨረሻም ተከታትሎ በተመለከታቸው ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ድምዳሜ ላይ ደረሰ። ከነበረው ላቅ ያለ የሂሣብ ችሎታ በተጨማሪ ቆራጥነትና ከፍተኛ የማወቅ ፍላጎት ነበረው። ደከመኝን የማያውቅ ሰው ስለነበረ የማርስን የእንቅስቃሴ ሠንጠረዥ ከመረመረ በኋላ 7,200 የሚያክሉ የተወሳሰቡ ስሌቶችን ሠርቶ አጠናቋል።

የኬፕለርን ትኩረት በመጀመሪያ የሳበችው ማርስ ነበረች። ሠንጠረዦቹን በጥንቃቄ ካጠና በኋላ ማርስ በፀሐይ ዙሪያ እንደምትዞርና የምትከተለው ምሕዋር ትክክለኛ ክብ እንዳልሆነ ተረዳ። ከተመለከተውና ካስተዋለው ሁኔታ በመነሳት ፀሐይን እንደ አንድ ማዕከል ያደረገችው ማርስ የምሕዋርዋ ቅርጽ ሞላላ መሆኑን ተገነዘበ። ይሁን እንጂ ኬፕለር የጠፈር አካላትን ምስጢር ለመፍታት ቁልፉ ማርስ ሳትሆን ምድር እንደሆነች ተሰማው። ፕሮፌሰር ማክስ ካስፓር እንደሚሉት “የኬፕለር የፈጠራ ችሎታ ተሞክሮ የማያውቅ አዲስ አቅጣጫ እንዲከተል አነሳሳው።” ሠንጠረዦቹን ከዚህ በፊት ተሞክሮ ለማያውቅ አዲስ ግልጋሎት አዋላቸው። ሠንጠረዦቹን ተጠቅሞ ማርስን ከመመርመር ይልቅ ራሱን ማርስ ላይ እንዳለ አድርጎ በማሰብ ምድርን ለመመርመር ተጠቀመበት። በፀሐይና በምድር መካከል የሚገኘው ርቀት እየቀነሰ በሄደ መጠን ምድር ፀሐይን የምትዞርበት ፍጥነት እንደሚጨምር በስሌት ደረሰበት።

በዚህ ጊዜ ኬፕለር ፀሐይ የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ብቻ እንዳልሆነች ተገነዘበ። ፀሐይ በራስዋ ዛቢያ ላይ እየተሽከረከረች ባላት የስበት ኃይል የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ ትቆጣጠራለች። ካስፓር “ከዚያ በኋላ ላደረገው ምርምርና ለደረሰባቸው ሕግጋት እንደ መመሪያ ሆኖ ያገለገለው ይህ ጽንሰ ሐሳብ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ለኬፕለር ፕላኔቶች አንድ ወጥ በሆኑ ሕግጋት የሚመሩ ግዑዝ አካላት ነበሩ። ስለ ማርስና ስለ ምድር ያወቃቸው ሁኔታዎች በሌሎቹ ፕላኔቶችም ላይ እኩል ተፈጻሚነት ሊኖራቸው ይገባል። በዚህም የተነሳ እያንዳንዱ ፕላኔት የእንቁላል ቅርጽ ያለውን ምሕዋር ተከትሎ ከፀሐይ በሚኖረው ርቀት መጠን በሚለዋወጥ ፍጥነት በፀሐይ ዙሪያ እንደሚዞር አረጋገጠ።

የኬፕለር የፕላኔቶች እንቅስቃሴ ሕግጋት

ኬፕለር በ1609 ኒው አስትሮኖሚ የተባለ መጽሐፍ ያሳተመ ሲሆን ይህ መጽሐፍ ስለ ዘመናዊው ሥነ ፈለክ ከተጻፉት መጻሕፍት የመጀመሪያውና በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከኬፕለር የፕላኔቶች እንቅስቃሴ ሕግጋት መካከል ሁለቱ ተካትተው ነበር። ሦስተኛው ሕግ በሊንስ፣ ኦስትሪያ ይኖር በነበረበት ወቅት በ1619 ሃርሞኒስ ኦቭ ዘ ወርልድ በተባለው መጽሐፉ ላይ ታተመ። የፕላኔቶች መሠረታዊ እንቅስቃሴ ማለትም ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ የሚዞሩበት ምሕዋር ቅርጽ፣ የፕላኔቶች እንቅስቃሴ ፍጥነት እንዲሁም አንድ ፕላኔት ከፀሐይ በሚኖረው ርቀትና ዙሩን ለመጨረስ በሚወስድበት ጊዜ መካከል ያለው ዝምድና የሚመራው በእነዚህ ሦስት ሕግጋት ነው።

