የኃይል ምንጭ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የኃይል ምንጭ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ሕፃኑ ማይካ የተወለደው ነሐሴ 2003 ነበር። እናቱን ወደ ማዋለጃ ሆስፒታል በፍጥነት ያደረሳት በቤንዚን የሚንቀሳቀስ መኪና ነው። ወደዚህ ዓለም በደህና እንዲመጣ ያስቻለው ሆስፒታል የኤሌክትሪክ መብራት የሚያገኘው በድንጋይ ከሰል ከሚንቀሳቀስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ነው። የመጀመሪያ ትንፋሹን የተነፈሰበትን ክፍል ያሞቀው ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ ነው። ከእነዚህ የተለመዱ የኃይል ምንጮች መካከል አንዱ እንኳ ቢታጣ የሕፃኑ ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር።
ይህ ሕፃን የመጣበት የዚህ ዘመናዊ ዓለም ሕልውና በተለያዩ የኃይል ምንጮች ላይ የተመካ ነው። ወደየሥራ ቦታችን ለመጓጓዝ፣ ምግባችንን ለማብሰል ወይም ለቤታችን የሚያስፈልገውን መብራት ለማግኘት ይብዛም ይነስም ከከርሰ ምድር በሚወጡ የነዳጅ ዓይነቶች እንጠቀማለን። ዘ ወርልድ ሪሶርስስ ኢንስቲትዩት እንደሚለው “ከዓለም አቀፉ የኃይል ፍጆታ 90 በመቶ የሚሆነውን የምናገኘው ከከርሰ ምድር ከሚወጡ የነዳጅ ዓይነቶች ነው።” ይህ ተቋም በ2000 ባወጣው ሪፖርት “በዓለም አቀፉ የኃይል አቅርቦት ረገድ 40 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ የሚያበረክተው ነዳጅ ዘይት ሲሆን የድንጋይ ከሰል 26 በመቶ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ 24 በመቶ ድርሻ በማበርከት በሁለተኛና በሦስተኛነት ይከተላሉ” ብሏል። *
ባዮሳይንስ የተባለው መጽሔት “አንድ አሜሪካዊ ለመጓጓዣ፣ ለማሞቂያና ለማቀዝቀዣ የሚጠቀመውን ጨምሮ በዓመት በአማካይ የሚፈጀው የኃይል መጠን በሰዓት 93,000 ኪሎዋት ሲሆን ይህም ከ8,000 ሊትር ነዳጅ ዘይት ጋር እኩል ነው” ብሏል። በአውስትራሊያ፣ በቻይና፣ በፖላንድና በደቡብ አፍሪካ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው ኤሌክትሪክ የሚመነጨው በድንጋይ ከሰል ከሚንቀሳቀሱ ኃይል ማመንጫዎች ነው። ሕንድ 60 በመቶ የሚሆነውን፣ ዩናይትድ ስቴትስና ጀርመን ደግሞ ከግማሽ የሚበልጠውን የኤሌክትሪክ ፍጆታ የሚሸፍኑት ከድንጋይ ከሰል ነው።
ጀረማያ ክሪደን የተባሉ ጋዜጠኛ “ላይፍ አፍተር ኦይል” በሚል ርዕስ በቀረበ ጽሑፍ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ባሁኑ ጊዜ የዓለም የምግብ አቅርቦት በነዳጅ ዘይት ላይ የተመካ መሆኑ እምብዛም አይታወቅም። ዘመናዊው እርሻ፣ ማዳበሪያ ከማምረት አንስቶ ምርት እስከ ማጓጓዝ ድረስ ያለው እያንዳንዱ ደረጃ በነዳጅ ዘይትና በተፈጥሮ ጋዝ ላይ የተመካ ነው።” (ኡትኔ ሪደር የተባለ መጽሔት) ይሁን እንጂ የዚህ ዘመናዊ ኅብረተሰብ ደም ሥር የሆኑት እነዚህ የኃይል ምንጮች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው? ከእነዚህ የኃይል ምንጮች የተሻለና ብዙ ብክለት የማያስከትል አማራጭ ይኖር ይሆን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ስለ ነዳጅ ዘይት አጠቃቀም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 8, 2003ን ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 3-12 ተመልከት።