በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ ነው?

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ ነው?

የግሪክ ደሴት በሆነችው በቲኖስ በየዓመቱ ነሐሴ 15 ላይ ትልቅ ሃይማኖታዊ በዓል ይከበራል። የኢየሱስ እናት ለሆነችው ለማርያምና ተአምራዊ ኃይል እንዳለው ለሚታመነው ምስሏ አምልኮ ለማቅረብ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሰበሰባሉ። * አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ከሁሉም በላይ ቅድስት በሆነችው በጌታችን እናት በድንግል ማርያም ልዩ እምነት ያለን ሲሆን በጣም እናከብራታለን። እንዲሁም ጥበቃዋ፣ አፋጣኝ ከለላዋና እርዳታዋ እንዳይለየን እንለምናታለን። ድንቅ ነገሮችን የሚፈጽሙት ቅዱሳን ወንዶችና ሴቶች መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን እንዲያሟሉልን እንማጸናቸዋለን። . . . የቅዱሳኑን ምስሎችና ቅርጾችም በጥልቅ አክብሮት እንሳለማቸዋለን እንዲሁም እናመልካቸዋለን።”

ክርስቲያን ነን የሚሉ ሌሎች በርካታ ሰዎችም የምስል አምልኮ የሚካሄድባቸው ሃይማኖታዊ ቡድኖች አባላት ናቸው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ይደግፋል?

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ በአምልኮ ረገድ ለምስሎች ትልቅ ቦታ ይሰጥ የነበረበትን የአቴና ከተማ በጎበኘበት ወቅት የተከሰተውን ተመልከት። ጳውሎስ ለአቴና ሰዎች አምላክ “የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። እርሱ . . . የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም። . . . እንግዲህ . . . አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም” በማለት ነግሯቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25, 29

እርግጥ ነው፣ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ምስልን በተመለከተ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ማስጠንቀቂያዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቲያኖችን “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:21) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው?” በማለት ጽፎ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 6:16) አብዛኞቹ የጥንት ክርስቲያኖች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ሃይማኖታዊ ምስሎችን ለአምልኮ ይጠቀሙ ነበር። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖታት ወደ እግዚአብሔር . . . ተመለሳችሁ” ብሎ ሲጽፍ ያንን ማስታወሱ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 1:9) በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው እነዚህ ክርስቲያኖች ስለ ምስሎች ያላቸው አመለካከት እንደ ዮሐንስና ጳውሎስ ነበር።

“ክርስቲያኖች” ምስሎችን ተቀበሉ

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “የክርስትና እምነት ከተቋቋመ በኋላ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት . . . በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም ዓይነት የክርስትና ሥዕል ያልነበረ ከመሆኑም በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱም አጥብቃ ትቃወመው ነበር። ለምሳሌ የእስክንድሪያው ክሌመንት (የአረማውያን) ሃይማኖታዊ ሥዕሎች ሰዎች ፈጣሪን ሳይሆን ፍጡርን እንዲያመልኩ ስለሚያበረታቱ አውግዟቸዋል።”

ታዲያ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ይህን ያህል ተቀባይነት ያገኘው እንዴት ነው? ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይቀጥላል:- “በሦስተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሥዕሎች ጥቅም ላይ መዋልና ተቀባይነት ማግኘት ጀምረው የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሥዕሎች መጠቀም የተጀመረው በ4ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሮም መንግሥት በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ አገዛዝ ሥር በሆነችበት ጊዜ ነበር፤ ከዚያ ወዲህ በክርስትናው ሃይማኖት ውስጥ ተቀባይነትን አግኝቷል።”

ክርስቲያን ነን በሚሉት በብዙዎቹ አረማውያን ዘንድ የንጉሠ ነገሥቱን ምስል ለአምልኮ መጠቀም የተለመደ ነገር ነበር። ጆን ቴይለር አይከን ፔይንቲንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “ንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ ይቀርብለት ስለነበረ ሰዎች በሸራዎች ወይም በእንጨት ላይ የተሠሩ የንጉሡን ምስሎች ያመልኩ ነበር። በዚህም ምክንያት ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ብዙም አልከበዳቸውም።” በዚህ መንገድ የአረማውያን የሥዕል አምልኮ የኢየሱስን፣ የማርያምን፣ የመላእክትንና “የቅዱሳንን” ሥዕሎች በማምለክ ተተካ። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተጀመረው የምስል አምልኮ ቀስ በቀስ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ በመሄዱ በየቤቱ ይመለክ ጀመር።

“በመንፈስና በእውነት” ማምለክ

ኢየሱስ የአምላክ አገልጋዮች “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ እንዳለባቸው ለአድማጮቹ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 4:24) ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን በተመለከተ አንድ ቅን ሰው እውነቱን ለማወቅ ቢፈልግ ከአምላክ ቃል መልስ ማግኘት ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ብሏል:- “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐንስ 14:6) ጳውሎስ “አንድ እግዚአብሔር አለና፤ ደግሞም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አንድ አስታራቂ [“መካከለኛ፣” የ1954 ትርጉም] አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ብሏል። እንዲሁም “ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል” በማለት ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 2:5፤ ሮሜ 8:34) ክርስቶስ “ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” የሚለውን ጥቅስ ስናነብ ደግሞ የኢየሱስ ሚና ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። (ዕብራውያን 7:25) ወደ አምላክ መጸለይ የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ኢየሱስን ሕይወት የሌለው ምስል ይቅርና ማንም ሌላ አካል ሊተካው እንደማይችል ግልጽ ነው። ‘አብን በመንፈስና በእውነት’ ለማምለክ የሚያስችለውን መንገድ ለማግኘትና ይህ ዓይነቱ ላቅ ያለ አምልኮ ከሚያመጣው በረከት ለመካፈል ሲል እውነትን ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውቀት ጠቃሚ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ “አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል” ሲል ተናግሯል።—ዮሐንስ 4:23

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ምስል የአንድ ሃይማኖት አባላት ለአምልኮ የሚገለገሉበት የአንድ ነገር አምሳያ ወይም ምልክት ነው። ለምሳሌ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንዶቹ ምስሎች ክርስቶስን፣ ሌሎች ሥላሴን፣ “ቅዱሳንን፣” መላእክትን ወይም ከላይ ተገልጾ እንደነበረው የኢየሱስ እናት ማርያምን የሚወክሉ ናቸው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምልኮ ለሚውሉት ምስሎች የተለየ አክብሮት አላቸው። ክርስቲያን ያልሆኑ አንዳንድ ሃይማኖቶችም የአማልክቶቻቸውን ምስሎች በማምለክ ረገድ ተመሳሳይ የሆነ እምነትና ስሜት አላቸው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Boris Subacic/AFP/Getty Images