የኬፕለር የሥራ ባልደረባ የሆኑ ሌሎች የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንዴት ተቀበሉት? የኬፕለርን ሕግጋት ጠቀሜታ መረዳት አልቻሉም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሕግጋቱን የሚታመኑ ሆነው አላገኟቸውም። ይሁን እንጂ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የእነርሱ አልነበረም። ኬፕለር ሥራዎቹን የጻፈው በጣም አስቸጋሪ በሆነ የላቲን የአጻጻፍ ስልት ነበር። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ የኬፕለር ሥራ ጠቃሚነት እውቅና አገኘ። ከ70 ዓመት በኋላ የተነሳው አይዛክ ኒውተን የእንቅስቃሴና የስበት ሕጉን ያወጣው የኬፕለርን ሥራዎች መሠረት በማድረግ ነበር። በዛሬው ጊዜ ኬፕለር በተለያዩ ዘመናት ከተነሱት ታላላቅ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ እንዲሁም ሥነ ፈለክን በመካከለኛው ዘመን ሰፍኖ ከነበረው ጨለማ አውጥቶ ወደ ዘመናዊው ዓለም ያስገባ ሰው እንደሆነ ተደርጎ ይታመናል።

አውሮፓ በሃይማኖት ጦርነት ታመሰች

ኬፕለር ሦስተኛ ሕጉን ባወጣበት ዓመት የሠላሳው ዓመት ጦርነት ፈነዳ። በጦርነቱ ዓመታት (1618-1648) አውሮፓ በሃይማኖታዊ ግድያና ዝርፊያ የወደመች ሲሆን ጀርመን የሕዝቦቿን ሲሶ አጥታለች። አስማተኞችና ጠንቋዮች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን ማደን በጣም የተለመደ ሆኖ ነበር። የኬፕለር እናት አስማተኛ ነች ተብላ ተከስሳ ስለነበር ከመገደል ያመለጠችው ለጥቂት ነበር። ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን አልፎ አልፎ ብቻ ደመወዝ ይከፈለው የነበረው ኬፕለር በጦርነቱ ወቅት ደመወዙን ጨርሶ እስከማጣት ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል።

ሉተራን የነበረው ኬፕለር ዕድሜውን በሙሉ ከሃይማኖታዊ ስደትና ጭፍን ጥላቻ እፎይ ብሎ አያውቅም። የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ለመሆን ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከግራትስ እንዲወጣ ተገደደ። ይህም ሥራውን፣ ቤቱንና ንብረቱን እንዲያጣ ያደረገው ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ችግሮች አስከትሎበታል። በቤናትኪ ደግሞ እምነቱን እንዲለውጥ እንደገና ግፊት ተደረገበት። ኬፕለር ግን የምስሎችንና የቅዱሳንን አምልኮ መቀበል አልሆነለትም። ይህ ዓይነቱ አምልኮ ለኬፕለር የዲያብሎስ ሥራ ነበር። በሊንስ አምላክ በሁሉም ቦታ ይኖራል ብለው ያምኑ ከነበሩ ሌሎች ሉተራኖች ጋር በመጋጨቱ በጌታ እራት በዓላቸው ላይ እንዳይገኝ ታገደ። (የሚያዝያ 2005 ንቁ! ገጽ 20, 21ን ተመልከት።) በፕላኔቶች መካከል የሚታየው ስምምነት በሰው ልጆች መካከልም መኖር አለበት ብሎ ያምን ለነበረው ኬፕለር ሃይማኖታዊ ጥላቻና አለመቻቻል እጅግ አስነዋሪ ነገር እንደሆነ ይሰማው ነበር። እምነቱን የሙጥኝ ብሎ በመያዝ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነ። ኬፕለር “ከቤት፣ ከእርሻ፣ ከአገርና ከወዳጆች ተለይቶ በመሰደድ ለሃይማኖት ብሎም ለክርስቶስ ክብር ከብዙ ወንድሞች ጋር መከራና ሥቃይ መቀበል ይህን ያህል የሚያረካ ነገር ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር” ሲል ጽፎአል።—ዮሃንስ ኬፕለር፣ በኧርንስት ዚነር

በ1627 ዋነኛ የሥነ ፈለክ ሥራው እንደሆነ የሚናገርለትን ሩዶልፊን ቴብልስ የተባለ መጽሐፍ አሳተመ። ይህ መጽሐፍ ከዚያ ቀደም ካሳተማቸው መጻሕፍቱ በተለየ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ባሕረኞችና የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ይጠቀሙበት ጀመር። በመጨረሻም ኬፕለር በ1630 በሬጌንስበርግ፣ ጀርመን ሞተ። አንድ የኬፕለር የሥራ ባልደረባ “ጠንካራ መሠረት ያለው ትምህርት፣ በጣም ጥልቅ ስለሆኑ ምስጢሮች የጠለቀ እውቀት” የነበረው ሰው እንደሆነ ተናግሮለታል። እነዚህ የአድናቆት ቃላት የሥርዓተ ፀሐይን ምስጢር ለፈታ ሰው የሚበዙ አይሆኑም።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኬፕለር በዘመናት ከተነሱት ታላላቅ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ እንዲሁም ሥነ ፈለክን በመካከለኛው ዘመን ሰፍኖ ከነበረው ጨለማ አውጥቶ ወደ ዘመናዊው ዓለም ያስገባ ሰው እንደሆነ ተደርጎ ይታመናል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በፕላኔቶች መካከል የሚታየው ስምምነት በሰው ልጆች መካከልም መኖር አለበት ብሎ ያምን ለነበረው ለኬፕለር ሃይማኖታዊ ጥላቻና አለመቻቻል እጅግ አስነዋሪ ነገር እንደሆነ ይሰማው ነበር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሳጥን]

የኬፕለር የከዋክብት ጥናትና ሃይማኖታዊ አመለካከት

ዮሐንስ ኬፕለር በሥነ ፈለክ መስክ በደረሰባቸው አንዳንድ ግኝቶች እውቅና ያተረፈ ቢሆንም በዘመኑ የነበረው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደነበረ ልብ ሊባል ይገባል። “ከዋክብት በሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ የሚለውን አስተሳሰብ በአብዛኛው” ይቃወም የነበረ ቢሆንም ስለ ከዋክብት ጥናት በሰፊው ጽፏል።

በተጨማሪም ሕዝበ ክርስትና በምታስተምረው የሥላሴ ትምህርት ላይ ጽኑ እምነት ነበረው። “(አብ::ማዕከል፤ ወልድ::የክበቡ ዙሪያ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በመሃል ያለውን ቦታ የሚሞላ ነው) በሚለው . . . መለኮታዊ ምስጢር በጥብቅ ያምን ነበር።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ

በአንጻሩ ደግሞ አይዛክ ኒውተን ስለ ሥላሴ ትምህርት ምን አመለካከት ነበረው? በሥላሴ ትምህርት አያምንም ነበር። ይህን ትምህርት ያልተቀበለበት ዋነኛው ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት ስለ ሥላሴ የሚያስተምሩትን ትምህርት የሚደግፍ ሐሳብ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ አለማግኘቱ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ሉዓላዊ አምላክ እንደሆነና ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሉት መሠረት ከአባቱ ያነሰ እንደሆነ ያምን ነበር። *1 ቆሮንቶስ 15:28

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.30 የሚያዝያ 15, 1977 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 244-247 ተመልከት።

[በገጽ 16-18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የኬፕለር የፕላኔቶች እንቅስቃሴ ሕግጋት

የኬፕለር የፕላኔቶች እንቅስቃሴ ሕግጋት ለዘመናዊው ሥነ ፈለክ መሠረት እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። እነዚህን ሕግጋት እንደሚከተለው በማለት ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል:-

1 እያንዳንዱ ፕላኔት ሞላላ ቅርጽ ያለውን ምሕዋር ተከትሎ ፀሐይን እንደ አንድ እምብርት በማድረግ በዙሪያዋ ይሽከረከራል

← ፀሐይ ←

↓ ↑

↓ ↑

ፕላኔት ● ↑

→ → →

2 እያንዳንዱ ፕላኔት ወደ ፀሐይ በቀረበ መጠን ፍጥነቱ ይጨምራል። አንድ ፕላኔት ለፀሐይ ቅርብም ይሁን ሩቅ በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚሸፍነው ስፋት ምንጊዜም እኩል ነው

የፕላኔቱ ፍጥነት ይጨምራል

የፕላኔቱ ፍጥነት ይቀንሳል

ሀ ● ለ

↓ ↑

↓ Sun

● ለ

● ለ

በመሆኑም፣ እዚህ ላይ በቀረበው በእያንዳንዱ ምሳሌ ላይ ፕላኔቱ ከሀ ተነስቶ እስከ ለመድረስ የሚወስድበት ጊዜ እኩል እስከሆነ ድረስ የሚሸፍነው ስፋትም እኩል ነው

3 እያንዳንዱ ፕላኔት ምሕዋሩን ተከትሎ ፀሐይን አንዴ ለመዞር የሚፈጅበት ጊዜ የፕላኔቱ ፔሬድ ይባላል። ይህ ፔሬድ እርስ በርሱ ሲባዛ የሚኖረው ውጤት ፕላኔቱ ከፀሐይ ያለው አማካይ ርቀት ሦስት ጊዜ እርስ በርሱ ሲባዛ ከሚኖረው ውጤት ጋር እኩል ነው

[ግራፍ/ሰንጠረዥ]

ፕላኔት ሜርኩሪ

ከፀሐይ ያለው ርቀት * 0.387

በዓመት የሚፈጅበት ፔሬድ 0.241

ፔሬድ2 0.058 *

ርቀት3 0.058 *

ፕላኔት ቬነስ

ከፀሐይ ያለው ርቀት 0.723

በዓመት የሚፈጅበት ፔሬድ 0.615

ፔሬድ2 0.378

ርቀት3 0.378

ፕላኔት ምድር

ከፀሐይ ያለው ርቀት 1

በዓመት የሚፈጅበት ፔሬድ 1

ፔሬድ2 1

ርቀት3 1

ፕላኔት ማርስ

ከፀሐይ ያለው ርቀት 1.524

በዓመት የሚፈጅበት ፔሬድ 1.881

ፔሬድ2 3.538

ርቀት3 3.540

ፕላኔት ጁፒተር

ከፀሐይ ያለው ርቀት 5.203

በዓመት የሚፈጅበት ፔሬድ 11.862

ፔሬድ2 140.707

ርቀት3 140.851

ፕላኔት ሳተርን

ከፀሐይ ያለው ርቀት 9.539

በዓመት የሚፈጅበት ፔሬድ 29.458

ፔሬድ2 867.774

ርቀት3 867.977

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.61 አንጻራዊው ርቀት ከምድር ርቀት ጋር ሲወዳደር። ለምሳሌ ያህል፣ ማርስ ከፀሐይ ያለው ርቀት 1.524 ሲባዛ በምድር ርቀት ያህል ነው።

^ አን.63 በዚህ ሠንጠረዥ ላይ እንደምትመለከተው የእያንዳንዱ ፕላኔት እነዚህ ሁለት ቁጥሮች እኩል ናቸው ማለት ይቻላል። ፕላኔቱ ከፀሐይ ያለው ርቀት በጨመረ ቁጥር በእነዚህ ቁጥሮች መካከል የሚፈጠረው ልዩነትም እንደዚሁ ይጨምራል። ከጊዜ በኋላ አይዛክ ኒውተን ስለ ስበት ባወጣው ሕግ ላይ የእያንዳንዱን ፕላኔትና የፀሐይን ክብደት በስሌቱ ውስጥ በማካተት በኬፕለር ሕግ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጓል።

^ አን.64 በዚህ ሠንጠረዥ ላይ እንደምትመለከተው የእያንዳንዱ ፕላኔት እነዚህ ሁለት ቁጥሮች እኩል ናቸው ማለት ይቻላል። ፕላኔቱ ከፀሐይ ያለው ርቀት በጨመረ ቁጥር በእነዚህ ቁጥሮች መካከል የሚፈጠረው ልዩነትም እንደዚሁ ይጨምራል። ከጊዜ በኋላ አይዛክ ኒውተን ስለ ስበት ባወጣው ሕግ ላይ የእያንዳንዱን ፕላኔትና የፀሐይን ክብደት በስሌቱ ውስጥ በማካተት በኬፕለር ሕግ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጓል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጁፒተር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮፐርኒከስ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብራኸ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኬፕለር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒውተን

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቬነስ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኔፕቱን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኬፕለር ቴሌስኮፕና መጻሕፍት

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳተርን

[ምንጭ]

Courtesy of NASA/JPL/Caltech/USGS

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ኮፐርኒከስና ብራኸ:- Brown Brothers; ኬፕለር:- Erich Lessing/Art Resource, NY; ጁፒተር:- Courtesy of NASA/JPL/Caltech/USGS; ፕላኔት:- JPL

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ቬነስ:- Courtesy of NASA/JPL/Caltech; ፕላኔት:- JPL

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ቴሌስኮፕ:- Erich Lessing/Art Resource, NY; ኔፕቱን:- JPL; ማርስ:- NASA/JPL; ምድር:- NASA photo